ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ከነማ የ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ተቀላቀሉ
ድሬዳዋ ከነማ የ2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ አሸናፊ ሆነ
የ2007 ዓ.ም. በድሬዳዋ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ውድድር ፍፃሜ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በፍፃሜ ውድድሩ ሆሳዕና ከነማ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ፤ ድሬዳዋ ከነማ ሆሳዕናን 3፡1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2007 ዓ.ም. ብሔራዊ ሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵ ስፖርት ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ድሬዳዋ ከነማን ለዋንጫ በማብቃት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም የመለሱት መሰረት ማኒ ሆሳዕና ከነማን 3፡1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለድል አብቅተዋታል፡፡
ድሬዳዋ ከነማ ለፍፃሜ የደረሰው የምዕራብ ኢትዮጵያ ወኪል ሆኖ ጫፍ የደረሰውን ጅማ አባ ቡና ክለብን 2፡0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነበር፡፡
ቀደም ሲል የእግር ካስ ተጫዋች የነበረውና የስፖርት ሳይንስ ባለሙያና መምህር ግርማ ታደሰ (መንቾ) የሚሰለጥነው የሆሳዕና ከነማ እግር ኳስ ክለብ አላባ ከነማን 3፡0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ተቀላቅሏል፡፡
የብሔራዊ ሊጉ የ2007 ዓ.ም. በተደረገው የደረጃ ጨዋታ አላባ ከነማ ጅማ አባ ቡናን 4፡2 በሆነ የፍፃሜ መለያ ምት በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
አላባ ከነማ ከሆሳዕና ከነማ ለሚያደርገው የፍፃሜ ውድድር ድጋፍ ለማድረግ አርብ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ማታ ወደ ድሬዳዋ ይጓዙ ከነበሩት የአላባ ከነማ ደጋፊዎች መካከል በምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ/ጭሮ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ 4ቱ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ 12ቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 12ቱ ደጋፊዎች ወደተሻለ ህክምና ሪፈር ስለተደረጉ እርዳታ ማስተባበር ስራ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ ሊጉ ሻምፒዮና ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ከነማ በያዝነው 2007 ዓ.ም. በፕርምየር ሊጉ መጨረሻ ላይ ከሚገኙት መካከል 16 ነጥብ ብቻ በማምጣት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልዲያ ከነማ እና በውድድር ዓመቱ 27 ነጥብ በማምጣት 13ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ሙግር ሲሚንቶን ተክተው በመጪው 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ምንጭ፡- ሶከር ኢትዮጵያ
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሚ የሰማያዊ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ
አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን በድጋሜ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
ትናንት ነሀሴ 16/2007 ዓ.ም ጉባኤውን የጀመረው ፓርቲው በዛሬው ሁለተኛና የማጠቃለያ ውሎው የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫን አድርጓል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሜ ለቀጣዩ ሦስት አመታት ፓርቲውን እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን፣ አምስት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትም በጉባኤው ተመርጠዋል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትንም መርጧል፡፡
ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀደም ብለው ፓርቲውን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብቻ ሲሆኑ፣ ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን ለመቀበል ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ራሱን በእጩነት የሚያቀርብ ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም በእጩነት ራሱን ያቀረበ አልነበረም፡፡
በመሆኑም በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን በጥቆማ ለማወዳደር ተገድዷል፡፡ በዚህም ጉባኤው ስድስት እጩዎችን የጠቆመ ቢሆንም አምስቱ ‹‹አንወዳደርም›› በማለታቸው ከተጠቆሙት መካከል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ብቻ ለመወዳደር ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፓርቲውን በህዝብ ግንኙነት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለሊቀመንበርነት መወዳደር ችለዋል፡፡
ለሊቀመንበርነት እጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ እጩዎች በጉባኤው ፊት በተመደበላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን ካስተዋወቁና የምረጡኝ ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ ወደ ድምጽ መስጠት መግባት ተችሏል፡፡ በተሰጠው ድምጽ መሰረትም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲን ለቀጣይ ሦስት አመታት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፤ በዚህም ኢ/ር ይልቃል ከተሰጠው ድምጽ 136 ድምጽ አግኝተው ሲያሸንፉ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው 60 ድምጽ በማግኘት ፉክክር አድርገዋል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ውሎው ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ አስመልክቶም በጉባኤው አባላት አጠቃላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህም ፓርቲው ወደፊት ማደራጀት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው የብሄራዊ ምክር ቤትና የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ሪፖርቶቹ የፓርቲው ሰነድ ሆነው እንዲፀድቁ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ማጠናቀቁን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡