Monthly Archives: August, 2015

አቶ ማሙሸት አማረ ለውሳኔ ተቀጠሩ

“ምስክርነቱ የሐሰትና የተጠና ነው!” ጠበቃቸው

Mamushet Amare

አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት ለተደረገውና ለዋናው (ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ነሃሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለነሃሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ለውሳኔ ተቀጠሯል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማቅረቡ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

አቶ ማሙሸት በአዲሱ ክስ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለመስማት ከ5 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደተመላለሰ የተገለፀ ሲሆን በተለይ አንዱ ምስክር በፖሊስ ተይዞ እንዲመጣ ቢጠየቅም ፖሊስ ሳያስፈፅም ቀርቷል፡፡ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ዛሬ የመሰከሩ ሲሆን “አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል” ሲሉ መስክረዋል፡፡

ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙ ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሲጠየቁ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ “የግል” ብሎ የነበር ቢሆንም በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡

ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡ ዳኛው “በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?” ሲሉት መልስ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡

የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ አመራባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አይ ኤ አይ ኤልን ለመቃወም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ረብሻ አንስተዋል በሚል በተመሰረተባቸው ክስ ሰዓትና ቀን፤ ፓርቲያቸው መኢአድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሌላ እንዲሰጥ መወሰኑን በመቃወም ፍርድ ቤት ክስ መስርተው ለክርክር በተጠቀሰው ሰዓትና ዕለት ችሎት ላይ እንደነበሩ የሚያስረዳ ደብዳቤ ፍርድ ቤቱ መፃፉ ይታወሳል፡፡

ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ከነማ የ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ተቀላቀሉ

ድሬዳዋ ከነማ የ2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ አሸናፊ ሆነ

የሆሳዕና ከነማ እና የድሬዳዋ ከነማ ፍፃሜ ውድድር መክፈቻ

የሆሳዕና ከነማ እና የድሬዳዋ ከነማ ፍፃሜ ውድድር መክፈቻ

የ2007 ዓ.ም. በድሬዳዋ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ውድድር ፍፃሜ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በፍፃሜ ውድድሩ ሆሳዕና ከነማ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ፤ ድሬዳዋ ከነማ ሆሳዕናን 3፡1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2007 ዓ.ም. ብሔራዊ ሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵ ስፖርት ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ድሬዳዋ ከነማን ለዋንጫ በማብቃት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም የመለሱት መሰረት ማኒ ሆሳዕና ከነማን 3፡1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለድል አብቅተዋታል፡፡
ድሬዳዋ ከነማ ለፍፃሜ የደረሰው የምዕራብ ኢትዮጵያ ወኪል ሆኖ ጫፍ የደረሰውን ጅማ አባ ቡና ክለብን 2፡0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነበር፡፡
ቀደም ሲል የእግር ካስ ተጫዋች የነበረውና የስፖርት ሳይንስ ባለሙያና መምህር ግርማ ታደሰ (መንቾ) የሚሰለጥነው የሆሳዕና ከነማ እግር ኳስ ክለብ አላባ ከነማን 3፡0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ተቀላቅሏል፡፡
የብሔራዊ ሊጉ የ2007 ዓ.ም. በተደረገው የደረጃ ጨዋታ አላባ ከነማ ጅማ አባ ቡናን 4፡2 በሆነ የፍፃሜ መለያ ምት በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
አላባ ከነማ ከሆሳዕና ከነማ ለሚያደርገው የፍፃሜ ውድድር ድጋፍ ለማድረግ አርብ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ማታ ወደ ድሬዳዋ ይጓዙ ከነበሩት የአላባ ከነማ ደጋፊዎች መካከል በምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ/ጭሮ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ 4ቱ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ 12ቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 12ቱ ደጋፊዎች ወደተሻለ ህክምና ሪፈር ስለተደረጉ እርዳታ ማስተባበር ስራ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ ሊጉ ሻምፒዮና ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ከነማ በያዝነው 2007 ዓ.ም. በፕርምየር ሊጉ መጨረሻ ላይ ከሚገኙት መካከል 16 ነጥብ ብቻ በማምጣት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልዲያ ከነማ እና በውድድር ዓመቱ 27 ነጥብ በማምጣት 13ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ሙግር ሲሚንቶን ተክተው በመጪው 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ምንጭ፡- ሶከር ኢትዮጵያ

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሚ የሰማያዊ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን በድጋሜ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
ትናንት ነሀሴ 16/2007 ዓ.ም ጉባኤውን የጀመረው ፓርቲው በዛሬው ሁለተኛና የማጠቃለያ ውሎው የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫን አድርጓል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሜ ለቀጣዩ ሦስት አመታት ፓርቲውን እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን፣ አምስት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትም በጉባኤው ተመርጠዋል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትንም መርጧል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ

የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ

ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀደም ብለው ፓርቲውን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብቻ ሲሆኑ፣ ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን ለመቀበል ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ራሱን በእጩነት የሚያቀርብ ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም በእጩነት ራሱን ያቀረበ አልነበረም፡፡
በመሆኑም በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን በጥቆማ ለማወዳደር ተገድዷል፡፡ በዚህም ጉባኤው ስድስት እጩዎችን የጠቆመ ቢሆንም አምስቱ ‹‹አንወዳደርም›› በማለታቸው ከተጠቆሙት መካከል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ብቻ ለመወዳደር ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፓርቲውን በህዝብ ግንኙነት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለሊቀመንበርነት መወዳደር ችለዋል፡፡
ለሊቀመንበርነት እጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ እጩዎች በጉባኤው ፊት በተመደበላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን ካስተዋወቁና የምረጡኝ ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ ወደ ድምጽ መስጠት መግባት ተችሏል፡፡ በተሰጠው ድምጽ መሰረትም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲን ለቀጣይ ሦስት አመታት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፤ በዚህም ኢ/ር ይልቃል ከተሰጠው ድምጽ 136 ድምጽ አግኝተው ሲያሸንፉ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው 60 ድምጽ በማግኘት ፉክክር አድርገዋል፡፡

ይልቃል ጌትነት ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

ይልቃል ጌትነት ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

የምርጫ ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ውሎው ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ አስመልክቶም በጉባኤው አባላት አጠቃላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህም ፓርቲው ወደፊት ማደራጀት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው የብሄራዊ ምክር ቤትና የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ሪፖርቶቹ የፓርቲው ሰነድ ሆነው እንዲፀድቁ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ማጠናቀቁን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ሰበር ዜና፤ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራሮች እና አንድ ሌላ ተከሳሽ በነፃ እንዲሰናበቱ ተወሰነ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ከአንድ ዓመት ከአንድ ወር አካባቢ ታስረው ከነበሩት መካከል አራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አንድ መምህር በነፃ እንዲሰናበቱ ወሰነ፡፡

Politicians
ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋና የቤተል ትምህርት ቤት መምህርና የሀገር አቀፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ አሸናፊ የነበረው መምህር አብርሃም ሰለሞን በነፃ የተሰናበቱት፣ የቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ ከጥርጣሬ ባለፈ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ ባለመቻሉ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡
በውሳኔው መሠረት አቶ ሀብታሙ የሚጠየቁበት ወይም ሌላ የሚፈለጉበት ጉዳይ ከሌለ በዛሬው ዕለት እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ የሺዋስ አሰፋ ከዚህ ቀደም ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸውን ቅጣት እንዳጠናቀቁ እንዲፈቱ ሲል መወሰኑ ታውቋል፡፡

አብርሃም ሰለሞን

አብርሃም ሰለሞን

በዚሁ ክስ መዝገብ በተመሳሳይ ተከሰው ከነበሩት 10ሩ መካከል ከላይ የተጠቀሱት 5ቱ እንዲፈቱ ሲወሰን፤ ቀሪዎቹ 5ቱ እንዲከላከሉ እንተበየነባቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁን ወቅት በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች እና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፈው ሶስት ጋዜጠኞች፤ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ሁለቱ ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ ሲሰናበቱ፤ የተፈረደባቸውን ፍርድ ከጨረሱት መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡

ሰበር ዜና፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ተፈረደባቸው

አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ምድብ ችሎት፤ ዛሬ ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው ከ3 ዓመታ በላይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ የኮሚቴው አባላትም ከ7 ዓመት እስከ 22 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ለ5 ዓመታት ከማኀበራዊ መብቶቻቸውም እንዲታገዱ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉ ተጠቁሟል፡፡

 የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት


የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት

ዛሬ በተላለፈባቸው የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው 18ቱ የኮሚቴው አባላት፡-
አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ እና ካሚል ሸምሱ እያንዳንዳቸው 22 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አቡበከር አለሙ እና ሙኒር ሁሴን እያንዳንዳቸው 18 ዓመት እስር ሲፈረድባቸው፤
ሼህ መከተ ሙሄ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ ሰኢድ አሊ ጁሃር፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም እያንዳንዳቸው 15 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
ቀሪዎቹ ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመር እና ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው እያንዳንዳቸው 7 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
የዛሬውን ፍርድ በተመለከተም ድምፃችን ይሰማ ተቃውሞውን በመግለፅ፤ የሚከተለውን የትግል ስልት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ 6 ነጥቦች ያሉት የአቋም መግለጫ ማውጣቱን ቢቢ ኤንን ጨምሮ የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከመቋቋሙ በፊት በጥር 2004 ዓ.ም. ይፋ ጥያቄ መነሳት የጀመረው በአዲስ አበባ አወሊያ ትምህርት ቤት ጋር ተያይዞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ የተጠ የቁ 3 መሰረታዊ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘታቸው አሁን የተፈረደበት ኮሚቴ ሊቋቋም መቻሉንና ኮሚቴው አባላት ከመታሰራቸው በፊት በመፍትሄው ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በይፋ ውይይት ሲደረግ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

%d bloggers like this: