በእስር ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተፈቱ
ዛሬ መስከረም 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲሁም በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የታሰሩት 26 የአንድነት አባላት ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ተፈተዋል፡፡ በፖሊስ ተይዘው ወደጣቢያ የተወሰዱት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን በእጩነት የቀረቡትና የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ተክሌ በቀለ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ሌሎች አመራሮችም ነበሩበት፡፡
አመራሮቹ የፊታችን እሁድ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊትለፊት ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አንድነት ፓርቲ ከ33 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለጠሩት የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በተለይ በአራዳ ክፍለ ከተማ በቅስቀሳ ላይ እያሉ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ቢሰጥም የከተማው ፖሊስ ለቅስቀሳ የሚሰማሩ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችን በተደጋጋሚ ያለምንም በቂ ምክንያትና ክስ እያሰረ መፍታቱ አዲስ አይደለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አመራሮቹንና አባላቱን ለምን እና በምን የህግ አግባብ ለሰዓታት እንዳሰረ ብንጠይቅም ታዘንነው ከማለት ውጭ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
Dr. Negaso Gidada and Ato Girma Seifu have been Deatained
The former Ethiopian President and the current Unity for Democracy and Justice (UDJ) party chairman Dr. Negaso Gidada and the only opposition party member of Ethiopian Parliament and vice chairman of UDJ Ato Girma Seifu, other UDJ Executives’ Ato Asrat Tassie, Ato Teklie Bekele, Ato Seyoum Menegesha, Ato Shemeles Habtie, Ato Daniel Tefera and other 19 the party members have been detained today September 27, 2013 afternoon in Addis Ababa Arada Sub city Police Station.
The party has been in a peaceful struggle campaign, “Millions of Voices for Freedom” since 3 months ago. On the coming Sunday September 29, 2013, morning the campaign is expected to be completed with Protesting public demonstration at Addis Ababa “Mesekel” Square. The Addis Ababa City administration recognized the coming Sunday UDJ party announcement of protesting public demonstration. Now after 3:45 hours jailed all they are released from police station.
የመንዝ ወረዳ ፖሊስ የአንድነት አባላትን አሰረ
በአማራ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አቶ ካሳዬ ዳኜን እና ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ደግሞ አቶ አዲሱ ተመሰለው የተባሉ የአንድነት ለዴሞክራደሲና ለፍትህ (አንድነት) የወረዳው አመራሮች በወረዳው ፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ምንጮቻችን በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ የታሰሩት የአንድነት ፓርቲ አባላት በወረዳው መሐል ሜዳ ከተማ በሚገኘው የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡
በጣቢያው አዛዥ የሆኑት ኢንስፔክተር ጥላሁን ወደስራ ሲሄዱ የተያዙትን ወጣቶች በቢሮአቸው ጠርተው መንግስትን እንለውጣለን ብላችሁ ህዝቡን እያስፈራራችሁ ነው የሚል ውንጀላ ሲያቀርቡባቸው ወጣቶቹ እኛ በሰላማዊ ትግል አስከፊውን የኢህአዴግን ስርዓት በህጋዊ መንገድ ለመቀየር የምንታገል የአንድነት ፓርቲ እንጂ ወንጀለኞች አይደለንም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ታሳሪዎቹ አዎ አባሎቻችንን በወረዳው በህጋዊ መንገድ እያደራጀን ነው ፤ይሄም መብታችን ስለሆነ በግልፅ ነው የምንሰራው እንጂ በድብቅ አይደለም፣ ከዚህ ውጭ ወንጀል ሰርታችኋል የሚል አካል ካለ ክስ ሊመሰርትብንና ሰርታችኋል የሚባል ወንጀልም ካለ በማስረጃ በማቅረብ ወደ ፍርድ ቤት ልትወስዱን ትችላላችሁ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ በመጨረሻም ለአንድ ቀን ካሰሯቸው በኋላ ፖሊስ ጣቢያው ምንም ምክንያት ሳይሰጥና ክስ ሳይመሰርት ለቋቸዋል፡፡
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጥላሁንን በጉዳዩ ዙሪያ ጠይቀናቸው ወጣቶቹ የታሰሩት ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው፣ የታሰሩትም እርስ በርስ በተፈጠረ ጠብ በመሆኑ ለቀናቸዋል፤ ከዛ ውጭ ምንም ዓይነት መረጃ ልሰጥ አልችልም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወጣቶቹ በበኩላቸው ወደስራ ስንሄድ ያዙን እንጂ እኛ ከማንም አልተጣላንም፤ እኛን ሲይዙ የነገሩን ምንግስትን እንቀይራለን ብላችሁ አስፈራራታችኋል ችንጂ ከግለሰብ ጋር ተጣልታችኋል በሚል አይደለም፤ ይሄ ሐሰት ነው፣ ተጣልተዋል የተባሉትንም ግለሰብ ማቅረብ ይችላሉ ሲሉ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡
ለሰዓታት ታስረው የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተፈቱ
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሽሮ ሜዳ ፖሊስ ማዘዣ እና የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ለሰዓታት ከታሰሩ በኋላ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ መፈታታቸው ታውቋል፡፡ ስለ ፖሊስ ጣቢያው የሰዓታት ቆይታ ሲጠየቁ፤ ዶ/ር ነጋሶ ተደንቀው “ክስ ስላልመሰረቱ ታስሬያለሁ ለማለት እቸገራለሁ፤ ግን አስገራሚ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከቅስቀሳ ስራ ላይ በቄራ አካባቢ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው ወጣቶች ግን እስካሁን ስለመፈታታቸው የታወቀ ነገር የለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለመስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.መ. አንድነት ለጠራው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ፖሊስ የፓርቲው አባላት ሲቀሰቅሱ ለምን እንደሚያስር ምላሽ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሻቸውን ለማግኘት አልቻልንም፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ታሰሩ
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ታሰሩ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የታሰሩት ዛሬ መስከረም 15 ቀን 2006ዓ.ም. አንድነት ፓርቲ አባላት በጉለሌ ክፍለ ከተማ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለተጠራው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በሽሬ ሜዳ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ሳሉ መታሰራቸውን ተከትሎ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ያዘዝኩት እኔ ስለሆንኩ ልጆቹን ልቀቁ፤ ከፈለጋችሁ እኔን ማሰር ትችላላችሁ በማለታቸው የጣቢያው ፖሊሶችme ዶ/ሩ ነጋሶን ማሰራቸው ተረጋግጣል፡፡
በአሁን ሰዓት የማዘዣው ፖሊሶች ዶ/ር ናጋሶን ከያዙበት ሽሬሜዳ ወደ ጉለሌ ፖሊስ መምሪያ በፖሊስ መኪና እና በበርካታ ፖሊሶች ታጅበው ተወስደዋል፡፡ እስካሁንም ዶ/ሩ ነጋሶን በፖሊስ መመሪያው የማዘዣው ፖሊሶች ከማድረስ ውጭ ያነጋገራቸው ፖሊስ የለም፡፡ በቅስቀሳ ላይ እያሉ የታሰሩትና ዶ/ር ነጋሶ ሊያስፈቱ ሄደው በምትካቸው በመታሰራቸው የተለቀቁት የአንድነት ፓርቲ አባላትም ቅስቀሳቸውን የቀጠሉ ሲሆን ሌሎች አባላትም እሁድ መስከረም 19 ቀን 2006ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘግይቶ በደረሰን የተያያዘ ዜና በዚሁ በአዲስ አበባ በቅስቀሳ ላይ ያሉት የአንድነት አባላት 16 አባላት ታስረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይም ሌሎች የአንድነት ፓርቲ ከፍተኘኛ ስራ አስፈፃሚ አመራሮች የታሰሩ አባላቱን ለማስፈታት ወደየ አካባቢው አቅንቷል፡፡