Daily Archives: January 14th, 2017

የመብት አራማጅ ንግስት ይርጋ የሽብር ክስ ተመሰረተባት

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ጎንድር ውስጥ ለእስር ተዳርጋ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተዛውራ ከአራት ወራት በላይ ያሳለፈችው አክቲቪስት ንግስት ይርጋና ሌሎች አምስት ሰዎች የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

nigest-yirga_amhara_resitance

ንግስት ይርጋ

የፌደራል አቃቤ ህግ ታህሳስ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፈውና ለተከሳሾች ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲደርሳቸው በተደረገው የክስ ቻርጅ ላይ እንደተመለከተው ንግስት ይርጋ ‹‹ከአርበኞች ግንቦት ሰባት የሽብር ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በሰሜን ጎንደርና በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች አመጽ በማስነሳት፣ አመጹን በበላይነት በመምራትና በማስቀጠል…›› የሽብር ወንጀል ድርጊት ተሳታፊ በመሆን ክስ ቀርቦባታል፡፡

ንግስት ይርጋ 1ኛ ተከሳሽ በተደረገችበት የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመለከተው፣ ተከሳሾች በ2001 ዓ.ም የወጣውን የጸረ ሽብር አዋጅ አንቀጽ 3/4/6ን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡

የመብት አራማጅ ንግስት ይርጋ ነሐሴ ወር ላይ በጎንደር ከተማ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ‹‹የአማራ ህዝብ አሸባሪ አይደለም›› የሚል ጽሁፍ የሰፈረበት ቲሸርት ለብሳ በሰልፉ ላይ መታየቷ ይታወሳል፡፡

ክሱ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበውን ክስ በንባብ ለማሰማት ለጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡
ምንጭ፦ EHRP

በእነጉርሜሳ አያኖ መዝገብ 5ት ቀሪ የአቃቤ የህግ ምስክሮችን ለመስማት ተጨማሪ ቀን ተሰጠ

አቃቤ ህግ ታህሳስ 27 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀሪ ምስክሮች ቀርበው እንደሆነ ሲጠየቅ፤ አምስት ምስክሮች እንደሚቀሩት እና ተገቢውን ጥረት ቢያደርግም ሊቀርቡ እንዳልቻሉ በመግለፅ የበለጠ ጉዳዩን እንዲያስረዱለት ከፓሊስ የቀረቡትን ረዳት ኢንስፔክተር ቴድሮስ አዳነ ጠይቋል።

Bekele Gerba

አቶ በቀለ ገርባ

ረዳት ኢንስፔክተሩ የተሰጣቸው ጊዜ አጭር በመሆኑ በተሰጠው ቀጠሮ ሁሉንም ማቅረብ አለመቻላቸውን፤ ምስክሮቹ አካባቢያቸውን አበመልቀቃቸው በአዲሱ አድራሻቸው እያፈላለጓቸው በመሆኑ፤ ራቅ ያለ ቦታ ያሉ ምስክር በመኖራቸው ከፍተኛ የጊዜ እጥረት ስለገጠማቸው በመሆኑ ጊዜ እንዲጨመርለት ጠይቋል። በመቀጠልም አቃቤ ህግ ከቀሩት 5ት ምስክሮች ውስጥ አንዱ ጉጂ ዞን የሚገኝ፣ አንዱ ፀበል ላይ እንደነበረ እና ማስረጃ እስኪያመጣ ጊዜ ስላጠረ፣ አንደኛው አድራሻ ቀይሮ ሌላ ቦታ በመሄዱ በተሰጠው ጊዜ ቀርበው መመስከር እንዳልቻሉ ተናግሮ የተቀሩት ሁለቱ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውን መመስከር ስላልፈለጉ አድራሻቸውን እየቀያየሩ እንዳስቸገሯቸው ተናግሯል። እስካሁን ይመሰክራሉ ከተባሉ 42 ምስክሮች ውስጥ 37ቱን እንዳሰማ የተናገረው አቃቤ ህግ የተከሰሱበትን የክስ ክብደት እንዲሁም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ተግባር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀሪ ምስክሮችን አቅርበው እንዲያሰሙ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች የተሰሙት ምስክሮች በችሎቱ ግፊት እንጂ አቃቤ ህግ ዳተኛ እንደነበረ፤ ምስክሮቹን ማቅረብ ስላልፈለገ እንጂ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበረ፤ የፍትህ ሂደት የሚለካው በሂደቱም ጭምር መሆኑን፤ ከባለፈው ቀጠሮ ጀምሮ በሰበብ አስባቡ ምስክሮችን ለማምጣት በሚል ቀጠሮ መሰጠቱን ተቃውመው እንደነበረ እና የዛሬው ቀጠሮም የመጨረሻው በሚል የተያዘ እንደሆነ ገልፀው ተጨማሪ ቀጠሮ መሰጠት እንደሌለበት ተናግረዋል።

“እንደሚታወቀው ከታሰርን ሁለት ወራችን አይደለም። አንድ አመት አልፎናል። እነሱ ቤታቸው እያደሩ እኛን እያሾፉብን ነው። በአንድ ቀን ብዙ ሺዎችን እያሰረ ያለ መንግስት፤ እንዴት ነው 5ት ምስክሮችን ማቅረብ ያልቻሉት? ” በማለት የኦፌኮ ም/ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ተጨማሪ ቀጠሮ መኖር የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል። አቶ ደጀኔ ጣፋም ተቃውሟቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል። “አቃቤ ህግ ሲናገር 2ቱ አዲስ አበባ ናቸው ብሏል። ለምን አልቀረቡም እስካሁን? ክሳችን መጀመሪያም የፓለቲካ ክስ ነው አሁንም የፓለቲካ ድምዳሜ ነው የምንሰማው። እንዲሁ እንደከሰሳችሁን እንዲሁ ፍረዱብን። ወይስ ፍትህ አለ ለማስባል ነው? የኛን እና የናንተን ጊዜ ለምን ይፈጃሉ? ጉጂ እኮ ወርቅ የሚዘረፍበት ነው። እንዴት ከዛ አንድ ሰው ማምጣት ይከብዳቸዋል? አቃቤ ህግ ሌላ ጫና ከሌለባቸው በህጉ አግባብ ይስሩ። ፍርድ ቤት በየጊዜው እያሳሰሰባቸው ነው ምስክር ይዘው ሚቀርቡት። ያልቀረቡ ምስክሮችን በተመለከተ ከቀበሌ ደብዳቤ ይዘው ቀርበዋል ወይ? አልቀረቡም! የፍርድ ቤት ትእዛዝ እየተከበረ አይደለም። እናንተም የካድሬ አይነት ሳይሆን የባለሙያነት አሰራር ስሩልን።” በማለት ሌላ ቀጠሮ መሰጠቱን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።

“አቃቤ ህግ ዛሬ አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን ብሏል በወቅቱ ቀጠሮ ሲሰጥ ለምን አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን አይበቃንም አላለም? ከቀበሌ ይቅረብ የተባለው ማስረጃ አልቀረበም። የችሎቱ ብይን መከበር አለበት። ማእከላዊ ሲያሰቃዩን የነበሩ ፓሊሶች ናቸው ዛሬ ቀርበው ያልተገባ ተጨማሪ ቀጠሮ እየጠየቁ ያሉት።” ሲል የተጨማሪ ቀጠሮውን ጉዳይ ተቃውሞ አሰተያየታቸውን የሰጡት አቶ አዲሱ ቡላላ ናቸው።

ዳኞች ከተማከሩ በኋላ አቃቤ ህግ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ፤ ተከሳሾችን ደግሞ የፓለቲካ እስረኛ ብሎ ነገር እንደሌለ፣ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚረዷቸው፣ እንዲያውም ማነፃፀር ባይገባም ከሌላው መዝገብ ሲተያይ በፍጥነት እየሄደ መሆኑን፣ እነሱም [ተከሳሾች] መከላከያ ምስክር በሚያሰሙበት ጊዜ ምስክሮችን ለመስማት ጊዜ እንደሚሰጡ በመግለፅ ፓሊስ በ15 ቀን ውስጥ ከየትም ፈልጎ ምስክሮቹን እንዲያመጣ፤ የማይገኙ ከሆነም ይኖሩበት ከነበረው ቀበሌ ደብዳቤ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥተዋል። አቃቤህግ የተሰጠው ጊዜ አጭር እንደሆነ በመግለፅ ትንሽ ረዘም ያለ ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ዳኞች ጥያቄውን ሳይቀበሉት፤ ፓሊስ የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ በቀጠሮው ቀን እንዲያቀርብ አዘዋል።

የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ መልካሙ የሚሰጠው ቀጠሮ የመጨረሻ እንዲሆን በሚል ላቀረቡት ሃሳብ፤ የመጨረሻ ቀጠሮ የሚባል እንደሌላ አሳማኝ ምክንያት ከተገኘ ሌላ ቀጠሮ ሊሰጥ እንደሚችል፤ አሳማኝ ምክንያት ካልተገኘ የመጨረሻ ባይባልም የምስክር የመስማት ሂደት ሊቋረጥ እንደሚችል በመጥቀስ ቀጣዩ ቀጠሮ የመጨረሻ መባል የለበትም ሲሉ ዳኞች መልስ ሰጥተዋል።

ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 15 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀጠሮ ተይዟል።

ምንጭ፦EHRP

በማንነት ፖለቲካው ምስቀልቅል የአማራ ብሔረተኛነት ተጽዕኖና ተግዳሮቶቹ

የሱፍ ያሲን
yussuf.yassin @gmail.com

yesuf-yasin

የሱፍ ያሲን

1. አማራ ከሰኔ (1983) ኮንፊረንስ እስከ ጥቅምት (2009) ስብሰባ

አማራ ወያኔ ኢሕዴአግ በጠራው የአዲስ አበባ 1983ቱ (1991) የሰኔ ኮንፊረንስ አልተወከለም ነበር። በቅርቡ በዋሽንግተኑ የጥቅምት 2009 (2016) በኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ (ኢሃን) ስብሰባ ላይም አልተወከለም ተባለ። በሁለቱም ስብሰባዎች አማራ ተገቢ ውክልና አላገኘም ነው አንዱ ቅሬታው። በመጀመሪያው ኮንፊረንስ ውክልና የተነፈገው በብሔረሰቡ ስላልተደራጀ ነው የሚል ምክንያት ነበር በኮንፈረንሱ አዘጋጆች የተሰጠው። ላሁኑ “አለመወከል” የተሰጠው ምክንያትም የአማራ ብሔረተኞችን አላረካም እንዲያውም አስቆጣ እንጂ። እንዲያውም የሚወክለው ሰው ጠፍቶ አማራ ባንድ ሰው ተወክሎ ነበር መባሉን በቅርቡ በሲያትል የተሰበሰቡት የአማራ ድርጅቶች ወኪሎች እንደ ስድብ ነው የቆጠርነው ነበር ያሉት። የመጀመሪያው ወይም የ 1983 ቱ “አለመወከል” አማራን አዲሱ መንግሥት እነሱን የሚመለከትበትን መነጽር አመላካችና የመከራ ደወል ጅማሮ ነበር ማለት ይቻላል። ምናልባት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አማራ በራሱ መደራጀት እንዳለበት የተገነዘቡበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው ማለት ይቻል ይሆናል። ለሁለተኛ ግን አማራ ከ25 ዓመት በኋላ በራሱ እንዲደራጅ ተጨማሪ አንደርዳሪ ግፊት አሳርፎ አልፏል። በተጨማሪም ምናልባት ሰሞኑን በማሕበራዊ ሜዲያ ለሚንመለከተው እንካ ስላንቲያና መፈራረጅ ቀጥተኛ ምክንያት ሆኗል ማለትም ያስኬዳል።

በሁለቱ ስብሰባዎች መሃል ግን በድልድዩ ሥር ብዙ ውሃ ፈሷል (so much water has passed under the bridge) ፈረንጆች እንደሚሉት። በሁለቱ ስብሰባዎችና መካከሎች የአማራ ማንነት በርካታ ውጣ ውረዶችን አስተናግዷል። በርካታ እንግልቶች በማህበረሰቡ ላይ ደርሰዋል። የአማራ የማንነት ትግሉ በርካታ አባጣና ጎርባጣ መንገዶችን ተጉዟል።

የአማራን በአማራነት አደረጃጀት እና ብሔረተኛነት ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እስከ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አመራር በርካታ የእድገት እርከኖች ተረማምዷል። ኢህዴንን ወደ ብአዴን ከቀዳማዊ መአሕድ እሰከ ዳግማዊ መአሕድ ከበደኖ ፍጅት እስከ ከጉራፈርዳና የቤን ሻንጉል መፈናቀሎች እንዳሉ ሆነው፡፡ በመሃሉ የእስታቲስትክስ ዋና መሥሪያ ቤት የአማራ ሕዝብ ቁጥር የመቀነሱ ዘገባ (ሪፖርት) በዚያ መሃል የተከሰተ ነበር። ሴቶች እንዳይወልዱ ከማምከን እስከ ጄኖሳይድ የሚደርሱ ሰቅጣጭ ወንጀሎች ድረስ ይሄዳሉ ክሶቹ። ወደ ኋሊት ተኬዶ እስከ ስመጥፉው የሕወሓት 1968ቱ ማኒፈስቶ ድረሰ መመለስ ይቻላል ይሆናል። እንዲያውም ትንሽ የኋሊት እንድርድሮሹን እስከ የ1969ኙ የዋለልኝ መኮነን “የብሔረሰቦች ጉዳይ” አርቲክል ድረስም መሄድም ይቻል ይሆናል። እነዚህ ሁለት ሰነዶች አማራን እንደ ጠላት የፈረጁና ለተከተለው ጥፋት ያመቻቹ ዋቢ መጣቀሻዎች ተብለው የሚገመቱት ናቸውና፣ በነገዱ ብሔረተኞች። የወልቃይት-ጠገዴ አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋልን ተከትሎ የተቀጣጠለው የጎንደርና የጎጃም ገበሬና የከተማ ሕዝብ መነሳሳት ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ኹነት ነው በተለይም ከኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ወደ ትግራይ መወሰድ በኋላ መፈክሩ አማራ ተደራጅ ሳይሆን ተነስ፣ ተባበር፣ መክት ነው! እንደ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የአማራ ማንነት ተጋድሎና ብሔረተኛነትን ያጦዘው ጉዳይ አልነበረም ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። ዛሬ አማራ በነገዱ ይደራጅ ወይስ?… የሚለው ጥያቄ የአማራ ተወላጆችንም ሆነ ቀሪውን ኢትዮጵያዊ አያሳስብም። መነጋገሪያ ርእስም አይደለም፣ ብዙዎቹ ዘንድ። ምክንያቱም አማራ ካንድ ድርጅት በላይ ተደራጅቶ ይገኛል። አዲስ የተቆጡ አማራ ወጣቶች (Angry Amhara Young Men) አመራር የተቆናጠጡበት ከግማሽ ደርዘን ያላነሱ የአማራ ድርጅቶች ተመስርተዋልና። ከፊሎቹም ሰሞኑን በአሜሪካ እየተዋሃዱ ይገኛሉ።

በ1983ቱ አለመወከልና በ 2009 “አለመወከል” ቅሬታ መሃል በአማራ አደረጃጀት መሠረታዊ ለውጥ ተካሄዶበታል። በቅርጽም በይዘትም። በአቅጣጫውም፣ ገላጭ ባሕርያቶቹም። አማራ አለ ወይም የለም የሚለው ክርክርም ሆነ በማንነቱ ይደራጅ ወይስ አይደራጅ እሰጥ አገባም ካበቃ ሰንበትበት ብሏል። አማራ በምን መልኩ ተደራጅቶ ነው ከአጥቂዎች ራሱን መጀመሪያ መከላከል ብሎም በስሙ የተደራጁትን እንዴት ተግባራቸውን አቀናጅተውና አስተባብረው እንዲያውም ተዋህደው ነገዱን በወያኔ ከተደገሰለት ጥፋት የማዳኑን ተግባር የቅድሚያ ቅድሚያቸው አድርገው መንቀሳቀሱን የሚያያዙት? የወቅቱ ጥያቄ አማራ አለ? የለም? የሚልም ወይም ይደራጅ? አይደራጅ? ሳይሆን የተቀጣጠለው የአማራ ተቃውሞና ተጋድሎ አቅጣጫው ወዴት ነው? በሃገሪቷ የነጻነት ትግል ላይም ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳርፋል። አልፎ ተርፎ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ ምን ዓይነት እንደምታ ይኖረዋል? እየሆነ መምጣቱ ግልጽ ነው።

የእነዚያ እድገቶችና ክሶች ትክክለኛነትንም ማጣራትም ሆነ መመርመር ከዚች አጭር መጣጥፍ ማቀፍና አቅም ውጭ ነው። የአማራ ብሔረተኛነት እንቅስቃሴን ውልደት፣ እድገትና ውጣ ውረዶቹን ቃኝተን እንቅስቃሴው በአሁኑ ወቅት ያለበትን ደረጃ በዚህ መጣጣፍ በሰፊው ለመተንተን መሞከር አስቸጋሪ ይሆናል፣ እዚህ የአማራ “ብሔረተኛነት” የደረሰበትን እድገት ደረጃ ተመልክቶ፣ በሃገሪቷ ለውጥ ብሎም በሕልውናዋ ላይ የሚያሳርፈውን ተጽእኖ፣ ጫናና የሚጫወተውን ሚና መቃኘቱ አስፈላጊ ነው። በተለይም በምንገኝበት ባሁኑ በአተረማማሹ የማንነት ፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ሆነን።

የአማራ “ብሔረተኛነት” እና የተደቀኑበት ተግዳሮቶች

በአሰባሳቢ ማንነት መጽሓፌ የኦሮሞ ብሔረተኛነት ራሱን በቻለ ምዕራፍ (የኦሮሞ ብሔረተኛነት፣ የማንነት ፖለቲካና ተፈታታኝ ተግዳሮቶቹ) እንዲፍታታ የተመረጠበት ምክንያት ብዙ አያመራምርም። የኦሮሞ ብሔርተኞች ጥያቄ ኢትዮጵያ አንደ አገር የመቀጠል ወይም የመበታተን ወሳኝ ሚና አለው ከሚለው እሳቤ በመነሳት ነው። በተባለው ምዕራፍ እንደተደረገው አዲሱን የአማራ ማንነት ታጋድሎና ብሔረተኛነት ከኦሮሞ ማንነት ተጋድሎና ብሔረተኛነት ጋር ማነጻጸሩ ማስኬዱ አጠያያቂ ነው። በምዕራፉ የተፍታቱት የኦሮሞ ብሔረተኛነት እድገት፣ አነሳስ፣ የወል የሰቆቃ ታሪክ፣ የኦሮሙማ አይድዮሎጂ ቀረጻና የታጋረጠበት ተግዳሮቶቹ ከሥር መሠረቱ ይለያሉ። ዛሬ በኢትዮጵያ ከሚታዩት የብሔረሰብ (ነገድ) ብሔረተኛነት ጋርም ቢሆን ማወዳደሩም ሆነ ማነጻጸሩ አግባብነቱም አጠያያቂ ነው። እንዲያውም በሌሎች ሃገራት ከተመለከትናቸው ከየትኛው ሃገር ብሔረተኛ እንቅስቃሴ የሚመሳሰልበት ገላጭ ባሕሪያት በቀላሉ ማግኘት አይታሰብም። ማንኛውም የሃገሪቷ አስተዳደር ያልተማከለ (Decentralize) የማድረጉ ጥረት በጥርጣሬ ዓይን በመመልከቱ ረገድ የአማራ ብሔረተኛነት ከቀድሞ ዩጎስላቪያው የሰርብ ሕዝብ ብሔረተኛነት ጋር የሚጋራው ገጽታ አለው። ሰርቦች ከቀድሞ ዩጎስላቪያ ሕዝብ 40% በመሆናቸው በጀርመንኛው ሊተረቸር ስታቲስ-ቮልክ (Staatsvolk) ወይም የሃገሬው ዋልታ ሕዝብ ይሰኙ ነበር። እርግጥ የቁጥር አብላጫ የሆነው ኦሮሞ ሳይሆን የኢትዮጵያ የሀገር-መንግሥት መሠረተ-ሕዝብ አማራ ነው ሊባል የሚቻል ይመስለኛል።

አማራው በዋናነት የተጋረጠበት ተግዳሮት ከኢትዮጵያዊነትና ከኢትዮጵያ ማንነት ጋር ያለው ቁርኝት ነው። የአማራ ብሔረተኛነት ከኦሮሞም ሆነ ከሌላ ሃገር ብሔረተኝነቶች ጋር የማይመሳሰልበት ገላጭ ባሕሪያትን ደግሞ መመልከት ተገቢ ነው። ከዚያ በፊት ራሱ የአማራ “ብሔረተኛነት” የብሔረተኛነት ፍቺ፣ ትርጉምና መመዘኛዎች ያሟላል ወይ መባሉ ሊያስፈልግ ነው። ለምን ቢባል? የአማራ ማንነት ትግልና ተጋድሎ ከራስ መንግሥት ወይም የራስ ትድድር መመሥረት ጋር የተቆራኘ ስሜት፣ እንቅስቃሴና ኢድዮሎጂ ባለቤት አለመሆኑን በእሳቤ ከወሰድን። አንዱና ዋነኛው የብሔርተኝነት መገለጫ የአንድ ማኀበረ ፖለቲካዊ ስብስብ በአንድ የራሱ መንግሥት ሥር ወይም የራሱ ራስ-ገዝ አሃድ ወይም ፌደራላዊ አሃድ መጠቃለል ከስሜት አልፎ ወደ ፖለቲካዊ አይድዮሎጂ የተቀየረ ፍላጎትና ምኞት መላበሱ ሂደት ነው። በኦሮሞ ብሔረተኞች ዘንድ የተመለከትነው “ኦሮሙማ” ዓይነቱ ርዮተ ዓለም መሰል አማራነት የሚሰኝ አይድዮሎጂ መመልከት እስካሁን አልቻልንም። ከኢትዮጵያዊነት በስተቀር የምትል ሓረግ መጨመር ሊያስፈልግ ነው።

አሁን ባለበት ሰዓት አማራ አለ ወይስ የለም ሙግት አብቅቶ፣ አማራ ይደራጅ ወይስ አይደራጅም ሙግትም እልባት አግኝቶ፣ ብዙዎቹ አማሮች የመደራጀቱን አስፈላጊነት ከተዋሃዷቸው በኋላም ቢሆን የአማራን ስሜት፣ እንቃስቃሴ እንደ ብሔረተኛ እንቅስቅሴ ራሱን የሚመለከትበት መነጸር ከሌላው ይለያል። የሞረሹ አቶ ተክለ የሻው አንድ የአሮሞ ነጻነት ግንበር ተወካይ Welcome to the club ባለው ጊዜ እኛ የተደራጀነው እናንተ ለተራጃችሁበት ዓላማ አይደለም ብዬ መለስኩለት ነበር ያለው ። ሁሉም አማራ በማንነት ወገንተኛነቱ የተደራጀው የደረሰበትን ጥቃት ለመመከት ነው የምትለዋን ልዩነት ሊያሰምርበትና አጽንኦት ለመስጠት ይሻል።

የአማራ ማንነትና ለማንነቱ ያቀጣጠለው ተጋድሎ ጥንካሬው እሱ ነው። ተግዳሮቱም እሱ ነው። ከአንድነት ኃይሎች ጋር የፈጠረው አለመግባባት ምንጩ ይኸው አስቸጋሪ ትስስር ነው ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። አብዛኛው የአማራ ኤሊት በኢትዮጵያዊነቱ እስከ ተደራጀ ድረስ እኔ አማራ በማንነቱ ቢደራጅ ግድ የለኝም ማለቱ ለእነዚህ በአማራ ድርጅት ለታቀፉ ወጣት አደራጆች ተግባር ቀላል አይሆንም። አልሆነምም።

ብሔርተኝነት አንድ ስብስብ የራሴ ናቸው የሚላቸውን አባላት በአንድ መንግሥት አሃድ ወይም (ትድድር) ሥር ለማጠቃለል ያለው ምኞት ተግባራዊ የሚያደርግበት ስሜት፣ እንቅስቃሴና አይድዮሎጂ ነው ብለን ከተቀበለን ዘንዳ ከመንግሥት ማዕቀፍ ውጭ ሊታሰብ የሚችል ብሔርተኛነት እምብዛም አያጋጥምም።

የራስ ስብስብ ጠቅልል መንግሥት እንደ መዳረሻ ግብ ያላደረገ እንቃስቃሴን እንደ አንድ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ መመልከቱ ያስኬድ እንደ ሆነ ራሱን የቻለ የቲዮሪ ጉዳይ ነው። አንድ ጉዳይ ግን ግልጽ ነው። በአማራው ወገንተኛነት ላይ የተመሰረተ ስሜትና እንቅስቃሴ ብንመለከትም ቅሉ የራሱን መንግሥት የማቋቋም ትልምና ዓላማ አንግቦ የተነሳ የአማራ ኃይል በቦታው የለም። የአማራ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ የራሱን መንግሥት የመመሥረት ዓላማ የለውም። አንዳንዶች የአማራ የራሱን መንግሥት ምስረታ እንደ አንድ አማራጭ ዕቅድ “Plan B” አድርገው ይዘዋል የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። አማራ ከኢትዮጵያዊ ማንነትና ብሔረተኛነት ጋር ያለው ቁርኝት አሁንም በቦታው እንዳለ ነው። ይህ ነው የአማራ ትግልንም ሆነ ብሔረተኛነት ከቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን የትግል አጋርነት ውስብሰብ ያደረገው። ወደ ቲዮሪ ብዙ ሳንዘፈቅ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በግምት ብንወስድ እንኳን። እርግጥ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የማንነት እውቂያ ጥያቄ ቢሆንም ቅሉ ያንድ በሌላ ክልል የተከለለ መሬቴ ወደ ራሴ ክልል እንደ ገና ተመልሶ ይካለልልኝ ባሕርዩና ገጽታው ነው ጎልቶ የሚታየው። ድንበራችን ተከዜ ነው የምትለው መፈክርም ድንበር አካላይ ይዘት አላት። ስለዚህ የእኛ መሬት ቁራጭ አካል የነበረው መሬት ይመለሰልን ነው ጥያቄው። ፈረንጆች irredentist የሚሉት መሬት አስመላሽ እንቅስቃሴ ነው። One who advocates the recovery of territory culturally or historically related to one’s nation but now subject to a foreign state ይላል irredentis ፍቺው። እሱም ቢሆን ለሰፊ የፖለቲካ ዓላማ መቀስቀሻ መሣሪያነቱ ነው የሚጎላው። ማንኛውም ሃገሪቷን ያላማከለ የአስተዳደር አወቀቃቀር የመጠርጠር ዝንባሌው ከቀድሞ ዩግስላቪያ ከሰርብ ብሔረተኛነት ጋርም ያመሳስሏል። ልክ ሰርቦች እንደሞከሩት ግዛታዊ አይደፈርነትና ሙሉነት (territorial integrity) አማራው በወልቃይት-ጠገዴ ወደ አማራ ክልል ተመልሶ እንደገና ይካለልልኝ የሚል ጥያቄ መልክ ተላብሷል።

ከላይ እንደተመለከትነው በአሮሞ ብሔረተኞች “Welcome to the Club” እንኳን ደህና መጡ! አቀባባልም ሆነ ስለ አማራ ብሔረተኛነት ዲሞክራሲያዊነት የተቸራቸውም ውዳሴም ሆነ የምስክር ወረቀት በጸጋ የተቀበሉ አይመስሉም። አንዱ የአማራ ብሔረተኛ ድርጅት እንዲያውም “አማራ የሚደራጀው እንደ ኦነግና ወያኔ ዘረኛ ለመሆን አይደለም። አማራ የሚደራጀው የተጋረጠበትን አደጋ ተቋቁሞ በሰፊው ያባቶቹ አገር የአገሩ ባለቤት ሆኖ ለመኖር የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር ነው። አማራ የሚደራጀው ለዚህ ቅዱስ ተግባር ነው!” ይላል። ይህ ዓይነቱ የራስን አደረጃጀት ልዩ መሆን ለይቶ ማመስገን ሥር የሰደደውን አለመተማመን የበለጠ ያጎላ እንደሆነ ነው እንጂ እምነትንና የትግል አጋርነትን አያጸናም መቼም። ብሔረተኛነትን ላይ “ቅድስና” መደረቡ ደግሞ ተጨማሪ ጥያቄን ይጭራል። “ቅዱስ” ብሔረተኛነት ካለ የግድ ተቃራኒው ሊኖር ነው መባሉ አይቀሬ ነው። ”ያልተቀደሰ ብሔረተኛነት” ማለቴ ነው። የአማራ ብሔረተኛነት መደረሻው ግቡ ኢትዮጵያዊነት ነው ይሉናል። ሌላው ብሔረሰብ ብሔረተኛነትስ መዳረሻ ግቡ ምን ሊባል ነው? የአማራ ብሔረተኛነት ዲሞራሲያዊ እየሆነ ነው እየተባለም ነው። እሱም በራሱ አጠያያቂ ነው። ልክ “ቅዱስ” ብሔረተኛነት ብርቅ እንደሆነ “ዲሞክራሲያዊ” ብሔረተኛነት እምብዛም አያጋጥምም። አልፎ ተርፎ ብሔረተኛነት ራሱ ዲሞራሲያዊ ሊሆን ይችላልን? መባሉንም ያስከትላል። “አማራነት ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ዜግነታችን ነው” የሚለው መፈክር ለሁሉም 80 በላይ ለሆኑት የሃገሪቷ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል የሚመለከት መፈክር መሆን አለበት ወይም ይገባዋል። አማራ ብቻ አይደለም በነገድ ማንነቱ ወገንተኛ የሚሆነው። መቼም ሁሉም በዜግነቱ “ኢትዮጵያዊ” ነኝ ባይ ነው። ምክንያቱ ዜግነት ግለሰብ ዜጋው ከሃገረ መንግሥቱ (State) ጋር ያለው ቁርኝት ነው እስከተባለ ድረስ።

የአማራነትና ኢትዮጵያዊነት ቁርኝት የአማራ “ብሔረተኛነትን” ወሰብሰብ አድርጎታል።  አሁንም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለው ቁርኝት የማይቆራረጠው ኢትዮጵያዊነት ዋልታና ማገር፣ ማግና ድር፣ ደምና ስጋ ስለሆነ ነው። እንደማይነጣጠሉ ለመግለጽ። “…. አማራና ኢትዮጵያዊነትን እለያያለሁ ማለት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ዓይነት አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስን እንለይ እንደ ማለት ነው“ ይላሉ አቶ ተክሌ የሻው። ዶር ተክሉ አባተ ደግሞ ሁለቱን መለያየት መመኮሩ ” ጸጉር ለመሰንጠቅ” መሞከር ያህል ነው ብለው ያምናሉ። የአማራ ማንነት ትግል ተግዳሮት የደቀነው ይህ ኢትዮጵያዊነቱና ማንነቱን መለያየት አለመቻሉ ነው። ጉዳዩ እንደ የኢትጵያዊነት ባለ አደራና የበላይ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ይበልጥ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ መመጻደቅ ተደርጎ በሌሎች ኢትዮጵያውያን መታየቱ ነው። ይህ ደግሞ በሌላው ኢትዮጵያዊ አማሮችን ኢትዮጵያዊነትን የራሳችሁ ብቻ አደረጋችሁት ተብሎ የሚሰማው ቅሬታ አለመተማመኑና በጥርጣሬ ዓይን የመተያየቱ ምንጭ ነው። ይህ ደግሞ አማራ በነገዱ ከተደራጀ በኋላም የሚከተለው መከራ ነው። እርግማን መባሉ ያስኬድ ይሆን? እነዚህ አባባሎች አማራ ኢትዮጵያዊነትን ከሌላው ጋር “ለመጋራት” ፈቃዳኝነት እንደሌለው ያስመስልበታል። ምንም እንኳን አማራ የሚደራጀው በራሱ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመመከት ነው መባሉ ትክክል ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዛሬ የሚቀበለው ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ ከሌሎች ብሔረሰብ ልሂቃን ጋር የነበረው አለመጣጣም አሁንም እንዳለ ነው። አማራ በኢትዮጵያዊነት ሽፋን ለተቀዳጀው የበላይነት ማስከበርያና ማዝለቂያ ነው እያሉ በውስጠ ታዋቂነት ጣታቸውን የሚቀስሩት ወደ አማራው ብሔረሰብ ነበር። አሁንም ይህንን አካሄድ ይህንኑ አለመተማመን ያጠናክር እንደሆነ ነው እንጂ አያለዝበውም። ዞሮ ዞሮ ከመጀመሪያው ክስና ጣት መቀሳሰር ጋር ይገናኝና ወደ መነሻ ነጥቡ ጋር ይመለሳል። የዚህ ሁሉ ጥቃት ዒላማ ያስደረገኝ ያው ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለኝ ቁርኝት ነው ከተባለው ጋር ግጥም ይላል። ለሌላው ይህ ኢትዮጵያዊነትን የእኔ የብቻዬ ንብረት ነው፣ የበላይ አደራ ጠባቂውም እኔው ነኝ ዓይነት መመጻደቅ ተደርጎ ይታያል።

ትልቁ የአማራ ብሔረተኛነት ተግዳሮት ከኢትዮጵያዊ ብሔረተኛነትና ማንነት ጋር የነበረውና ያለው እትብትና ትስስር መበጠስ ወይም አለመበጠስ ሁለት ልብነት ነው ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። አጠቃላይ ጥንካሬው እንደ የተጠበቀ ሆኖ ለውድቀት ሊዳርግ የሚችል ተጋላጭ ስስ ብልትና የአቺለስ ተረከዝ (Achilles’ heel) መሆኑ ነው። ጥንካሬውም እሱ ነው፣ ስስ ብልቱም እሱ ነው ማለት የሚቻል የመስለኛል። የሁለቱ ዲያሌክቲካዊ (ተቃርኗዊ ዝምድና?)  ትስስር የዳይሌማው ወይም የመንታ ልብነት ምንጭ ነው። አማራው ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለው ያልተበጠሰ ቁርኝትና ትስስር ጋር መቆራረጡ ወይም መፋታቱ (disengage) አይታሰብም፡፡ ዛሬ ሁሉን እያተረማመሰ የሚገኘው የማንነት ፖለቲካ የአማራ ተወላጆችን ይበልጡኑ ድብልቅልቃቸውን ያወጣል፣ የማንነታቸውን ትግልም ይበልጡኑ ያወሳስበዋል። አወሳስቦት፣ እያናቆረን ነው። የአማራ ኤሊቶችን ብቻ ሳይሆን ውሎ-ገብ ዜጎችንም ጭምር በተመሰቃቀለው የማንነት ፖለቲካ ይበልጥ እያተተረማመሱ ናቸው።

ከ1983 ወዲህ ከላይ እንደተመለከትነው አማራ ልክ እንደ ሌላው በነገዱ እንዲደራጅ የተፈለገበት ምክንያት ነበር። ከኢሕአፓ የተገነጠለው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዲን) ወደ ብሔረ አማራ ዲሞራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እንዲለወጠ የተደረገበት ምክንያት አንድ ነው። ማንንም እሰከ ምርጫ 97 ድረስ በማንነት ወገንተኛነት ካልሆነ በስተቀር በሃገራዊ ማንነቱ ወይም በሕብረ ብሔራዊነትና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ እንዳይደራጅ የተፈለገበትም ምክንያትም ያው ነው። በግለሰብ ካርድ መታወቂያ ላይም የጎሳ (የዘር?) ማንነት እንዲመዘገብ የተፈለገበት የፖሊሲ መመሪያም ያው ነው። ሁሉም በዘሩ ወይም በነገዱ እንጂ አደረጃጀቱ የሕብረብሔር ቅርጽም ሆነ ይዘት እንዲኖረው አልተፈለገም። ባጭሩ መመሪያው በሥልጣን ያለው ፖለቲካዊ ኃይል ንድፍና እቅድ ሆኖ በመተግበር ላይ ስለሆነም ነው።

ይህ ሁሉ ድብልቅልቅ የወያኔ ተንኮልና ሴራ ውጤት ብቻ ነው ማለት የሚያስኬድ አይመስለኝም። በአማራ ማንነት ትግልና ብሔረተኛነት ተግዳሮት የደቀነው ይህ ኢትዮጵያዊነቱና ማንነቱን የመለየቱ ችግር ብቻም አይደለም። ይህ በተራው ካንድነት ኃይሎች ጋርም በተቃራኒነት እንዲቆም አድርጎታል። ይህ ዛሬ በግልጽ እየወጣ ነው። ከኢትዮጵያዊነት ጋር ባይቆራረጥም ቅሉ ካንድነት ሃይሉ ጋር እየተራራቀ መጥቷል። ይህን በተራው በርካታ ያለመተማመኑን ንብብሮሽን እያገዘፈ ይገኛል። ይህ ሁሉ ተደምሮ እያራራቃቸው እንደሆነ ነው እንጂ የተቀራረቡና የትግል አንድነታቸው እየጸና አይደለም። ድሮ ያንድነት ኃይል የአማራ ማንነት ማሽሞንሞኛ አባባል ነው ወይ ብዬ እኔ ራሴ የጠየቅኩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ዛሬ በመሬት ላይ የምንመለከተውን እውነታ እንደ ገና እንድፈትሽ እያስገደደኝ ነው።  “አማራውን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ልሂቃን እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ማጋጨት የታክቲክም የስትራቴጂም ጥቅም የለውም” (ፈቃደ ሸዋቀና) ቢባልም አማራ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእነዚህ ጋር እየተጋጨ ነው።

በምርጫውና ፊያስኮው ሳቢያና በማግሥቱ በቅንጅት ድርጅቶችና መሪዎቻቸው መካከል የተከሰቱ አይነቱ አለመግባባቶቹና የክስ ጣት መቀሳሰሩ እንደ ገና አገርሽቶበታል። ፍርስራሻቸው የወጣ የቀድሞ ትብብሮችና ሕብረት ተሞክሮዎች ትምህርት የተቀሰመባቸው አይመስልም።

ለጥርጣሬው ምክንያቶችን መፈተሽ ተገቢ ነው። ሞረሽ ወገኔ የአማራ አርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅትን በማሰመልከት “የድርጅቱን እንቅስቃሴ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ በሚገባ ተከታትለናል። በቅርቡ በአንድ የአማራ ድርጅት የወጣውና በክትትላችን ያገኘነው ውጤት አርበኞች ግንቦት ሰባት በራሱ ማንነት ላይ ያልቆመ፣ ማንነቱን ከሌሎች ጋር በሚፈጥረው ጥምረት፣ ውሕደት፣ ቅንጅት ወዘተ ለማሳደግ የሚጥር፣ ተፈጠረ የሚባለው ጥምረት የት እንደ ደረሰ ሳይታወቅና የመጀመሪያው ጥምረት ፊርማ ሳይደርቅ፣ ሌሎች ጥምረቶች የሚፈሉበት መሆኑን ታዝበናል። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ጥምረት የሚመሠረተው አማራውን በዐውራ ጠላትነት ከፈረጁ ብሔርተኛ ድርጅቶች ጋር መሆኑ እርሱም በተዘዋዋሪ መንገድ የአማራው ጠላት መሆኑን እያሳየ መጥቷል” ይላል። ከዚህ አንጻር ጉዳዩ እየከረረ መጥቶ ወደ መፈራረጁ ደረጃ ተደርሷል ማለት ነው። ቀላል ክስ አይደለም።

ባንጻሩ በአርበኞች ግንቦት 7 አመራር እናንተ የአንድነት ኃይሎች የእኛዎች ናቸሁ (የት ትሄዱብናላችሁ) ብለን በቅድሚያ ካንድነት ጎራ ያፈነገጡትን ወደ አንድነት በረት እንመልስ ብለን ነው ከእነሱ መደራደሩን ያስቀደምነው መባሉ እንደ ሽንገላ ቢወሰድ አይገርምም። በተግባር የታየውም ይህው ነው። የት ትሄዱብናላችሁ የተባሉት የአንድነት ኃይሎች በእጅ የሉም ዛሬ። አሁን እነሱን ፍለጋ ሊኬድ ነው። “የእንትና ብሄር አልተወከለም አትበሉን ይህ ፓርላማ አይደለም” መባሉም እንዲሁ አለመተማመኑን ያጸና እንደሆነ እንጂ አያቀራርብም። የአማራ ብሔረተኞች ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ያላቸው ቅራኔ ይህ ብቻ አይደለም። የወልቃይት-ጠገዴ ማንነት እውቂያ ጉዳይ፣ በሰሜን (ጎንደርና ጎጃም) የተቀጣጠለው የመሣሪያ ተጋድሎ ባለቤትነትና በስሙ አለመጥራት በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው። ጣት መቀሳሰሩን አቁመን፣ የኋላ ታሪኮችም በቅጡ ፈትሸን ለዚህ ችግር መፍትሔ በአስቸኳይ መፈለግ አለበት።

3 ማጠቃለያ

ከላይ የተመለለከትናቸው ተግዳሮቶቹ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው። በአማራ ብሔረተኛነት ላይ ሌሎች ተጨማሪ ግን ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች ተጋርጦበታል። የወያኔ የቆየ ሤራ፣ ቂምና እቅድ ማለቴ ብቻም አይደለም። የአማራ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ በክልሉ በውስጡ ባቀፋቸው እንደ አማራ የሚቆጥራቸው አገው፣ ቅማናት፣ ወይጦ፣ አርጎባ ፣ሺንሻ ያላቸው ተሳትፎ፣ በድርጅቶች መሃል ያለው ሽኩቻ፣ የአመራሮቹ ልምድ ማነስ፣ ወዘተ እንደ ተግዳሮት በግምት አልተወሰዱም። በጸረ አማራነት ከመደቧቸው ድርጅቶች ጋር ያላቸው ትስስር ይወዛገባሉ። ባንድነት ኃይሉ መሃል ያለ አለ መተማመን፣ የብሔረሰቦቹ ኤሊቶች ብቻ ሳይሆን በአንድነት ኃይሎች መካከል መካሰስ፣ መሸነጋገል ዛሬም እንዳለ ነው።

የሁሉት ታላላቅ ነገዶች (አማራ ብሔረተኞች ኦሮምኛ የተሰኘውን ጎሳ ቃል ላለመጠቀም የሚወስዱትን ቃል እንጠቅምና) ማቀራረብ የሚችል መግባባት ፈጣሪ ድርጀት ወይም መሪ ማስፈለጉ የማይታበል ሃቅ ነው። ምክንያቱም ዶር መረራ ጉዲና ብዙ ጊዜ የሚያነሷቸው የሦስቱ ብሔረሰቦች ኤሊቶች ወደ መሃል የማገናኘቱ ከባድ ኃላፊነትና አደራ እስካሁን ሊወጣ የቻለ ግለሰብም ሆነ ፖለቲካዊ ኃይል አይታይም። ደጉ ዜና ወያኔና አንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያዊነት የማምራት አዠማሚያ እያሳዩ ነው። ባንጻሩ የአማራ ወጣቶች በብዛት ወደ ነገድ አደረጃጀት እየነጎዱ ነው። ምናልባት በመሃል በመንገድ ከተገናኙ መልካም ነው። የተራራቁ ጫፎችን መሃል ላይ እንዲገናኙ ማድረግ ካልተቻለ ግን ተደጋግሞ የሚወሳው የወያኔ ኢሕዴአግ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሙ አይቀሬ ነው የሃገሪቷ እጣ ፋንታ ጉዳይ ይበልጥ ሊያሳስብ ነው ማለት ነው።

ወያኔ ኢሕዴአግ አደርጋለሁ የሚለው “ጥልቅ ተሃድሶ” ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ ከተቃዋሚዎች ጋር መነጋገር ፣ የሃይማኖት ድርጅቶች የእርቅ ሰላም የማውረዱ ሚና ወዘተ ሁሉ በመሃል የማገናኘቱ በጎ እርምጃዎች ተደርገው ሊታዩ ይገባል።
የ “ቆም ብለን እናስብ!” እና “ሰከን በል” ጥሪዎች ከሁሉም አቅጣጫ ቢዥጎደጎዱም በመጯጯህ ጫጫታ እየተዋጡ ናቸው። ቆም ብሎ ማሰብ አልተቻለም። ሁላችን ቆም ብለን እናስብ! በመጨረሻ ሁሉ ሰክኖ የትግል ስልቶቹና ሥሌቶቹን መርምሮ እኩልነትን ተቀብሎ፣ በመሃል ተገናኝተው፣ መሸነጋገል፣ጥርጣሬና ፍራቻ አስወግደው ባንዲት አገር በኢትዮጵያዊነት አስተሳሳሪ አቃፊ-ደጋፊ ሃገራዊ ሽርክና ለመጀመር ያለንን ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያው ቆም ብሎ መነጋገርና መግባባት ነው፡፡

በበርካታ እርስ በርስ ጦርነቶች በበጣጠቋቸው ሃገራት እንደሚንመለከተው ማንም በማንም ላይ በጦር ሜዳ በላይነትም ሆነ የማያዳግም ድል ቢቀናው እንኳን የማታ የማታ ማሳረጊያው በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ላይ የተደረሰ ተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት ነው። በዚያ ላይ አንዱ ወገን በተፋላሚው ላይ የተወሰነ ነጥቦች በደም ካስመዘገበ በኋላ መሆኑንም አሁንም አልሳትኩም። እርግጥ ይህ ሁኔታ በኃይል ሚዛን መለወጡ ነው አንዱ ተፋላሚ በፊት አሻፈረኝ የሚለውን እውነታ በመቀበል የአቋም መንፏቀቅ አስፈላጊነትና አስገዳጅነት የሚመነጨውም ከእዚህ ነው። ይህንንም አልሳትኩም።

አማራን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን “አማራው የራሱን ሕልውና አስከብሮ ከዚያም የኢትዮጵያዊነቱን ግዴታ ከሌሎች ጎሣዎች ጋር በእኩልነት እንዲወጣ ማድረግ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ተልዕኮ ነው” ነበር ፕሮፌሰር አሥራት በባህርዳሩ መአሕድ መስራች ጉባኤ ላይ ያሉት። ደግማዊ መአሕድም ሆነ ሌሎች የአማራ ድርጅቶች ከዚህ የተለየ ተልዕኮ ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም። የሰሞኑ ተከታታይ የአማራ አቀፍና ሃገር አቀፍ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ምክክር ጉባኤ ዓይነቶቹ ምናልባት ለዚህ መተማመን እርሾ መፍጠር ቀዳሚ ሥራ ሊይዝ ይገባል። “ካልደፈረሰ፣ አይጠራም” በሚለው ብሂል ድፍርስርሱን ባወጣ ማግሥት ለመልካም እድል አጋጣሚ ሊፈጠር ነው ከተባለም ሁሉ ሰከን ብሎ በምር መነጋገር ይጀመር! የሰሞኖቹ የዋሽንግተን ጉባኤዎችና ስብስባዎች መልካም አጋጣሚዎች ናቸው። ሌሎች መወያያ መድረኮችም ውይይቶችን ያስተናግዱ። ሰሞኑን ኢሳት በእንወያይ ፕሮግራሙ በአማራ ወጣቶች መካከል እንዳስተናገደው ማለቴ ነው ፡፡የሺ ማይል ጉዞ ባንድ እርምጃ ነው የሚጀመረው የሚሉት ቻይናውያን ናቸውን? እኛም ረዥሙን መንገድ በቀላሉ እርምጃዎች እንያያዘው!!

በዮናታን ተስፋዬ ላይ መከላከያ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ

ቀደም ባሉ ቀናት በዋለው ችሎት በጊዜ እጥረት ምክንያት መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ባለመቻሉ ታህሳስ 26 ቀን 209 ዓ. ም. ተቀጥሮ ነበር። ዮናታን ተስፋዬ እንዲከላከሉለት ከዘረዘራቸው የሰው ምስክሮች ከአንዱ (ዶ/ር መረራ ጉዲና) በስተቀር የተቀሩት መከላከያ ምስክሮች መቅረባቸውን የዮናታን ጠበቃ የሆኑት አቶ ሽብሩ በለጠ ለችሎት አሳውቀዋል፡፡ መከላከያ ምስክሮች መሰማት ከመጀመራቸው በፊት አቶ ዮናታን የራሱን የምስክርነት ቃል አቅርቧል፡፡

yonatan-tesfaye

ዮናታን ተስፋዬ

“በፌስቡክ አካውንቴ እፅፍ የነበረው ሃሳቤን ለመካፈል ፈቃደኛ ለሆኑት ጓደኞቼ ብቻ ነው፡፡ ህዝብ ቀስቅሷል የሚባለው ነገር የማይመስል ነገር ነው፡፡ እድሉን አግኘቼ እንኳን ለህዝብ ደርሶ ቢሆን የሽብርን ድርጊት የሚያበረታታ አይደለም የፃፍኩት ነገር፡፡ በሃገሪቷ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልፁ እና የሚዳስሱ ናቸው፡፡ እንዚህን ሃሳቦች ከጓደኞቼ ጋር መወያየቴ ሃሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴን መጠቀሜ ነው፡፡ “ህግ መጨቆኛ መሳሪያ ሲሆን፡ አመፅ የህሊና ህግ ይሆናል፡፡” የሚለው ሃሳብ የተፈጥሮ እና አለም ዓቀፋዊ ህግ ነው፡፡ ማንም ሊቀይረው አይችልም፡፡ የፍልስፍና መርህም ነው፡፡ ምናልባትም ያን የተናገርኩ ጊዜ የሚሰማ አካል ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁላ ችግር ባልደረሰም ነበር፡፡ በህዳር 2008 ዓ.ም. አካባቢ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኘው ጭልሞ ጫካ ለባለሃብት ከተሸጠ በኋላ ህብረተሰቡ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ምናልባትም ጥያቄያቸው በትክክለኛው አግባብ ቢያዝ ተቃውሞው አይስፋፋም ነበር፡፡ እኔም የሚደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ መንግስት የህብረተሰቡን ደህንነት መጠበቅ ሲኖርበት በተቃራኒው የመንግስት አካል ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በተለያየ መንገድ ህዝቡ ራሱን እንዲከላከል የተለያየ ሃሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ የአንድ ሰው ህይወት ዋጋ አለው፡፡ እኔ ከመታሰሬ ቀደም ብሎ 62 የዩቨርስቲ ተማሪዎች ተገድለው ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ነገ ይህችን ዓለም ሊቀይሩ ይችሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት ችግሩ የተከሰተው በመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን አምነው ይቅርታም የጠየቁበት ጉዳይ ነው። አንድ ሚሊዮን ብር ከሚያወጣ ንብረት ይልቅ የአንድ ሰው ህይወት ዋጋ አለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሹፌር 20 ተሳፋሪ ይዞ ፍሬን እምቢ ቢለው መኪናውን አጠገቡ የሚገኝ ግንድ ወይም ግንብ አጋጭቶ ቢያቆመው፡ ሹፌሩ መኪናው ላይ በደረሰው አደጋ ሊቀጣ አይገባውም፡፡ በአደባባይ ሰዎች ሲሞቱና ሲገደሉ እነርሱን ዲፌንድ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ይህንንም ሃሳቤን የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ የተለያየ ሃሳብ አቅርቤያለሁ፡፡ ይሄ ጥፋት የሚባል ከሆነ እቀበለዋለሁ፤ ለኔ ክብሬ ነው፡፡ ፍርዱን ከታሪክ እና ከእግዚአብሄር አገኘዋለሁ፡፡” ይህን የምስክርነት ቃሉን ዮናታን ካቀረበ በኋላ የሙያ ምስክርነታቸውን የሚሰጡትን ሶስት ምስክሮች ጠበቃው ዘርዝረዋል፡፡

የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ያእቆብ ኃይለማርያም እና የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የሙያ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ሲሆን ዮናታን የፃፈው ፅሁፍ ሃሳብን ከመግለፅ ነፃነት አንፃር እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ህጎች አንፃር ገደቡን ያለፈ አለመሆኑን እንደሚያስረዱ፤ እንዲሁም ሶስተኛው የሙያ ምስክር ጦማሪ እና የመብት አራማጅ በፍቃዱ ሃይሉ ደግሞ በፌስቡክ በግለሰብ አካውንት የሚለጠፉ ፖስቶች ከመደበኛ ሚዲያ እና ከዜና ድህረገፆች የሚለይበትን እንደሚያስረዳ ጠበቃው አቶ ሽብሩ በጭብጥነት አስመዝግበዋል፡፡ አቃቤ ህግ በሶስቱም የሙያ ምስክሮች ላይ ተቃውሞ እንዳለው ከተናገረ በኋላ ህግን መተርጎም ያለበት ፍርድ ቤት እንደሆነ ከዚህም ካለፈ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማየት እንዳለበት ጠቅሶ ምስክሮች የፍርድ ቤቱን ሚና መውሰድ ስለሌለባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምስክሮች [ዶ/ር ያእቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው] መሰማት የለባቸውም በማለት እንዳይሰሙ ሲል ጠይቋል፡፡ በፍቃዱ የሚመሰክርበትን ጭብጥም በተመለከተ ከክሱ ጋር የማይገናኝ ስለሆነ መመስከር የለበትም ብሎ ለችሎቱ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ጠበቃ አቶ ሽብሩም “አቃቤ ህግ ዮናታንን ወንጀል ሰርቷል ብሎ ምስክር ሲያሰማ የዳኞችን ሚና ወሰደ አልተባለም፡፡ የደንበኛዬ የመከላከል መብት በሰበብ አስባብ ሊጣስ አይገባም፡፡” ብለው ከተናገሩ በኋላ ዶ/ር ያዕቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው ከልምዳቸው እና ከትምህርት ዝግጅታቸው አንፃር የዮናታን ፅሁፍ ከገደብ አለማለፉን በተረዱት መጠን እንደሚያስረዱ፤ በፍቃዱ የሚመሰክረውም ዮናታን የተከሰሰበት የሽብርተኝነት ህግ አንቀፅ 6 በህትመት ደረጃ ስለሚፃፉ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ ፅሁፎች ስለሚል ልዩነቱን እንዲያስረዳ ነው በማለት ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አግባብነት አስረድተዋል፡፡ ዳኞችም የግራ ቀኙን ሃሳብ ከሰሙ በኋላ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ቃሉ ተመዝኖ መጨረሻ ላይ የሚታወቅ በመሆኑ ምስክሮች እንዲሰሙ ወስነዋል፡፡

በመጀመሪያ ለመመስከር የቀረቡት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ የህግ ምሩቅ መሆናቸውን፣ የህግ አማካሪ እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር መሆናቸውን ገልጸው በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል አጣሪ ቡድን አባል ሆነው እንደሰሩ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህግ አማካሪ ሆነው እንደሰሩ ገልፀዋል፡፡ ስለሽብር ወንጀል ምንነት እና ከዮናታን ፅሁፍ ጋር አያይዘው እንዲመልሱ ተጠይቀው፤ “የሽብር ወንጀል አስከፊ ነው፤ ከጦር ወንጀል እና ከዘር ማጥፋት ጋር የሚሰለፍ ነው፡፡ የሽብር ወንጀል ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው፡፡ አንድን ሽብር ፈጣሪ የትኛውም ሃገር ቢሄድ የሚጠየቅ ነው የሚሆነው፡፡ በኬኒያ እና ሌሎች የአለማችን ክፍሎች በርካታ ህዝቦች ያለቁበትን ሁኔታዎች በአለም አቀፍ ሁኔታም የሽብር ድርጊት የሚባሉ ናቸው፡፡” ካሉ በኋላ የዮናታንን በፌስቡ ከጓደኞቹ ጋር ለመወያየት የፃፋቸው ሃሳቦች ከጠቀሷቸው አለም አቀፍ የሽብር ድርጊቶች ጋር አንድ ማድረግ የሽብርተኝነት ድርጊትን ማቃለል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የፀረ ሽብር ህጉ ህገመንግስቱን እና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀበለቻቸውን ህጎች እንደሚጥስም ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎ ለመመስከር የቀረቡት ዶ/ር ዳኛቸው ናቸው፡፡ የህግ ፍልስፍና ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን እና መምህር መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ እአአ ከ 1948 ዓ. ም. ጀምሮ የተካሄዱ አራት አለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጥቀስ እነዚህ ድንጋጌዎች ማእከል ያደረጉት የመናገር መብትን መሆኑን እንዲሁም ንግግር በይዘቱ እንደማይፈተሽ እና ማንም ዜጋ ሃሳብ የማዋቀር መብት እንዳለው ድንጋጌዎቹ በግልፅ ያሰፈሩት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል -ዶ/ር ዳኛቸው፡፡ እነዚህን ህጎች ኢትዮጵያ ከመቀበል ባለፈ ከመጀመሪያው ጀምሮ በማርቀቁ ሂደት ተሳታፊም እንደነበረች ገልፀዋል። ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መኖር ለመንግስት ቅቡልነትን እንደሚያመጣ ዲሞክራሲም የሚለካው በዚህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ፅሁፉን አይቼዋለሁ፡፡ እምነቱን አሳይቷል፡፡ የራስክን አይዲዎሎጂ ፃፍክ ነው የሚለው ክሱ፡፡ እኔ እዚህ ሃገር ከመጣሁ ስምንት አመት ሆኖኛል፡፡ ስምንት አመት ሙሉ የራሴን አይዲዮሎጂ መንግስትን እየተቃወምኩ ስፅፍ ነበር፡፡ አልታሰርኩም፡፡ እሱም መታሰር አልነበረበትም፡፡ ልጁ [ዮናታን] የፃፈው ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ አስተማሪው ብሆን ፅሁፎቹን አይቼ ሲ እና ዲ ልሰጠው እችላለው፡፡ ያ ማለት ግን ወንጀል ሰርቷል ማለት አይደለም፡፡ መንግስት ጥሩ ነው የማለት መብት እንዳለ ሁሉ መንግስት ጥሩ አይደለም የማለት መብትም መኖር አለበት፡፡ ንግግር እና ፅሁፍን በመፍቀድ ከሚመጣው ችግር ንግግር እና ፅሁፍን በመገደብ የሚመጣው ችግር ይበልጣል፡፡” ካሉ በኋላ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤት የመመስከር ፍቃድ አሎት ወይ ብሎ ሲጠይቃቸው፡ የትምህርት ዝግጅታቸውን፣ የስራ ልምዳቸውን እና ከዚህ ቀደምም በፍርድ ቤት መስክረው እንደሚያውቁ ገልፀው፤ ፍርድ ቤት ለመመስከር ፍቃድ የት እንደሚሰጥ አላውቅም፤ የሚሰጥ አካል አለ? የት ነው የማገኘው? በማለት በችሎት የነበረውን ሁሉ ፈገግ አሰኝተዋል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የሙያ ምስክርነቱን የሰጠው ጦማሪ እና አክቲቪስት በፍቃዱ ኃይሉ ነው፡፡ አቶ በፍቃዱ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳለው፤ በመደበኛ (ህትመት እና ራዲዮ)፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና የዜና ድህረገፆች ያለውን ልምድ ተናግሯል፡፡ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም እያንዳንዱ ሰው አካውንት ሊኖረው እንደሚገባ፤ የሚፅፉትንም ለማየት ጓደኞች ሊኖሩ እንደሚገቡ፤ መደበኛ ሚዲያ በዋነኝነት ለሽያጭ የሚቀርብ እና ከማህበራዊ ሚዲያ የበለጠ ተደራሾች እንደሚኖሩት፤ የዜና ድረገፅን ለመጠቀም ኢንርኔት አጠቃቀም ከማወቅ በዘለለ የግል አካውንት መፍጠር እንደማያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ስለ ግለሰብ ፌስቡክ አካውንት፣ የፌስቡክ ፔጅ እና ፋን ፔጅ ልዩነቶች አስረድቷል፡፡ ዮናታን ስለፃፈው ፅሁፍ ተጠይቆ፤ ፅሁፎቹን እንደሚያውቃቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መፃፍ እንደሚወድ ተናግሯል፡፡ በወቅቱ በነበረው ተቃውሞ በመንግስት የተገደሉ ወጣቶችን በመቃወም ሲፅፍ እንደነበር፤ እንዲያውም የወጣቶችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል እና ለማሸበር ሳይሆን በተቃራኒው የወጣቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲታገል እንደነበረ ተናግሯል አቶ በፍቃዱ፡፡

መንግስት ወጣቶችን ይገድላል ወይ ተብሎ ለአቶ በፍቃዱ ከዳኞች ለቀረበለት ጥያቄ፤ የመንግስት ፀጥታ አካላት ወጣቶችን መግደላቸው ዩንቨርሳል ትሩዝ እንደሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፓርት እንኳን 173 ሰዎች በፀጥታ አካላት መገደላቸው የተገለፀ መሆኑን ገልፇል። ይህን የሙያ ምስክርነት ለመስጠት ፈቃድ እንዳለው አቃቤ ህግ ጠይቆት፤ በአዲስ አበባ መስተዳደር በሚተላለፍ የራዲዮ ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ማኔጀር ሆኖ እንሰራ፤ የውይይት የመፅሄት ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንደሰራ፤ የሚፅፋቸው ፅሁፎች በአዘጋጅነት ይሰራበት የነበረውን የውይይት ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ላይ ይታተሙ እንደነበረ፣ ዞን ዘጠኝ የተባለ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጦምር ቡድን አባል እንደሆነ እና በቅርቡም አዲስ ስታንዳርድ የሚባል የመፅሄት ድረገፅ ላይ ፅሁፍ እንደታተመለት በመግለፅ ልምዱን በአጭሩ አብራርቷል፡፡ ይህም ልምዱ በጉዳዩ ላይ ለመመስከር ብቁ እንደሚያደርገው ተናግሮ፤ “ምስክርነት ለመስጠት ፈቃድ የሚሰጥ አካል የለም” ብሏል።

በመቀጠል የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ እና አቶ በቀለ ገርባ መሆናቸውን የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሽብሩ ተናግረው፤ በህዳር 2008 ዓ. ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች የጀመረበትን ምክንያት እና የነበረውን ሁኔታ እንደሚያስረዱለት በጭብጥነት አሲዟል።

አቃቤህግ አሁንም በምስክሮቹ ላይ ተቃውሞ እንዳለው ለፍርድ ቤት አሳውቋል። ምስክሮቹ በህግ ጉዳይ ላይ መመስከር እንደማይችሉ እና ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመናገር ምስክሮቹ እንዳይመሰክሩ ጠይቋል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የምስክር መስማት ሂደቱ ሲጀምር ተመሳሳይ ጥያቄ አቃቤ ህግ አንስቶ ውሳኔ ተሰጥቶት ያለፈ ጉዳይ መሆኑን በተጨማሪም ምስክሮቹ የፓለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆናቸው መጠን የሞያውቁትን የሰሙትን እና ያዩትን የሚመሰክሩ መሆናቸውን ገልፀው ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አግባብነት አስረድቷል። ዳኞች የግራቀኙን ክርክር አድምጠው የምስክሮቹን የሚመሰክሩበት ጭብጥ ይዘት በኋላ ላይ የሚመዘን በመሆኑ፤ ተከሳሽ እራሱን የመከላከል መብቱን ከመጠበቅ አንፃር ምስክሮቹ ቢሰሙ እንደሚሻል ጠቁመው የምስክሮቹ የመሰማት ሂደት እንዲቀጥል አዘዋል።

በቅድሚያ ለመመስከር የቀረቡት አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው። አቶ ሙላቱ በ2008 ዓ. ም. ስለተነሳው ኦሮሚያ ስለተነሳው ተቃውሞ መንስኤ ስለሆነው ነገር ሲናገሩ፤ ከ2007 ዓ. ም. ምርጫ በኋላ ተቃውሞ እየበረከተ መምጣቱ፣ በኦፌኮ በኩል ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ሲደረግ እንደነበረ፣ ህዳር ወር ላይ 2008 ዓ. ም. በጊንጪ ከተማ የከተማው አስተዳደር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረውን ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ወሰዱ መባሉን ተከትሎ ተማሪዎች ተቃውሞ እንደጀመሩ፤ ተማሪዎቹም ትምህርት ቤቱን ማስመለስ መቻላቸውን፤ የከተማው ስታዲየምም በተመሳሳይ መልኩ ተወስዶ ሲከፋፈሉት ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበረ፤ የጭልሞ ጫካ ለባለሃብቶች መሸጥ ህዝብ ላይ ቅሬታ እንደፈጠረ እና ተቃውሞ እንደተነሳ፤ በዚህም ሳቢያ ከጊንጪ አካባቢ ብቻ 70 የኦፌኮ አባላት እንደታሰሩባቸው ገልፀዋል። ይሄ በእንዲህ እንዳለም የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለው ፕላን ይተግበር መባሉ ብዙ ተቃውሞ ማስነሳቱን ገልፀዋል አቶ ሙላቱ።

ዳኞች ቀጣዩ ምስክር [አቶ በቀለ ገርባ] ጭብጡ ተመሳሳይ ስለሆነ አዲስ ነገር የሚመሰክሩት ከሌላ ባይሰሙ የሚል አስተያየት አቅርበው ነበር፤ ሆኖም ጠበቃ ሽብሩ ቀድመው ከመሰከሩት ምስክር [አቶ ሙላቱ ገመቹ] የተለየ ሚመሰክሩት እንዳለ በመናገራቸው ዳኞችም ባልተመሰከረበት የጭብጥ ሃሳብ ላይ ብቻ እንዲመሰክሩ አዘዋል።

በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ማስተር ፕላኑን ተቃውመው እና ጭልሞ ጫካ ለግለሰቦች በመሰጠቱ ምክንያት እንጂ ዮናታን በፃፈው ፅሁፍ እንዳልሆነ አቶ በቀለ ገልፀዋል። በተጨማሪም ፅሁፎቹ ህዝቡ ያነሳው ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመከላከያ የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ቀርበው የነበሩት አባቱ ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሳ፣ ጓደኛው አቶ ኤፍሬም፣ እህቱ ገዳምነሽ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእለቱ ችሎት ለመስማት ጊዜ ስላለቀ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተነግሯቸዋል። በዛሬው ቀን ያልቀረቡት ምስክር ዶ/ር መረራ ጉዲና ያሉበትን ቦታ ጠበቃ ሽብሩ ከገለፁ በኋላ ዳኞች መጥሪያ እንዲደርሳቸው እና ፓሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ቀን እንዲያቀርባቸው ትእዛዝ ሰጥተዋል።

ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 18 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀጠሮ ተይዟል።
ምንጭ፦ EHRP

%d bloggers like this: