ቅድስት ስላሴ ኮሌጅ የተፈጠረው ችግር ዛሬም እልባት አላገኘም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርታቸው ከመጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋርጧል፡፡በተማሪዎቹ በመማር ማስተማር ሂደት ወቅት በረካታ አስተዳደራዊ በደል እየደረሰባቸው እንደሆነና ለጥቄያቸው መልስ የሚሰጥ አካል ባለመገኘቱም ምግብ የመብላትና ትምህርት የማቆም አድማ ካደረጉ እነሆ ዛሬ 15 ቀን ሆኖኗቸዋል፡፡ የምግብ አድማ ካደረጉም በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2005ዓ.ም. የ5ኛ ዓመት ደቀመዝሙር የሆኑት አባማቲያስ፣ የ2ኛ ዓመት በኃይሉ ሰፊ እና ገብረእግዚአብሔር የተባሉ የኮሌጁ ደቀመዛሙርት ታመው ወደ ሆስፒታል መሄዳቸው ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ለኮሌጁ የተመደበው በጀትም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደማይውልና የሙስና ወንጀል እንደሚፈፀምበት ያነጋገርናቸው ተማሪዎች አክለዋል፡፡
በተለይ ተማሪዎቹ እንደገለፁት ከሆነ የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን መምህር ፍስሐፅዮን ደመወዝ እና የቀን ተማሪዎች አስተባባሪ መምህር ዘለዓለም ረድኤት ከቤተክርስቲያኗም ሆነ ከዓለማዊው የመንግስት የትምህርት ተቋም የሌሉ የስነምግባር ጥሰቶች በመፈፀም ተማሪዎችን መሳደብና መምታትን ጨምሮ በማስፈራራት እየዛቱ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው የሚል ቅሬታን ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም መምህራን ክፍያ የሚፈፀምላቸው ባስተማሩት ኮርስና ክፍለ ጊዜ መሰረት በመሆኑ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው በርካታ መምህራን እያሉ አብዛኛውን ኮርስ እነሱ ብቻ እየሰጡ ሲሆን በውጤት አሰጣጥ ላይም ችግር እንደሚስተዋልበቻው ተጠቁሟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተፈጠረው የአስተዳደር ችግር ምክንያት የምግብ አቅርቦትና ጥራት ችግር በመስተዋሉ ለበላይ አስተዳደሩ ቅሬታ ቢቀርብም ከማስፈራራት ውጭ አዎንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አስታውሰዋል፡፡
ተማሪዎቹ ካነሷቸው የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የ5ኛ ዓመት ደቀመዝሙር ኃይለፅዮን መንግስቱ የተባለ ከማደሪያው በመንግስት የደህንነት ሃይሎች ሌሊት ታፍኖ ተወስዶ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩንና እስካሁንም አለመለቀቁ ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም ደቀመዛሙርቱ ቅሬታቸውን ለኮሌጁ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ ለመንገር ቢፈልጉም አቡኑ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አርብ መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅድስት ማርያም መንበረ ፓትርያርክ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በመሄድ ቅዱስ ፓትርያረኩ ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ለማናገር ከቅዳሴ በፊት በስፍራው ብንገኝም ከውጭ አንድ ደህንነት ወደ ውስጥ በመግባት እንዳይወጡ አዟቸው ሳይወጡ ቀርተዋል፡፡ በዕለቱም ፓትርያርኩ እኛን እንዳያናግሩ በመፈለጉ ቅዳሴ እንኳ ሳይገቡ በመቅረታቸው ጥላ ይዘው ሊቀበሏቸው የሄዱ አባቶች ጥላቸውን አጥፈው ሊመለሱ መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በነጋታው ፓትርያርኩ ጥቂት የተማሪዎች ተወካዮች እንዲያናግሯቸው ቢጠሩም አቤቱታችንን ከሰሙ በኋላ ምላሻቸው ግን ሄዳችሁ ተማሩ ብቻ ሆኗል ይላሉ ተማሪዎቹ፡፡ ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ በድጋሚ ከአባ ሰረቀብርሃን ጋር ባደረጉት ውይይት መጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. ትምህርት መጀመራቸው ቢታወቅም አስተዳደራዊና የምግብ ችግሩ ግን እስካሁን እልባት ባለማግኘቱ በግቢው ውስጥ የሚዘጋጅ ምግብ መመገብ አለመጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትምህርት ተቋማት የበላይ ጠባቂ የሆኑት አባ ሰረቀብርሃን ኮሌጁ ግቢ ድረስ በመምጣት ካናገሩና የተማሪዎቹ ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝና የታሰረው ደቀመዝሙርም በነጋታው ተፈቶ በመምጣት የመማር ማስተማሩ ሂደት እንደሚቀጥል ቃል ከገቡ በኋላ በነጋታው ሲመጡ ቃላቸውን በማጠፍ ጭራሽ ማስፈራሪያና ዛቻ በመፈፀም እንደተመለሱ አዲስሚዲያ ያነጋገራቸው የኮሌጁ ተማሪዎች ገልፀውል፡፡ አባሰረቀ ብርሃን ከዚህ በፊት የማኀበረ ቅዱሳንን ስም በተደጋጋሚ በማጥፋት ተከሰው ዜግነታቸው አሜሪካዊ በመሆኑ ወወደ አሜሪካ በመሄድ ክሱ ተቋርጦ በፊት ከነበሩበት የቤተክርስቲያኗ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊነት ተነስተው በአቡነጳውሎስ ፈቃድና መመሪያ የትምህርት ተቋማት የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ መሾማቸውምና በቤተክርስቲያኑ የኑፋቄ ትምህርት አራማጅ ናቸው በሚልም እንደሚጠረጠሩ ይነገራል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ሚዲያ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ህዝቄልን ጠይቆ ውሳኔ ለመስጠት ስብሰባ ላይ መቀመጣቸውን ከመግለፅ ያለፈ ምንም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ከስብሰባው በኋላ የደረሱበትን ውሳኔ ለማጣራትም በድጋሚ ብፁዕ አቡነ ህዝቄል ጋር ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን አላነሱልንም፡፡ በኮሌጁ የቀን መርሃ ግብር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የነበሩት ከየ ሀገረስብከቱ የመጡ በአጠቃላይ 180 ደቀመዛሙርት እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የነ አንዱዓለም እና ጋዜጠኛ እስክንድር ፍርድ ለሌላ ጊዜ ተላለፈ
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንንና ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም እና አቶ ምትኩ ዳምጤ ይግባኝ ውሳኔ ለዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. ተቀጥሮ ቢሆንም ውሳኔው ለአራተኛ ጊዜ ተላለፈ፡፡ በተለይ የክሱን ሂደት ከሚከታተሉት የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሽመክት አሰፋ፣ በላቸው አንሺሶ እና ዳኜ መላኩ መካከል የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ከችሎት ውጭ ከጠዋቱ 3፡40 ሰዓት የተከሳሽ ጠበቆችን 6 ኪሎ በሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ህንፃ ቢሮ ቁጥር 9 በመጥራት ጠበቆችን “ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ወንጀል ነፃ ናቸውና በነፃ ሊለቀቁ ይገባል የሚል ክርክር ስላነሳችሁ ውሳኔውን ለመስጠት ክሱን በደንብ እየመረመርነው ስለሆነ” በሚል ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
የመሐል ዳኛው ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ እስኪሰጡ ድረስ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ከቀጠሮው በኋላ ግን አቃቂ ቃሊቲ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም እና አቶ ምትኩ ዳምጤን የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች ይዘዋቸው ቢቀርቡም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮውን ችሎት ሳይገቡ በመስማታቸው ተመልሰዋል፡፡
ይህ በእዲህ እንዳለ ቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር አልቀረቡም፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ ሚዲያ ባደረገው ማጣራት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮው የተሰጠውና እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌ ያልተገኙት የቃሊቲው ወህኒ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ ሰርጀንት ዘውድነሽ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ ለመጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. እንዲቀርቡ የተሰጣቸውን ማዘዣ ወህኒ ቤቱ አስተዳደሮች ማዘዣው አልደረሰንም በሚል ክደው ተከሳሾቹ በቀጠሮዋቸው እንዲቀርቡ ባለመፍቀዳቸው እንደሆነ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በተከሰሱበት “ሽብር” ወንጀል ከ14 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወቃል፡፡
ኸረ ዛሬም በአጃቢዎች እየተጠበቁ ነው !
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት እያሉ የጥበቃ አጃቢዎችን ብዛት ላየ የምር የሚሞቱ አይመስልም ነበር፡፡ ግን የማይሞት የለ እንዲሉ አቶ መለስ ስንቱን ኢትዮጵያዊ በግፍ ጨካኝ አመራራቸው ሲያስጨንቁ 21 ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. መሞታቸው በአምላኪዎቻቸው ይፋ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ አምላኪዎቻቸው ነሐሴ ሞቱ ቢሉንም እሳቸው የሞቱት ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያንን ካስጨነቁ በኋላ በቤልጂየም ብራሰልስ ሴይንት ሉክ ሆስፒታል በሞትና በህይወት መካከል ከተጨነቁ በኋላ ፓርቲያቸው ይቆዩልን ቢሉም ሳይሰናበቷቸው በጨበጣ ያለፈቃዳቸው የላይኛው ጥሪ በልጦ ላይመለሱ ሄደዋል፡፡ ያኔ ግን ትዝ ይላችኋል? ነሐሴ 15 ቀን 2004ዓ.ም. አቶ በረከት ስምዖን የአቶ መለስን መሞት በጠዋቱ ሲያረዱን “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባጋጠማቸው ኢንፌክሽን ትናንት ሐምሌ 14 ቀን 2004ዓ.ም.ከምሽቱ 4 ሰዓት ህይወታቸው አልፏል” አሉ፡፡ ግን አቶ በረከት የሰውየውን መሞት ለማርዳት የፈጠኑ አልመሰሏችሁም? በድናጋጤ እንዳንሞት እንኳ አላዘኑልንም፤ ያው ኢህአዴግ በተፈጥሮው “ግልፅ, ዴሞክራትና ዘመናዊ አስተዳደርም” አይደል? ለዛ ነው ቶሎ የነገሩን ፤ቢዘገየም ብራቮ! አቶ በረከት ብያለሁ፡፡
የአምባገነኑን ጨካኝ ለኢህአዴግዎች ቅዱስ የሆኑት መሪ ሞታቸውን ዓለም ይወቅልን፣ ነፍሳትም ያንቡ፣ ህዝቡም ይሰናበታቸው፣.…ተብሎ እምባ ማይታክታት ሀገር ህዝቡ ከነጭፍሮቻቸው በፈፀሙት የግፍ አገዛዛቸው 21 ዓመታትን ማልቀሱ ሳያንሰው ሞታቸው ከተነገረ ጀምሮ 13 ቀናት ምድሯን በጥቁር ልብስ ገበያ ካደሩ በኋላ ምክንያቱ ሳይታወቅ አስከሬኑ ለህዝብ ሳይታይ ባማረው የውጭ ሳጥን ነሐሴ 27 ቀን 2005ዓ.ም ግብዓተ መሬታቸው አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ግቢ ተፈፅሟል፤ ወዳጆቻቸው እንዳሉን ከሆነ፡፡ ምክንያቱም ደጉ ለሀገሪቱ ህዝብ አላስ…የሆኑት አምባገነን መሪያችንን አስከሬን እንደነ ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ፣ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌና አቡነ ጳውሎስ አስከሬኑ ለህዝብ አልታየማ! ባለማየታችንም ቢሆን ቅር አይለንም፣ አንኮነንም…”ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አይደል የሚለው ቃሉ? ደግሞስ እንኳን የእሳቸውን መሞት ቀርቶ የሀገራችንን ዕድገትስ በነገሩን ብቻ ያልኖርንበትን ሳናይ 11 በመቶ አድገናል ሲሉን እያመንን አይደል?….፤ታዲያ እሳቸው ከኢትዮጵያ በምን ያንሳሉ?…ምክንያቱም በህይወት እያሉ እራሳቸውን ብቻ ተቋምም፣ሀገርም ፣ህዝብ አርገው ይቆጠሩ ነበርና፡፡
አሁን ግን ግብዓተ መሬታቸው የተፈፀመበት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን በወጣቶች ስፖርትና መዝናኛ(ወወክማ) አቅጣጫ ባለው መካነ መቃብራቸው ቦታ ግዙፍ የማያልቁ ትላልቅ ሻማዎች እየበሩ(እሳቸው ግን ተፍተዋል) በሁለት የጦር መሳሪያ በታጠቁ መከላከያ ሰራዊት ዘወትር ይጠበቃል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ሰውዬው ሞተውም ይፈራሉ እንዴ? ወይ አምባገነን ለካ ሞቶም አያርፍ…..!
ሌላው ያስገረመኝ ጉዳይ ቤተክርስቲያን ሊሳለምና ፀሎቱን ሊያደርስ የሚሄድ ምዕመን ድንገት ዓይኑን አዲስ ወደ ሆነበት መካነ መቃብር አቅጣጫ መልከት ቢያደርግ አስከሬኑ ያረፈበት አጠገብ በተጠንቀቅ የተቀመጡት የመከላከያ ሰራዊቶቹ ግልምጫና ፍጥጫ ምን እሚሉት ነው? ደግሞስ ለሙት የሚደረገው ጥበቃ እና እኒያ ግዙፍ አራቱ ሻማዎች በጀት ከማን ይሆን የሚሸፈነው? መቼም ጉድ እማይሰማ የለ! ከሀገሪቱ በጀት ነው እንዳይባል፣ አያደርጉትም አይባልማ! እንዲህ ከሆነማ በቁማቸው ሀገሪቷንና ህዝቡን የጋጡት የኢህአዴግ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሲሞቱ እንዲህ የሀገር በጀት የሚባክን ከሆነ ምን ቀረን…?
ግድ የለም ጎበዝ!…ከእንግዲህ ሞተውም በዛ ክፉ መንፈሳቸው ሀገር ማተራመስና ማራቆት ስለማያቆሙ አትሙቱብን፣ በቁማችሁ ጋጡና ጨርሱን ብለን እንፀልይላቸው ይሆን ወይስ…..? ኦ…ኦ…የረሳሁት ትዝ አለኝ!…ግን መከላከያ ሰራዊቱ የሞተ አስከሬን እንዲጠብቁ የተደረጉት የአቶ መለስ አምላኪ ኢህአዴጋዊያን አውጠተው የሙዚየሙን ስራ ያስተጓጉላሉ ተብሎስ ይሆን? የሀገሪቱ ካዝና ይመስል ምናልባት ሼም ስለማያውቁ ሊሆን ይችላል፤ አለበለዚያ ሰውዬው በምድር ለሰሩት ግፍ ወደላይኛው ቅጣት እንዳይሄዱ/እንዳያርጉ ታስቦስ ይሆን? ኸረ መላ በሉን ጎበዝ! ሞተውና ተቀብረውም ስፍራው በመከላከያ ጦር መጠበቁ ለምን ይሆን?
ተፈጥሮን በማዛባት ልማትን ማምጣት ይቻል ይሆን?
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
በኢትዮጵያ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የደን ሽፋን 40 በመቶ ነበር፡፡ የቀድሞው የሀገሪቱ ኢህዴሪ መንግስት (ደርግ) በነበረ ወቅት ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ይሰጥ የነበረው ግምት ከፍተኛ በመሆኑ በሀገሪቱ ያሉ ደኞች ከነ ዱር እንሰሳቱ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን ምንም እንኳ የአካባቢ ጥበቃ ምንነት በውል የታወቀ ባይሆንም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ እና የዱር አራዊትም እንደልባቸው ይቦርቁበትና ቱሪስቶችም እንዳሻቸው ይጎበኙ እንደነበር ይነገራል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ከደደቢት በረሃ የመጡት ታጣቂዎች ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 1983ዓ.ም. ጀምሮ ያሉት የደን ሽፋኖች እጅግ እየመነመኑ ሄደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ በፊት 40% የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 3% በመውረድ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ወደ 2.5% መውረዱን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ለ21ዓመታት እስካሁንም በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ያለው አመለካከት እጅግ የወረደ በመሆኑ ቀደም ሲል በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ዙሪያ ያሉ ደኖች በካድሬዎች ፈቃድ ለገዥው አባላት ጊዜያዊ ጥቅም ሲባል እየተጨፈጨፈ ቦታው ለመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ለዚህም በአሁን ወቅት የአዲስ አበባን ሰሜንና ምዕራብ(ሳንሱሲ፣ ጉለሌ፣ሽሮሜዳ፣የካ…የመሳሰሉ በደን የተሸፈኑ አካባቢዎች) መመልከት በቂ ነው፡፡
በተለያየ ምክንያት ከፍተኛ የደን ክምችት ያለባቸው እንደ ባሌ ተራራዎች፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ ደኖች እየተቃጠሉ ይዘታቸው ቢመናመንም መልሶ እምዲለሙ ሲደረግ አልተስተዋለም፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንሰሳት ወደሌላ ሀገር እንዲሰደዱ ምክንያት በመሆን ሀገሪቱ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቀርታለች፡፡ በደኖቹ ዙሪያ ያሉ በግብርና ስራ( መሬት በማረስና እንሰሳት በማርባት)የሚተዳደሩ ገበሬዎች በአካባቢያቸው በተፈጠረው የተፈጥሮ መዛባት ምርቶቻቸው እየቀነሰ ወደ ከተማ እንዲፈልሱ አስገድዷቸዋል፡፡
ሌላው ለደኖች ውድመት ገዥው መንግስት ተጠያቂ ከሚሆንበት አንዱ የደን ውጤቶችን ለየ አካባቢው የገዥው ቡድን አመራሮች ሙስና መጠቀሚያ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ገንዘብ እንዲሸጡ መደረጉ ነው፡፡ ለዚህም ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አቅጣጫ 123 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረብርሃን አካባቢ ያለው ደን በ2004ዓ.ም. እያንዳንዱን ዛፍ በ40ሳንቲም ሂሳብ ለመሸጥ የዞኑና የከተማው መስተዳደሮች ከተስማሙ በኋላ በአካባቢው ማህበረሰብ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ አሁን ካሉት የደን ክምችቶችም ከተወሰኑ ብሔራዊ ፓርኮች በስተቀር አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ዙሪያ ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ንብረትነታቸው የመንግስት የሆኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን(የአሁኑ ኢትዮ ቴሌኮም) ለመስመር ዝርጋታ የሚያገለግላቸውን የምሰሶ እንጨት የሚጠቀሙት ከሀገሪቱ ደን በመቁረጥ ቢሆንም በቆረጡበት ምትክ ግን መልሰው ሲያለሙ አይታይም፡፡ ባለፈው 2004 ዓ.ም ደግሞ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ክልል ያሉ ከፍተኛ የደን ክምችቶች መሬቱን ለውጭ ባለሃብቶች ለመስጠት በሚል ተጨፍጭፈው ቢያልቁም መልሶ የተካም ሆነ ዜጎችን አፈናቅሎ ለባለሃብቶቹ ከመከስጠት ያለፈ ለምን ያለ የመንግስት አካል አልነበረም፤የለምም፡፡ ደኑን እንዲመነጠር የፈቀደትና ቦታውን የመሩት የፌደራሉ እና የክልሉ መንግስታት ናቸውና፡፡
በከተሞች ውስጥ ያለውን የተመለከትን እንደሆነ ዕፅዋቶች ሙሉ በሙሉ እንዲወድሙ ተደርጎ የድንጋይ ካብ ህንፃ ብቻ መገንባት እንደስልጣኔና እንደዕድገት እየተወሰደ በመምጣቱ ቀደም ሲል በየከተሞቹ የነበረው የአየር ፀባይ እንዲቀየር አስገድዶታል፡፡ እዚህ ላይ ስለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ አነስተኛ ግንዛቤ ያላቸው ደካማ መሪዎችን ፈለግ በመከተል ነዋሪዎችም የአካባቢውን ተፈጥሮ በማዛባት ትልቅ ሚና መጫወታቸው እሙን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ላይ ያልተለመደ የአየር ፀባይ እየተስተዋለ ቢሆንም ገዥዎች የራሳቸውን ድክመት ሳይቀርፉ የተለመደውን የገንዘብ ሱስ ለመወጣት ሌሎች ላይ ምክንያት ሲደረድሩና የገንዘብ ካሳ ብቻ ሲያባርሩ ይስተዋላል፤ የቤታቸውን የአደባባይ የአካባቢ ጥበቃ ችግር ገመና ግን እየኖረ ያለው የሀገሬው ሰው የሚያውቅ ሐቅ ነው፡፡
የወሬ ዘመቻ የማይታክተው ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2000ዓ.ም.(ሚሊኒየም) ክብረ በዓል ወቅት እያንዳንዱ ሰው ችግኝ እንዲተክል ለማበረታታት በሚል የውሸት ዘመቻ ሁለት ዛፍ በሁለት ሺህ ሲባል ቢከርምም እንክብካቤ ተደርጎላቸው የፀደቁ ችግኞችና ዛፍ የሆኑትን ልናይ አልቻልንም፡፡ በርግጥ በወቅቱ ዓላማው የተፈጥሮ መዛባትን ከመከላከል አኳያ የሚበረታታ ተግባር ቢሆንም ኢህአዴግ በባህሪው ከወሬ ዘመቻ ባለፈ የተግባር ቁርጠኝነት ስለማይታይበት ይባሰ ያሉትም ደኖች እየወደሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ የተነዛበትና ከፍተኛ በጀት የፈሰሰበት “ሁለት ችግኝ ለሁለት ሺህ” የሚለው ፕሮጀክት ከወሬ ባለፈ የታሰበው ሳይሆን ይኸው 5ኛ ዓመት ላይ ደርሰናል፡፡
በአጠቃላይ ተፈጥሮን እያዛቡ ልማት ማምጣት የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን መንከባከብ፣ የተራቆቱ መሬቶችን በደኖች ማልማት፣ በከተሞች የሚሰሩ ህንፃዎች በእያንዳንዳቸው ግቢ እንደየስፋታቸው መጠን ቢያንስ አምስትና ከዛ በላይ ዕፅዋቶችን(ዛፎች) እንዲተከሉ አስገዳጅ ህግ በማውጣት መተግበር ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ተፈጥሮን በማዛባት ልማት ማምጣት ቅዥት ካልሆነ እውን ሊሆን ስለማይችል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮን መንከባከብ ከሰብዓዊ መብት ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡