Daily Archives: June 14th, 2016

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በድጋሚ ወደ ሐምሌ 4 ተራዘመ

(አዲስ ሚዲያ)  ከሰኔ 27 እስከ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ የታሰበው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በድጋሚ ተራዘመ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሊሰጥ የነበረው ፈተና መከካከል ሁለት የትምህርት ዓይነቶች ቀድመው በማኀበራዊ ሚዲያ ከነመልሶቻቸው መለቀቃቸውን ተከትሎ እንዲቋረጥ የተደረገው ፈተና ከሰኔ 27 እስከ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመስጠት ትምህርት ሚኒስቴር መርሃ ግብሩን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ቅሬታና ተቃውሞ አስከትሎ ነበር ፡፡

Ethiopian Minstry of education
በተለይ ከሰኔ 27-30 ቀን 2008 ዓ.ም. መካከል የረመዳን ፆም ፍቺ በዓል ላይ የሚውል ተቃውሞ በመቅረቡ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቅሬታ በመቅረቡ ፈተናው በአንድ ሳምንት ተራዝሞ ከሐምሌ 4-7 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚሰጥ አስታውቋል ፡፡

ቀደም ሲል ግንቦት ሊሰጥ የታሰበውን መርሃ ግብር እንዲቀየር ያስገደዱት የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎችም ከሐምሌ 4 እስከ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሰጠው አዲሱ መርሃ ግብር ላይ ሌላ ተቃውሞ እንደማያስነሱና ከባለስልጣናቱ ጋር እልህ መጋባቱ አላስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተማሪዎች ከሐምሌ 4 እስከ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ተረጋግተው እንዲፈተኑ ጠይቀዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር እና የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች በየበኩላቸው በየአካባቢው ያሉ መምህራን፣ ወላጆች፣ አስተዳደሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ለተማሪዎች እንዲያደርጉላቸው የትብብር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ዳግም ግጭት ተከሰተ

(አዲስ ሚዲያ)እሁድ ሰኔ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር መካከል ዳግም ግጭት ተቀሰቀሰ፡፡ ግጭቱ የተቀሰቀሰው በሁለቱም ሀገራት ድንበር አካባቢ በሚገኘው ፆረና ግንባር ሲሆን፤ ዘግይተውም ቢሆን ሁለቱም ሀገራት ግጭት መኖሩን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡ ግጭቱን በተመለከተ ቀደም ብሎ መግለጫ የሰጠው የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስቴር “የህወሓት አገዛዝ በፆረና ማዕከላዊ ግንባር ጥቃት ሰንዝሮብኛል፣ አጠቃላይ ዝርዝር መረጃውን በሚመለከት ይፋ እናደርጋለን” ሲል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በበኩሉ “የኤርትራ መንግሥት በፆረና በኩል ትንኮሳ ሲጀምር የአፀፋ ርምጃ ወስደናል፣ ትንኮሳውንም ካላቆመ ተመጣጣኝ ርምጃ መውሰዱን እንቀጥላለን” ማለቱን አስታውቋል፡፡

Ethio_Eritrea conflict area

ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ለእሁዱ ግጭት መከሰት ዋነኛ ምክንያት እና በሁለቱም በኩል ስለደረሰ ጉዳት መንግሥታዊ ይፋ የሆነ ማብራሪም ሆነ መግለጫ የለም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ኤርትራ ፕሬስ ከሆነ፤ የኤርትራ ሰራዊት ሰኞ ጠዋት በወሰደው የመልሶ ማጥቃት ከባድ ውጊያ በደቡብ ፆረና ኩዱ ሃዋይ ወታየኢትዮጵን ድንበር ጥሶ በመግባት 52 ወታደሮች መማረካቸውን ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በተከሰተው ግጭት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ወደፊት እንደሚገልፁ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የአገር መከላከያ ሰራዊት የወቅቱን ትንኮሳ ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ሁለት ቀናት የኤርትራን መንግስት ለታላቅ ኪሳራ የሚዳርግና ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ላደረገው ትንኮሳ መልስ የሚሆን እርምጃ ወስዷል” ብለዋል።

በሁለቱም ሀገራት ድንበር መካከል የተከሰተውም ግጭት ትናንት ከሰዓት በኋላ መቆሙን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳስታወቀ ሀገር ሸገር ኤፍ ኤም በቀትር ዜና እወጃው ዘግቧል፡፡
በተለይ በሁለቱም ሀገራት መካከል በ1990/91ዓ.ም. ከተደረገው ጦርነት ጀምሮ በድንበር አካባቢ “ሰላምና ጦርነት አልባ” ስጋት እንዳንዣበበ ይታወቃል፡፡

%d bloggers like this: