ሰበር ዜና፤ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራሮች እና አንድ ሌላ ተከሳሽ በነፃ እንዲሰናበቱ ተወሰነ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ከአንድ ዓመት ከአንድ ወር አካባቢ ታስረው ከነበሩት መካከል አራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አንድ መምህር በነፃ እንዲሰናበቱ ወሰነ፡፡
ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋና የቤተል ትምህርት ቤት መምህርና የሀገር አቀፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ አሸናፊ የነበረው መምህር አብርሃም ሰለሞን በነፃ የተሰናበቱት፣ የቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ ከጥርጣሬ ባለፈ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ ባለመቻሉ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡
በውሳኔው መሠረት አቶ ሀብታሙ የሚጠየቁበት ወይም ሌላ የሚፈለጉበት ጉዳይ ከሌለ በዛሬው ዕለት እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ የሺዋስ አሰፋ ከዚህ ቀደም ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸውን ቅጣት እንዳጠናቀቁ እንዲፈቱ ሲል መወሰኑ ታውቋል፡፡
በዚሁ ክስ መዝገብ በተመሳሳይ ተከሰው ከነበሩት 10ሩ መካከል ከላይ የተጠቀሱት 5ቱ እንዲፈቱ ሲወሰን፤ ቀሪዎቹ 5ቱ እንዲከላከሉ እንተበየነባቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁን ወቅት በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች እና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፈው ሶስት ጋዜጠኞች፤ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ሁለቱ ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ ሲሰናበቱ፤ የተፈረደባቸውን ፍርድ ከጨረሱት መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡