Daily Archives: June 13th, 2015

አቶ ዳዊት አስራዳ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ ከፍሎ ታሰረ

ከግራ ወደቀኝ ዳዊት አስራደ እና አለነ ማፀንቱ

ከግራ ወደቀኝ ዳዊት አስራደ እና አለነ ማፀንቱ

የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳዊት አስራደ ትናንት ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በ5,000 ብር ዋስ እንዲፈታ ዋስትና የተፈቀደለት ቢሆንም ገንዘቡን ካስያዘ በኋላ ዋስትናው እንደተነሳ ተነግሮት በእስር ላይ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ በትናንትናው ችሎት ፖሊስ ተከሳሾቹ ምስክሮችን ያባብሉብኛል በሚል ምስክሮችና መረጃዎችን አሰባስቦ እስኪያቀርብ ጊዜ ድረስ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቆ የነበር ቢሆንም አቶ ዳዊት አስራደ፣ ሌላው የቀድሞው አንድነት ስራ አስፈፃሚ አባል እና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማፀንቱና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ የ5,000 ብር ደሞዝ ያለው የሰው ዋስ ወይንም ገንዘብ አስይዘው ከእስር እንዲወጡ ፈቅዶ ነበር፡፡
ይሁንና የአቶ ዳዊት አስራደ ቤተሰቦች መፍቻ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ሲሄዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ፖሊስ አቶ ዳዊትን ለቄራ ፖሊስ ጣቢያ ማስረከቡን እንደገለጸላቸው ጠበቃው አቶ ገበየሁ ይርዳው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የቄራ ፖሊስ ጣቢያም ከአሁን ቀደም አቶ ዳዊት አስራደ በተመሳሳይ ክስ ተፈቅዶለት የነበረውን ዋስትና ማንሳቱን በመግለጽ እንዳሰረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በተፈቀደለት ዋስትና መሰረት 5000 ብር ያስያዘውን አቶ አለነ ማህፀንቱን ፖሊስ መጀመሪያ ወደ ማታ እፈታዋለሁ፣ እንዲሁም ከቆይታ በኋላ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሎ እስር ላይ ቢያቆየውም አሁንም ድረስ ይግባኝ ሳይጠይቅ በእስር ላይ እንደሚገኝ ጠበቃው ገልፀዋል፡፡
መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰረው አቶ ዳዊት አስራዳ በተመሳሳይ ክስ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ እያስያዘ እንደገና በእስር ላይ የቆየ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ 25 ሺህ፣ በቀጣይነትም 6 ሺህ፣ እንዲሁም ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌላ 5 ሺህ ብር በአጠቃላይ 36 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ እንደገና ታስሯል፡፡ አቶ ዳዊት አስራደና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ ሚያዝያ 14 መንግስት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ሰበብ በአንድ ጉዳይ ሁለት ክስ ተመስርቶባቸው በሁለት ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ በቄራና ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያም በፈረቃ ሲታሰሩ መቆየታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በሽብር የተከሰሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ የአቃቤ-ህግ ምስክሮች መሰማት ተጀመረ

᎐መገናኛ ብዙኃን የምስክሮችን ቃል መዘገብ አይችልም ተብሏ

prisoners

በሽብርተኝነት ተከሰው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች መሰማት ተጀመረ፡፡ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተካተቱት አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ አሉኝ ያላቸውን የሰው ማስረጃዎች ምስክርነት ዛሬ ሰኔ 01 ቀን 2007 ዓ.ም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ማሰማት ጀምሯል፡፡
ምስክሮች መሰማት ከመጀመራቸው በፊት አከራካሪው ጉዳይ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት ይሰሙ ወይስ በዝግ ችሎት የሚለው ነበር፡፡ በዚህም አቃቤ ህግ የጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 32 ላይ የተመለከተውን የምስክሮች ጥበቃ ድንጋጌ በመጥቀስና ምስክሮቹ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው በማውሳት ችሎቱ ምስክሮችን በዝግ እንዲሰማ ጠይቋል፡፡ ተከሳሾች በበኩላቸው ህገ መንግስቱን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት በማስረጃ ያልተደገፈ ስለሆነ ችሎቱ ግልጽ እንዲሆን ተከራክረዋል፡፡
ሶስተኛ ተከሳሺ አቶ ዳንኤል ሽበሺ “አቃቤ ህግ እስከ ሞት በሚያደርስ ወንጀል ከሶናል፤ ይህን ጉዳይ በግልጽ መከታተል አለብን፡፡ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብም መፍረድ አለበት” በማለት ችሎቱ ምስክሮችን በግልጽ እንዲሰማ አሳስቧል፡፡ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ “እኛ ዋስትና ተከልክለን በእስር ቤት ነን፤ የምስክሮች ስም ዝርዝር እንኳ አልተገለጸልንም፡፡ ታዲያ ማን ነው ምስክሮች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚያደርስባቸው?” ሲል አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት ችሎቱ ግልጽ እንዲሆን ጠይቋል፡፡
አቶ ሀብታሙ ሁሉንም ተከሳሾች በመወከል እንዳስረዳው ደግሞ ፍርድ ቤቱ ምስክሮችን በዝግ የሚሰማ ከሆነ ሁሉም የግፍ ፍርደኛ ሆነው ወደ እስር ቤት ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ “ሁሉንም ወክየ ነው የምናገረው…በዝግ ችሎት ምስክሮችን የምትሰሙ ከሆነ ዛሬውኑ የግፍ ፍርደኞች ሆነን ወደ እስር ቤት ለመመለስ ዝግጁዎች ነን፤ ከዚህ በኋላም አንዳችንም ክርክር አናደርግም፡፡”
ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግና በተከሳሾች መካከል የተነሳውን ክርክር መርምሮ ብይን የሰጠ ሲሆን በብይኑ መሰረትም የአቃቤ ህግ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ወስኗል፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ የህትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የምስክሮችን ቃል ዝርዝር በተመለከተ መዘገብ እንደማይችሉ በብይኑ ላይ አመልክቷል፡፡
ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. መሰማት የጀመረው የአቃቤ ህግ ምስክሮች እስከ ሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.እንደሚቀጥል ቀጠሮ ተይዞ እንደነበርም ታውቋል፡፡
በዚሁ መዝገብ ተከሳሾች መካከል አምስተኛ ተከሳሽ የሆነው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ ዳኞቹ ሲሰየሙና ስሙ ሲጠራ ከመቀመጫው ባለመነሳት በችሎቱ ላይ ተቃውሞውን ገልጹዋል፡፡ አቶ የሺዋስ ዳኞቹ ለምን እንደማይነሳ ሲጠይቁት በዝምታ ያለፋቸው ሲሆን፣ ተነስ ሲባልም ያለምንም ንግግር በተቀመጠበት ተረጋግቶ እንደነበር ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

%d bloggers like this: