በአዲስ አበባ የዳቦ እጥረት ተከሰተ
በአዲስ አበባ ከተማ ዳቦ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ እንዳልሆነ ተገለፀ፡፡የከተማው ነዋሪዎች በየዳቦ ቤቱ ዳቦ ለመግዛት ሲሄዱ ዳቦ አለመኖሩ እየተነገራቸው በተደጋጋሚ እየተመለሱ መሆኑንና ችግሩም እስካሁን እንዳልተቀረፈ ሰንደቅ ጋዜጣ በጥቅምት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል፡፡ እንደጋዜጣው ዘገባ ከሆነ አንዳንድ ዳቦ መሸጫ ሱቅ የሥራ ኃላፊዎችና ባለቤቶች በተገኘው መረጃ መሰረት በዳቦ መሸጫ መንግሥት ከተመነው ዋጋ አንፃር ሲታይ አንድን ዳቦ ለገበያ በማቅረብ የሚገኘው የትርፍ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ዘርፉ አበረታች አለመሆኑ ተገልፁዓል፡፡
እጥረቱን በተመለከተ ጋዜጣው ያነጋገራቸው በንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ሰይድ፤ የዳቦ ዋጋ ትርፍን በተመለከተ መንግስት ተመኑን ሲያስቀምጥ ያሉትን ወጪዎች ታሳቢ አድርጎ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የተፈጠረውንም የዳቦ እጥረት በተመለከተ ስንዴ በእህል ንግድ በኩል ተገዝቶሀገር ውስጥ ሲገባ መንገድ ላይ በተፈጠረው መዘግየት የተፈጠረ መሆኑን ኃላፊው አመለክተዋል፡፡ ያም ሆኖ እህል ንግድ ከመጠባበቂያ ክምችቱ በማውጣት ለአዲስ አበባም ሆነ ለክልል የዱቄት ፋብሪካዎች እንደተቀመጠላቸው ኮታ እንዲያከፋፍል መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
መንግስት በሀገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በሚል በ 2003 ዓ.ም. በበርካታ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን ከጣለ በኋላ በስተመጨረሻ የሌሎች ተመን ሲነሳ የስኳር፣ የዘይትና የስንዴ ምርቶችን የማከፋፈል ስራ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ውሎ እስከ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ይሁን እስካሁን በስርጭቱ ረገድ በስኳር ላይ ተደጋጋሚ ችግር እየታየ ሲሆን አሁን ደግሞ በዳቦ ስንዴ ላይ ችግሩ እየተንፀባረቀ መሆኑን ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
“ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መሞታቸው ተነግሮናል” አቶ ስብሃት ነጋ
በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ወቅት ያበሩት የነበረው የጦር አውሮፕላን ተከስክሶና ቆስለው በሻዕብያ እጅ ለሁለተኛ ጊዜ የወደቁት ጀግናው ኢትዮጵያዊ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ በኤርትራ እስር ቤቶች በስቃይ ቆይተዋል፡፡
ጦርነቱ አብቅቶ ሁለቱ አገሮች የጦር ምርኮኞቻቸውን ሲቀያየሩ የኢትዮጵያ መንግስት በኮሎኔሉ ጉዳይ ገፍቶ መሄድ ባለመቻሉ በዛብህ ወደ አገራቸው ሳይመለሱ በኤርትራ እስር ቤት መቅረታቸውን የመንግስት ተቃዋሚዎች ይናገራሉ፡፡
የኮሎኔሉ ቤተሰቦች ደህንነታቸውን ይሰሙ የነበሩት ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ሰራተኞች የነበረ ቢሆንም ግንኙነቱ መቋረጡን ለአብራሪው ቤተሰቦች ቅርበት ያላቸውና የኮሎኔሉ ወንድም ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለላይፍ መጽሔት ሰጥተውት በነበረ ቃለ ምልልስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የኮሎኔሉ ቤተሰቦች በተለያዮ ጊዜያት ወደ መንግስት አቤት በማለት አብራሪውን በዲፕሎማሲ ጥረት ከእስር እንዲያስፈቱ ሲወተውቱ ቢቆዮም መኖር አለመኖራቸውን እንኳን የሚያረጋግጥላቸው እስከማጣት መድረሳቸው ጉዳዮን ለፈጣሪ ከመስጠት የዘለለ አማራጭ እንዳይኖራቸው አድርጓል፡:
የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ኢንስቲትዮትን የሚመሩት የቀድሞው የህወሃት ነባር ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋ አሜሪካን አገር ጎራ ባሉበት አጋጣሚ ከገዛ ፓልቶክ ሩም ተሳታፊ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ‹‹ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መሞታቸው ተነግሮናል፡፡አሁን እየጠየቅን የምንገኘው ከሞቱም ሬሳቸውን እንዲያሳዮንና የአሟሟታቸውን ምክንያት እንዲነግሩን ነው፡፡››በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡የፓልቶኩ አቅራቢም በኮሎኔሉ ሞት የተሰማትን ሀዘን በፓልቶኩ ስም ገልጻለች፡:
የስብሃትን ንግግር ተከትሎ የኮሎኔሉ ቤተሰቦች በስብሃት የተነገረውን ከዚህ ቀደም መስማታቸውን ለማረጋገጥ ሞክረናል፡፡ የኮሎኔሉ ቤተሰቦች በዛብህ ሞተዋል ተብለው በይፋ አለመረዳታቸውን ባደረግነው የማጣራት ሙከራ ለማወቅ ችለናል፡፡ ስብሃት ነጋ በኤርትራ 27 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የጦር ምርኮኞች እንደሚገኙ በቃለ ምልልሳቸው አስታውቀዋል፡፡
ምንጭ፡- ዘ-ሐበሻ ድህረ ገፅ
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የመጀመሪያው ማጣሪያ ጨዋታ በናይጄሪያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለብራዚሉ ዓለም ዋንጫ 2014 ማጣሪያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ከናይጄሪያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 1 ተሸነፈ፡፡ በውጤቱም ኢትዮጵያ 1፡ 2 ናይጄሪያ በመሆን ተጠናቀቋል፡፡ በጨዋታውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከፍተኛ ብልጭ የበላይነቱን ቢያረጋግጥም፤የኢትዮጵያ የፊት አጥቂ ሳላዲን ሰይድ ያገባት ጎል በዳኛው ተሽራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የበረኛው ክልል አካባቢ በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ባለቀ ሰዓት ናይጄሪያ ልታሸንፍ ችላለች፡፡
ሁለቱም ቡድኖች ጎሉን ያስቆጠሩት በሁለተኛ አጋማሽ ሰዓት ሲሆን ለኢትዮጵያ በ56ኛው ደቂቃ የመሪነት ጎሉን በግራ አቅጣጫ ያስቆጠረው በኃይሉ አሰፋ (ቱሳ) ነው፡፡ ናይጄሪያ ደግሞ አንዱን በጨዋታ ስታገባ ሁለተኛውን ጎል ግን በተሰጣት ፍፁም ቅጣት ምት ነበር፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ስታዲየም በተመልካቾች የብሔራዊ ቡድኑን መለያ በመልበስ እጅግ አሸብርቀው ለሜዳው ደምቀት ሰጥተውታል፡፡ ቀጣዩ የደርሶ መልስ በናይጄሪያ በሚደረገው ጨዋታ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ውጤት ይታወቃል፡፡
በጎጃም ሶስት ወረዳዎች መንግስትን አስደነገጡ
በጎጃም ጎንቻ ሲሶ፣ ሁለት እጁ እነብሴ እና እነብሴ ሳር ምድር ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ሰሚ ያጣ ህዝብ በሚል
መንግስት ጥያቄዎቻችንን ባስቸኳይ ካልመለሰልን የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡ በተለይ
ነዋሪዎቹ ቢቸና፣ደጀን፣ሞጣ ባህርዳር ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ለማስራት ከዚህ ቀደም የሞቱት ጠቅላይ ሚኒስትር
አቶ መለስ ዜናዊ ቃል ቢገቡም እስካሁን አልተሰራም፤ አሁን ደግሞ የመንገድ ግንባታው ተሰርዟል ተብለናል በሚል
መስከረም 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ማታ በወረዳዎቹ ከተሞች ላይ በራካታ መፈክሮች ያሉት ፖስተሮችን ለጥፈው
አድረዋል፡፡
በደል የወለደው ቁጭት በሚል ርዕስ ግብር ያለልማት ብዝበዛ ነው፣አንድ መንግስት መንገድ ለመስራት ስንት ዓመት
ይፈጅበታል፣ የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካት ጥያቄዎችንም ማንሳታቸው ታውቋል፡፡ይህንም የአካባቢው
አመራሮች መስከረም 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት አይተው በመደናገጥ ፖስተሮችን ያስቀደዱ ሲሆን፤ ህዝቡ አሁንም
ጥያቄያችን ካልተመለሰ በአካባቢያችን ያሉ ትምህርት ቤቶች፣ ሶቆችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተዘግተው የተቃውሞ
ሰልፍ እንወጣለን ሲሉ በማስጠንቀቃቸው እስካሁንም በአካባቢው ውጥረቱ አይሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ የአካባቢውን
ባለስልጣናት ለማናገር ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡
አምባሳደር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ፕሬዘዳንት ሆነው ተሾሙ
ዛሬ መስከረም27 ቀን 2006 ዓ.ም. ለ12 ዓመታት በፕሬዘዳንትነት ያገለገሉት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተሰናብተው በምትካቸው አዲስ ተሾመ፡፡ በተለይ 547 አባላት ያሉት የህዝብ ተወካዮች እና 187 አባላት ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስራ ዘመን መጀመሩን ያበሰሩት ፕሬዘዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የስንብት ንግግራቸውንም አድርገዋል፡፡ በምትካቸውም ለቀጣዩ 6 ዓመታት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር(ፕሬዘዳንት) ሆነው ለማገልገልም በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ሙላቱ ተሸመ ዊርቱ ተሾመዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት አዲስ ፕሬዘዳን ከቀድሞዎቹ የተለየ ምንም ዓይነት የተለየ ስራ ማከናውን የማይችሉ ሲሆን ዋነኛ ስራቸውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡትን አምባሳደሮች መሾም፣ የውጭ ሀገር አምባሳደሮች በኢትዮጵያ የሹመት ደበዳቤ መቀበል፣የእንኳን አደረሳችሁ የበዓላት መልዕክት ማስተላለፍ፣ ከተጋበዙ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲጠናቀቅ ማስመረቅ ነው፡፡
ከተጠሱት ይልቅ ርዕሰ ብሔሩ ስልጣን አላቸው የሚባለው ለተከሰሱ ሰዎች ይቅርታ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን በኢህአዴግ ፍትህ ሚኒስቴር ሹሞች እና ለይስሙላ የተቋቋመው የይቅርታ ቦርድ ሲያቀርብ ብቻ የሚከናወን ነው፡፡ ስለዚህ ከአዲሱ ፕሬዘዳንት ከቀድሞ ምንም አዲስ የተለየ ነው የሚባል መልካም ነገር የሚፈጥሩበት ዕድል ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም የስራ ድርሻቸው በህገመንግስቱ ተገድቦ የተሰጠ ቁንፅል በመሆኑና ሁሉም ስራ በኢህአዴግ ፍላጎትና ፈቃድ በ”ጠቅላይ ሚኒስትሩ” ጠቅላይነት የሚፈፀም መሆኑ በግልፅ ተቀምጧልና፡፡