ሚኒስትሩ ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ በተናገሩት ላይ ጥርጣሬ አለኝ!
ብስራት ወልደሚካኤል
ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት የአማርኛው ፕሮግራም ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ በተናገሩት ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ጥርጣሬም የመኘጨው ከኢህአዴግ ባህርይ እና ሴራ በመነሳት ሲሆን፤ይህም አስቂኝ እና ምናልባትም እጅግ አጠራጣሪ እና ሊሆን የማይችል ንግግር ሚኒስትሩ በመናገራቸው ነው፡፡ ጥርጣሬየንም እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
1ኛ. የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ሰኔ 2006 ዓ.ም. በየመን የፀጥታ ኃይሎች ትብብር ታፍነው ለህወሓት መንግሥት ተላልፈው ከተሰጡ ጀምሮ በኢትዮጵያ እስር ቤት ከመገኘታቸው ውጭ የት እንደታሰሩ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ….እንዳይታወቅና ማንም ቤተሰብ እንዳይጎበኛቸው ተደርጓል፡፡ በብዙ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ አምባሳደር ግሪጎሪ ዶሪ ብቻ ሁለት ጊዜ እንደጎበኟቸው ይታወቃል፡፡ ይሄንንም በተመለከተ አምባሳደሩ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ደህንነት ሁኔታ ስጋት እንዳደረባቸው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ነገር ግን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቤተሰብም፣ በወዳጅ ዘመድም ሆነ በኃይማኖት አባት እንዳይጎበኙ የተከለከሉትን እና እስካሁንም የትኛው ወህኒ ቤት እንዳሉ ያልታወቁትን አቶ አንዳርጋቸውን የሀገሪቱን ልማት በተለይም ከአዲስ አበባ አዳማ ያለውን እንዲጎበኙ ተደርገው መደነቃቸውን እንዲሁም በሚሰቃዩበት ወህኒ ቤት ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተር ተፈቅዶላቸው መፅሐፍ እየፃፉ ወደ መጨረሱ እንደደረሱ ነግረውናል፡፡ ዘይገርም ነው፡፡ ቢሆን ደስ ይላል፤ ግን ሊሆን የማይችልና የማይታመን ነው፡፡
ከህወሓት/ኢህአዴግ ባህርይ አንፃር በቤተሰብ ያውም በወላጆቻቸውና በእህቶቻቸው እና ወንድሞቻቸው እንኳ እንዲጎበኙ ያልተፈቀደላቸው ግለሰብ፤ ላፕ ቶፕ እንዲገባላቸውና መፅሐፍ እንዲፅፉ ሊፈቀድ አይችልም፡፡ ይህ የሚሆን ከሆነ ለምን እነ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ (ወህኒ ቤት ሳሉ)፣….ወዘተ በእጅ ፅሑፍ እንኳ የፃፉት ተራ ማስታወሻ እንኳ በየጊዜው እየተበረበረ ሲወሰድ እና ድጋሚም ምንም ዓይነት ነገር እንዳይፅፉ፤ እንደውም ለረጅም ጊዜ ማንኛውም መፅሐፍ እንኳ እንዳይገባላቸው ይከለከሉ እንደነበር እናውቃለን፡፡ በአሁን ሰዓት ራሱ በተለያዩ የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች እንኳን ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተር ሊፈቀድ ይቅርና ሊያነቡት የጠየቁት መፅሐፍ እንኳ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የዕውቀትና አስተሳሰብ ደረጃ ተመዝኖ ካልተፈቀደ እንደማይቻል ይታወቃል፡፡
ታዲያ ለአቶ አንዳርጋቸው ምን ያህል ቢራሩ ነው ላፕ ቶፕ የፈቀዱት? እውነት ከራሩ ለምን በቤተሰብና በአድናቂዎቻቸው እንዲጎበኙ አልተፈቀደም; ከዶ/ሩ እና አመራሮቻቸው መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ቀላል ጥያቄ የVOA ጋዜጠኛዋ ለሚኒስትሩ ሳታቀርብ እንዴት እንዳለፈችው ገርሞኛል፤ ደንቆኛልም፡፡ ምናልባት የትናንቱ ላይ ተንተርሳ ድጋሚ ተዘጋጅታበት ልታነሳው ካሰበችም እንጠብቃለን፡፡
2ኛ. ከህወሓት/ኢህአዴግ ልምድና ባህርይ አንፃር ሌለው አስገራሚ ነገር፤ አቶ አንዳርጋቸው እየፃፉ ነው የተባለው መፅሐፍ በማን አማካኝነት ከወህኒ ቤት ወጥቶ ለንባብ ሊበቃ ነው? ይሄ ደግሞ ሌላ መልዕክት አለው፡፡
ከዚህ በፊት በስልጣን የቁም እስረኛ የሆኑት ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ ሳይወዱ በግድ ስማቸውን በማዋስ በስማቸው መፅሐፍ መፃፉን ስንቶቻችን እንደምናውቅ አላውቅም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ለህወሓት በተለይም ለራሳቸው የስልጣን መደላደል ይሆን ዘንድራሳቸው በመሰላቸውና በሚፈልጉት መንገድ ስለ ኦሮሞ ትግል መፅሐፍ ፃፉ፡፡ ከዚያም በህወሓት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ መሰረት አቶ አባዱላ ገመዳ ፈቃዳቸው ሳይጠየቅና የመፅሐፉን ረቂቅ ሳያዩት በስማቸው ለገበያ እንዲበቃ ተደርጎ ራሳቸውም ከአንባቢው እኩል አነበቡት፡፡ በስልጣን የቁም እስረኛም ስለሆኑ ቅሬታም ሆነ አስተያየት መስጠት አልቻሉም፤ በመለስ ዜናዊ ተፅፎ በአባዱላ ገመዳ ስም ግን ገበያ ላይ ውሎ ተነቧል፡፡
አሁን ደግሞ ምንም ዓይነት አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ነፃነት እንዳይኖራቸው በማይታወቅ ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስም፤ አቶ በረከት ስምዖን እና ሌሎች ተባባሪዎቻቸው በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ስም መፅሐፍ ለንባብ ሊያበቁ እያዘጋጁ መሆኑን ሚኒስትሩ አምልጧቸው የነገሩን ይመስለኛል፡፡ የመፅሐፉም ይዘት የኢህአዴግን “ልማት በማድነቅ” ፣ የተቃዋሚዎችን ስህተት፣ በተለይ የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉትን እነ አርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ትህዴን፣ አዴኃን፣ ኦብነግ፣ሲአግ፣አርዱፍ፣ … ወዘተ ድርጅቶችን በማብጠልጠል ላይ ተንተርሶ፤ አቶ አንዳርጋቸው ራሳቸውን ተሳስተው እንደነበርና በመፅሐፉ ይቅርታ ጠየቁ የሚል አዝማሚያ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህም የተወሰነ የፖለቲካ ድል ለማግኘትና ተቃዋሚዎችንም ለመምታት እንደ አንድ መንገድም ሊጠቀሙበት ያሰቡም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ጨወታው የዓለም አቀፉን በተለይም የአውሮፕንና የእንግሊዝን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማርገብና ኢትዮያውያንን ለማታለል የታሰበ እንጂ፤ አካላዊና አዕምሯዊ ነፃነት ተነፍገው ባሉበት ሁኔታ አቶ አንዳጋቸው መፅሐፍ ይፅፋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
እውነት ህወሓት/ኢህአዴግ ርህራሄ ተሰምቶት አቶ አንዳርጋቸውንም ሆነ አሁንም በጅምላ እየታሰሩ ያሉትንና የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞች ለምን በነፃ አያሰናብትም?
በተለይ ለአቶ አንዳርጋቸው ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ተፈቅዶላቸው መፅሐፍ እየፃፉ ወደማገባደዱ ላይ ናቸው ሲሉ ሚኒስትሩ አይደለም አቶ አንዳርጋቸው አንድ ተራ ደራሲም ሆነ ፀሐፊ በግፍ ላሰረውና እያሰቃየው ላለ ዘረኛ፣ ጨካኝና አረመኔ አገዛዝ በምን ሂሳብ፣ በምን የዋህነት ነው መፅሐፍ ፅፈው እየጨረሱ መሆናቸውን ሚናገሩት? ሌላው ቀርቶ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሩ የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ባለቤትና የአቶ አንዳጋቸው ጽጌ እህት ወ/ሮ አይኔ ጽጌ እንኳ እንዲገበኟቸው ባልተፈቀደበት፣ አዲስ አበባ ከሞላ ቤተሰብና ወዳጆቻቸው እንኳ አንድ ሰው እንዲገበኝ ባልተፈቀደበት፤ ላፕቶፕ ተፈቅዶ መፅሐፍ እየፃፉ ነው መባሉ፤ አቶ አንዳርጋቸው ላይ ሌላ ሴራ እየተሰራ ነው ወይም ተሰርቶ አልቆ አደባባይ ሊያበቁት ተዘጋጅተዋል ማለት ነው፡፡
3ኛው ጥርጣሬ፤ አይበለውና* በአሁን ሰዓት ኢህአዴግ አቶ አንዳርጋቸው ላይ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ምርመራ በሚያደርግበት ወቅትም ይሁን ሆን ብለው ህይወታቸው ላይ ከባድ አደጋ አድርሰው በስማቸው እጅግ የረከሰና ለኢህአዴግ አመራሮች የሚመጥን አስተሳሰብ ለገበያ ካቀረቡ በኋላ፤ አቶ አንዳርጋቸው በህመም ምክንያት አሊያም ራሳቸው ላይ በወሰዱት ርምጃ እንደተጎዱ ተደርጎ ድራማ ሊሰራ አሊያም ተሰርቶ አልቆም ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት እንደ ሟርት ሊቆጠር አይችልም፡፡ ምክንያቱም አቶ አንዳርጋቸውን ለመግደል አስመራ ድረስ ትልቅ ተልዕኮ ተሰንቆ መክሸፉ የአደባባይ ምስጢር በሆነበት እና እጅግ ለሚፈሩትና አጥብቀው ለሚፈልጉት አንዳርጋቸው እውነትም ራርተው ከሆነ ይልቀቋቸውና ርህራሄያቸውን እንመን፡፡ ካልሆነም ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም አድናቂዎቻቸው እንዲጎበኗቸው በይፋ ይፍቀዱና እንያቸው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ላፕ ቶፕ ገብቶላቸው መፅሐፍ እየፃፉ ነው፣ ሊጨርሱ ነው…ማለት ከኋላው የተሰራና የተጠናቀቀ አሊያም ሊሰራ የታሰብ ሴራ መኖሩን ከማረጋገጥ ውጭ እውነት ነው ብሎ መቀበል በ24 ዓመታት ውስጥ ኢህአዴግን ካለማወቅ በሚመነጭ የዋህነት ካልሆነ መረጃውን ትክክል ነው ማለት ሞኝነት ይመስለኛል፡፡
በአጠቃላይ ጥርጣሬዬ ህወሓት/ኢህአዴግ እንደለመደው ስንኩል ፖለቲካዊ ሴራ ድራማውን ለማጠናቀር ይረዳው ዘንድ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስም መፅሐፍ እያዘጋጀ መሆኑን አሊያም አዘጋጅቶ መጨረሱን በጓዳ ርስ በርስ ሹክ የተባባሉትን አምልጧቸው እንደተናገሩት እቆጥረዋለሁ፡፡ ቢቻል በአሁን ወቅት የእንግሊዝ መንግሥት ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ሄዶ ማረጋገጥ እንዳለበትም መጠቆሙ የሚከፋ አይመስለኝም፡፡
ሌላው ሚኒስትሩ ጥሩ ናቸው በሚል ባይሆንም ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በተናገሩት “መረጃ” ዙሪያ ማመስገኑ የሚከፋ አይመስለኝም፡፡ ለነገ የሚሆን መረጃ ጀባ ብለውናል ብዬ ስለማምን፡፡
በተረፈ አቶ አንዳርጋቸው ባሉበት ፈጣሪ ጠብቆ በሙሉ ጤንናትና ሰላም እናያቸው ዘንድ ተመኘሁ፡፡
የእስረኛው ማስታወሻ፤ በኢትዮጵያ እውነትና ፍትህ ከትቢያ የተሻለ ቦታ ቢኖራቸው ኖሮ…
ውድ ኢትዮጵያውን፡-
ሕዝብ የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነበት ሃገር ፍትህ ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ትቀመጣለች፡፡ እውነትም ምሰሶና ወጋግራ ሆና ፍትህን ዘወትር የመደገፍ እድሏን ትጎናጸፋለች፡፡ በኢትዮጵያ የፍትህና የእውነትን የክብር ቦታና ሚና አፈ-ሙዝ ወስዶታል፡፡ ፍትህና እውነት ደግሞ ትቢያ ላይ ተጥለዋል – ምንም እንኳ እንደወደቁ ባይኖሩም፡፡
በኢትዮጵያ ፍትህና እውነት ትቢያ ላይ ባይጣሉ ኖሮ ለዓመታት ይቅርና ለሰዓታት እንኳን በእስር ቤት ግርጌ መጣል ባላስፈለገንም ነበር፡፡ ፍትህና እውነት በኢትዮጵያ አድራሻ ቢኖራቸው ኖሮ ለዚህ ዓለም እንግዳ የሆኑት ልጆቼ ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን የአባታቸውን ፍቅር በግፍ ባልተነጠቁ ነበር፡፡ ፍትህና እውነት የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን ብትሆን ኖሮ ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን ባለቤቴ ከእኔ ጋር የመኖር ሰብዓዊ መብቷን ተገፋ በወጣትነት እድሜዋ የመበለትነት ህይወት የመግፋት እዳ ባልወደቀባት ነበር፡፡ ፍትህና እውነት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንኳን መንሳፈፍ ቢችሉ ኖሮ በሃሰት ዶሴ ከታሰርኩ በኋላም ለዓመታት በእስር ቤት ውስጥ ተጨማሪ የግፍ ፅዋ እንድንጎነጭ ግድ ባልሆነብኝም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እውነትና ፍትህ ከትቢያ የተሻለ ቦታ ቢኖራቸው ኖሮ ረጅም ርቀት አቆራርጠው ሊተይቁኝ የሚመጡ ጠያቂዎቼ የመጠየቅ መብታቸውን ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን ባልተነፈጉም ነበር፡፡
በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊቷ ኢትዮጵያ እኔና ቤተሰቤ ፍፁም ኢሰብዓዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተላምደን፤ በሞትና በህይወት መካከል ያለው ልዩነት እስኪጠፋን ድረስ በአባቶቻችን፣ በራሳችንና በልጆቻችን ሃገር፤ በህዝባችን ፊት በማናለብኝነት ጥቂት አፄዎች ጢባጢቢ እንዲጫወቱብን ተበይኖብናል፡፡ በውል የማውቀውን የራሴን ጉዳይ በዋናነት ባነሳም የእኔና የቤተሰቦቼ ህይወት የእነ እስክንድር ነጋንና ሌሎች አንባቢ ፈፅሞ የማይዘነጋቸው ኢትዮጵያውያንና ቤተሰቦቻቸውም ፅዋ መሆኑን ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም፡፡ በየትም ቢሆን አንድ ዜጋ የግፍ ፅዋ እንዲጎነጭ ሲገደድ የሚጠጣው የኢ-ፍትሃዊነት ስቃይ ጥልቅ ነው፡፡ በተለይ ግን በሚወደው ህዝቡ ፊትና የእኔ ብሎ በሚኮራበት ሃገሩ እንደርሱ ደምና ስጋ የለበሱ ጥቂቶች ያሻቸውን ሲፈፅሙበት የግፉ ስቃይ ከመቼውም በላይ ይከፋል፡፡ ይህንን ከመሰለው የኢፍትሃዊነት ስቃይ ለአፍታም ቢሆን የሚያሳርፋቸው ግን አንድ ነገር አለ፡፡ አንባቢ የማይዘነጋቸው ወይዘሮ ሮዛ ፓርክስ መቀመጫቸውን ለቀው የኋላ ወንበር ላይ እንዲቀመጡ አሊያም ከአውቶብስ እንዲወርዱ ሲጠየቁ በእግራቸው መሄድን መምረጣቸው ብቻ ሳይሆን ለምርጫቸው የሰጡት አመክንዮ ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡ ‹‹በእግርሽ ይሄንን ያህል ማይል መጓዝ ይሻላልን›› ለሚለው ጥያቄ ‹‹እግሮቼ ይደክማሉ ነፍሴ ግን ታርፋለች›!›› ብለው ነበር፡፡
እኔም በምወዳት ሃገሬ በህዝቤ ፊት ከእነቤተሰቤ የግፍ ሰለባ ብሆንም ህሊናዬን የሚጎረብጠኝ ነገር ባለመኖሩ የእኔም ነፍስ እረፍት አላጣችም፡፡ የሌሎች በግፍ የታሰሩ ጓደኞቼም ህሊናቸውው ፍፁም እረፍት የተጎናፀፈ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ትልቁ የህሊና እዳ በሃሰት ካሰሩኝ በኋላም በግፍ ተግባራቸው የሚመፃደቁት አሳሪዎቼ እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል የተገደደ እኔን የሚመስል ዜጋ ሞትንም እንኳን ቢሆን በክብርና በደስታ ለመጋፈት ይዘጋጃል እንጂ ህሊናውን ሰላም በሚያሳጣ ድር ተጠልፎ አይወድቅም፡፡
ውድ አንባቢ በእኔ ጫማ ውስጥ ቢቆሙ ከዚህ የተለየ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ በሃገርዎ፣ በህዝብዎ ከምንም በላይ በህልውናዎና በእጣዎ ላይ የግል አቋምዎን እንዳያራምዱ በሃሰት ዶሴ ተጠርቀው መቀመቅ ቢወርዱ ከዚህ የተለየ አቋም ሊኖርዎት ይችል ይሆን በሚያምኑበት ጉዳይ ተሸብበው የሚነገርዎትን ብቻ እንዲፈፅሙ ቢነገርዎት ይስማማሉን የመብቶቹ ባለቤት ላልሆነ ዜጋ ሰው መሆን ማለት ምን ትርጉም ይሰጣል ይኸ ሁሉ አንሶ በእሾህ በታጠረ የፖለቲካ ሰርጥ ውስጥ በተቦዳደሰ እግርዎ እያነከሱ እንዳይንከላወሱ እንኳን ‹‹እግር በመቁረጥ›› ፈሊጥ የተካኑ ገዥዎች እግርዎን ቢቆርጡት ምን አይነት ስሜት ይፈጥርብዎታል ጥቂት ዙፋን ላይ የተቀመጡ ባለጊዜዎች ምን ማሰብ እንዳለብዎ እንኳን ሳይቀር ሲወስኑልዎ እና ባጠቃላይ የርስዎ ህልውናና ተፈጥሮአዊ መብትዎችዎ በነሱ መዳፍ ስር ያሉ፤ ከፈለጉ ብቻ ቆንጥረው የሚሰትዎ ካላሻቸው የሚነፍጉት ሲሆን ምን አይነት ትርጉም ይሰጥዎት ይሆን
አዎ ሀገር በጭቆና ቀንበር ስር ስትወድቅ ድጋፍ ብቻ እንጅ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት ስርየት የሌለው ሃጢያት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ለገዥዎች በታጠረው አጥር ውስጥ በድፍረት ለማቋረጥ ሲሞክሩ ‹‹ቀዩን መስመር አልፈዋል›› በሚል አይቀጡ ቅጣት ይቀጣሉ፡፡ በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ግፎች እንደነውር ወይም ግፍ ሳይሆን አገዛዙን ለማስቀጠል የሚያስፈልጉ፤ ከትልቅ አዕምሮ የተቀዱ ልዩ የፖለቲካ ቀመሮች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
በአገዛዙና የግፍ ሰለባ በሆነ እኔን በመሰለ ዜጋ መካከል የሚደረገው ትግል ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ አገዛዙ እስረኛውን ለማምከን ሲተጋ እኔን የሚመስል እስረኛ በግርግም ውስጥም ሆኖ ደግሞ ህይወት በከንቱ እንዳይባክን ይታገላል፡፡ ለዚህም ነው አገዛዙ እስር ቤት ውስጥ እንኳን ከሌሎች አያሌ እስረኞች በተለየ ግፍ የሚፈፀምብኝ፡፡ እኔም እኔን የመስበር ተልኳቸው ገብቶኛልና ግብግቡን ለማሸነፍ ፍፁም በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኘ ለሀገሬ ይበጃል ያልኩትን ሀሳብ በሁለት መፅሐፎች ለማድረስ ሞክሬያለሁ፡፡ ከነጉድለቱም ቢሆን ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› ከብዙ ፈተና በኋላ ለአንባቢ ሲደርስ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡ አሁን ደግሞ የፈጣሪ ፀጋ በዝቶልኝ ታምር በሚመስል መልኩ ‹‹የሀገር ፍቅር ዕዳ›› የተሰኘውን ሁለተኛ መፅሐፌ ለአንባቢ በመድረሱ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በሀገር ፍቅር ዕዳ የግል ህይወቴን ጭምር ጨልፌ ለማካፈል ሞክሬያለሁ፡፡ የእኔ የዝቅታ ህይወት የሚሊዮኖችን ኢትዮጵያውያንን ህይወት እንደሚወክል በማመን፡፡ ምንም እንኳ የሚያስኮፍስ ያለፈ ታሪክ ባይኖረኝም ታሪክ የሚያኩራራው ብቻ አይደለምና ከተመላለስኩባቸው ውሃ አልባ ሸለቆዎች አንባቢዎች የሚቃርሟቸው ጥቂት ቁምነገሮች አይጠፉም፡፡ የህይወት ከፍታ ከሩቅ ስለሚታይ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ዝቅታን ለማሳየት ግን ጉልበት ይጠይቃልና ለማሳየት በመሞከሬም እንዲሁ ደስታ ይሰማኛል፡፡
በሀገር ፍቅር ዕዳ የእኔን ከፍና ዝቅ ህይወት ብቻ ሳይሆን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለኝን እይታ ያለምንም ማድበስበስ ለአንባቢ ለማካፈል ሞክሬያለሁ፡፡ ያልተሄደበት መንገድ ላይ በሩቁ የሰማኋቸውን አስተያየቶች በዚህኛው ለማረም ተፍገምግሜያለሁ፡፡ አንባቢ እንደሚረዳው መፅሐፌም እንደኔ ነፃነት የተነፈገ በመሆኑ እንደሌሎች መፅሐፍቶች ከመታተሙ በፊት በተለያዩ ሰዎች ተገምግሞ እንደገና አርሜው የመውጣት እድሉን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ግድፈቶች ካሉ አንዱ መንስኤ ይሄው ነው፡፡
ህይወቴ አንባቢን የሚስያተምሩ፣ ነገሮችን ከተለየ ማዕዘን ለማየት የሚረዱ፤ ከተቻለም ፈገግ የሚያሰኙ ነገሮች እንዲገኙበት ትልቅ ምኞት አለኝ፡፡ በህላዌ ዘመናችን ስንመላለስ የህይወትን ትርጉም ከሚሰጡ ምግባሮች መካከል አንዱን ለመከወን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ምን ያህል ተሳክቶልኝ ይሆን ይህንን ለናንተ ልተወው፡፡
ለዘመናት ልባችን በናፍቆት ለዛለላት የዴሞክራሲና የነፃነት ጀምበር የምትወጣበት ታላቅ የንጋ ቀን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀረበ መሆኑን በፍፁም በማመን፡፡
አንዱዓለም አራጌ (ከቃሊቲ፤የህሊና እስረኛ)
አቃቤ ህግ እስማኤል ዳውድ ላይ ምስክሮቹን ሲያስደምጥ፤ የአቶ አለነ ማህፀንቱ የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
ኢዩኤል ፍስሃ ዳምጤ
የአንድነት ፓርቲ አባልና የሚሊየኖች ድምፅ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው ወጣት እስማኤል ዳውድ በዛሬው እለት በአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት ቀረበ፡፡
ወጣት እስማኤል፣ በፍርድ ቤት የቀረበው መዝገቡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማድመጥ በዛሬው እለት በተያዘው ቀነ ቀጠሮ መሠረት ነው፡፡ አቃቤ ሀግ በእስማኤል ላይ እንዲመሰክሩ ካዘጋጃቸው 4 ምስክሮች መሃል ሁለቱን ማስደመጡን የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ገበየሁ ይርዳው ገልፀዋል፡፡ አንደኛ ምስክር እስማኤል፣ ሰልፉ ላይ መገኘቱን ገልጾ ፈፀመ ስለተባለው ድርጊት እንደማያውቅ ማስረዳቱን ያወሱት አቶ ገበየሁ ሁለተኛው ምስክር በበኩሉ እስማኤል፣ መስቀል አደባባይ ተገኝቶ ድንጋይ ወርውሯል፣ እጁን በማነባበር ተቃውሞውን ገልጿል በማለት ምስክርነት መስጠቱን የተከሳሹ ጠበቃ አስረድተዋል፡፡ ጠበቃው የተለያዩ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ለሁለቱም ምስክሮች ማቅረባቸውን አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዚሁ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና የአንድነት ፓርቲ ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማህፀንቱ፣ ከጠዋቱ 3፡00 ሰባራ ባቡር የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትናውን ጉዳይ በሚመለከት ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ተሰይሞ እንደነበር የገለፁት አቶ ገበየሁ፣ ፍርድ ቤቱ የደምበኛቸውን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ አቃቤ ህግ ‹‹ተከሳሹ ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈፅም ስለሚችል›› የዋስትናው ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ ለፍርድ ቤቱ ያመለከት ሲሆን የተከሳሹ ጠበቃ በበኩላቸው ‹‹የአቃቤ ህግ መከራከሪያ በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳ በመሆኑ፣ አቃቤ ህግም ካስያዘው ጭብጥ ውጪ የሆነ መከራከሪያ ነጥብ በማቅረቡ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደመሆኑ መጠን አቃቤ ህግን ይህን መከራከሪያ ሊያቀርብ የሚችልበት የህግ አግባብ›› እንደሌለ ገልፀው የደምበኛቸው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ከህግ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለውና በድጋሚ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡ አቶ አለነ ማህፀንቱ፣ ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥ እንዲሁም ምስክሮቹን እንዲያስደምጥ የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር የጠበቃ ተማም አባቡልጉን የጥብቅና ፈቃድ ማገዱ ታወቀ
የታዋቂው ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የጥብቅና ሙያቸው የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የጥፋተኝነት ብይን በተላለፈበት ቀን መሰረዙ ታወቀ፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር የአቶ ተማም አባቡልጉን ጥብቅና ለአንድ ዓመት ከሰባት ወር የጥብቅና ፈቃዳቸው መታገዱ ታውቋል፡፡
የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና በተለያዩ የህግ ጉዳዮች ጠበቃ የሆነው ጠበቃ ተማም አባቡልጉ በፍርድ ቤት ላይ በሚያደርጋቸው ክርክሮች በተለይም መንግስት ከጅሃዳዊ ሀረካት ጀምሮ የሰራቸውንና ኢትዮጵያ ውስጥ የፍትህ ስርዓቱን ዝቅጠት በመረጃና በህግ በማጣቀስ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በማጋለጣቸው ምክንያት ከዚህ ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወቃ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ማስፈራሪያና ዛቻዎች ከመፈጸማቸው ሌላ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ይታወቃል፡፡ ይህ እስከ ተዘገበበት ድረስ የፈቃዱ መሰረዝ ምክንያት አልታወቀም፡፡
ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ተፈታች፤ መንግሥት የተወሰኑ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችን እና ተማሪዎችንም መፍታት ጀመረ
በፍትህ ሚኒስቴር በፌደራሉ አቃቤ ህግ በ”ሽብርተኝነት” ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው በርካታ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች፣ ፖለቲከኞች እና ተማሪዎች መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን ጨምሮ ጥቂቶች ተለቀዋል፡፡
ከእስር ከተለቀቁት መካከል የእርስ ጊዜዋን የጨረሰችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ በሚያዚያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በጅምላ ከታሰሩት ጋዜጠኞች እና የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮጊስ፣ኤዶም ካሳዬ፤ እንዲሁም የዞን 9 ብሎገሮች ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን ይገኙበታል፡፡
ከእስር ከተለቀቁት ተማሪዎች መካከል ከአዲስ አበባ አዲስ ማስተርፕላን ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ ከኦሮሚያ ክልል ከታሰሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩት አዱኛ ኬሶ፣ ቶፊቅ ራሺድ፣ሌንጂሳ አለማየሁ፣ አብዲ ከማል፣ መገርሳ ወርቁ፣ ቤሊሱማ ዳመነ እና ተሻለ በቀለ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ይህን እንጂ አሁንም ሆን በስፋት ከታወቁት የህሊና እስረኞች መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ, ውብሸት ታዬ እና የዞን 9ኙ በፈቃዱ ኃይሉን ጨምሮ 13 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች፣ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ ኦልባና ሌሊሳ ፣አብርሃ ደስታን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ከነበሩት የኦሮሚያ ተማሪዎች መካከል ተማሪ አስላን ሐሰን በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዳለ በደረሰበት ድብደባ ህይወቱ ማለፉም ተጠቁሟል፡፡
መንግሥት ቀደም ሲል ጋዜጠኞችን፣ ብሎገሮችን ፣ ፖለቲከኞች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን በተመሳሳይ “የሽብር ክስ ወንጀል” ቢመሰርትባቸውም ከተከሳሾች ጀምሮ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኀበረስ፤ የተመሰረቱት ክሶች የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ ከወንጀል ጋር የተያያዘ እንዳልነበር በመጠቆም ከፍተኛ ተቃውሞ ያስከተለ ሲሆን፤ ተቃውሞው አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡