Daily Archives: June 7th, 2016

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ መከላከል አትችሉም ተባሉ

ማህሌት ፋንታሁን

የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ( ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ) አቃቢ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በአንድ የሰው ምስክር ማስረጃዎች አስረድቷል በሚል ተከሳሾች መከላከል ይገባቸዋል ሲል ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

Eyerusalem Tesfaw

ውሳኔውን ተከትሎም መከላከያ ማስረጃዎች ያቀርቡ እንደሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ጠይቆ፣ ተከሳሾች 200 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በጋራ እንደሚያቀርቡ አሳውቀው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በነበሩ ቀጠሮዎችም ምስክሮቻቸውን በዝርዝር አስገብተው ነበር፡፡ እንዲሁም ከዛሬ ግንቦት 30 እስከ ሰኔ 8 ቀን 2008ዓ.ም. ድረስ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፤ የቀጠሯቸው ቀን ሳይደርስ፤ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ጭብጥ እንዲያሲዙ ተጠይቀዋል። እነሱም የምስክርነት ጭብጥ ምስክሮች መሃላ ሳይፈፅሙ መያዝ እንደሌለበት ለፍቤቱ አስረድተው ውሳኔውን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥረው ነበር።

Birhan Tekleyared, et.al

ይሁን እንጂ አራት ወር ሙሉ ፍርድ ቤቱ ሲሰጥ ከነበረው ትዕዛዝ በተለየ “መከላከያ ምስክር ማሰማት የለባችሁም ስለዚህ ለፍርድ ብይን ሃምሌ 13, 2008 ቅረቡ” የሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
ምንጭ፡-ከማህሌት ፋንታሁን ፌስቡክ ገፅ የተወሰደ

በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የቀረበው የሽብር ክስ በንባብ ተሰምቷል

*ተከሳሹ ጥቁር ልብስ ለብሰሃል በሚል በቀጠሮው ሰዓት አለመቅረቡ ታውቋል

Getachew Shiferaw

የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የፌደራል አቃቤ ህግ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሰረተው የሽብር ክስ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡

ተከሳሹ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ሊነበብለት የነበር ቢሆንም ከጠበቃው ጋር ሳይመካከር ክሱ እንዲነበብለት እንደማይፈልግ በመግለጹ በቀጠሮ ሰንብቶ ዛሬ ተነቦለታል፡፡ ከክስ ዝርዝሩ መረዳት እንደተቻለው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ የቀረበው ክስ የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት መተላለፍ የሚል ሆኗል፡፡

አቃቤ ህግ በክሱ ላይ እንዳመለከተው ተከሳሹ ከ24/05/2006 ዓ.ም እስከ 13/04/2008 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ግንቦት ሰባት ከተባለ የሽብር ድርጅት አመራሮች ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስቡክ እና ስልክ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ ተልዕኮ የተለያዩ መረጃዎች በማስተላለፍና በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ፈጽሟል ሲል ጠቅሷል፡፡

ተከሳሹ ‹‹…በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር እየተገናኘ መረጃ በመሰብሰብ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የሽብር ቡድኑ አመራሮች መረጃ በማስተላለፍ….›› በሽብር ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ችሎቱ ክሱን በንባብ አሰምቶ ሲያጠናቅቅ በተከሳሹ ላይ የተጠቀሱ የአቃቤ ህግ የማስረጃ ዝርዝሮችን በተመለከተ እንደገለጸው፣ ተከሳሹ የተጠቀሰበት ማስረጃ የሰነድ ማስረጃ ብቻ መሆኑ ተገልጹዋል፡፡
ተከሳሹ ከግንቦት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በጠዋት እንዲቀርብ የሚል ቢሆንም የእስር ቤቱ አስተዳደር ‹‹ጥቁር ልብስ ለብሰህ ፍርድ ቤት መሄድ አትችልም›› በሚል ጠዋት ሳያቀርቡት ከቆዩ በኋላ ከሰዓት ሊያቀርቡት ችለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ የክስ መቃወሚያን ለመቀበል ለሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- EHRP

ታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታ አሰሙ

(አዲስ ሚዲያ)ታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት በአዲስ አበባ ስታዲየም በይፋ ባደረጉት ውይይት በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ተወያይተው፤ በጉዳዩ ዙሪያ ከፌዴሬሽኑ እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየት 10 ኮሚቴዎችን ሰይመዋል፡፡ በውይይቱ ላይም አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ አትሌት አሰለፈች መርጊያ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አትሌት ፋንቱ ሜጊሶ፣ አትሌት የማነ ፀጋዬ፣ ኮማንደር አበበ መኮንን እና ሻምበል ቶሎሳን ጨምሮ በርካታ ስመ-ጥር አትሌቶች ተገኝተዋል፡፡

logo-olympic-games

አትሌቶቹ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. (እ.አ.አ ከነሐሴ 5-21 ቀን 2016 ዓ.ም.) በብራዚል ለሚካሄደው የሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦሎምፒክ ብቃት ያላቸው አትሌቶች ሊመረጡ እንዳልቻሉ እና አሁንም የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድሮች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መስራት እንደሚፈልጉ እና ለማራቶን ውድድር የተመረጡትንም ቢሆን በስነ ልቦና ደረጃ ሊያግዝ የሚችል ብቃት ያለው አሰልጣኝም ሆነ አመራር ስለሌለ በመጪው ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችላቸው ድሎች አስጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አሁን ያለው ፌዴሬሽን በብቃትም በገንዘብ አቅምም እየተዳከመ ምጣቱን እና አስጊ ደረጃ ላይ መገኘቱን በመጠቆም ብዙ የለፉበትና የለፉለት ተቋም እስኪፈርስ ድረስ መጠበቅ እንደሌለባቸው አስታውሷል፡፡ ያለውን ችግር ለመቅረፍና ለመነጋገር ከዚህ ቀደም የአትሌቶች ማኀበር ፕሬዘዳንት የሆነውን አትሌት ስለሺ ስህንን የአትሌቶች ፒቲሽን የተፈረመበት ደብዳቤ ይዞ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ቢጠይቅም፤ አትሌት ስለሺ አልጠራም በማለቱ ለዛሬው መሰባሰብና ውይይት ምክንያት እንደሆነም ተናግሯል፡፡ አሁን ያለውን ችግርም ለመቅረፍ ከአትሌቶቹ የተውጣጣ ኮሚቴ እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ራሱን ከኮሚቴው አንዱ አድርጎ ዕጩ ማድረጉን በመጠቆም የመጪው ኦሎምፒክ ውጤት አሁን ባለው የፌዴሬሽኑ አሰራር በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ የሴቶች ውድድር ካልሆነ በስተቀር ሀገሪቱ የወርቅ ሜዳሊያ ስለማግኘቷ ጥርጣሬ እንዳለውም ሲናገር ተደምጧል፡፡

በተመሳሳይም አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ገብረእግዚአብሔር፣ አትሌት ፋንቱ ሜጊሶ፣ አትሌት ዳዊት፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት የማነ ፀጋዬ እና መቶ አለቃ መኮንንን ጨምሮ የተለያዩ አትሌቶች በፌዴሬሽኑ እና ተጠሪነቱ ከአትሌቶቹ ይልቅ ለፌዴሬሽኑ በሆነ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኀበር ላይ የነበሩ ብልሹ አሰራሮች እና ቅሬታዎችን ሲያነሱ ተደምጧል፡፡

በተለይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጥሩ አቋም ላይ እያለ እና ብቃት እያለው በማራቶን እጩዎች ውስጥ አለመካተቱ ስፖርቱን በሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ማስነሳቱ ቢታወቅም፤ በታዋቂ አትሌቶችም ዘንድ የቀነኒሳ በቀለ በማራቶኑ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ እንዳይገኝ መደረጉ ተመሳሳይ ቅሬታ እንዳደረባቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ የአትሌት ቀነኒሳ በኦሎምፒኩ ላይ መሳተፍ ውጤት ብቻ ሳይሆን ቀነኒሳ በውድድሩ ላይ መካተቱ በራሱ ለሀገሪቱ ትልቅ ጥቅም እንዳለው በሲድኒ የነበረውን የራሱን እና የደራርቱ ቱሉን ተሞክሮ አስታውሷል፡፡ በጥሩ ብቃት እንዳለና ለኦሎምፒኩም ዝግጁ ሆኖ ሳለ ባለመካተቱ ቀነኒሳም ቅሬታ እንዳደረበት ያልሸሸገው ቀነኒሳ፤ አሁን የተመረጡ ልጆችንም ቢሆን በስነ ልቦናም ሆነ በቴክኒክ ሊያግዝ የሚችል ብቃት ያለው አስልጣኝም ሆነ አመራር ባለመኖሩ ልናግዛቸው ይገባል፤ በበኩሌ አሁን ቢጋብዙኝም በውድድሩ አልገባም ሲል ተደምጧል፡፡

በነበረው ውይይትም በአትሌት ስለሺ ስህን እና በአትሌት መሰረት ደፋር የሚመራው የአትሌቲክ ማኀበር ቢሮም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት ያለው በአትሌቲክ ፌዴሬሽን በመሆኑ ነፃ ሆኖ ለአትሌቶቹ ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጥ ስላልቻለ አዲስ የአትሌቶች ማኀበርም መቋቋም እንዳለበትም ሐሳብ ተነስቷል፡፡ በተለይ አትሌቶቹን ወክሎ ከሚመለከተው አካል ጋር ለመነጋገ፣ ከ2 ወራት በታች ለቀሩት የኦሎምፒኩ ውድድርም ብቃት ያላቸውና ተገቢ አትሌቶች ተሳትፈው የሚፈለገውን ውጤት ይዘው እንዲመጡ ለማገዝ እና ለአትሌቶቹ መብትና ጥቅም የቆመ ማኀበርንም በተመለከተም ለመነጋገር 10 ኮሚቴዎችን በመምረጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

በውድድሩ በ42 የተለያዩ ስፖርት ዘርፎች 206 ያህል የዓለም ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ5 የስፖርት በተለይም በሩጫ፣ በብስክሌት፣ በቦክስ በዋና እና በቴክ-ዎንዶ ውድድር ዘርፎች ለመሳተፍ ማቀዷን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል፡፡ በዚህ ብራዚሉ ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 4 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያ ለማግኘት ግብ ማስቀመጧን ከኦሎምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና መርሃ ግብር በድጋሚ ተቃውሞ ገጠመው

(አዲስ ሚዲያ) የትምህርት ሚኒስቴር ከግንቦት 22-25 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ ያዘጋጀውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በገጠመው ተቃውሞ ፈተናው ከመሰጠቱ ቀናት አስቀድሞ የእንግሊዘኛ እና ሒሳብ ትምህርት ፈተናዎች ከነመልሶቻቸው በማኀበራዊ ገፅ ይፋ በመደረጉ ምክንያት ፈተናው ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ ከሰኔ 27-30 ቀን 2008 ዓ.ም. ብሔራዊ ፈተናውን ለመስጠት አዲሱ መርሃ ግብሩ ይፋ አድርጓል፡፡

 

Ethiopian Minstry of education

ይሁን እንጂ ይህ አዲሱ የዩነቨርስቲ መግቢያ ፈተና ቀደም ሲል በተለይም በኦሮሚያ ለወራት በዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት በመቋረጡ ፈተናው እንዲራዘም የጠየቁት ጥያቄ በመንግሥት በኩል በጎ ምላሽ ባለመገኘቱ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች እርምጃውን እንደወሰዱ አስታውቀው፤አዲስ የወጣውም የፈተና መርሃ ግብር ቢያንስ ለሁለት ወራት እንዲራዘም ምክረ-ሐሳብ አቀርበዋል፡፡ በተለይም እንደ አስተባባሪዎቹ ገለፃ ከሆነ፤ ከሰኔ 27-30 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ የታሰበው ፈተና በኦሮሚያ አካባቢ የነበረውን የትምህርት መቋረጥ እና አለመረጋጋት ግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑ በተጨማሪ በሀገሪቱ የሙስሊሞች ረመዳን በዓል የሚውለው ፈተናው ሊሰጥ በተገለፁ ቀናቶች በመሆኑ በድጋሚ የፈተናው መርሃ ግብር እንዲራዘም ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድምፃችን ይሰማ አስተባባሪዎችም አዲሱ የፈተና መርሃ ግብር የሙስሊም ተማሪዎች በፆምና በዓል ምክንያት ፈተናው ላይ ተረጋግተው ሊቀመጡ ስለማይችሉ ፈተናው ሊራዘም እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው ለፋና ቢሲ እንደገለፁት ከሆነ አዲሱ የፈተና መርሃ ግብር የሙስሊሞችን በዓል ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ እና በዓሉ ከሰኔ 27-30 ቀን 2008 ዓ.ም. ውስጥ ከዋለ፤ በበዓሉ ዕለት ፈተና እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ኃላፊው አቶ መሐመድ ሲራጅ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው አዲሱን የፈተና መርሃ ግብር ሲያወጣ በዓሉን ሳይዘነጋ መሆኑን እና ከፈተናው ጋር ተያይዘው በሚኖሩ ዝግጅቶች፣ የተማሪዎች ጭንቀት እና ከፈተና በኋላ በሚኖር እርማት፣ ውጤት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ምደባ ጊዜንም ታሳቢ በማድረግ ስለሆነ መርሃ-ግብሩ በችግር የወጣ ነው፤ ያለውን ጫና ህዝቡ ይረዳልናል ብለን እናምናለን ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ፈተናው ቢያንስ ለሁለት ወር እንዲራዘም የጠየቁት ጥያቄ እና ምከረ-ሐሳባቸው በመንግሥት በኩል ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ እና ፈተናው ከሰኔ 27-30 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚሰጥ ከሆነ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ፤ በዚህም ምክንያት ለሚደርሰው ማንኛውም ኪሳራ መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል፡፡

ከሰኔ 22-25 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ የታሰበው ፈተና እንዲሰረዝ በመደረጉ ምክንያት ከ285 ሚሊዮን ብር ያላነሰ መንግሥት ላይ ኪሳራ ማድረሱ አይዘነጋም፡፡

 

 

 

%d bloggers like this: