በደብረማርቆስ ማረሚያ ቤት 5 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ
በደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት በደረሰ ቃጠሎ በእስር ላይ የሚገኙ 5 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በርካቶች መቁሰላቸው ተገለፀ፡፡ በተለይ ከስፍራው ምንጮቸችን እንደገለፁት ከሆነ ቃጠሎው የተከሰተው ታህሣሥ 12 ቀን 2005ዓ.ም. ከሌሊቱ 5 ሰዓት እንደሆነ እና እስረኞቹ ላይ ጉዳት ሊደርስ የቻለው በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ያሉት ክፍል ሲቃጠል በላያቸው ላይ ተዘግቶ የነበረውን በር የሚከፍትላቸው አጥተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አዲስ ሚዲያም የቃጠሎውን መንስኤ እና ቃጠሎው ባጠቃላይ ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የደብረማርቆስ ማረሚያ ቤት አስተዳደርና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ጥረት ቢደርግም አልተሳካም፡፡
! …….. የኢትዮዽያ ፖለቲከኞች ………!
አብርሃ ደስታ (ከመቀሌ)
በኢትዮዽያ የፖለቲካ ድርጅቶች (ፓርቲዎች) ኣመሰራረት ርእዮተ ዓለም (Ideology) ወይ ሳይንሳዊ መርህ መሰረት (Principle based) ያደረገ ሳይሆን በዘረኝነት ወይ ጎሰኝነትና ጎጠኝነት የተቃኘ በመሆኑ ነው። የዚ ሁሉ ምክንያት ምንድነው?
1) የማህበረሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማነስ ነው። በኢትዮዽያ መርህ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ማራመድ የህዝብ ድጋፍ ኣያስገኝም። የፖለቲካ rationality የለም። ድጋፍ ለማግኘት የጎሰኝነትና ጎጠኝነት ቅስቀሳዎች ጠቃሚ ናቸው። ‘እንደዚህ ተበደልን፣ እንዲህ ኣረጉን …’ ስትል የህዝቡን ስሜት (ወይ ቀልብ) መግዛት ትችላለህ። የተለያየ ጎሳና ጎጥ የተለያየ ፓርቲ ያመርታል። ለምሳሌ ህወሓት ድጋፍ የሚሰበስበውና ስልጣን የያዘው በዚ መንገድ ነው።
2) የኣብዛኞቹ ፖለቲከኞች ዋና ዓላማ ስልጣን መሆኑ ነው (ስልጣን መያዝና መሪ ሁኖ መከበር በቃ)። ለዚህም ጥሩ ኣማራጭ የየራሳቸው ፓርቲ በመመስረት የፓርቲው ሊቀመንበር (ፕረዚደንት) መሆን ያምራቸዋል። ለዚህም ነው በሀገራችን እነዚህ “33 የተቃዋሚ ፓርቲዎች “ የሚባሉ ጨምሮ ከ60 በላይ ፓርቲዎች ኣሉ የሚባለው።
3) የገዢው ፓርቲ ሴራዎች:: ህወሓት/ኢህኣዴግ ጥሩ ነገር በመስራት ተቃዋሚዎችን ለማሸነፍ ከመሞከር ይልቅ የመንግስትን ሃብትና መዋቅር በመጠቀም ተቃናቃኞችን በማፍረስና ማዳከም ሴራ መጠመዱ ሌላው ምክንያት ነው። በሚያደርገው በስለላ የተደገፈ conspiracy የተቃዋሚ መሪዎች (የገዢው ፓርቲ የጥፋት ስራ መሆኑ ስለማይገነዘቡ) እርስበርሳቸው እንዳይተማመኑና ኣንድነት እንዳይፈጥሩ ስለሚያደርግ ነው።
4) የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳሳተ የትግል ኣቅጣጫ (Game Theory)። ኣንዳንድ ፖለቲከኞች (እንዳውም ኣብዛኞቹ) የህዝብን ስሜት ለመግዛት ሲባል ዘረኝነትን የሚቃወሙ እየመሰሉ በተግባር ግን ራሳቸው ዘረኝነትን (ጎሰኝነትን) ያጠቃቸዋል። እንደውጤትም ሁሉም ዘረኛ ሁነው ይገኛሉ። ሌሎች ከነሱ ጋ ከመቀላቀል ይልቅ ከነሱ ራሳቸው ለመከላከል ሲሉ ሌላ ድርጅት መመስረት ይፈልጋሉ። ፓርቲዎችም ይበዛሉ።
ለምሳሌ
(ሀ) ኣንዳንድ ዘረኝነት ወይ ጎሰኝነትን እንቃወማለን፣ በዘር መከፋፈል ይቅር እያሉ የሚሰብኩ ኋይሎች ግንቦት -7 ከዴምህት (ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ ወይ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ኣብሮ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለው ይከሳሉ (ይወቅሳሉ)። ይሄ ፓርቲዎች በዘር ተከፋፍለው እንዲቀሩ ያደርጋል።
(ለ) ህወሓት/ኢህኣዴግ በራሱ ጎጠኝነትን እቃወማለሁ እያለ “ዓረና ትግራይ ፓርቲ ከጠላቶቻችን ሸዋ ፖለቲከኞች በማበር የትግራይን ህዝብ ለመግደል እየተንቀሳቀሰ ነው “ በሚል ስም ያጠፋል። ታድያ ዓረና ፓርቲ ኮ ትግራይ የመገንጠል ዓላማ የለውም፤ ከሌሎች የኢትዮዽያ እህት ፓርቲዎች ይሰራል እንጂ ለብቻው መሆንኮ ኣይደገፍም። ኣብሮነት ጥሩ ነው። ዙሮዙሮ ግን ይሄም ፓርቲዎች እንዳያብሩ ምክንያት ይፈጥራል።
(ሐ) ሰመያዊ ፓርቲ የመሰረቱ ፖለቲከኞች (እንደሚባለው) የኢትዮዽያ ኣንድነት ይሰብካሉ። ዘር ወይ ጎሳ መሰረት ያደረገ ፓርቲ እንደማይደግፉም ይነገራል። እነዚህ ሰዎች ታድያ (የሰማሁት ትክክል ከሆነ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ኣስተሳሰብ ከፖለቲከኛ ኣይጠበቅም) የኣንድነት ፓርቲ ኣባላት የነበሩ ሲሆን ፓርቲው (ኣንድነት) እነሱ የማይፈልጉዋቸውን ሰዎች (እነ ስየ ኣብርሃ የትግራይ ተወላጆችን በኣባልነት ስለያዘ) ከፓርቲው ለቀው በመውጣት “ኣዲሱ”ን ሰማያዊ ፓርቲ መሰረቱ። (የፓርቲዎች ቁጥር ጨመረ)።
ይህንን መረጃ (ምሳሌ ‘ሐ’) ትክክል ከሆነ ማለትም ሰመያዊ ፓርቲ ከሌሎች ብሄሮች (ለምሳሌ ትግራይ) በኣባልነት ካልተቀበለ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? እንበልና ሰማያዊ ፓርቲ ስልጣን ያዘ (የኣንድ ፓርቲ ዓላማ ስልጣን መያዝ ስለሆነ) ከዛ እንዴት ኣድርጎ ሀገርን ያስተዳድራል? ወይስ ኣማራ ክልልና ኣዲስ ኣባባ ብቻ ገንጥሎ ሀገር ሊመሰርት ነው?
ጎሰኝነት ወይ ዘረኝነት ኣንቀበልም ስንል ከተለያዩ ብሄሮች በኣባልነት ኣንቀበልም ማለት ሊሆን ኣይገባውም። በኣጭሩ በኢትዮዽያ ፓርቲዎች እንደ ኣሸን የሚፈሉ ገዢ የሆነ ርእዮተ ዓለም መሰረት ያደረገ የፓርቲ ስርዓት ስለሌለ ነው።
በመጨረሻም
በኢትዮዽያ ፓርቲዎች የሚመሰረቱ በርእዮተ ዓለም ልዩነት ምክንያት ኣይደለም ካልን ታድያ የጋራ ነጥባቸው ምንድነው? በኢህኣዴግ ሙስና መሰረት ያደረጉ ጥቅማጥቅሞች ያገናኛቸዋል። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኣንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ ደግሞ ገ ዢውን ፓርቲ መጥላታቸው ነው።
የመጨረሻ መጨረሻ
በመርህ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች የሉም ማለት ግን ኣይደለም። ይኖራሉ ግን የህዝብ ተቀባይነት በቀላሉ ለማግኘት ይቸገራሉ። ስለዚ ኣናያቸውም።
የኢትዮዽያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሆይ፡ እባካቹ ኣንድ ጠንካራ ድርጅት ፍጠሩ። 33፣65 እየተባላቹ ኣታሳፍሩን።
It is so!!!
በኮብልስቶን ስራ በተፈጠረ የእርስ በርስ ግጭት 8 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ
በአዲስ አበባ በሚገኘው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ ቦሌ ለሚ በሚባል አካባቢ ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2005ዓ.ም. ኮብልስቶን በሚሰሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 8 ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ተጠቁሟል፡፡ ከአካባቢው ምንጮቻችን የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የግጭቱ መንስኤ የሞባይል መጥፋት እንደሆነ እና በዚህም ኮብልስቶን ትሰራ የነበረች የአንዲትን ሴት ጡት ሌላው ሰራተኛ በመቁረጡ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በዛው ዕለት ፀቡን ለማረጋጋት የሞከረ ፖሊስም በኮብልስቶን ተመቶ ወዲያው ህይወቱ ማለፉን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ወደ ዘረኝነት ስሜት ተለውጦ ግጭቱ እስከ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን መዝለቁንና ህይወቷ ያለፈው ወጣት የአካባቢው ኦሮሚያ ተወላጅ በመሆኗ ጉዳዩ ወደ ማኀበረሰቡ በመድረሱ በርካታ የአካባቢው ሰዎች ከአያት ኮንዶሚኒየም እስከ ቦሌ ለሚ ድረስ ከበባ በማድረግ በሰራተኞች መካከል የኢህአዴግ አደራጅና ሰላይ ናቸው የተባሉ 6 ሰዎችን በመግደልና በርካታ ሰዎችን በማቁሰላቸው በአካባቢው ከ 3 ተሸከርካሪ ያላነሱ የፌደራል ፖሊሶች ግጭቱን ለማረጋጋት ቢገኙም እንዳልቻሉና በርካቶችንም ወስደው እንዳሰሩ የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ከፖሊስ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡ የዝግጅት ክፍሉ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል ወደተባለው ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መረጃ ክፍል ስለጉዳዩ ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም፡፡
ዘገባው ወደህዝብ እንዲደርስ እስከተደረገበት መጋቢት 7 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ ቀደም ሲል በርካታ ሰዎች የኮብልስቶን ስራ ይሰሩበት የነበረው አያት ጨፌ እና ቦሌ ለሚ የሚባል አካባቢ ማንም ሰው እንዳይገባ የተደረገ ሲሆን ከሰራተኞች ጋር እዛው በሚገኝ ቀበሌ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ የመንግስት ባለስልጣናት እያወያዩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ችግሩ እስኪፈታም በአካባቢው እስከ ሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ ስራ እንደለሌም ምንጮቻችን ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ በስፍራው የኮብልስቶን ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩና አሁን በውስጡ የቆየና እየተስፋፋ የመጣው የዘረኝነት ስሜት አስፈሪ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ፤ ቀደም ሲልም ችግሩ እንዲቀረፍ ቢገለፅም ከማባባስ ውጭ መፍትሄ የሚሰጥ የመንግስት አካል ባለመኖሩ ዳግም ወደስራው እንደማይመለሱ በመግለፅ “ይህ ዜጎችን በዘረኝነት ከፋፍሎ የማጫረስ የአቶ መለስ ዕራይ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያሳያል ሲሉ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የንግድ ስራ ችግር ገጠመው
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የንግድ መቀዛቀዝ እየታየ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያትና የገዥው ኢህአዴግ የአየተከተለ ያለው የንግድ ስርዓት አድሎነት የተሞላበት ከመሆኑም በተጨማሪ ለስርዓቱ ከቀረቡት ጥቂት ነጋዴዎች እና ንብረትነቱ የህወሃት/ ኢህአዴግ እንደሆነ የሚነገርለት ኤፈርት ኩባንያ ውጭ ያሉ ነጋዴዎች ከአቅማቸው በላይ ግብር እየተጫነባቸው በመሆኑ የንግድ ስራቸውን ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እያዛወሩ መሆኑን ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ኢትዮጵያውያን የኩባንያ ባለቤቶች አስታወቁ፡፡
እንደባለሃብቶቹ ገለፃ ከሆነ በአሁን ሰዓት ምንም ዓይነት የባንክ ብድር እንዳናገኝ አበዳሪ ባንኮች ለእኛ የሚያበድሩ ከሆነ ከሚያበድሩን ገንዘብ ላይ 27 በመቶ ለአባይ ግድብ እንዲያውሉ ጥብቅ መመሪያ በመተላለፉ ባንኮቹ ለማበደር ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በዚህም ምክንያት በንግድ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ችግር በመፈጠሩ በሀገሪቱ ላይ የዕቃ አቅርቦት ችግር እየተከሰተ መሆኑንም ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከውጭ ዕቃ ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ ነጋዴ ከመደበኛው የአሜሪካን ዶላር ምንዛሪ ውጭ በአንድ ዶላር እስከ 25 ሳንቲም ተጨማሪ ክፍያ በህገወጥ መንገድ ለባንክ አስተዳደሮች እንዲሰጡ እየተገደዱ መሆኑን በማስታወስ እንደ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ያሉትም ከውጭ ምንዛሪው እጥረት በተጨማሪ የስኳር አቅርቦት ችግር በመከሰቱ የምርት እጥረት መኖሩም ተጠቁሟል፡፡
ከላይ ተፈጠረ የተባለውን የንግድ ችግር በተመለከተ የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አማከለ ይማም በበኩላቸው “የተባለው ችግር አልተፈጠረም፣ ይህን በሚመለከት ጥያቄያችሁን በፅሑፍ ማቅረብ አለባችሁ” ከሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተመለከተ ደግሞ የብሔራዊ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ እንግዳው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በተመለከተ የባንኩ ገዥ እና ምክትላቸው ለኢቴቪ ከሰጡት ውጭ ሌላ ምላሽ እንደሌላቸው ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡
ከደመወዛቸው ላይ በግድ ለአባይ ግድብ መቆረጡን ሰራተኞች ተቃወሙ
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ከዚህ በፊት ለአንድ ዓመት አቅማችን ሳይፈቅድ ከወር ደመወዛችን ላይ ሲቀቆረጥ ነበር፤ አሁን ግን ካለብን የኑሮ ውድነት የተነሳ አቅማችን አይፈቅድም ስለዚህ ያለፈቃዳችን ሊቆረጥብን አይገባም ሲሉ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ፒቲሽን ተፈራርመው ማስገባታቸው የደረሰን መረጃ አየመንግስት ሰራተኞች በግድ ለአባይ ግድብ ከደመወዛቸው ላይ እንዳይቆረጥብን ሲሉ ፒቲሽን መልክቷል፡፡
ሰራተኞቹ በቁጥር ወደ 36 የሚደርሱ በዞኑ በተለያየ የመንግስት መስሪያ ቤት የሚሰሩ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን እስካሁን የተሰጣቸው ምላሽ ግን የለም፡፡ እንደሰራተኞቹ ገለፃ ከሆነ “በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተከስቶ እያለ ያለፈቃዳችን ለአንድ ዓመት ያህል ተቆርጧዋል፤ አሁን ግን አንችልም፡፡ ስለዚህ አሁንም በኢህአዴግ ካድሬዎች አማካኝነት ያለፈቃዳችን ከደመወዛችን ላይ እንዳይቆረጥ እስከመጨረሻው እንታገላለን” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በተለይ በዞኑ አረካ ወረዳ ያሉ የግብርና ሰራተኞች ድርጊቱን ተቃውመው አቤቱታ ለወረዳው አስተዳደርና ግብርና ፅ/ቤት ቢያቀርቡም አቤቱታቸውን ውድቅ እንዳደረጉባቸው በመግለፅ በጋራ የተስማሙ ሰራተኞች እስከ ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ ክስ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል፡፡ ስለጉዳዩ ለማጣራት የዝግጅት ክፍሉ ወደወረዳው ዋና አስተዳደር አቶ ደመቀ ደጀኔ ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡፡
ይሁን እንጂ በድጋሚ ወደወረዳው ግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጴጥሮስን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው “ተቆረጠ የተባለው ደመወዝ ሰራተኞቹ በተስማሙት መሰረት ነው፤ በርግጥ በታህሣስ 2005 ዓ.ም. ሊቀረጥ ሲል ወቅቱ በዓል ስለነበረ እንዳይቆረጥብን ስላሉ ቅሬታቸውን የተቀበልን ቢሆንም ኋላ ከጥር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ 2ኛ ዙር እንዲቆረጥ በተስማሙት መሰረት መቆረጥ ተጀምሯል፡፡ በዚህም ዙሪያ አንዳንድ ግለሰቦች ከወር ደመወዛቸው ላይ እንዳይቆረጥ ቅሬታ ያቀረቡ ቢሆንም ከተጀመረ በኋላ ማስተናገድ እንደማንችል ተነጋግረን ተግባብተናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አረካ ወረዳ በደቡብ ክል ወላይታ ዞን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተወለዱበትና ምርጫ የተወዳደሩበት ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡