Daily Archives: June 10th, 2016

የሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ አል-ሸባብ 43 የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደሉን አስታወቀ

(አዲስ ሚዲያ) አል-ሸባብ ጥቃቱን የፈፀመው ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በስተሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሃልገን ከተማ፤ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ልዑክ( አሚሶም) አባል በሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ መሆኑን ሮይተርስ እና አል-ጀዚራን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

Ethiopian troops in Somalia

በተለይ የታጣቂ ቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ ሺክ አብዱዓሲስ አቡ ሙሳብ ለሮይተርስ እንደገለፁት ከሆነ፤ ትናንት ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በማዕከላዊ ሶማሊያ ሂራን ክልል ከተማ በሆነችው ሃልገን በፈፀሙት ጥቃት 43 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግደላቸውን፣ ቁጥሩን በይፋ ባይገልፁም በነበረው ውጊያ ከራሳቸው ከታጣቂ ቡድኑም የተገደሉ እንዳሉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በቃል አቀባዩ በኩል በኢቢሲ በኩል ባስተላለፈው መግለጫ 245 የአልሸ-ሸባብ ታጣቂዎችን መግደሉን ቢያስታውቅም፤ በውጊያው ምን ያህል የኢትዮጵያ ወታደር እንደተገደለ የገለፀው ነገር የለም፡፡

የኢትዮጵያ ጦር በኢህአዴግ ውሳኔ ወደ ሶማሊያ ከገባ ጀምሮ በርካታ ወታደሮች እንደተገደሉና ጉዳት እንደደረሰባቸው በተወሰነ ደረጃ ታጣቁ ቡድኑ በተለያየ ጊዜ ካሰራጨው የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ስም እና ማንነት በስተቀር፤እስካሁን በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ስለደረሰ ጉዳት በመንግሥት በኩል ለህዝብ የተሰጠ መግለጫም ሆነ ማብራሪያ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ለተመሳሳይ ተልዕኮ በአፍሪካ ህብረት አሚሶም የተሰማሩ የኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ ወታደሮች ከአል-ሸባብ ጋር በተደረጉ ውጊያዎች የደረሱ ጉዳቶችንም ሆነ ድሎች በተለያየ ጊዜ ለህዝባቸው ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡

የኢህአዴግ መራሹ መንግሥት በይፋ ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ ካዘመተ ከ7 ዓመታት በላይ ቢሆንም፤ እስካሁን በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ስለደረሰው ጉዳት በመንግሥት በኩል ይፋ ተደርጎ ባያውቅም፤ የስርዓቱ ደጋፊ ብሎገሮች በትናንትናው የአል-ሸባብ ጥቃት 9 ያህል የኢትዮጵያ ወታደሮች ሞታቸውን እና 248 የታጣቂው ቡድንም በኢትዮጵያ ወታደሮች እንደተገደሉ ገልፀዋል፡፡

በሐሙሱ የአል-ሸባብ ጥቃት በሶማሊያ ውስጥ ስለተገደሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች የኢትዮጵያ መንግሥት ምን የገለፀው ነገር ባይኖርም፤ ጥቃቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን በይፋ አውግዘዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የቀረበበት ክስ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት አመልክቷል

ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን አስተላልፏል በሚል የሽብር ክስ የቀረበበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ክሱ ተሰርዞለት በነጻ እንዲሰናበት በክስ መቃወሚያው አምልክቷል፡፡

Getachew Shiferaw_Addismedia

ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ጌታቸው አራት ገጽ ያለው የክስ መቃወሚያውን ለችሎቱ አስገብቷል፡፡

ተከሳሹ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጽ 7(1)ን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ያቀረበበት ክስ “በማናቸውም መልኩ በሽብር ተግባር መሳተፍ” የሚለው፣ አንድ ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመን ድርጅት ስም መጥራት፣ የሽብር ድርጅቱ በሚጠቀምበት ሚዲያ መጠቀም ወይም የሽብር ድርጅት አባል ነው የተባለን ሰው ለሽብር ድርጅቱ አንዳችም ፋይዳ በሌለው ነገር ላይ ማነጋገር ሁሉ ይጨምራል በሚል ተለጥጦ መቅረብ እንደሌለበት በመቃወሚያው ላይ አመልክቷል፡፡

ተከሳሽ አቃቤ ህግ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ስለነበሩ ክስተቶች የሽብር ድርጅት አመራር ናቸው ላላቸው ሰዎች መረጃ ማስተላለፍን በሽብር ድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከህጉ አላማም በእጅጉ የራቀ ነው ሲል ተከሳሹ ተቃውሟል፡፡

ስለሆነም የአዋጁን አንቀጽ 7(1) ጠቅሶ ክሱን ማቅረብ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ አንቀጽ 112 ላይ በወንጀል ጉዳይ በሚቀርብ ክስ ስለ ወንጀሉ እና የወንጀሉ ሁኔታ ስለሚሰጠው ዝርዝር ወንጀለኛው የፈጸመውን ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር የተቀራረበ መሆን አለበት የሚለውን አስገዳጅ ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ መጠቀሱ አግባብ አይደለም ተብሎ ክሱ እንዲሰረዝለት አመልክቷል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው በሁለተኛነት ያቀረበው መቃወሚያ የህጋዊነት መርህን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ህገ-ወጥነቱ በህግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጥረውና ቅጣት ሊወስንበት እንደማይገባ በማስታወስ በክሱ ዝርዝር ላይ የተመለከቱ በህግ ወንጀል ናቸው ተብለው ያልተደነገጉ ድርጊቶችን ጠቅሶ ክሱ እንዲሰረዝለት የሚጠይቀውን መቃወሚያ አስገብቷል፡፡

ተከሳሹ በሦስተኝነት ያቀረበው የመቃወሚያ ነጥብ የተከሰሰበትን ወንጀል ለይቶ በማወቅ መልስ ለመስጠት እንዲያስችለው ግልጽ ሊሆኑለት የሚገቡ ነጥቦችን በመጥቀስ ነው፡፡ በዚህ መቃወሚያ ስር ተከሳሹ ከሽብር ቡድኑ ተልዕኮ እንደተቀበለ ከመጠቀሱ በቀር ተልዕኮው ምን እንደሆነ፣ መቼ፣ ከማን እና በምን አይነት መንገድ ተልዕኮውን እንደተቀበለ ከሳሽ ግልጽ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ ተከሳሹ ‹‹የሽብር ቡድኑ በሚጠቀምበት ሚዲያ›› በሚል የቀረበበት ክስ በህግ ቋንቋ ምን ማለት እንደሆነም አልተገለጸም ሲል ጠቃውሟል፡፡

በመሆኑም ከሳሽ እነዚህና ሌሎች በመቃወሚያው ላይ የተመለከቱ ነጥቦችን ግልጽ እንዲያደርግ፣ ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ ግን ክሱ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት ተከሳሹ ለችሎቱ በመቃወሚያው ላይ አመልክቷል፡፡
ችሎቱ አቃቤ ህግ ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያ ተመልክቶ መልስ እንዲሰጥበት ለመጠባበቅ ለሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-EHRP

ኦብነግ የኢትዮጵያን መንግሥት በጭፍጨፋ ከሰሰ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የመንግሥት ወታደሮችና የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ጥቃት አድርሰው ሃምሣ አንድ ሰው ገድለዋል ሲል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ስሞታ አሰምቷል፡፡

ONLF_logo3

ሶማሌ ክልል ውስጥ ጃማ ዱባድ በሚባል መንደር ሰሞኑን የመንግሥት ወታደሮችና የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይሎች በመንደርተኞች ላይ ጥቃት አድርሰው 51 ሰው ገድለዋል ሲል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር – ኦብነግ ከስሷል፡፡

“የመንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች በሌሎች አካባቢዎችም በተለያዩ የቅርብ ጊዜያት ከሦስት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል” ያሉት የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ ሃሰን አብዱላሂ ድርጅታቸው ጉዳዩን ለዓለምአቀፍ ተቋማት ለማድረስ ማስረጃዎችን እያጠናቀረ መሆኑን ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የቪኦኤ የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍል ወደ አካባቢው ደውሎ ያነጋገራቸው የጎሣ መሪ ወታደሮቹ ስድስት ሕፃናትና ሴቶችንም ጨምሮ ሃያ አራት ሰዎችን መግደላቸውን አመልክተዋል፡፡ ሌሎች ምንጮች ደግሞ ወታደሮቹ መንደሪቱን ማቃጠላቸውንና አሥር ሰዎች የገበቡበት እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡ ስለጉዳዩ ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡

ምንጭ፡- VOA Amharic service

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካን ሀገር የፈፀመውን ህግወጥ የቦንድ ሽያጭ ገንዘብ ከነወለዱ እንዲመልስ ተወሰነበት

(አዲስ ሚዲያ) የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካን ህገወጥ የቦንድ ሽያጭ በማድረግ የሰበሰበውን ገንዘብ እንዲመልስ ተወሰነበት። የአሜሪካን የቦንድ ሽያጭና ግዥን የሚቆጣጠረው ኮሚሽን ባቀረበው ክስ መሰረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን በአሜሪካን ባልተመዘገበ የቦንድ ሽያጭ የሰበሰበውን 5.8ሚሊዮን ዶላር እና 6 መቶ ሺህ ዶላር ወለድን ጨምሮ በድምሩ 6.45 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል ተስማምቷል።

sec-logo

የኢትዮጵያ መንግሥት ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. በህገወጥ መንገድ ገንዘቡን ሰብስቦት የነበረው ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ከሆኑ 3,100 ኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ ስለሆነም በቦንድ ግዥ የተሰበሰበው ገንዘብ በሙሉ ከነ ወለዱ እንዲመለስ የተደረገው፤ የአሜሪካን ሴኩዩሪቲ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን (SEC) ህግን ተላልፎ በመገኘቱ መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የአሜሪካን ህግ በመጣስ የቦንድ ሽያጭ ማካሄዱን በማመን፤ የቦንድ ሙሉ ሽያጩን ከነ ወለዱ ለአሜሪካ መንግሥት ለሚመለከተው አካል ለመክፈል መስማማቱን ኮሚሽኑ በዋሸንግተን ዲሲ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

ምንጭ፡- http://www.sec.gov/news/pressrelease/2016-113.html

%d bloggers like this: