በችግር የተተበተበው የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት
ዮሐንስ አንበርብር
– ከ630 ሺሕ ሔክታር መሬት የለማው 76 ሺሕ ሔክታር ብቻ ነው
– መሬቱን የተረከቡ ባለሀብቶች 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር አግኝተዋል
– የቀረጥ ነፃ መብትን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ተገኝተዋል
በጋምቤላ ክልል ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንት በአቋራጭ ለመበልፀግ የጓጉ ባለሀብቶችን የሳበ፣ ከባንኮች የተወሰደውን ብድር ላልተገባ ዓላማ እንዲውል ያደረገና በኪራይ ሰብሳቢነት የተተበተበ እንደነበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥናቱ እንዲካሄድ የወሰኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሆናቸውን፣ 14 ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተወከሉበትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተውጣጡ ባለሙያዎች ያካሄዱት መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በጥናቱ መሠረት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለ623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት የተላለፈ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 409,706 ሔክታር በጋምቤላ ክልል መተላለፉን፣ ቀሪው 220,812 ሔክታር ደግሞ የፌዴራል የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በውክልና ከወሰደው መሬት ያስተላለፈው መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡
ከተላለፈው መሬት ውስጥ እስከ 2008 ዓ.ም. በድምሩ መልማት የቻለው 76,862 ሔክታር ብቻ መሆኑን የጥናት ውጤቱ ይጠቁማል፡፡
መሬቱ ላለመልማቱ በጥናቱ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ባለሀብቶች ለልማቱ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ አብዛኛው ባለሀብት መሬት የሚወስደው አልምቶ ራሱንና አገርን ለመጥቀም ሳይሆን ከባንክ ብድርና ከቀረጥ ነፃ መብት ጋር ተያይዞ የሚገኘውን ጥቅም በማጋበስ በአቋራጭ ለመክበር እንደሆነ ይገኙበታል፡፡
የመሬትና የይዞታ ካርታ መደራረብ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉትም ተጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደርና ደን ልማት ቢሮ ከተመዘገቡ 651 ይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ውስጥ 381 የሚሆኑት ካርታዎች በተለያየ መጠን እርስ በርሳቸው የተደራረቡ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
መሬት ከተረከቡት 623 ባለሀብቶች የእርሻ መሣሪያ ያላቸው 226 ሲሆኑ፣ የእርሻ መሣሪያ የሌላቸው 397 መሆናቸውን ተገልጿል፡፡ ከአጠቃላይ የእርሻ ኢንቨስትመንቶቹ ውስጥ 479 የሚሆኑት ሥራ አስኪያጅ እንደሌላቸው ተጠቁሟል፡፡
ባለሀብቶቹ ከቀረጥ ነፃ መብት የመበዝበዝ አዝማሚያ እንዳላቸው የሚገልጸው ጥናቱ፣ ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 29 ባለሀብቶች የት እንደሆኑ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከወሰዱት መሬት በላይ ትራክተሮችን ወይም ሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስገቡ፣ እነዚህ ትራክተሮች እንዲሁም እንደ ፒክአፕና ሲኖትራክ ያሉ ተሽከርካዎች ደግሞ በእርሻ ቦታው እንደሌሉ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
ከሁሉም በላይ አሳዛኝ ገጽታን የያዘው ከባንክ ብድር አለቃቀቅ ጋር በታያዘዘ ጥናቱ የደረሰበት ግኝት ነው፡፡ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ባላቸው ስምንት ወረዳዎች በተገኘው የመስክ መረጃ መሠረት ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 200 የባንክ ብድር አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 27 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ 161 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጅማ ቅርንጫፍና 12 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ጥናቱ ይዘረዝራል፡፡
ከ200 የባንክ ብድር ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሁለት ተበዳሪዎች በባንክ ዝርዝር ውስጥ ያልተገኙ ቢሆንም፣ በመስክ በተደረገው ማጣራት ተበዳሪ ሆነው መገኘታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ለ200 ባለሀብቶች ለመሬት ልማት፣ ለካምፕ ግንባታ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለማሽነሪ፣ ለሥራ ማስኬጃና ሌሎች ወጪዎች የተፈቀደላቸው ብድር 4.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ እነዚሁ 200 ባለሀብቶች የተረከቡት መሬት 454,261 ሔክታር ሲሆን፣ 194 ለሚሆኑት የዚህ መሬት ባለቤቶች 1.99 ቢሊዮን ብር ብድር መለቀቁን ይገልጻል፡፡ በዚህ ብድር እስከ 2008 ዓ.ም. ብቻ 314,645 ሔክታር መሬት መልማት የሚጠቀምበት ቢሆንም፣ እስካሁን የለማው ግን 55,129 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
ለሥራ ማስኬጃና ለሌሎች ወጪዎች በሚል ርዕስ 1.16 ቢሊዮን ብር ብድር የተለቀቀ ቢሆንም፣ ለምን ዓላማ እንደዋለ ግን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ለካምፕ ማደራጃ ተብሎ የተለቀቀው ብድር 326,876,702 ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 180 ካምፖች በብሎኬትና በቆርቆሮ ሌሎች 19 የሚሆኑት ደግሞ በሳርና በቆርቆሮ መሠራታቸውን ይገልጻል፡፡
በልማት ባንክ ብድር 122፣ እንዲሁም በንግድ ባንክ 62፣ በድምሩ 184 ተሽከርካሪዎች ተገዝተው የተሰራጩ ቢሆንም፣ በመስክ ምልከታ የተገኙት 159 መሆናቸውን ጥናቱ ያስረዳል፡፡
‹‹የብድር ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ስናስገባ በቀጥታ በስልክ ተደውሎ ጉቦ ካልከፈልክ ለሥራ አስኪያጁ አይቀርብልህም፤›› በማለት አጥኝዎቹ ያነጋገሯቸው መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
በተመሳሳይም ‹‹መሬቱን ተገኝተው ሳያዩት ውኃ ይተኛበታል፣ በስልክ ጥቆማ ደርሶናል፤›› በማለት ገንዘብ ካልተሰጣቸው ብድር እንደማይፈቀድላቸው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
የጥናት ዝርዝሩ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱትን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህርን ያካተተ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች በውል ተረክቦ የሚያስተዳድረው መሬት ውል እንዲቋረጥና ክልሎች እንዲያስተዳድሩ ወስኗል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሚና ክልሎችን ማገዝ እንዲሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ለባለሀብቶች የሚሰጥ ብድር ጠንካራ ክትትል እንዲደረግበት፣ እንዲሁም ለተባለው ዓላማ ያልዋሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክትትል በማድረግ ዕርምጃ እንዲወስድ አዘዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹በውይይቱ ወቅት የተሰጡን አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በእኛ በኩል ያሉ ችግሮችን ገምግመን የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንወስዳለን፤›› ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ ገልጸዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ውድነህ ዘነበ አስተዋጽኦ አድርጓል)
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ
በዝዋይ ወህኒ ቤት እስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አሁን የት እንዳለ አለመታወቁን ቤተሰቦቹ አስታወቁ
(አዲስ ሚዲያ) የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና መስራች የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ህዳር 2007 ዓ.ም. በመንግሥት በተመሰረተበት ክስ የ3 ዓመት ፅኑ እስር ተፈርዶበት ዝዋይ ወህኒ ቤት የነበረ ቢሆንም፤ ከፋለፈው ማክሰኞ ህዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረበት ዘዋይ ወህኒ ቤትን ጨምሮ ቃሊቲ፣ የአቃቂ ቂሊንጦ እና ሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ጥበቃ ሰራተኞችና ኃላፊዎች፤ ጋዜጠኛ ተመስገን የት እንዳለ ከቤተሰቦቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ በተጠቀሱት ወህኒ ቤቶች እንደሌለ በመግለፅ በአሁን ወቅት የት እንዳለ ግን እንደማያውቁ መናገራቸውን የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ይፋ አድርገዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ፎቶ ከማኀበራዊ ገፅ
አዛውንቱ ወላጅ እናቱን ጨምሮ ሌሎች የጋዤተኛው ቤተሰቦችና ወዳጆች ቀደም ሲል ታስሮ የነበረበትን እና በፌደራል ደረጃ የሚታወቁ ወህኒ ቤቶች በሙሉ በመሄድ ያለበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ሙከራ ቢያደርጉም ሊያገኙት እንዳልቻሉ የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ በዕድሜ የገፉ አዛውንት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ፋንታዬ እርዳቸው በከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ጋዜጠኛው ቀደም ሲል በእስር ላይ እያለ በደረሰበት ህመም ምክንያት የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት ጠይቆ በተደጋጋሚ መከልከሉ አይዘነጋም፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ ጋዜጠኛ ተመስገን በፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሑፎችን ዋቢ በማድረግ በመሰረተበት ክስ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ማስተዋል ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅትደግሞ 10 ሺህ ብር እንዲቀጣ መበየኑ ይታወሳል፡፡ጋዜጠኛ ተመስገን ከመታሰሩ በፊት መንግሥት ይፈፅማል ያላቸው የመብት ረገጣዎችና ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመተቸት ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ በገዥው የኢህአዴግ መንግሥት 11 ጋዜጠኞችና 1 ብሎገር ኢትዮጵያውያን እንዲሁም 3 የውጭ ዜጋ ጋዜጠኖች በአጠቃላይ 15 ጋዜጠኞችና ብሎገር በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በእስር ከሚገኙ ጋዜጠኞች መካከል ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ፈቃዱ ምርከና፣ጌታቸው ወርቁ፣ አናኒያ ሶሪ፣ ኤልያስ ገብሩ፣ በፈቃዱ ኃይሉ፣ ከድር መሐመድ፣ ዳርሰማ ሶሪ እና የደ ብርሃን ብሎገር ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እንደ ሀገር ውስጥ የሰብዓዊና የፕሬስ ነፃነት መብት ተሟጋቾች እና እንደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መረጃ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የፕሬስ ነፃናት ከሌለባቸው የዓለም ሀገራት ተርታ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዷ ስትሆን፤ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር በአፍሪካ ከጎረቤት ኤርትራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡
ክርስቲያንና ሙስሊም በገለምሶ
አፈንዲ ሙተቂ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለገለምሶው መምሬ ሙላቱ የምትተርክ አንዲት ጽሑፍ ለጥፌ ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ግን ያቺ ጽሁፍ መሀል መንገድ ላይ ተቆርጣ የቀረች ሆና እየታየችኝ ነው፡፡ ስለዚህ ለናንተም፤ ለወገንም፣ ለታሪክ ጸሓፊያንም እንዲጠቅም ይህችኛዋን ሐተታ እጨምርበት ዘንድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በ1981 የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ይመስለኛል፡፡ ከትምህርት ቤት መልስ የጨዋታ ጓዶቼን ፍለጋ “ኒብራ” ከተሰኘው የገለምሶ ከተማ ዋነኛ ጎዳና ወረድኩ፡፡ ጓዶቼን ብዙም ርቀት ሳልሄድ ከትልቁ የጋሽ መሐመድ በከር መደብር በረንዳ ላይ አገኘኋቸው፡፡ እዚያም የኳስ ጨዋታ ሰዓታችን እስኪደርስ ድረስ በትረባና በፉገራ መናቆር ጀመርንና አንዱ ሌላውን ለማብሸቅ ይሞካክር ገባ (በጊዜው ትረባ፣ ፉገራና ለከፋ ጊዜያችንን የሚገፋልን ትልቅ መዝናኛችን ነበር)፡፡ እኛ የነበርንበትን በረንዳ በስተግራ በኩል ተጎራብቶ ወደ ታላቁ የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድና “ሐድራ” ወደሚባለው እስላማዊ ማዕከል (መስጊዱ የሐድራ አንድ ክፍል ነው) የሚያስወጣ መንገድ አለ፡፡ መንገዱ በወቅቱ በጎርፍ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ወደ አስር የሚደርሱ የቀን ሰራተኞች ድንጋይ እየቀጠቀጡ የተቦረቦረውን የመንገዱን የመሀለኛውን ክፍል ይሞሉትና በድንጋዩ ላይ አሸዋ እየመለሱ ይደመድሙት ነበር፡፡
ይህ የምላችሁ መንገድ በጎርፍ የተጠቃው በዚያን ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ዘወትር ክረምቱን ጠብቆ ከካምቦ ተራራ በሚወርደው ሀይለኛ ጎርፍ እየተደረመሰ አሳሩን ያያል፡፡ የከተማው ማዘጋጃ ቤት በመንገዱ ዳርና ዳር የፍሳሽ መውረጃ ቢሰራለትም ጎርፉ በጣም ከባድ በመሆኑ የተሰራለትን መውረጃ በመተው ወደ መሀል መንገድ ዘው ብሎ እየገባ መንገዱን ማበላሻሸቱ የየዓመቱ ትዕይንት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መኪና ይቅርና ሰዎችና የጋማ ከብቶችም በዚያ ዳገታማ መንገድ ሲወጡና ሲወርዱ መከራቸውን ነው የሚያዩት፡፡
ክረምቱ ካለፈ በኋላ መንገዱ ይጠገናል፡፡ ጥገናው የሚከናወነው በአብዛኛው በነጋዴ ግለሰቦች እንጂ በማዘጋጃ ቤቱ አይደለም፡፡ ታዲያ ከላይ በጠቀስኩትና ወሩንና ቀኑን በዘነጋሁት የ1981 አንደኛው ዕለት መንገዱን የሚያስጠግነው ግለሰብ ከወትሮው የተለየ ሆነብኝና በደንብ አየሁት፡፡
ሰውየው ቄስ ነው፡፡ መንገዱ ደግሞ ወደ መስጊድ የሚያስወጣው ትልቁ መንገድ ጎዳና፡፡ ቄሱ ወደ መስጊድ የሚያስወጣውን ትልቁን መንገድ ያስጠግናል!! አጃዒብ! በልጅነት አዕምሮዬ ተገረምኩ፡፡ በጣም ተደመምኩ፡፡ እናም በአቅራቢያችን የነበሩትን ጋሽ መሐመድ በከርን ስለሰውየውና ስለመንገድ ጥገናው ጠየቅኳቸው፡፡
“ዛሬ መንገዱን የሚያስጠግነው ቄስ ነው እንዴ?”
“አይ ቄሱ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ነው”
“የቱ ቤተክርስቲያን?”
“መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ነዋ! በገለምሶ ስንት ቤተክርስቲያን ነው ያለው?”
“ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? የመስጊድን መንገድ ነው እንዴ ቤተክርስቲያን የሚያስጠግነው?”
“እንዴት ሊሆን አይችልም? እነርሱስ ቢሆኑ የኛ ሰዎች አይደሉም እንዴ? እኛስ ቤተ ክርስቲያናቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ቢጠቃ ዝም ብለን እናያለን እንዴ?”
ጋሽ መሐመድ የነገረኝ ነገር እውነት መሆኑን በደንብ ያረጋገጥኩት በአስር ሰዓት ገደማ ቄሱ ለሰራተኞቹ ክፍያ በፈጸሙበት ወቅት ነው፡፡ በነጋታውም እኒያ ቄስ ሰራተኞችን አሰማርተው መንገዱን ሲያስጠግኑ ነበር የዋሉት (እኚያ ቄስ የአካባቢያችን ተወላጅ አልነበሩም፤ ለዚህም ነው ስማቸውን ያልያዝኩት፡፡ ሆኖም ቀጠን ብሎ ዘለግ ያለው ሰውነታቸው፣ ጠይም መልካቸውና ሰልካካ አፍንጫቸው እስከ አሁን ድረስ ይታወሱኛል፤ ብዙ ጊዜም ሰማያዊ ቀለም ያለው ቆብ ነው በራሳቸው ላይ የሚያደርጉት)፡፡
ልብ ያለው ይበል! እንዲህ አይነት ታሪክ በገለምሶ ተፈጽሟል፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ወደ ሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ የሚያስወጣውን መንገድ በራሷ ገንዘብ አስጠግናለች፡፡ በገለምሶ የክርስቲያንና ሙስሊሙ ፍቅር እስከዚህ ድረስ ነበር፡፡ ዛሬ በአካል እዚያ ባልኖርም ይህ የጥንት ፍቅራችን አሁንም ድረስ እንዳልቀዘቀዘ ቤተሰቦቼ ያወጉኛል፡፡
“የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድስ ለክርስቲያኖችና ለቤተክርስቲያኒቷ ምን አድርጎ ያውቃል?” ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም መቼስ! እንዲያ ከሆነ የሚከተለውን ታሪክ ላጋራችሁ፡፡
የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ “ሐድራ” የሚባለው እስላማዊ ማዕከል አንዱ ክፍል ነው- ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ይህ ሐድራ የሚባለው ማዕከል ከትልቁ መስጊድ ሌላ የቁርአን መማሪያ (ቁርአን ጌይ)፣ የዒልሚ መማሪያ (ቤይተል ዒልሚ)፣ የሴቶች መማሪያና መስገጃ፣ የዚክሪና አውራድ ማድረጊያ፣ የአዛውንቶችና የሽማግሌዎች መኖሪያና ሌሎች በርካታ ቤቶች አሉት፡፡ እንዲሁም “ቤይቱል ሐድራ” የሚባለውና የሁሉም እንግዶች ማረፊያ የሆነው ቤት (በስፋቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ልደት አዳራሽ የሚያክል) በዚሁ ሐድራ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህ ቤቶች ሁሉ ከዓመት እስከ ዓመት ተመሳሳይ አገልግሎት ነው የሚሰጡት፡፡ በመውሊድ ጊዜ ግን አገልግሎታቸው ይቋረጥና በበዓሉ ለመታደም የሚመጡትን እንግዶች ያስተናግዳሉ፡፡ በየቤቶቹ ውስጥ ሰለዋትና መንዙማ ይደረጋል፡፡
በገለምሶ የሚከበረው መውሊድ ሞቅ ደመቅ ያለ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለሀገራት ይመጣሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር (ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና የመን) በርካታ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን እንግዶች ለማስተናገድ በትንሹ አስራ አምስት በሬዎችና ሶስት ግመሎች ይታረዳሉ፡፡ ግመሎችና በሬዎቹን የሚገዙት ግን የሐድራው ሰዎች አይደሉም፡፡ ድሮ በሼኽ ዑመር አሊዬ እጅ የተማሩ ሼኮችና ሌሎች የሼኽ ዑመር ወዳጆች ናቸው ከብቶቹን የሚያመጡት፡፡
ታዲያ የሐድራው ሀላፊዎችና የመስተንግዶ መሪዎች ወደነርሱ የሚመጡትን ከብቶች በሙሉ አያርዷቸውም፡፡ በቅድሚያ አንድ ወይም ሁለት በሬ ለሴቶች ይሰጥና የከተማው ሴቶች ከልዩ ልዩ ክፍለ ሀገራት የሚመጡ ወይዛዝርትን እንዲያስተናግዱበት ይደረጋል (በሐድራ ውስጥ ሴትና ወንድ መቀላቀል ክልክል ነው፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ምግባቸውን ለየራሳቸው ነው የሚያዘጋጁት፤ ደግሞም የሁለቱም ጾታ ሰዎች ከተፈቀደላቸው ክልል ውጪ መውጣት የለባቸውም)፡፡
በማስከተልም አንድ በሬ ለስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎች ይሰጣል፡፡ እንዲህ የሚደረግበትን ምክንያት በትክክል ባላውቅም በዘመኑ በነበረው ልማድ የተነሳ የበሽታው ተጠቂዎች መሸማቀቅ ሳይደርስባቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተናግዱ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይመስለኛል፡፡ በሬዎቹ ለሴቶችና ለስጋ ደዌ ህሙማኑ የሚላኩት ግን ለግብዣና ለፌሽታ ብቻ አይደለም፡፡ በመስተንግዶው የሚታደሙት ሰዎች ሰለዋት ስለሚያደርጉና የነቢዩን ገድል በመንዙማ ስለሚያወድሱ ነው፡፡ እንዲያ የማያደርግ ጀመዓ ለመውሊድ ከመጣው በሬ አንዳች ድርሻ የለውም፡፡
ነገር ግን ይህ መመሪያ የማይመለከተው አንድ ክፍል አለ፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን! በዓሉን የማታከብር ሆኖም ከመውሊድ በሬዎች የራሷ ድርሻ የነበራት ብቸኛ አካል እርሷ ነበረች፡፡ ለዚያውም ለርሷ የሚደርሳት አንድ በሬ ብቻ አይምሰላችሁ! ሁለት በሬዎችን ነው በየዓመቱ የምታገኘው፡፡
የዚህ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ዕድሜዬ ከፍ ካለ በኋላ ግን ምክንያቱን የሐድራው መሪ የሆኑትን ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅን ጠይቄ ከአንደበታቸው ተረዳሁ (ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ የሐድራው መስራች የነበሩት የሼኽ ዑመር አሊዬ ልጅ ናቸው- አሁን ዕድሜአቸው ከዘጠናው ተሻግሮ ወደ መቶ ዓመት እየተጠጋ ነው)፡፡
ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ሁለት በሬዎች በየዓመቱ ለቤተክርስቲያን የሚሰጥበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ነበር ያስረዱኝ፡፡
“እነዚህ ክርስቲያኖች ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንደኛው የአዳም ልጆች ናቸው፡፡ በሀይማኖት ብንለያይም የአንድ ሀገር ሰዎች ነን፡፡ ከዚያም አልፎ የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ነን፡፡ በሬዎቹ ወደኛ የሚመጡት በዓላችንን በደስታ ለማክበር እንድንችል ነው፡፡ እኛ በሬዎቹን አርደን በዓላችንን በደስታ ስናከብር ክርስቲያን ወገኖቻችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ እስልምናችን ጎረቤቶቻችንንም ማስደሰት እንዳለብን ያዘናል፡፡ ስለዚህም ነው በሬዎቹን ወደ ቤተክርስቲያን የምንልከው”፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ውብ ባህል ምንድነው የምትሉት? “መቻቻል” ነው የሚባለው ወይስ ሌላ ስም አለው? እኔ ግን “መቻቻል” አልለውም፡፡ ይህ በተመን የማይመነዘር ፍቅር ነው እንጂ “መቻቻል” የሚለው ዘመን ወለድ ታፔላ የሚለጠፍለት አይሆንም፡፡ “መቻቻል” ሲባል አንዱ ወገን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሌላውን የሚያስከፋ ድርጊት በሚፈጽምበት ጊዜ ሌላኛው ወገን በትዕግስት ችሎ ማለፍ ይገባዋል የሚል እድምታ ያለው ይመስለኛል፡፡ በኔ ከተማ ግን ፍቅር ሰባኪ የሆኑት ሼኮች እና ቄሶች ክፋት ሊፈጸም የሚችልባቸውን ሽንቁሮች ሁሉ ቀድመው የደፈኗቸው በመሆኑ “መቻቻል” የሚባለው አነጋገር እዚያ ዘንድ ተራ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ በዚያች እትብቴ በተቀበረባት መሬት ያየሁትና የሰማሁት “ፍቅር” ነው እንጂ “መቻቻል” አልነበረም፡፡
በኔዋ የገለምሶ ከተማ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ነበረን፡፡ በሌላው ኢትዮጵያስ ቢሆን? ዲግሪው (መጠኑ) ይለያይ ይሆናል እንጂ ተመሳሳይ ታሪኮች ሞልተዋል፡፡ እንዲህ በህብረት የኖረውንና ፍቅርን የተቋደሰውን ህዝብ የፖለቲከኞች ወሬ ሆድና ጀርባ ሊያደርገው ከቶ አይቻለውም፡፡ ፖለቲከኞች በሌሎች ሀገራት በስለት እንኳ ተፈልጎ የማይገኝ ይህንን ውብ ባህላችንን በዓለም ዙሪያ ቢያስተዋውቁልን ነው የሚያምርባቸው፡፡
እኛ አንድ ነን፡፡ ወንድማማቾች ነን፡፡ ፍቅር ነን፡፡ ክብር ነን፡፡ ህብር ነን፡፡ ሰሞነኛ ወሬ አያለያየንም፡፡
—–
ተፃፈ በአፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 21 ቀን 2005
እውቁ ፖለቲከኛ እና የኦፌኮ/መድረክ ከፍተኛ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና ታሰሩ
(አዲስ ሚዲያ)የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንደነግ ግንባር (መድረክ) ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ታሰሩ፡፡ ዶ/ር መረራ የታሰሩት በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በተጋበዙት መሰረት ንግግር አድርገው ረቡዕ ህዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸው ታውቋል፡፡ ዶ/ር መረራ የታሰሩት አብረዋቸው ከነበሩ ከሁለት የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጋር እንደነበርም ታውቋል፡፡
ገዥው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ ዶክተር መረራ የታሰሩት “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ቁጥር አንድ አንቀጽ 2 ላይ የተመለከተውን መመሪያ ተላልፈው በመገኘታቸው እና ከአርበኞች ግንቦት 7 መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተው መግለጫ ሰጥተዋል“ በሚል መሆኑን በልሳኑ ፋና ብሮድካሲቲንግ ኮርፖሬት ዘገባ ይፋ አድርጓል፡፡
መንግሥት ባለፈው ህዳር 2008 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን የኦሮሚያ ክልል የፀረ አገዛዝ ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ፤ በተመሳሳይ መልኩ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል እና በደቡብብ ክልል ኮንሶ የተዛመተውን ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ተከትሎ ከ1400 በላይ ዜጎች ሲገደሉ ከአንድ ሺህ ያላነሱ በፀጥታ ኃይሎች ወታደራዊ ርምጃ የቆሰሉ ሲሆን፤ ከ50 ሺህ ያላነሱ ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የፖሊስ መረጃዎችና የሰብዓዊ መብት አራማጆች መረጃ አመልክቷል፡፡የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎችም ዶ/ር መረራ በአውሮፓ ፓርላማ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሚታሰሩ የሚያመለክት ቅስቀሳ ሲያደሩ እንደነበረም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በተለይ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ገዥው መንግሥት መስከረም 28 ቀን 2009 ኣ.ም ጀምሮ ለ6 ወራት ተግባረዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ዚጌ አዋጅ አውጥቷል፡፡ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ጋዜጠኞች፣ የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ የመብት አራማጆችንና ሲቭል ማኀበረሰቡን ጨምሮ በአንድ ወር ብቻ ከ11,706 ማሰሩን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ በጡረታ እንዲሰናበቱ ከመደረጋቸው በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርነት ለ28 ዓመታት ያገለገሉና የፓርላማ አባል የነበሩ ሲሆን፤ ላለፉት 20 ዓመታትም በሀገሪቱ ፖለቲካ ባላቸው ተሳትፎ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቁና ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የፓርቲያቸው ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ ዋና ፀሐፊያቸው አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ደስታ ዲንቃን ጨምሮ በርካታ አመራሮችና አባሎቻቸው ከአንድ ዓመት በፊት መታሰራቸው ይታወቃል፡፡