Daily Archives: May 17th, 2016

ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ አረፉ

(አዲስ ሚዲያ) ለረጀም ጊዜ የኢትዮጵያ ረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር አሰልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ69 ዓመታቸው ትናንት ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል ኢትዮጵያ ከነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ እና ምሩፅ ይፍጠር በኋላ በጋራም ሆነ በግል በሚገኙ አትሌቶች የድል ውጤት ዋነኛ ተጠቃሽ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

Dr.-Woldemeskel-Kostre

በተለይም አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ጠሩነሽ ዲባባ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ፣ አትሌት ጌጤ ዋሚ፣ አትሌት ወርቁ ቢቂላ፣ አትሌት ፊጣ ባይሳ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት ስልሺ ስህን፣…የመሳሰሉ ስመጥር አትሌቶችን ያፈሩ በማፍራት በርካታ የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ ሽልማቶችን ከአትሌቶቹ በተጨማሪ ሀገሪቷም እንድታገኝ ያስቻሉ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ከ1964 ዓ.ም. ጀምሮ ለ30 ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የረጅም ርቀት አሰልጣኝነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ በሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሰጣቸው ዕውቅናም ሆነ ሽልማት ባይኖርም፤ የዓለም አቀፍ አትሌቲክ ማኀበር (IAAF) በ1998 ዓ.ም. (እ.አ.አ በ2006) ምርጥ አሰልጣኝ በሚል ተሸላሚ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

በአርባምንጭ አካባቢ የመንግሥት ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈፀመ

(አዲስ ሚዲያ) በአርባ ምንጭ ነጭ ሳር አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የመንሥት ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት አደረሱ፡፡ በጥቃቱ የአካባቢው ወታደራዊ አዛዥን ጨምሮ ከ20 ያላነሱ የመንግሥት ወታደሮች መገደላቸውን እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ወታደሮችም ጉዳት ደርሶባቸው በአርባምንጭና በአካባቢው ባሉ የጤና ተቋማት የህክምና ዕርዳት እየተደረገላቸው መሆኑን ከስፍራው የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ኢሳት ዘግቧል፡፡ የተፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ መንግሥት በመግለጫው እንዳተተው ከሆነ፤ ጥቃቱ የፈፀሙ አካላት ከኤርትራ ስልጠና ወስደው በዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሞያሌ አድርገው ወደ አርባምንጭ አከባቢ እንደመጡ፤ ጥቃት አድራሾችም በፀጥታ ኃይሉ እንደተማረኩ አስታውቋል፡፡

Arbegnoch ginbot 7 force

መንግሥት ጥቃት አድራሾቹ እነማን እንደነበሩ እና ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡
ይሁን እንጂ በስሩ ባሉ መገናና ብዙኃን እና በመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገፅ ላይ ጥቃት አድራሾቹ ከነትጥቃቸው እንደተማረኩ በማስመሰል በአንድ ወቅት አሜሪካ በኢራቅ ከታጣቂዎች ማረኩት ብላ ያሰራጨው ምስል በማኀበራዊ ሚዲያ ከተጋለጠ በኋላ መንግሥት ማረኩት ያለውን የተሳሳተ መረጃ ምስልን ከአንድ ቀን በኋላ ከገፁ ላይ አንስቶታል፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በዚህ በአርባ ምንጭ አካባቢ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ለተፈፀመው ጥቃት ስርዓቱን በሁለገብ ትግል ለመጣል በይፋ የሚንቀሳቀሰው አርቦኞች ግንቦት 7 ለአንደነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ (አርበኞች ግንቦት 7) ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ በተለይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ እና ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ አርበኞች ግንቦት 7 በመንግሥት ወታደሮች ላይ በአርባምንጭ አካባቢ ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ ከሆነ ድርጅቱ ሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው እና በደቡብ ካለው አነስተኛ ቡድን የተሰነዘር ጥቃት መሆኑን እና የጦር መሳሪያውንም ቢሆን ያገኙት ከራሱ ከመንግሥት ኃይሎች መሆኑን በማረጋገጥ በሌሎች የአሀገሪቱ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ጥቃት በመንግሥት ላይ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ አክለውም አርበኞች ግንቦት 7 የሚታገለው ኤርትራ ውስጥ ሳይሆን ሀገር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን እና በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ የአርባምንጩ ጥቂት ማሳያ እንደሆነ በመግለፅ የስርዓት ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ወደፊትም ተመሳሳይ ጥቃቶች በመንግሥት ላይ የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በጥቃቱም ከአርበኞች ግንቦት 7 በኩል በመንግሥት ወታደሮች በተወሰደ የፀፋ ርምጃ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡

%d bloggers like this: