እነ አቶ በቀለ ገርባ በባዶ እግራቸው፣ ከፈል ሰውነትን በሚያሳይ የውስጥ ካናቴራ እና በቁምጣ ፍርድ ቤት ቀረቡ
“ምግብ ሳንመገብ በካቴና ታስረን ጨለማ ቤት ነው ያለነው” አቶ በቀለ ገርባ
በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የሽብር ክስ በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ የተመሰረተባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች አመራሮች ዛሬ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ግማሾቹ በባዶ እግር ሌሎቹ በፓካውት እና በቁምጣ ቀርበዋል፡፡
ፍርድቤቱ ተከሳሾቹን ለዛሬ የቀጠረው ግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ለምን ተከሳሾቹን ፍርድቤት እንዳላቀረበ መልስ ለመቀበል እና የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለመስማት ነበር፡፡
የክስ መቃወሚያቸውን ከአንደኛ ተከሳሽ እስከ አራተኛ ተከሳሾች በአንድ ላይ አቅርበዋል፡፡ ከአምስተኛ እስከ ሃያ ሁለተኛ ተከሳሾች ደሞ በጋራ መቃወሚያቸውን አስገብተዋል፡፡ ሰባተኛ ተከሳሽ ደግሞ መቃወሚያቸው ለፍርድቤቱ በቃል እንዲደመጥ ጠይቀው ፍርድቤቱ መቃወሚያውን አድምጧል፡፡
ተከሳሾች አቃቤህግ ያቀረበው ክስ እንዲስተካከል አሊያም ውድቅ እንዲደረግ የተለያዩ ነጥቦችን በማንሳት ፍርድቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ጉዳይ ለማየት ያለውን የሥረ- ነገር እና የከባቢ የዳኝነት ( Jurisdiction) ስልጣን በተመለከተ ባቀረቡት መቃወሚያ ክሱ ውስጥ ወንጀል ተፈፅሟል የተባለው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/88፣ 138/01፣ 321/95 እና አዋጅ 141/200 መሠረት ይህንን ጉዳይ ለማየት ስልጣን ያለው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድቤት በመሆኑ ይህ የተከበረው ፍርድ ቤት የሥረ- ነገር ስልጣን የለውም ብለው ተቃውመዋል፡፡
የህጋዊነት መርህን በተመለከተ ባቀረቡት መቃወሚያም፡አቃቤህግ በክሱ “ተከሳሾች የአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልማት ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን እና የኦሮሚያ ከተሞች የዕድገት ፕላን የኦሮሚያን ህዝብ ቋንቋ እና ባህል የሚያጠፋ የኦሮሞን ህዝብ ከመሬቱ ሚያፈናቅል ነው በማለት እንደ ፓርቲ ወስነው በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች ህብረተሰቡ ወደ አመፅ እንዲገባ በመቀስቀስ ወይም በማነሳሳት በሰው ህይወት እና አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል ” በማለት የከሰሰውን በተመለከተ ተከሳሾች ሲቃወሙ አንድ ፓርቲ ሕገመንግስቱን ጥሶ ከተገኛ መከሰስ ያለበት አባላቱን ሳይሆን ድርጅቱ እንደሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተደንግጎ በክሱ እንደተጠቀሰው “እንደ ፓርቲ ወስነው” ከሆነ እንኳን እንደግለሰብ መከሰሳቸውን ተቃውመዋል፡፡
ክሱ የእኩልነት መርህን እንደሚጥስም ጠቅሰው መቃወሚያ ያቀረቡት ተከሳሾች መንግስት በማያሻማ ሁኔታ በህዝብ የተጠየቁ ጥያቄዎች ትክክለኛ እንደሆኑ እና በመልካም አስተዳደር ችግር በወቅቱ መልስ ስላልተሰጣቸው ወደ ረብሻ መቀየሩን እና የሶስተኛ ወገኖች ተሳትፎ እንደሌለበት ገልፆ ኃላፊነቱን በመውሰድ ማሰተር ፕላኑ እንዲቀር ወስኖ ሳለ ተከሳሾችም የዚሁ ህዝብ አካል በመሆናቸው ህዝቡ ይቅርታ ተጠይቆ እነሱ የሚከሰሱበትን አግባብ ተቃውመዋል፡፡
በክሱ እያንዳንዱ ተከሳሽ የሽብር ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለበት ቦታ እና ጊዜ በአግባቡ አለመጠቀሱን የተቃወሙት ተከሳሾች ፈፀሙ በተባለው የወንጀል ድረጊት ክሱ ወደመ ብሎ ሰለሚገልፀው ንብረት ያለበት ቦታ፣ ንብረቱ መቼ እንደወደመ፣ ማን ተጠያቂ እንደሆን በግልፅ ስለማያስቀምጥ ክሱ ውድቅ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን በተመለከተም መቃወሚያ ያስገቡት ተከሳሾች የኢፌዲሪ ብሔራዊ ደህንነት እና አገልግሎት መረጃን ሰብስቦ የማቅረብ ስልጣን ያለው እንጂ መረጃዎችን ሰብስቦ መደምደሚያ እና ትርጉም የመስጠት ስላልሆን አቃቤህግ ያቀረበው ማስረጃ በመስሪያቤቱ የቀረበ መደምደሚያ ስለሆን ወድቅ ይሁንልን ብለዋል፡፡
የሰው ምስክሮችን በተመለከተ አቃቤህግ ያለፍርድቤት ትዕዛዝ ፍርድቤት የምስክሮች ህይወት አደጋ ላይ ሰለመሆኑ ሳይወሰን የምስክሮች ስም ዝርዝር በክሱ አለመካተቱን ተቃወመው እንዲካተትላቸው ፍርድቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ፍርድቤቱ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ከሰማና መተቀበለ በኃላ አቃቤህግ ምላሽ እንዲሰጥ አዟል፡፡
የእስረኞች አያያዝ በተያያዘም የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ማረሚያ ቤቱ ተከሳሾቹን ግንቦት 3 ቀን 2008 ያላቀረበበት ምክንያት የፍርድቤት ትዕዛዝ ስላልደረስን ነው የሚል ምላሽ እንደሰጠ የዕለቱን ችሎት የመሩት ዳኛ ታደለ ተገኝ ደብዳቤውን በማንበብ ለችሎቱ አሰምተዋል፡፡
ተከሳሾች በበኩላቸው ግንቦት 3 ቀን 2008ዓ.ም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለመቅረታቸው ምክንያት የሆነውን ጉዳይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ተከሳሾቹን በመወከል ለፍርድ ቤቱ በቃል አሰምተዋል፡፡
“በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ በመንግስት ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን ለመግለፅ ጥቁር ልብስ ለብስን ወደ ፍርድቤት ልንመጣ ስንል ካላወለቃችሁ አትሄዱም ተባልን፡፡ የትኛውንም ልብስ ለመልበስ የሚከለክል ህግ ስለሌለ አናወልቅም አልን፡፡” ያሉት አቶ በቀለ ገርባ ከፍርድቤት ለመቅረታቸው ምክንያት የለበሱት ልብስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
“ትናንትና ደግሞ በዚህ ክስ መዝገብ ውስጥ ያለን 22 ተከሳሾች በጠቅላላ ልብሳቹን ይዛችሁ ውጡ ተብለን ከማረፊያው ክልል ስንወጣ ልብሶቻችንን ወስደው ሜዳ ላይ ጣሉት፡፡ እኛን ጨለማ ቤት ከተቱን፡፡ ያለምንም ልብስ ምግብ ሳንበላ በካቴና ታስረን ውለን አድረናል” ሲሉ ተናግረው ልብሶቻቸው በጠቅላላ ሰለተወሰደባቸው በባዶ እግር፣ በፓካውት እና በቁምጣ ለመምጣት መገደዳቸውን በሃዘን ሰሜት ተሞልተው ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ ጥቁር ልብስ በተመለከተ የወሰደውንም እርምጃ ሲገልፁ “ከታሰርንም በኃላ ግማሾቻችን ላይ ድብደባ እየተፈፀመብን ነው፡፡ ከኛ የክስ መዝገብ ውጪ በሌላ ክስ ተከሰው በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ክሳቸውን እየተከታተሉ ያሉ ጥቁር የለበሱ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ከሌሎች ክልል ተወላጆች እየተመረጡ እየተደበደቡ ነው፡፡ ይህ በኦሮሚያ ህዝብ ላይ እየተደረገ ያለ ጥቃት ነው” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ተከሳሾቹን ወክለው የተናገሩት አቶ በቀለ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል “በቤተሰቦቻችን እንዳንጎበኝ በማረሚያ ቤቱ ተከልክለናል ፡፡ እንደዜጋ እየታየን አይደለም፡፡ እኔም ላይ በተደጋጋሚ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰብኝ ነው፡፡ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ለህይወታችን ስጋት ሰለሆን ፍርድቤቱ ሌላ ማረሚያ ቤት እንዲያሰቀምጠን እንጠይቃልን፡፡ በዳግም ቀጠሮ ከዚህ ማረሚያ ቤት በህይወት ስለመመለሳችን እርግጠኛ አይደለንም”ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ፍርድቤቱን ወክለው የመሃል ዳኛው ታረቀኝ አማረ በግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን በተመለከተ ብይን ሲሰጡ ማረሚያ ቤቱ በሁሉም ችሎት ማረሚያ ቤቱን ወክሎ የተከሳሾችን ችሎት የሚከታተል የችሎት አሰፈፃሚ እያለ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልደረሰንም ማለቱን በቂ ሆኖ አላገኘነውም ብለዋል፡፡
ተከሳሾች በማረሚያ ቤቱ እየደረሰብን ነው የሚሉትን የመብት ጥሰት አስመልክቶም ዳኛ ታረቀን “አቤቱታችሁን ለፍርድቤቱ በፅሁፍ አስግቡ፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ተመልክቶ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ችሎቱ አለባበስን በተመለከተ ይህን ልበሱ ይህን አትልበሱ የሚልበት ምክንያት የለውም፡፡ የጊዜ ቀጠሮን የሚያስተናግድ ሌላ ማረሚያቤት ስለሌለ ማረሚያቤቱ በአቤቱታችሁ ላይ መልስ እንዲሰጥ አቤቱታውን በፅሁፍ አቅርቡ ብለዋል፡፡
ዳኛው ታረቀኝ ተከሳሾቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደረሰብን የሚሉ ከሆነም ከፍርድቤቱ ትዕዛዝ በተጨማሪ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማመልከት እንደሚችሉም ለተከሳሾቹ ተናግረዋል፡፡
ፍርድቤቱ የስዋኽሊ ቋንቋ አስተርጓሚ እንዲመደብ እና አቃቤህግ የክሰ መቃወሚያውን ተመልክቶ አስተያየቱን እንዲሰጥ ተለዋጭ ቀጠሮ ለሰኔ 20፣ 2008 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ስጥቷል፡፡
ተከሳሾች በከፍተኛ ወከባ፣ ጥበቃና አጀብ በጀርባ በር ተደብቀው የገቡ ሲሆን ታዋቂው ጠበቃ አምሃ መኮንንን እና አቶ ወንድሙን ጨምሮ ስድስት ጠበቆቻቸው አብረዋቸው ነበሩ ፡፡
ምንጭ፡- EHRP
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተመረጡ፤ ፓትርያርኩ በከባዱ ተገሥጸዋል
ለዋና ጸሐፊነት የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የደቡብ ምዕ. ሸዋ ወሊሶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ(በግራ)፤ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የደቡብ እና ምሥራቃዊ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ(በቀኝ)
•ፓትርያርኩ፣ የአስመራጭ ኮሚቴውን ዕጩዎች ካልተቀበሉ ነባሮቹን ብፁዕ ዋና ጸሐፊ እና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለድጋሚ የሦስት ዓመታት የሥራ ዘመን እንደሚያስቀጥላቸው አሳስቧቸው ነበር፤
•“እነርሱንስ ከምታስቀጥሉ እኔን አንሡኝ፤” ያሉት ፓትርያርኩ፣ ማሳሰቢያውን ተከትሎ በምልዓተ ጉባኤው በተሠየመው አስመራጭ ኮሚቴ የቀረቡትን ዕጩዎች በመቀበላቸው፣ በምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ መሠረት፣ የብፁዕ ዋና ጸሐፊው እና የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ምርጫ ተከናውኗል፤
•ለቀጣይ ሦስት የአገልግሎት ዓመታት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ድምፅ ከሰጡት 38 የምልዓተ ጉባኤው አባላት የ22ቱን በማግኘት፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ድምፅ ከሰጡት 38 የምልዓተ ጉባኤው አባላት የ26ቱን በማግኘት በቅዱስ ሲኖዶሱ ተመርጠዋል፤
•በምልዓተ ጉባኤው በአብላጫ ድምፅ የተመረጡት፣ አዲሱ ብፁዕ ዋና ጸሐፊ እና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሚጻፍላቸው ደብዳቤ ይሾማሉ፤
•ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው፥ የቋሚ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊም ሲኾኑ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳዎችን የማዘጋጀት፤ ውሳኔውንና ትእዛዙን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለሚመለከታቸው ማስተላለፍና በተግባር ላይ መዋላቸውን እየተከታተሉ ስለአፈጻጸማቸው ለምልዓተ ጉባኤው ሪፖርት የማቅረብ ሓላፊነት አለባቸው፤
•የመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስፈጻሚ የኾኑት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፥ ከፍተኛ የአስተዳደር አካል የኾነው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ባለሥልጣን እንደመኾናቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚወስናቸውን ጉዳዮች በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ይፈጽማሉ፤ ያስፈጽማሉ፤ መምሪያዎችንና ድርጅቶችን ኹሉ በበላይነት ይመራሉ፤ ማንኛውም ንብረት፣ የገንዘብ ገቢና ወጭ በቤተ ክርስቲያኒቱ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ደንብ፣ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት መከናወኑን ይከታተላሉ፤ ይቆጣጠራሉ፤ በየዓመቱ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም፣ ዕቅድ ክንውናቸውን ያቀርባሉ፤ ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋሉ፤
•ፓትርያርኩ የጥዋቱ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ሲጀመር፣ ከመንበራቸው ተነሥተው፡-“አባቶቼ፣ ወንድሞቼ፥ ይቅርታ አስቀየምኋችኹ” ብለው ትላንት በምርጫው ሒደት ላይ ለፈጠሩት መስተጓጎል የተጸጸቱ መስለው ቢታዩም፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተመልሰው ደግሞ፤ “ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስንና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን አውጡልኝ” በማለታቸው ምልዓተ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝነዋል፤ ይህም ከባድ ተግሣጽም አስከትሏባቸዋል፤
•ምልዓተ ጉባኤው ከስሕተታቸው የማይማሩትን ፓትርያርኩን በሚከተለው ቃል ነበር የገሠጻቸው፡- “የእርስዎ መሠረታዊ ችግር፣ ይህችን ቤተ ክርስቲያን አያውቋትም፤ ለ35 ዓመታት ውጭ ስለኖሩ የአህጉረ ስብከቱን ይኹን የቤተ ክህነቱን የየዘርፍ ሥራዎች አያውቋቸውም፤ ባልዋሉበትና ባላወቁት ሓላፊነት በመቀመጥዎ ሕግንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገው መሥራት አልቻሉም፤ የሚያሳዝነው፥ በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ላይ እጁን ያነሣ አካል አኹንም እርስዎን ሾመብን፤ አኹንም ከጀርባ ኾኖ ያበጣብጠናል፤ ወደ ሰላም፣ ወደ ልማት፣ ወደ ዕድገት እንዳትሔድ፤ ዘወትር የብጥብጥ ዐውድማ እንድትኾን እየሠራ ያለ አካል መኖሩን እኛም እናውቃለን፣ ሕዝቡም ያውቃል፡፡”
•ምልዓተ ጉባኤው ለቀጣይ ስድስት ወራት(ከግንቦት እስከ ሐምሌ እና ከነሐሴ እስከ ጥቅምት) በቋሚ ሲኖዶስ አባልነት የሚያገለግሉ የስድስት ብፁዓን አባቶች ምርጫም አካሒዷል፡፡ ከግንቦት እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሰላማ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፤ ከነሐሴ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓ.ም.፡- ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል እና ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እንዲያገለግሉ በቅዱስ ሲኖዶሱ ተመርጠዋል፡፡
ምንጭ፡-ሐራ ዘተዋሕዶ
ሕገ መንግሥቱን አልተቀበሉም ተብለው ከዳኝነት የተሰናበቱት የሕግ ባለሙያ የጥብቅና ፈቃድም ተከለከሉ
ታምሩ ጽጌ
•ክልከላውን በመቃወም ወደ ሰበር እንደሚሄዱ ገልጸዋል
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በዳኝነት ሲሠሩ የነበሩትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ሆነው አልተገኙም›› በማለት ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዳኝነት ሥራቸው እንዲነሱ ያደረጋቸው የሕግ ባለሙያ፣ የጥብቅና ፈቃድም መከልከላቸውን ገለጹ፡፡
የዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ በተደረገ ውይይትና የአገሪቱ መሠረታዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር በተደረገ ውይይት ላይ፣ ባደረጓቸው ንግግሮች ወይም በሰጡት ሐሳብና በ1997 ዓ.ም. ምርጫን አስመልክተው የተናገሩትን በመጥቀስ፣ ‹‹ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አይደሉም›› ተብለው ከዳኝነት ሥራቸው የተነሱት አቶ ግዛቸው ምትኩ ናቸው፡፡ በስምንት ዓመታት የዳኝነት አገልግሎታቸው ዘመን ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው እንደማያውቁ የሕግ ባለሙያው አቶ ግዛቸው ይናገራሉ፡፡
አቶ ግዛቸው ከዳኝነት ሥራቸው ከተነሱ በኋላ በጥብቅና አገልግሎት ሥራ ለመቀጠል ፈቃድ ለመውሰድ ለፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ የሰጣቸው አጭር መልስ ከዳኝነት የተነሱት ‹‹ሕገ መንግሥቱን አልቀበልም›› ብለው መሆኑን ጠቅሶ፣ ለፍትሕ ሥራ አካሄድ መልካም ሥነ ምግባር አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ ፈቃድ እንደ ከለከላቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ግዛቸው የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጥብቅናውን የከለከላቸው፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 199/1992 ከሚደነግገው ውጪ መሆኑን፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በእሳቸው ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዳኝነት ያነሳበትን ዝርዝር ማስረጃ ዳይሬክቶሬቱ ሳይመረምርና ትችት ሳይሰጥበት መሆኑን ጠቅሰው ለፍትሕ ሚኒስትሩ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ሚኒስትሩም የዳይሬክቶሬቱን ውሳኔ አፅድቀው እንደከለከሏቸው አቶ ግዛቸው አስረድተዋል፡፡
የጥብቅና ፈቃድ መከልከላቸው አግባብ አለመሆኑንና የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ሕገ መንግሥቱን አለመቀበል ፈቃድ እንደሚያስከለክል እንደ መሥፈርት አለመቀመጡን፣ ለስምንት ዓመታት በዳኝነት ሲሠሩ አንድም ጊዜ በሥነ ምግባር ጉድለት ተጠይቀው እንደማያውቁና ለዳኝነት ሲመለመሉ በዋና መሥፈርትነት ተቀምጦ የነበረውን ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር ሲተገብሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ከተመደቡበት የዳኝነት ሥራ ውጪ በተደረጉ ውይይቶች ላይ በሰነዘሩት ሐሳብ ‹‹ሕገ መንግሥቱን አልተቀበልክም›› ተብለው ከዳኝነት ሥራቸው በመነሳታቸው፣ የጥብቅና ፈቃድ ሊከለከሉ እንደማይገባ በመግለጽ ክስ መመሥረታቸውን ጠበቃቸው አቶ ዳማው አስፋው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ያቀረቡትን የክስ ማመልከቻ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎትም፣ የሕግ ባለሙያው የጥብቅና ፈቃድ ቢሰጣቸው የሚገናኙት ወይም አገልግሎት የሚሰጡት ወደ ዳኝነት አካሉ ሄደው መሆኑን ጠቅሶ፣ ‹‹ለፍትሕ ሥራ አካሄድ መልካም ሥነ ምግባር ያስፈልጋል›› በማለት የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጥብቅና ፈቃድ የከለከለበትን መንገድ ተቀብሎ ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አለመሆን በየትኛውም ምዘና ለጥብቅና ፈቃድ ክልከላ ሊውል እንደማይችል የሚናገሩት ጠበቃቸው አቶ ዳማው፣ በሥነ ምግባር ደንቡ አንድ ጠበቃ በተደራቢነት የፖለቲካ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል አስቀምጦ እያለ፣ ‹‹አንድ የሕገ መንግሥት አንቀጽ እንዲሻሻል ጠይቀሃል›› በሚል፣ ከዳኝነት የተነሳን ሰው በፍትሕ ሥራ ውስጥ ገብቶ እንዳይሠራ ፈቃድ መከልከል ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንድ ሰው ሙያውን መርጦ መሥራት እንደሚችል ደንግጎ እያለ፣ ‹‹ይህንን አመለካከት ይዘህ ላንተ ፈቃድ አልሰጥም›› ማለት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ላይ ለዜጎች እኩልነት የሰጠውን ድንጋጌ መቃረንና በዜጎች መካከል ልዩነት መፍጠር መሆኑንም አክለዋል፡፡
የዳኞች አስተዳደር ጉባዔም በውሳኔው ያስታወቀው አንድ ዳኛ በሥራ ላይ ባለበት ወቅት የራሱ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት ሊኖረው ቢችልም፣ ያንን አመለካከቱን በዳኝነት ሥራው ላይ ሊያንፀባርቅና ወገንተኛ ሊሆን እንደማይችል እንጂ፣ ከሐሳብ ሊነፃ እንደማይችል መግለጹን ጠቁመዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አቶ ግዛቸው ከዳኝነት ኃላፊነታቸው ባነሳበት ወቅትም፣ ስለወደፊት የጥብቅና ሥራቸው ምንም ያለው እንደሌለና አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ከጥብቅና ፈቃድ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ሲያነሱ ምክር ቤቱ በዝምታ ማለፉን አስታውሰዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየውም በአንድና በሁለት ስብሰባዎች ላይ በተሰነዘረ ሐሳብ ከሁሉም የሕግ ሥራዎች ላይ መነሳት ሳይሆን፣ ጉባዔው ባመነበትና ጠቅሶ ያሳለፈውን ውሳኔ ማፅደቅ ብቻ እንደሆነም አክለዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረንና ተገቢነት የሌለው በመሆኑ፣ አቤቱታቸውን ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚያቀርቡ የአቶ ግዛቸው ጠበቃ አቶ ዳማው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ