ማንም ከኢትዮጵያዊነት ማማ ሊያወርደኝ አይችልም!

bedlu

በድሉ ዋቅጅራ

ሰሞኑን በፌስቡክ አድራሻዬ የጓዳ መልእክት ደረሰኝ፡፡ ‹‹አንተ በእርግጥ ማንነት አለህ? አንድ ጊዜ ኦሮሞነትህን ክደህ ጉራጌ ነኝ ትላለህ፡፡ ሌላ ጊዜ ኦሮሞ ነኝ ትላለህ፡፡ ያልገባህ ግን ጉራጌውም ሆነ ኦሮሞው ካንተ ሺህ ጊዜ የሚሻሉ ምሁራን አለው፡፡ አይፈልጉህም፡፡ የእንዳንተ አይነቱ መጠራቀሚያ ትምክህተኛ አማራ ስለሆነ እሱን ብትመርጥ ይሻልህ ነበር፡፡ . . . ›› ብሎ ይጀምርና ዋና ሀሳቡ ከዚህ ያልዘለለ አንድ አንቀጽ ይጨምራል፡፡

‹‹ሁሉም ነገር ለበጎ ነው›› እነሆ ታክቶኝ የተውኩትን ፌስቡክ እንድመለስበት አደረገኝ፡፡
ስለማንነት እኔ የማስበው እንዲህ ነው፡፡ . . . .
ትልቁ የራስ ማንነት መስፈሪያ የጎሳ ቁጭበሉ አይደለም፡፡ ሰው እንኳን ከጎሳው ከብሄራዊ መስፈሪያም የሚተርፍ ፍጡር ነው፡፡ የሰው ልጅ ነኝና ጉራጌነት ወይም ኦሮሞነት ሙሉ ማንነቴን አይገልጸውም፡፡ እንኳን ከጎሳ ከኢትጵያዊነትም ይተርፋል ማንነቴ፡፡ በኢሬቻ ላይ ስለሞቱት የምቆስለው ኦሮሞ ስለሆንኩ አይደለም፤ በቅርብ ጊዜ በአማራ ክልል በተፈጠረው ሁከት ስለተጎዱት አማራ ስላልሆንኩ የማይሰማኝ ከሆነ ሰብአዊ ፍጡር ነኝ አልልም፡፡ የሆነ የልቤ ጥግ ላይ በሶርያ ንጹሀን ላይ ስለሚደርሰው የሚደማ ክፍል አለ፡፡ ማንኛውም ሰው በአንድ ቋንቋ ተግባብቶ፣ አንድ የተለየ ባህል አዳብሮ በቋንቋውና በባህሉ ከመገለጹ አስቀድሞ ሰው በመሆኑ ይገለጽ ነበር፡፡ ፈጣሪም አዳም/አደም እና ሄዋን/ሀዋን ሲፈጥር ጎሳ ይቅርና ዜግነት አልነበራቸውም፡፡

ለእኔ ቋንቋዬ የሀሳብ መግለጫ፣ ባህሌ የአኗኗሬ መንገድ ብቻ ነው፡፡ እናቴ ጉራጌ ናት – ክስታኔ፡፡ አባቴና አባቱ ክስታንኛ አቀላጥፈው የሚናገሩትን ያህል ኦሮምኛም ይናገራሉ፡፡ በድሉ – ዋቅጅራ – ደበላ – ወልደጊዮርጊስ – ካሳ እያለ የሚዘልቀው የአባቴ ወገን መጠሪያ ሌሎችን የሚያስጨንቃቸውን፣ ግራ የሚያጋባቸውን ያህል እኔን አስጨንቆኝ አያውቅም፤ ግራም አያጋባኝም፡፡ የማያስጨንቀኝ እነሱን ስለምጠየፍ አይደለም፡፡ የማያስጨንቀኝ በማኛቸውም ማንነት ማንነቴን መበየን፣ ስለማልፈልግ ነው፡፡ እናቴ ኬርአለም ክስታኔ ናት፤ አባቴና አያቴ የኦሮሞና የጉራጌ ድብልቅ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወልደጊዮርጊስና ካሳ ትግሬ ወይም አማራ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ እኔ ውስጥ ያለው ግን ከነዚህ ሰዎች ጎሳ በላይ ነው፡፡ እኔ ውስጥ በደም ከዝርያዎቼ ከተቀበልኩት ይልቅ፣ ካደግኩበት የኦሮሞ ማህበረሰብ ከልጅነት እስከ ጉርምስና የቀሰምኩት ይበልጣል፡፡ በወጣትነቴ ባሌ ለሶስት አመታት፣ ጎንደርና ጎጃም ለአስር አመታት ስኖር ማንነታቸውን አትመውብኛል፡፡ ባህር ተሻግሬም አውሮፓ ላይ ያን ያህል ኖሬያለሁ፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የእኔን ማንነት በእናትና አባቴ ጎሳ (ምንም ይሁን ምን) የሚገለጸው? አዎ የክስታኝና ቋንቋን አፌን ፈትቼበታለሁ፤ እርግጥ ነው በጉራጌና በኦሮሞ ባህል ከልደት እስከ ጉርምስና ጥሪት ቋጥሬበታለሁ፤ አንድም ቀን ግን እራሴን ጉራጌ ወይም ኦሮሞ ብዬው አላውቅም፡፡ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ማንነትን በጎሳ የመበየን ፖለቲካ ተንሰራፍቶ እንኳን ጎሳዬን የማንነቴ መበየኛ አድርጌው፣ ወይን ሆኖ ተሰምቶኝ አላውቅም፡፡ ለዚህ ነው ጉራጌ ወይም ኦሮሞ መሆን አለመሆኔ የማያስጨንቀኝ፡፡ እኔ ከዚያ የበለጠ ሳልሸራረፍ የሚገልጠኝ ማንነት አለኝ – ኢትዮጵያዊንት፡፡

በ1991 አ. ም. የውጭ ትምህርት እድል አገኘሁና ፓስፖርት አስፈለገኝ፡፡ ኢምግሬሽን መስሪያ ቤት ሄጄ እንዲሰጠኝ አመለከት፡፡ ለወራት ጠብቅ አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ በሳምንት ውስጥ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ከአንዲት ሀላፊ ዘንድ አቀረቡኝና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተጻፈልኝን የተባበሩት ደብዳቤ አሳይቼ ጉዳዩን አስርዳሁ፡፡ ያን ጊዜ ከዛሬው የተሻሉ ሀላፊዎች ነበሩ፡፡ በሳስት ቀን እንደሚደርስ ነግራኝ እራስዋ ፎርሙን ትሞላልኝ ገባች፡፡ የተጠየቅሁትን ስመልስ ትጽፋለች፡፡ የባለቤቴን ዘር/ጎሳ ጠየቀችኝ፤ ‹‹አላውቅም›› ስላት፣ ልታምን አልቻለችም – በፍጹም፡፡ ‹‹የልጅህን እናት ማንነት አታውቅም›› ከተጋባን አመት ተመንፈቃችን ነበር፡፡ ጉዳዩ ከህሊናዋ በላይ እንደሆነ ሁኔታዋ ይናገራል፡፡ ‹‹ማንነትዋን አውቃለሁ፣ የማላውቀው ጎሳዋን ነው›› ስላት፣ ስምዋን ጠየቀችኝና ስነግራት፣ ‹‹አማራ›› ብላ ፎርሙ ላይ ሞላች፡፡ ወደባህር ዳር ስመለስ ባለቤቴን ብጠይቃት፣ የኦሮሞና የአማራ ድብልቅ ልትሆን እንደምትችል ነገረችኝ፤ እርግጠኛ ግን አልነበረችም፡፡ ይህን መናገሬ ጎሳን ለማንነት መገለጫ አድሬጌ አለመቀበሌ፣ የዛሬው የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረብኝ የጎንዮሽ ጉዳት አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

የሀገሬ ሰው በጎሳ ተደራጅቶ ለሀገሩን ችግር መፍትሄ ለመስጠት ሲሞክር ማየት፣ በተለይ በዚህ ሉላፊነት እንደሰደድ እሳት እየተዛመተ ባለበት ክፍለ ዘመን፣ ከማሳዘን አልፎ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ በተለይ በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ በጎሳ እየተደራጀ፣ ‹‹የዚህ ጎሳ ተጠሪ እኔ ነኝ አንተ አይደለህም›› እየተባባለ ሲራኮት ማየት፣ ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ታሪክ፣ አሁን ላለችበት ሁኔታ ያላቸው አረዳድ በወቅቱ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተኮርኩሮ የገነፈለ እንደሆነ ለመገመት ምርምር አይጠይቅም፡፡ ‹‹ኦሮሞዎች ተደራጅተን የኦሮሞን መብት እናስከብር፤ አማራዎች ተደራጅተን የአማራን መብት እናስከብር፤ ጉራጌዎች ተደራጅተን የጉራጌን መብት እናስከብር፤ . . . ወዘተ. ብሎ መነሳት፣ በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ዘለቄታዊ የህዝቦች መብት መከበርንና ሰላምን አያመጠም፡፡ እያንዳንዱ ጎሳ የራሱን መብት ማስከበርን ዋና አላማው አድርጎ ከተደራጀ፣ ከሰማንያ በላይ ጎሳዎች በሚኖሩባት ሀገር የህዝቦችን መብት ተከብሮ በሰላምና በፍቅር፣ በመተሳሰብ መኖር ያዳግታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ወይም ኦሮሞ ህዝብ መብት ሊከበር የሚችለው፣ የሀገሪቱ ህዝቦች በሙሉ የእነሱ መብት መከበር እንዳለበት አምነው ለመብታቸው መከበር ከታገሉላቸው ብቻ ነው፡፡ አንዱ ህዝብ ለሁሉም ህዝቦች፣ ሁሉም ህዝቦች ለአንዱ ህዝብ መብት ከታገሉ ብቻ ነው የኢትዮጵያ ህዝቦች መብታቸው ተከብሮ አብረው በሰላምና በፍቅር የሚኖሩት፡፡

ጎሳዊ አስተሳሰብን የሀገራችን ችግሮች መፍቻ አድርጎ ማሰብ ገኖ የወጣው በዚህ ባለንበት ፖለቲካዊ አስተዳደር ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ‹‹የሀገራችን ችግሮች ምንጭ ይህ ጎሳን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነው›› ብለው ተቃውመው የተነሱ ወገኖች እራሳቸው በጎሳ መደራጀታቸው ነው፤ ችግሩን የፈጠረውን አስተሳሰብ ህዳግ ተከትለን፣ አንድን ችግር ለመፍታት መነሳት የህልም ጉዞ ነው – እስከምንባንን እውን የሚመስል፡፡ ችግርን ለመፍታት የችግሩ ምንጭ ከሆነው አስተሳሰብ ማፈንገጥ ያሻል – ለአዲስ መፍትሄ በአዲስ መንገድ ማሰብ፡፡ ‹‹የእኔ ማንነት አዲስ የማንነት መገለጫ፣ ያልነበረ ነው›› ለማለት አይቃጣኝም፤ ግን ከወቅታዊው ጠባብ አስተሳሰብ ካሰፈነው የማንነት መገለጫ ያፈነገጠ ነው፡፡ ክስታንኛ ቋንቋዬ ነው፡፡ በክስታንኛና በኦሮምኛ ባህል ውስጥ አድጌያለሁ፡፡ ግን ሁለቱም ማንነቴን አይበይኑም፡፡ በቋንቋዬ ክስታኔ ስሆን፣ የኦሮሞ ባህሌ ይጎድላል፡፡ በባህሌ ኦሮሞ ስሆን፣ ቋንቋዬ ክስታንኛ ይጎድላል፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነቴ ውስጥ እንኳን ግዝፍ የነሳ ቋንቋና ባህሌ፣ ረቂቁ ህልምና ቅዠቴ አለ፡፡ ኢትዮጵያዊ ስሆን ሙሉ እሆናለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊ ነኝ!

ኢትዮጵያዊ ነኝ!
በላሊበላ አስቀድሼ፣ ሸህ ሁሴን ባሌ የተገኘሁ፤
በአባ ገዳ ተመራርቄ፣ መካ ላይ እርዝቅ ያገኘሁ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ሳነቴ ላይ ውርጭና ጉም፣ ዳሽን ጫፍ ግግር በረዶ፤
ደሎ መና የአዋራ ጭስ፣ ዳሎል ላይ የእሳት እርጎ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ጎጥ አይበቃኝ – የሀገር ስፍር፤
ጎሳ አይገልጠኝ – የሰው ስእል፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!

ኢትጵያዊ ነኝ!!
ይርጋለም ያጋጥኳትን ላም፣ ወለጋ ላይ አሰርሬ፤
ትኩስ እንገርዋን የጠጣሁ፣ አክሱም ላይ ጥገት አስሬ፤
ሰሜን ያለብኩትን ወተት፣ በአርሲ ጮጮ የሞላሁ፤
ጋምቤላ ወተቱን ንጬ፣ የሀረሪ ቆንጆ የቀባሁ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!

ኢትጵያዊ ነኝ!!
ጃውሌ የደንጊያ እጣን፣ ከርቤ ከጊንር ቋጥሬ፤
አቦዳይ ጫት ተዘይሬ፤
ከጂማ አባጁፋር መንደር፣ ከአዎል – በረካ ጀባ፤
ሶዶ ዋዳ ተዘፍኖልኝ – ጎዴ ላይ ቃጢራ አድሬ፤
አፋር ላይ በግመል እንገር፣ ምርቃናዬን የሰበርኩ፤
የሀገሬን ባንዲራ፣ ለአፋር ግመል ማተብ ያሰርኩ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: