አንድነት ፓርቲ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፔቲሽን ሊያስፈርም ነው

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በመላ ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የዜጎች ማፈናቀል እንዲቆም፣ ተዘዋውሮ የመኖር ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ የመስራትና ሀብት የማፍራት መብት እንዲከበር እንዲሁም በሀገሪቱ ያለውን ለከት ያጣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት በመቃወም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚተባበርበትን ዘመቻ ጀመረ፡፡
ይህንን አስመልክቶ የህዝብ ግንኙነት ክፍል እንደገለፀው ይህንን ሀገራዊ ዘመቻ በበላይነት የሚመራው የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሲሆን ዕቅድ በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ የተግባር ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡
በዕቅዱም መሰረት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀገራዊ ዋስትና እንዲኖራቸውና መብታቸውን ማስጠበቅ የሚችሉባቸውን ዕቅዶች አውጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት በቅድሚያ ሀገራዊ ይዘት ያለውን ማፈናቀል ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም፤ የተፈናቀሉትም ወደነበሩበት ስፍራ እንዲመለሱና ካሳ የሚገባቸውም ተገቢ ካሳ እንዲፈፀምላቸው፤ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ፔቲሽን በማስፈረም ወደሚመለከተው አካል ማስገባት ቀዳሚው ነው፡፡ በተጨማሪም በሀገራቀፍ ደረጃ ምሁራን የተሳተፉበት የፓናል ውይይት በማካሄድ ከሙህራኑ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠበቅ ሲሆን በሀገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ ማድረግ ሌላው ዓላማ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ህዝቡ መብቱን ለማስከበር እንዲችል ህዝባዊ ውይይቶችና ሰላማዊ ሰልፎች የሚደረጉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ከህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ምንጭ ፡- ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

Leave a comment