Daily Archives: October 1st, 2013

የአለም ሻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለአለም ኮከብ አትሌትነት እጩ ሆኑ

የአለም ኮከብ እጩዎቹ ጥሩነሽ፣ መሐምድ እና መሰረት

athlets
የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ባለሞያዎች ቡድን እ.አ.አ በ2013 ዓ.ም የአትሌቲክስ ውድድር አመት አትሌቶች በሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ ውድድሮች ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች እና ሌሎች መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ባደረገው የኮከብ አትሌቶች እጩዎች ምርጫ ኢትዮጵያዊያኖቹ የረጅም ርቀት ሩጫ ድንቆች ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር፣ እንዲሁም የወቅቱ የ800 ሜትር ሩጫ ኮከብ መሀመድ አማንን ጨምሮ በወንዶች 10፣ በሴቶች 10 አትሌቶችን እጩ አድርጎ አቅርቧል።
በሞስኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው 14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ሺህ ሜትሩን 30፡43.35 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በርቀቱ ሶስተኛዋ በአጠቃላይ ደግሞ አምስተኛዋ የሆነው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር ርቀት ባደረገቻቸው 11 ተከታታይ ውድድሮች አንድም ውድድር አለመሸነፏ እና በ2013 ዓ.ም በተለያዩ ርቀቶች ባደረገቻቸው ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪነቷን በተደጋጋሚ ለማሳየት መቻሏ ለእጩነት አብቅቷታል።
የ 2007 ዓ.ም የአለም ኮከብ መሰረት
ሌላዋ ለአለም ኮከብነቱ እጩ የሆነችው ኢትዮጵያዊ አትሌት መሰረት ደፋር በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማጣሪያውን በቀላሉ ካለፈች በኋላ በፍጻሜው ውድድር ወቅት በተለመደው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃቷ በመታጀብ 5 ሺህ ሜትሩን 14:50.19 በሆነ ጊዜ አጠናቃ ለሁለተኛ ጊዜ በርቀቱ የአለም ሻምፒዮን ከመሆኗ በተጨማሪ አመቱ ጥንካራ ተፎካካሪዋ ጥሩነሽ ዲባባን በዳይመንድ ሊግ ያሸነፈችበት እና በተደጋጋሚ አስደናቂ ብቃቷን ያሳየችበት ሆኖ ነው የተጠናቀቀው።
እ.አ.አ በ 2007 ዓ.ም መሰረት ደፋር እጅግ በጣም ውጤታማ አመትን በማሳለፏ በአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) የአመቱ ኮከብ ሴት አትሌት ተብላ በመመረጥ ይሄንን ክብር ያገኘች በታሪክ ሁለተኛዋ ሴት አፍሪካዊት አትሌት ለመሆን ከመቻሏ በተጨማሪ ሶስተኛዋ ኢትዮጵያዊትም ለመሆን መቻሏ ይታወሳል። ከመሰረት በፊት ታላላቆቹ ሀይሌ ገብረስላሴ (1998 ዓ.ም) እና ቀነኒሳ በቀለ (2004 እና 2005 ዓ.ም) የአመቱ የአለም ኮከብ አትሌቶች ተብለው ተሸልመዋል።
በወንዶቹ በኩል ለኮከብ አትሌትነት ዘንድሮ እጩ ሆነው ከቀረቡት አስር አትሌቶች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሀመድ አማን 2013 ዓ.ም እጅግ በጣም ስኬታማው አመት ነበር። በሞስኮው 14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድንቅ የአጨራረስ ብቃት 800 ሜትሩን በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ሶስተኛው ፈጣን ሰአት ሆኖ በተመዘገበ 1:43.31 በሆነ ጊዜ አጠናቆ ለኢትዮጵያ በታላላቅ ሻምፒዮናዎች ከ5 ሺህ ሜትር በታች በሆነ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘ በታሪክ የመጀመሪያው አትሌት የሆነው መሀመድ አማን በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን በፍጹም የበላይነት ነበር የዘንድሮውን የውድድር አመት ያጠናቀቀው።
እ.አ.አ ከጥቅምት 1 ቀን 2013 ጀምሮ እስከ ፊታችን ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ *የአለም አትሌቲክስ ቤተሰብ* በኢሜል መልእክቶች በሚያደርገው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ከፍተኛ ድምጽ የሚያገኙ ሶስት ወንድ እና ሶስት ሴት አትሌቶች ወደፍጻሜው የሚያልፉ ሲሆን፣ ከዛ በኋላ የአለም አቀፉ አትሌቲክ ፋውንዴሽን ምክርቤት የአለም ኮከብ በመሆን የሚያሸንፉት ወንድ እና ሴት አትሌቶችን መርጦ አሸናፊዎቹ እ.አ.አ ህዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ሞናኮ ውስጥ በሚካሄድ ስነ-ስርአት በይፋ ይታወቃሉ።
የዘንድሮውን የአለም ኮከብ አትሌትነት ክብር ጃማይካዊያኖቹ የአጭር ርቀት ውድድር ኮከቦች ዩሴን ቦልት እና ሼሊ-አን ፍሬዘር-ፕራይስ ይወስዱታል ተብሎ ይጠበቃል።
ዩሴን ቦልት እና አሜሪካዊቷ አሊሰን ፊልክስ የ2012 ዓ.ም የወንዶች እና ሴቶች የአለም ኮከብ አትሌቶች ተብለው መመረጣቸው ይታወሳል።
ምንጭ፡- ፍስሃ ተገኝ “ቶታል 433 “ ስፖርት

Teddy Afro chosen for World Cup 2014 Official Singer for Africa

tedyIn the grand tradition of music for the 2014 FIFA World Cup, the most Ethiopian young popular singer Tewodros Kassahun (Teddy Afro ) has been chosen to represent the world’s most popular sports competition. Teddy Afro’s Song will be featured as the official song for the 2014 World Cup for Africa.
According to the source Teddy afro was selected by Coca Cola to represent Africa for the 2014 FIFA World Cup song. It seems like Teddy Afro took Ethiopia to world cup already.
Teddy Afro’s finished Song and Video Clip that was shot in Kenya will be available world wide very soon.

የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተደረገ የመዝጊያ ንግግር

የተከበራችሁ የሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚዎች፤
የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤
የተከበራችሁ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች፤
ክቡራንና ክቡራት!

አስቀድሜ የማክበር ሰላምታየን እያቀረብኩ መብታችንን አደባባይ ወጥተን ለምንጠይቅበት፣ ያልተሸራረፈ ነፃነታችንን ለማረጋገጥ ጉዞ ወደቀጠልንበት ታሪካዊ ቀን ሁላችንንም እንኳን አደረሰን፡፡dr.negaso

በመቀጠልም ለዚህ ዝግጅት መሳካት የተባበሩንን፣ የረዱንን፣ ያገዙንንና በቅስቀሳ ወቅት መስዋዕት ከፍለው ለዚህ ላደረሱን የአንድነትና የ33ቱ አባላት፣ አመራሮችና ደጋፊዎቻችን ከፍ ያለ ምስጋናየን ከአክብሮት ጋር ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በስትራቴጅው መሰረት በመጀመር፤ በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን በማንቀሳቀስ ሕዝቡን ያሳተፈ ትግል በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማከናወኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የሚልዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነገበ ሲሆን እንደ ሁልጊዜውም ፓርቲው ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ ነገር ግን ሕጋዊ መብቱን ሳያስነካ፤ መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት በመክፈልና በቁርጠኝነት ንቅናቄውን በታቀደለት መሰረት ከአባላቱና አመራሩ ጋር በመሆን በማከናወን ለኢትዮጵያ ሕዝብ መመኪያ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ዛሬ የተሰለፍንበት ዋና ምክንያትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሰለፈለትን፣ የሞተለትን፣ በአጠቃላም አንድ ትውልድ ትልቅ ዋጋ የከፈለለትን ግን ደግሞ እስካሁን መረጋገጥ ያልቻሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለምንም መሸራረፍ የሰፈነባት የሁላችን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲደረግ የቆየውን ትግል በማያዳግም መልኩ ከህዝቡ ጋር በመሆን እውን ለማድረግ ነው፡፡

የምንታገለው ለመብታችን መከበር፣ ለነፃነታችን መረጋገጥ፣ ለሀገር ሉዓላዊነታችን፣ ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ የታሰሩ የፖለቲካና ህሊና እስረኞች እንዲፈቱና ማንም ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ፣ በእምነቱና ሃሳቡን በነፃነት ስለገለፀ የማይታሰርባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው፡፡ እንዲሁም የፀረ-ሽብር ህጉ መሰረታዊ ዜጎችን መብቶችና ሕገ-መንግስቱን በግልፅ የሚንድ በመሆኑ የሚሊዮኖችን የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሰረዝ ለማድረግ ነው፡፡

ዛሬ የተሰለፍነው ኢህአዴግና የኢህአዴግ መንግስት እንደሚከሰን ሁከት ለመፍጠር አይደለም፣ ሽብር ለመፍጠር አይለም፣ አሸባሪዎች ስለሆንን አይደለም፣ የአሸባሪዎች መደበቂያ ስለሆንንም አይደለም፣ የሻዕቢያ መልዕክት አድራሾች ስለሆንን አይደለም፣ በአቋራጭ የመንግስት ስልጣን ለመያዝም አይደለም፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በገዥው ፓርቲ የተነጠቅናቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስመለስ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በአመለካከታችን የማንታሰርባት ኢትዮጵያ ስለምታስፈልገን ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በጉልበትና አፈና መግዛት እንዲበቃና እንደሌሎች ሀገሮች ሀገራችን ዴሞክራሲ የሰፈነባት እንድትሆን ነው፡፡negaso

ክቡራንና ክቡራት!
ፓርቲያችን አንድነት ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚገባትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ በሰላማዊ የትግል መስመር ለማረጋገጥ ትግል ከጀመረ አምስት ዓመቱን ይዟል፡፡ በነዚህ ዓመታትም ፓርቲያችን ወደ ፍፁም አምባገንነት እየሄደ ያለውን ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ አካሄድ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ነጠቃ እንዲቆም አጥብቆ ታግሏል፣ እየታገለም ይገኛል፡፡

በትግሉ ሂደትም ስርዓቱ በግልፅና በስውር ፓርቲያችን ላይ ጥቃት ፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል፡፡ አመራሮቻችንና አባሎቻችንም ስለ ቁርጠኛ ዓላማቸው ያለምንም ማፈግፈግ የሚከፈለውን መስዋእትነት ከፍለዋል፣ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ስለ ዴሞክራሲና ነፃነት ሲሉ ጨለማ ክፍል የተጣሉትን ወጣት የፖለቲካ አመራሮች፣ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ እስር ቤት የተጣሉ ጋዜጠኞችና የዕምነት ጣልቃ ገብነትን የተቃወሙ የሙስሊም ወገኖች መፍትሄ አፈላላጊ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቀለን፡፡ ዜጎችን ለማሰር እያገለገለ ያለው የጸረ-ሽብር አዋጅም በአስኳይ እንዲሰረዝና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እየሰሩ ያሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ውይይት እንዲጀመርና በሀገራችን ጉዳይ ላይ መፍትሄ እየሰጠን እንድንሄድ፤ ለዚህም ገዥው ፓርቲ ፈቃደኛም፤ ቁርጠኛም እንዲሆን ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የሀገራችን ፖለቲካ በኢህአዴግ ብቻ አይፈታም፡፡ በሌላ አንድ ፓርቲ ብቻም ይፈታል ብለንም አናምንም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመተባበር፣ በመቀናጀትና ውህደት በመፍጠር ትልቅ የፖለቲካ አቅም መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

የተከበራችሁ ሰላማዊ ሰልፈኞች!

አሁንም ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ለውጥና ማሻሻያ ለማድረግ ፍላጎትም አቅምም የለውም፡፡ በ3 ወር ህዝባዊ ንቅናቄችን ያረጋገጥነው ይሄንኑ ነው፡፡ ምክንቱም አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዥ ሀይል በሰላማዊ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ አሁንም ለጥያቄ አቅራቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርገው ሩጫ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ እየጨፈለቀና እነዚህ መብቶች ይከበሩ ዘንድ የሚጠይቁ አባላቶቻችንን ከህግ አግባብ ውጪ በገፍ እያሰረም ቢሆን ህዝባችን ጋር ለመድረስና ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለማሰማት ችለናል፡፡ ይሄው በማሰማት ላይም እንገኛለን፡፡ ሰላማዊ የተቃውሞ ትግላችንን አጠናክረን በመቀጠል አምባገነኖችን በሚያንቀጠቅጥ የተቃውሞ ትግል እንደምናሸንፍ አልጠራጠርም፡፡

በጎንደርና ደሴ ከተማ በ7/11/2005 የጀመርነው የተቀውሞ ሰልፎች በባህርዳር፣ በአርባምንጭ፣ በጅንካ፣ በአዳማ፣ በፍቼ በተሳካ ሁኔታ የተካሄዱ ሲሆን በመቀሌና ባሌ ሮቤ በከፍተኛ ጫናና ህገወትነት ሳካሄዱ ቀርተዋል፡፡ በወላታ ሶዶና አዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተከናውነዋል፡፡ ከላይ በጠቀስናቸው ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎቹን ለማሰናከል ሃላፊዎቹ የየአካባቢዎቹን ሚሊሻዎች፣ የደንነት ሰዎች፣ ታጣቂዎችና ፖሊሶች በመጠቀም አባላቶቻችንን አስረዋል፣ አስፈራርተዋል፣ ደብድበዋል፣ አዋክበዋል፡፡ ከአንድ የመንግስት አካል በማይጠበቅ መልኩም አመራሮቻችንን አግተዋል፣ የተለጠፉ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ወረቀቶችን እንዲቀደዱ በማድረግና ህዝቡ በሰልፎቹ እንዳይገኝ በካድሬዎች አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማካሄዳቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር በማድረግ ከየከተሞቹ አቅራቢያ ከሚገኙ ወረዳዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለማሰማት እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ ከህዝብ የተነጠለ መሆኑንና ህዝቡን እየመራሁ ነው የሚለው ህዝብን በማሸማቀቅና በጉልበት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ችለናል፡፡

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን!

ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ተቋምና የፍትህ ስርዓት ያስፈልገናል፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የፖሊስና የደህንነት ተቋምም ያስፈልገናል፡፡ ነፃና ገለልተና የዴሞክራሲ ተቋማትም መፈጠር አለባቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ተቋማት የሚፈጠሩት ግን በልመና አይደለም፡፡ እነዚህን ተቋማት ነጻ ሆነመው እንዲፈጠሩ የምታደርጉት እናንተ ናችሁ፡፡ ነፃነት ከፍርሀት አይገኝምና፣ በሀገር ጉዳይ አይፈራምና ነፃነታችንንና መብታችንን የሚነጥቁንን እምቢ ማለት አለብን፡፡ አትችሉም ማለት አለብን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ገዥዎችን የምንፈራብ ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ ገዥ ህዝቡን ይፈራል እንጅ ሕዝብ ገዥዎችን አይፈራም፡፡

ከላይ የተናገርኩትን የሚያጠናክር መረጃ ላቅርብ፡፡ ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይያዛሉ፣ አስገድው በአካል ፈሳሽና ናሙና በመውሰድ ምርመራዎች ይካሄዳሉ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ በውሸት ማስመስከርና አስገድዶ መረጃ ማውጣጣት፣ ቶርቸር፣ ዜጎች በራሳቸው ላይ እንዲመሰክሩ ማስገደድና ሌሎች የማሰቃያ ዘዴዎች አገዛዙ ፍርሃት እንዲፈጠር ለማድረግ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ስርዓቱ ዜጎች ካላግባብ ከየመኖሪያ ቀያቸው በገጠርም ሆነ በከተማ በግፍ እንዲፈናቀሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሄው ሀገራዊ ይዘት ያለው ማፈናቀል ሦስት አይነት መልክ ያለው ሲሆን በዘር ላይ ተመሰረተ ማፈናቀል፣ በልማት ስም ማፈናቀልና ለመሬት ወረራ ማፈናቀል ናቸው፡፡ ዘርን መሰረት ያደረገው ማፈናቀል በቅርቡ ብቻ በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎችና ሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተው ነው፡፡ በልማት ስም የሚከናወነው ማፈናቀል በአብዛኛው በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ዋናው መሰረቱ የገዥው ፓርቲ የመሬት ፖሊሲ ነው፡፡ መሬት በባለቤቱ ፈቃድ የሚሸጥና የሚለወጥ ባለመሆኑ ያለበቂ ካሳና ማስጠንቀቂያ ለማህበራዊ ትስስር ቁብ ሳይኖረው ልማት የሚል ስም ብቻ በማንሳት ዜጎች የሚፈናቀሉበት ነው፡፡ ሌላው የማፈናቀል አይነት ደግሞ ከመሬት ወረራ ጋር በእጅጉ የተቆራኘና በእርሻ መሬት ሰበብ ዜጎች እየተፈናቀሉ ለውጭና ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በጥቂት ሳንቲም የሚሰጥ ነው፡፡ ይሄም በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች በስፋት የታየና እየታየ ያለ ነው፡፡ ሀገራቀፉን ማፈናቀል አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በአስቸኳይ እንዲቆምም እንጠቃለን፡፡

ከመፈናቀሉ በተጨማሪም ቅጥ ያጣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ጣሪያ ያስነካው የዋጋ ግሽበት ዋና መንስኤው ስርዓቱ የሚከተለው የተሳሳተ አጠቃላይ ፖሊሲ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ የወለደው ነገር ቢኖር ሀገራችን በታሪኳ አይታ የማታውቀው ስደት ነው፡፡ ዜጎች ከፊት ለፊት ሞት እንደሚጠብቃቸው እያወቁ ተጋፍጠው ለስደት የመነሳታቸው መንስኤ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር የነፃነት እጦት ሲታከልበት የችግሩን መልክ ውስብስብ አድርጎታል፡፡

የንግዱን ማህበረሰብም ስንመለከት ከመቼውም በባሰ ሁኔታ ነጋዴ መሆን ወንጀለኛ መሆን የሚል ትርጉም ይዟል፡፡ በተጨማሪም አንድ ፓርቲ ነጋዴና አንድ ፓርቲ ህግ አውጭ በሆነበት ሁኔታ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ስለዚህ የግሉ ሴክተር የልማት ሚና አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ካላግባብና በግምት የሚጣል ታክስ መክፈል ሃገራዊ ግዴታ የመሆኑን ለዛ አሳጥተውታል፡፡ አንዳንዱ በብልጣብልጥነት ስርዓቱን እንደመታወቂያና ከለላ በመጠቀም፣ ከባለስልጣናት ጋር በመሻረክ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሀብት ማማ ላይ ሲወጣ እንመለከታለን፡፡ ይሄም በንፁህ ንግድ ላይ ያልተመሰረቱ ለበርካታ ዜጎች አደጋ ነው፡፡ ከዚያም ልቆ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሃዊ የንግድ አሰራር እንዲኖር እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ማስገንዘብ የምወደው በሀገራችን የስልጣን ሽግግር ታሪክ እንዱ እንዱን በአፈሙዝ እየገደለ፣ መንድም ወንደሙን ጠላት እያደረገ ነው፡፡ ይህም የርስ በርስ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ትውልድ ብቻ ሁለት አብዮቶች ተካሂደዋል፡፡ በአገራችንንና በትውልዱ ላይም በገንዘብ የማይተመን ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ዛሬም በተለይም ወጣቱ ትውልድና ዋጋ የከፈሉ አባቶች ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ምኞታችን ከፍተኛ ቢሆንም ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ እየዘጋው ያለው ዴሞክራሲያዊ መንገድና ዜጎች እየደረሰባቸው ካለው ስቃይ አንፃር ወደ ሕዝባዊ አመፅ ተቀይሮ ወደ ሶስተኛው አብዮት ቢገፋ ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክትም ምንም እንኳ የወረሳችሁድ ዕዳ ብዙ ቢሆንም በቁርጠኝነት ታግላችሁ ሀገራችንን እንደሰለጠኑት ሀገሮች እንደምታደርጉ ተስፋ አለኝ፡፡ ከ50 ዓመት በላይ ዋጋ የተከፈለበት ዴሞክራሲ እውን እንድታደርጉ አደራ እያልኩ እንደምታሳኩትም ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

አንድነት ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በስኬት ተጠናቀቀ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የ3 ወር ህዝባዊ ንቅናቄ ፍፃሜ በአዲስ አበባ ዛሬ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠናቀቀ፡፡ ፓርቲው ከሰኔ ወር ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ መካከል  በደሴ፣ በጎንደር፣ በአርባምንጭ፣ በጂንካ፣ በባህርዳር፣ በአዳማ(ናዝሬት)፣ በባሌ ሮቤ፣ በፊቼ እና በመቀሌ ከተሞች የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራ ቢሆንም በባሌ ሮቤና በመቀሌ ከተማ በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሲሰናከል ቀሪዎቹ በሙሉ በስኬት መጠናቀቃቸው ይታወቃል፡፡udj1 UDJ2 udj3

የመርሃ ግብሩን ፍፃሜ መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ቢደረግም የከተማው መስተዳደር በበኩሉ የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ሰልፉ ወደ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲዛወርለት በጠየቀውና እውቅና በሰጠው መሰረት ባለፈው ሳምንት ቅስቀሳ እየተካሄደ ነበር፡፡ በቅስቀሳው ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፣ በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካይና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ ስራ አስፈፃማና አባላት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ለ3 ተከታታይ ቀናት በፖሊ መታገታቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው ከ33 ቱ ፓርቲዎች ጥምረት ጋር በጋራ በመሆን የዛሬውን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰለፍ ሲያስተባብር ቢቆይም የሰልፉ መዳረሻ ቦታን ግን መስተዳደሩ ከፓርቲው ፍላጎትና ያቄ ውጭ በጃንሜዳ እንዲደረግ ቢወስንም ፓርቲው መስቀል አደባባይ ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ ቅስቀሳው ተካሂዷል፡፡

ፓርቲው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን ከፓርቲው ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ቀበና መድኃኔዓለም ፊት ለፊት ከሚገኘው ዋና ፅህፈት ቤት በመጀመር ወደመስቀል አደባባይ ሊያመራ ሲል በ4 ኪሎ መስቀል አደባባይ ወደሚያመራው በሙሉ በበርካታ ፖሊሶችና በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ሊገታ ችሏል፡፡ በመጨረሻም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣አባላትና ደጋፊዎች እስከ 4፡50 ሰዓት ድረስ ባሉበት ቦታ ከከተማ መስተዳደሩና ደብዳቤ ከተፃፈላቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ምላሽ አልተገኘም፡፡ የዝግጅት ክፍሉም የእገታውን ምክንያት ለማጣራት የከተማው ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣ ምክትላቸው አቶ አባተ ስጦታው፣ የመንግስት ኮሞኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር ተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን በመዝጋታቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

ይሁን እንጂ የአቶ ሬድዋን ምክትል ወደሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ጋር ብንደውልም ስልካቸውን በተደጋጋሚ ሊያነሱልን አልቻሉም፡፡ የፖሊስ ኃላፊዎች በበኩላቸው እገታ እንዲያደርጉ ትዕዘዝ ከመቀበል ውጭ እኛም ምክንያቱን አናውቅም የሚል ምላሽ የሰጡ እንዳሉ ሁሉ ምክንያቱን ሲጠየቁ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑም አልታጡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም መስቀል አደባባይ፣ ሜክሲኮ፣ አስኮ፣ ፒያሳ፣ሳሪስ፣መርካቶ፣ኮተቤና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ሰልፉ ወደዳለበት ቀበና እንዳይሄዱ ፌደራል ፖሎስን ጨምሮ በአዲስ አበባ ፖሊሶች መታገቱን ለማየት ችለናል፡፡ በሰልፉ ላይ ከተሰሙ መፈክሮች መካከል እነ አንዱዓለም አራጌ፣አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ከሚቴዎች እነ አቡበከር የነፃነትና የመብት ጠያቂዎች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም፣ የፀረ-ሽብር ህጉ የህገመንግስት ጥሰት ነው፣ ለኑሮ ውድነቱ መንግስት ተጠያቂ ነው፣ህገመንግስቱ ይከበር፣ ውሸት ሰልችቶናል፣ለአምባገነኖች አንበረከክም የሚሉ ይገኙበታል፡፡

በመጨረሻም ሰላማዊ ሰልፉ ቀበና አደባባይ አካባቢ ወደ መገናኛም እንዳይሄድ ከፊትና ከኋላ በፖሊስ እገታ በመፈፀሙ የመርሃ ግብሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ትዕግስቱ አወሉ፣ የ33ቱ ፓርቲዎች ተወካይ አቶ ግርማ በቀለ እንዲሁም የአቶ አንዱዓለም አራጌ ፣ የአቶ በቀለ ገርባ እና የሌሎች የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ከቃሊቲና ከዝዋይ እስር ቤቶች የተላከ ደብዳቤ ከተነበበ በኋላ ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ላይ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በተገኙበት ሰልፉ በታገተበት ቀበና አደባባይ ፊትለፊት በስኬት ተጠናቋል፡፡

%d bloggers like this: