የአቶ ሀብታሙ አያሌው ጤና አደጋ ላይ በመውደቁ ከሀገር እንዳይወጣ የተጣለበት እግድ እንዲነሳ ተጠየቀ
(አዲስ ሚዲያ) የቀድሞው የአንደነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ሀብታሙ አያሌው የጤናው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ተገቢውን ህክምና ማግኘት አለመቻሉ ታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ህመሙ ይበልጥ ተባብሶ ራሱን በመሳቱ በአቅራቢያ ወደሚገኘው ዋሸንግተን ሆስፒታል ቢወሰድም ተገቢውን የህክምና ዕርዳታ ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ቢወሰድም ተገቢውን የህክምና ርዳታ ባለማግኘቱ ወደ ካዲስኮ ሆስፒታል ተወስዶ በማስታገሻ ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ይዞ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
አቶ ሀብታሙ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ”ን ጨምሮ ለ18 ወራት ያህል በታሰረበት ባጋጠመው ህመም ምክንያት የህክምና ዕርዳታ ቢጠይቅም ከመንግሥት በጎ ምላሽ ባለመገኘቱ ከእስር በነፃ ከተለቀቀ በኋላ ህመሙ እንደተባባሰ ተጠቁሟል፡፡
አቶ ሀብታሙ በሀገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ የህክምና ተቋማት ተገቢውን የህክምና ክትትል ለማድረግ ቢንቀሳቀስም ህመሙ ካለበት ከፍተኛ ደረጃ አንፃር አቅም ካለው ከሀገር ውጭ ሄዶ ቢታከም የተሻለ እንደሆነ ከዶክተሮቹ በተነገረው መሰረት በውጭ ሀገር ህክምና ማድረግ ቢፈልግም፤ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሀገር እንዳይወጣ በጣለው እግድ መሰረት ተገቢውን ህክምና ባለማግኘቱ ማክሰኞ ራሱን መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡ በአቃቤ ህግ ይግባኝ ምክንያት ከሀገር እንዳይወጣ የተጣለው የፍርድ ቤት እግድ እንዲነሳ አቶ ሀብታሙ በጠበቃቸው አቶ አምሃ መኮንን አማካኝነት ፍርድ ቤቱን ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ እንዳልተገኘ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን በማኀበራዊ ሚዲያ እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል አቶ ሀብታሙ ከሀገር እንዳይወጣ የተጣለበት እግድ እንዲነሳ እና ተጊቢውን የህክምና ዕርዳታ እንዲያገኝ ሊፈቀድ ይገባል ሲሉ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ የማኀበራዊ ሚዲያ ዘመቻው እስከነገ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡ ይህ እስከ ተዘገበበት ድረስ አቶ ሀብታሙ ራሱን ስቶ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ በካዲስኮ ሆስፒታል ተኝቶ እስኪነቃ በሚል ከሚሰጠው ማስታገሻ በስተቀር ምንም ዓይነት መደበኛ የህክምና ዕርዳታ እንዳልጀመረ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ በመንግሥት እና በህዝብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የአዲስ አበባ ፖሊሶች ተገደሉ!
(አዲስ ሚዲያ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፈለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ፉሪ ሐና ማርያም ቀርሳ ኮንቱማ እና ማንጎ ሰፈር በሚባል ስፍራ ትናንት ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. እና ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በነዋሪውና በከተማ አስተዳደሩ መካከል በተፈጠረ ግጭት ከ4 ያላነሱ የአዲስ አበባ ፖሊሶች፣ 1 አፍራሽ ግብረ ኃይል እና 1 የአካባቢው የወረዳ ባለስልጣን መገደላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እንደ አካባቢው የዓይን እማኞች ገለፃ ከሆነ፤ ከነዋሪዎችም በርካታ ሰዎች በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መቁሰላቸውን እና የህክምና እርዳታም እንዳያገኙ መደረጋቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በተፈጠረው ግጭት የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ዛሬ በተፈጠረው ግጭት ሁለት ፖሊስ እና የአካባቢው የወረዳ ባለስልጣን መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት መንግሥት በአካባቢው ያሉ 30 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ከመንግሥት እውቅና ውጭ በህገ ወጥ መንገድ ቤት ሰርተው እየኖሩ ያሉ ሰዎች ቤታቸውን አፍርሰው ከአካባቢው መነሳት አለባቸው የሚል ውሳኔን ተከትሎ፤መንግሥትም ቤቶቹን ለማፍረስ የቤት አፍራሽ ግብረ ኃይል፣ የአዲስ አበባ ፖሊሶች፣ አራት ሲቪለ የለበሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የመብራት ኃይል ሰራተኞች እና ሁለት የአካባው የወረዳ አመራር ወደስፍራው ልኮ እንደነበር ታውቋል፡፡
የቤታቸውን መፍረስ በመቃወም የአካባቢው ሴቶችና ህፃናት ወደ አዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ቅሬታ ለማቅረብ ቢሄዱም ሰሚ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሐና ማርያም አካባቢ የሚገኘው የወረዳው አስተዳደር የአካባቢውን ነዋሪ በቤት መፍረሱ ጉዳይ ኑና እንነጋገር በሚል ከጠራ በኋላ፤ በጎን ወደነዋሪዎቹ አካባቢ አፍራሽ ግብረ ኃይል መላኩ ነዋሪውን ይበልጥ እንዳበሳጨውና ለህይወት መጥፋት ዋናው መንስኤ እንደሆነ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ቤቶቻቸው በኃይል እንዲፈርስ ከተደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ምንም ዓይነት ካሳ እና ምትክ ቤትም ሆነ ቦታ በመንግሥት እንዳልተሰጣቸው የጠገለፀ ሲሆን፤ እንዲፈርሱ በተወሰነው የመንደሩ ነዋሪዎች በርካታ አዛውንት፣ ህፃናት፣ ነፍሰጡር እናቶች እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ ወቅቱ ከፍተኛ ዝናብ የሚዘንብበት ክረምት በመሆኑ፤ ነዋሪዎች ቤቶቻቸው ያለምንም ምትክ ቤትና ካሳ ቤቶቻቸው የሚፈርሱ ከሆነ ህፃናትና ነፍሰጡር እናቶችን ጨምሮ ሁሉም ለጎዳና ህይወት እንደሚዳረጉ እየተናገሩ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግሥት በኩል ስለምትክ ቤትና ቦታም ሆነ ካሳን በሚመለከት እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በአካባቢው አሁንም ውጥረት እንደነገሰ ነው፡፡
ባለፈው ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በተመሳሳይ መልኩ በቦሌ ልፍለከ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ወረገኑ በሚባል ስፍራ 20 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ያሉበትን ቤት፤ መንግሥት ህገወጥ ነው በሚል ለማፍረስ በመንቀሳቀሱ በተፈጠረ አለመግባባት የሰው ህይወት መጥፋት የአካል ጉዳት ማስከተሉ አይዘነጋም፡፡
የግዕዝ ጉባዔ በጅማ ዩኒቨርስቲ “ዓይን ቅንድብን ያየበት” ተካሄደ
በሔኖክ ያሬድ
የቡናዋ ገበታ ጅማ ከተማ መሰንበቻውን በጅማ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ቋንቋ ግእዝን የተመለከተ አገር አቀፍ ጉባኤ አስተናግዳ ነበር፡፡
“የግእዝ ቋንቋ ሀብት ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ሦስተኛው ጉባኤ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት፣ ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከልና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው፡፡ በጉባኤው አሥር ወረቀቶች ቀርበውበታል፡፡
“ግእዝን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክና ባህል የተጻፈበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ብሔረሰቦች ሊቃውንት በጋራ ያሳደጉትና ያበለጸጉት ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ነው፤” የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ሥርግው ገላው እንደማሳያነት ያቀረቡት ቀደምት የኦሮሞ ሊቃውንት ድርሻን በማሳየት ነበር፡፡
እንደ አፄ ሱስንዮስ ታሪክ ጸሐፊ አዛዥ ጢኖ (አለቃ ተክለሥላሴ)፣ እንደ ዝነኛው የቅኔና መጻሕፍት መምህር አለቃ ገብረሥላሴ ክንፉ፣ እንደ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ታሪክ ጸሐፊ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ፣ እንደ ዝነኛው የቅኔና መጻሕፍት መምህር መምህር ጥበቡ ገሜና ሌሎችም በርካታ የኦሮሞ ሊቃውንት ለግእዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ያደረጉትን አስተዋጽኦ ዶ/ር ሥርግው አስታውሰዋል፡፡
አዛዥ ጢኖ የጻፉት የአፄ ሱስንዮስ (1597-1625) ዜና መዋዕል ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከተጻፉት ዜና መዋዕሎች በብዛትም (የአፄ ሠርፀ ድንግልን ሳይጨምር) ሆነ በጥራት ከሁሉም የተሻለ ነው ብለውታል አጥኚው፡፡
ዶ/ር ሥርግው በማሳያነት ያቀረቡት ሌላው ሊቅ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ ከታሪክ ጸሐፊነታቸው በተጨማሪ በሠዓሊነትም ይታወቃሉ፡፡ በ1860 ዓ.ም. አካባቢ ወለጋ ኩታይ [ጉድሩ] ውስጥ የተወለዱት አለቃ ተክለኢየሱስ የጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት ታሪክ ከመጻፋቸውም ሌላ በ1961 ዓ.ም. የልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የአውሮፓ ጉብኝትና የዚህ ጉብኝት ተሳታፊ በነበሩት በራስ ኃይሉ አለመኖር ምክንያት በደብረ ማርቆስ ከተማ የተፈጠረውን ግርግር አካትተው የጻፉት ይጠቀሳል፡፡
የግእዝ ቋንቋ በአፍ መፍቻነት ያገለግል በነበረበት ጊዜ እንደማንኛውም ቋንቋ ባህላዊ ዘፈን ሲዘፈንበት የቆየ መሆኑን ያመለከቱት ሌላው ጥናት አቅራቢ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ሙሉቀን አንዱዓለም ናቸው፡፡ ‹‹ማሕሌተ ገንቦ›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ ማሕሌተ ገንቦ የሚባለው የግእዝ ዘፈን ከጥንት ጀምሮ ሲዘፈን የመጣ የዘፈን ዓይነት ነው፡፡ ሰይህ ዓይነት ዘፈን የሚዘፈነው በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክህነት ሰዎች ሲሆን ዘፈኑ የሚከናወንባቸው ዐውዶችም የተለያዩ ናቸው፡፡ በዋናነት ሠርግን፣ ማኅበርን፣ የዓመት በዓልን፣ ክርስትናን፣ በአጠቃላይ ካህናቱ በሚጠሩባቸው የደስታ ድግሶች ሁሉ ይከናወናሉ፡፡
የማሕሌተ ገንቦ ዘፈኖች በአሁኑ ሰዓት የሚዘፈኑት ለካህናት ሆነው የሚዘፈኑባቸው ዐውዶችም ሠርግ፣ የዓመት በዓላት፣ ክርስትና፣ ማኅበር ወዘተ. ቢሆኑም ለዚህ ጥናት የቀረቡት የሠርግ ግጥሞች ናቸው፡፡ በማሳያነት ከቀረቡት መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
‹‹ዝ ጠላ ከመ ወይን ጣእሙ፤ እስኪ ድግሙ ድግሙ እስኪ ድግሙ
ይህ ጠላ ጣዕሙ እንደ ወይን ነው፡፡ እስኪ ድገሙ፤ እስኪ ድገሙ፡፡
እመይቴ ጥሩ ዓይነት እጅሽን ይባርከው መልሶ መልሶ፣
ያደረግሽው ጠላ በማር ተለውሶ፣
ቁርጥማት አይንካው ጥሩዬ እጅሽን፣ ይህንን ጠላና ጠጅ ያረገውን፣
ይህን ጠላና ጠጅ የጠጣችሁ ኹሉ፣
ጥሩ ዓይነት ጥሩ ዓይነት እጡብ ድንቅ በሉ››
እንደ ዶ/ር ሙሉቀን ማብራሪያ፣ ይህም በኢትዮጵያ ባህል የደገሰውን ሲበሉለት፤ የወለደውን ሲስሙለት ባለቤቱ በጣም ደስተኛ ስለሚሆን የማስደሰት ኃይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ መልእክቱም የሚጠጣው ጠላ እጅግ ተወዳጅ በሚሆንበት ጊዜ ደጋግመው እንዲጠጡ ጥያቄ የሚያቀርቡበትና ጠላውን የሚያደንቁበት ስንኝ ነው፡፡
ከሴትዮዋ ስም ጋር በማስተባበር ዓይነቱ ጥሩ እንደሆነ አመስጥረውበታል፡፡ ይህ ስንኝ በሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍም ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
‹‹ወይቤላ ንዒ ከመ ንትዋነይ››
የዚህ ስንኝ ትርጉምም፡- ሙሽራው ሙሽሪትን እንጫወት ዘንድ ነዪ አላት፡፡ ለማለት ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ የማሕሌተ ገንቦ ግጥሞች ደራሲያቸው ስለማይታወቅና በምሁራን የማይደረሱ የሕዝብ በመሆናቸው እንደ ቅኔ ጠንካራ ሕግ የላቸውም፡፡ በግእዙ ስንኝ ላይ ያለውን ስንመለከት ባለቤቱ (ጠሪውም ተጠሪዋም) በግልጥ አልተቀመጡም፡፡ ሲፈልግ የአማርኛ፣ ሲፈልግ የግእዝ ወይም ደግሞ እያቀላቀለ ግጥሞችን ያስገባል፡ በምሳሌነት የሚከተለውን አጥኚው አሳይተዋል፡- ‹‹ወይቤላ ንዒ ከመ ንትዋነይ፡፡
ተማሪ ተማሪ ተማሪ ቢሉሽ፤
ከጉድጓድ የወጣ ገብስ አይምሰልሽ፤
መደረቢያው ካባ መጠምጠሚያው ሻሽ፤
ወይቤላ ንዒ ከመ ንትዋነይ፡፡
ተማሪውና ሙሽራዋ በሚጋቡበት ጊዜ ሙሽራዋ የቄስ ተማሪ ስታገባ ቅር እንዳይላት በካባ፣ በሻሽ የተንቆጠቆጠ ምሁር እንጂ ከጉድጓድ እንደ ወጣ ገብስ የተናቀ አይደለም ለማለት ነው ሲሉ አጥኚው አብራርተዋል፡፡
በዚህ ጥናት ውስጥ ኅብረተሰቡ አብሮ በግእዝ ይዘፍን እንደነበረ፤ ቋንቋውም እንደማንኛውም ቋንቋ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለዓለማዊ ዘፈንም አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረና የዜማው ሁኔታም ሲታይ የራሱ የሆን ውበት ቢኖረውም ከቅዱስ ያሬድ ዜማ አጠርና ፈጠን ያለ ምት እንዳለውና የኅብረተሰብን የአኗኗር ሁኔታ የሚዳስሱ ማኅበራዊ ግጥሞች በመሆናቸው ማሕሌተ ገንቦ በደምብ ሊጠና ይገባል የሚል ምክር አዘል መልእክት ጥናት አቅራቢው አቅርበዋል፡፡
በሦስተኛው ጉባኤ ከቀረቡት ጥናቶች መካከል የዝዋይ ሐይቅ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ቅርሶችን የዳሰሰ፣ ግእዝ ለአማርኛ የፍልስፍና ቃላት ያደረገው አስተዋጽዖ፣ በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስለሚገኘው የሥነ ፈለክ ትምህርት፣ እውቀት እንደ ሕንጻ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ፍልስፍና እና የግእዝ ግሶች ሥነ ድምፅ የሚተነትን ሶፍትዌር ለመሥራት የተደረገውን ጥረት አመልካች ጥናቶች ይገኙበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ 346 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘውና ጉባኤውን ባስተናገደው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ አነጋገር፣ በግእዝ ቋንቋ የተከማቹ የመረጃ ሀብቶች ለአገሪቱም ይሁን ለጠቅላላው የሰው ልጆች በርካታ ጥቅም ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ዕውቀቶች ያዘሉ ናቸው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እነኚህን በርካታ ዕውቀቶች አውጥቶ ለዘመናዊው የኑሮ ሥርዓት ጥቅም ላይ ለማዋልም ይሁን ለቋንቋዎቻችን ዕድገትና ልማት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በሚመለከታቸው የመንግሥትም ይሁን ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በመዋቅር፣ በአደረጃጀትና በስትራቴጂ የሚሠራ አካል እምብዛም እንደማይታይ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፣ ከአገሪቱ ይልቅ ምዕራባውያን ከቋንቋውና ቋንቋው ከያዘው መረጃ ተጠቃሚ ለመሆን ለበርካታ ዓመታት በቋንቋው ላይ ጥናት ከማከናወናቸው ባሻገር፣ በዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ተመራማሪዎችንና አማካሪዎችን በማፍራት ራሳቸውን የቻሉ የግእዝ የትምህርት ክፍሎች ከፍተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም፣ የግእዝ ቋንቋ በውስጡ አምቆ የያዛቸውን የሕክምና፣ የምህንድስና፣ የሥነፈለክ፣ የሥነትምህርትና የኪነጥበብ ትሩፋት የሚጣጣሙበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለወደፊቱ ለአገር ዕድገት መሠረታዊ የሆኑ ዕውቀቶች እየተመረመሩ ከዘርፉ የሚገኘውን አገራዊ ጥቅም የሚያድግበት እንደሚሆን ተስፋቸው መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ፣ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችና መረጃዎች የሕክምና ጥበብ ምንጭና የባህላዊ መድኃኒቶች መሠረት የሚጠቁሙ፣ የነገሥታት አስተዳደር፣ የሕጋዊ የዳኝነት ሥርዓት፣ የሕዝቦች የመቻቻልና የመደጋገፍ ጥበብና ሥርዓት፣ እንዲሁም የዘመን አቆጣጠር መነሻና መሠረት ምንጭ መሆኑ ያመለክታሉ ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ጮሻ፣ ይህም የግእዝ ቋንቋ የሥራ፣ የመግባቢያና የመተዳደሪያ ቋንቋ እንደነበረ ያመለክታል ብለዋል፡፡ የግእዝ ጉባኤ መካሄዱ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ግንዛቤውን ለማሳደግ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡
ሃቻምና በአክሱም የተጀመረው የግእዝ ጉባኤ፣ አምና ሁለተኛውን ጉባኤ በባሕር ዳር ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው ጉባኤ ማጠቃለያ በተደረገው ውይይት በሦስቱ ጉባኤዎች ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሥራ መሠራቱ ተመልክቷል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስና ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ደጀኔ ገመቹ፣ ጉባኤ ከማዘጋጀት ባለፈ ለወደፊት ምን መሠራት እንደሚኖርበት የሚጠቁም ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሌሎችም የሚውጣጣ ግብረ ኃይል መቋቋም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ለየት ያለ ሐሳብ ያነሱት ዶ/ር ሙሉቀን በሦስት ዓመት ውስጥ ብዙ ውጤት ለማየት የመጓጓት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፣ ነገር ግን ኅብረተሰቡ በደንብ የተረዳው ስላልሆነ ሰፊ የማስገንዘቢያና የቅስቀሳ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
‹‹ለተወሰነ ቡድን ከሚሰጥ ሁሉም እንደባለቤት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር መፍጠር አለበት፤ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንደተካሄደው ዓይነት ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ከገቡበት ውጤት ሊመጣ ይችላል፡፡ ወደታችም ሁለተኛ ደረጃ መለስተኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም መውረድ አለበት፡፡ ተተኪውን ትውልድ ማስተማር አገር በቀሉን ዕውቀት ለማስተላለፍ ያስችላልና፡፡››
በዓለም አቀፍ ደረጃ ግእዝን የሚመለከቱ እስከ አሥር የሚደርሱ ጆርናሎች በየዓመቱ እንደሚወጡ ያመለከቱት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የቋንቋ ባለሙያና የጉባኤው አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው ናቸው፡፡ ግእዝን የመመርመር አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዲህ አመላከቱት፡፡
‹‹የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግእዝን ለምን አተኩሮ ያጠናል? እኛስ ለምንድን ነው የማናጠናው? ጥያቄ መሆን ያበት ይኼ ነው፡፡ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዕውቀት እናምጣ ካልን ከሩቅ ከባሕር ማዶ ከምናመጣቸው ዕውቀቶች ይልቅ፣ ከባህላችን ጋር ተሰናስለው የተፈጠሩ በግእዝ የተጻፉ ሀብቶች አሉን፡፡ እነዚህን ጥንታዊ ዕውቀቶች ፈልፍለን አውጥተን፣ ለዛሬው ኑሮ ሥርዓታችን የመጠቀምና ያለመጠቀም ምርጫ ነው፡፡ ይጠቅመናል ካልን እንመርምረው፣ እንፈትሸው እናውጣው፣ አይጠቅመንም ካልን እንተወው፣ ስለዚህ መጥቀም አለመጥቀሙን ለማወቅ በመስኩ ለተሰማራን የግንዛቤ ሥራ ያስፈልጋል፡፡››
አንዱ ጉባኤተኛም በሦስቱ ዓመታት በአክሱም፣ በባሕርዳርና በጅማ የተካሄዱትን ሦስቱን የግእዝ አዝመራ ጉባኤዎች አያይዘው፣ ‹‹ዓይን ቅንድብን ያየበት›› መድረክ ነው ሲሉ አወድሰውታል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ
ዮናታን ተስፋዬ ያቀረበው መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ የእምነት ክህደት ቃል ሰጥቷል
“ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ጽፌያለሁ” ዮናታን ተስፋዬ
በኦሮምያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀጠል ተንቀሳቅሰሃል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበበት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሰብዓዊ መብት አራማጅ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያና አቃቤ ህግ ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠውን መልስ መርምሮ ብይኑን ያሰማው ፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የተከሳሹን የእምነት ክህደት ቃል ተቀብሏል፡፡
አቶ ዮናታን የቀረበበት የሽብር ክስ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት በክስ መቃወሚያው መጠየቁ ይታወሳል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ በተከሳሹ ለቀረበው መቃወሚያ መልስ ሰጥቷል፡፡ ግራ ቀኙን ፍርድ ቤቱ እንደመረመረው የገለጹት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ታረቀኝ አማረ የተሰጠውን ብይን በንባብ አሰምተዋል፡፡
ተከሳሹ ‹‹….አመጽና ብጥብጥ ለማስቀጠልና ለማነሳሳት በፌስቡክ ድረ ገጽ ቀስቃሽ ጽሁፎችን መጻፍ ድርጊት›› በተከሳሹ ላይ ከተጠቀሰው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 4 ጋር የተቀራረበ አለመሆኑን የወ/መ/ሕግ/ሥ/ሥ/ቁ.112 ጠቅሶ፣ ከድንጋጌው ውጭ የቀረበና ‹‹የሽብርተኝነት ተግባር›› ስላለመሆኑ ያቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ‹‹የተመለከተውን ድንጋጌ አያሟላም ያሟላል የሚለው በማስረጃ ምዘና የሚታይ ይሆናል›› በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡
ተከሳሹ የቀረበበት አመጽና ብጥብጥ ‹‹….የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር….›› እንጂ የኦ.ነ.ግ ተግባር ያለመሆኑ የህግ ግምት ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበው መቃወሚያ ‹‹ክሱ ተቃውሞውን ስለማስቀጠል በተመለከተ የቀረበ በመሆኑ መቃወሚያውን አልተቀበልነውም›› በሚል ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጽፎታል ተብሎ በማስረጃነት የቀረበው ጽሁፍና ፈጽሞታል ተብሎ የቀረበበት ድርጊት የወንጀል ኃላፊነትን የማያስከትልና ህገ-መንግስታዊ ጥበቃ የተደረገለት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መሆኑን በማስመልከት ክሱ እንዲሰረዝና በነጻ እንዲሰናበት ያቀረበውን ተቃውሞ ደግሞ ‹‹ህገ መንግስቱ አንቀጽ 29(6) ገደቦችንም ያስቀመጠ በመሆኑና አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ንብረት ማውደምን ጠቅሶ ያቀረበው ክስ የተሟላ ስለሆነ በማስረጃ የሚታይ ይሆናል›› በማለት ተቃውሞውን ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
ተከሳሹ የቀረበበት ክስ ግልጽ ያለመሆኑንና የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር ግልጽ አለመደረጉን በተመለከተ ላቀረበው መቃወሚያ በጸረ-ሽብር አዋጁ ላይ የተመለከተውን የምስክሮች ደህንነት ጥበቃ በመጥቀስ ማስረጃ ዝርዝሩ (ምስክሮቹ) እንዲገለጹ የቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጓል፡፡ በዚህም ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን ለመስጠት ዝግጁ ስለመሆኑ ጠይቆ ተከሳሹ ቃሉን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ አቶ ዮናታን የቀረበበት ክስ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸም አለመፈጸሙና ጥፋተኛ ስለመሆን አለመሆኑ ተጠይቆ ‹‹ክሱ በቀረበበት መንገድ የተገለጸውን የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ግን ጽፌያለሁ፡፡ በመሆኑም የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም›› ብሏል፡፡
ተከሳሹ በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት አልፈጸምኩም በማለቱ አቃቤ ህግ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙ እንዲታዘዝለት የጠየቀ ሲሆን፣ ተከሳሹ በበኩሉ ፌስቡክ ላይ ጽፏቸው ከኮምፒውተር ሲገለበጡ አይቻለሁ የሚሉ የደረጃ ምስክሮች ከሆኑ ባልተካደ ጉዳይ ላይ ፍትህን ማጓተት እንዳይሆን ግንዛቤ ይያዝልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክር የማሰማት መብቱ የእኔ ነው በማለት ምስክሮቹ እንዲሰሙለት አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቀርበው እንዲሰሙ ለሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሁለት ሳምንታት በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና ዛሬም ከጨለማ ክፍል እንደሚገኝ ጠቅሶ አያያዙ እንዲሻሻልለት ማመልከቻ አስገብቷል፡፡ ተከሳሹ በማመልከቻው ላይ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ መፍትሄ እንዲበጅለት ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ግን በተሰጠው ቀጠሮ (ሐምሌ 20 ቀን 2008) ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት እናዝዛለን በማለት አልፎታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ባቀረበው መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ መልስ ሰጥቷል
ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን አስተላልፏል በሚል የሽብር ክስ የቀረበበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ላቀረበው የክስ መቃወሚያ አቃቤ ህግ መልስ ሰጥቷል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በተከሳሹ የክስ መቃወሚያ ላይ ለተነሱ ነጥቦች በጽሁፍ መልሱን ለችሎቱ አስገብቷል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው አቃቤ ህግ ያቀረበበት ክስ ‹‹በማናቸውም መልኩ በሽብር ተግባር መሳተፍ›› የሚለው፣ አንድ ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመን ድርጅት ስም መጥራት፣ የሽብር ድርጅቱ በሚጠቀምበት ሚዲያ መጠቀም ወይም የሽብር ድርጅት አባል ነው የተባለን ሰው ለሽብር ድርጅቱ አንዳችም ፋይዳ በሌለው ነገር ላይ ማነጋገር ሁሉ ይጨምራል በሚል ተለጥጦ መቅረብ እንደሌለበት ላቀረበው መቃወሚያ፣ አቃቤ ህግ ድንጋጌውና የወንጀል ዝርዝሩ በሚመጣጠን መልኩ ክሱ ቀርቧል ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም መቃወሚያው በአግባቡ ያልቀረበ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
ተከሳሽ አቃቤ ህግ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ስለነበሩ ክስተቶች የሽብር ድርጅት አመራር ናቸው ላላቸው ሰዎች መረጃ ማስተላለፍን በሽብር ድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከህጉ አላማም በእጅጉ የራቀ ነው፣ የህጋዊነት መርህንም የተከተለ አይደለም በሚል ላቀረበው መቃወሚያ፣ አቃቤ ህግ ክሱ የህጋዊነትን መርህ ባከበረ መልኩ የቀረበ መሆኑን በመጥቀስ የወንጀል ድርጊቱ በማስረጃ የሚረጋገጥ ይሆናል በማለት መቃወሚያው ውድቅ ይደረግልኝ ሲል አመልክቷል፡፡
አንድ ድርጊት ወንጀል ነው አይደለም የሚለው ፍ/ቤት ማስረጃ ከሰማ በኋላ የሚወሰን ስለመሆኑ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም ፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ መስጠቱን በማስታወስ የወንጀል ድርጊቱ ላይ የተነሳው መቃወሚያ ከማስረጃ መሰማት በፊት ሊነሳ የማይገባው ነጥብ ስለሆነ ውድቅ ይደረግልኝ ብሏል፡፡ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ አንቀጽ 111 እና 112 መሰረት አድርጎ ተሟልቶ መቅረቡንም በመልሱ ላይ ገልጹዋል፡፡
ተከሳሹ ከሽብር ቡድኑ ተልዕኮ እንደተቀበለ ከመጠቀሱ በቀር ተልዕኮው ምን እንደሆነ፣ መቼ፣ ከማን እና በምን አይነት መንገድ ተልዕኮውን እንደተቀበለ ከሳሽ ግልጽ አላደረገም በሚል ለጠቀሰው መቃወሚያ፣ አቃቤ ህግ ‹‹ተልዕኮ መቀበል ሲባል የሽብር ቡድኑ አላማን በመቀበል የድርጅቱን አላማ በማራመድ በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ህብረተሰቡን ለማስፈራራትና የሀገሪቱን መሰረታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ህገ-መንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ…ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ በሚንቀሳቀስ የሽብር ቡድን ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ›› እንደሆነ ገልጾ የመቃወሚያው መቅረብ የህግ መሰረት የሌለው በመሆኑ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል አመልክቷል፡፡
አቃቤ ህግ በአጠቃላይ ያቀረብኩት ክስ ህጉን መሰረት ያደረገና የክስ ዝረዝርና የህግ ድንጋጌውን ባጣጣመና በተገቢው መንገድ የቀረበ ስለሆነ በከሳሽ በኩል የቀረበው መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ ክርክራችንን እንድንቀጥል ሲል ጠይቋል፡፡
ችሎቱ ተከሳሹ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ 14ኛ ወንጀል ችሎት ቦታው በሙሉ በተከሳሾች ተይዟል በሚል ችሎቱን ለመታደም የቻለ የለም፡፡
ምንጭ፡- EHRP