በቂሊንጦ ለደረሰው ቃጠሎ ተጠያቂዎች ናችሁ በሚል በሽብር የተከሰሱት እስረኞች ላይ የሚደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ቀጥሏል
*ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ጨለማ ቤት እንዲታሰሩ ተደርገዋል
ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ፎቶ ከሲውድን ሬዲዮ
ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ለጠፋው የሰው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመት ተጠያቂዎች ናችሁ በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ በፍይደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የሽብር ክስ መስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት 38 ተከሳሾች ላይ የሚፈጸምባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀጥሏል፡፡
ተከሳሾች ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ ወቅት በእስር ቤት እየደረሰብን ነው ያሉትን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በተመለከተ አቤቱታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ወደ እስር ቤቱ ሲመለሱ ጨለማ ክፍል፣ በጠባብ ቤት ውስጥ ታጭቀው እንዲታሰሩ መደረጋቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በህክምና ላይ የሚገኙት የ66 ዓመቱ ኢትዮ- ሲውድናዊው የልብ ህክምና ባለሙያ እና የ “አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል” መስራች ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ በእነ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የቀረበባቸው 38 ተከሳሾች፣ የጸረ-ሽብር ህጉን አንቀጽ 3 (1፣ 2፣ 4 እና 6) ስር የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ተላልፈዋል በሚል አቃቤ ህግ በህዳር 13 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ ክስ እንደመሰረተባቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ክስ በተጨማሪም ሌሎች 131 ሰዎች ላይ በተመሳሳይ ክስ መከፈቱ ለመንግስት ቅርበት ባላቸው መገናኛ ብዙሃን ተዘግቦም ነበር፡፡
ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት እጅግ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸው እንደነበር በተደጋጋሚ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንኑ የተፈጸመባቸውን ድርጊት ለችሎት ለማስረዳት መሞከራቸውን ተከትሎ ደግሞ አሁን ላይ በጨለማ ክፍል እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡
በታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ ዳኞቹ ወደ ችሎት ሲገቡ ሁሉም ተከሳሾች ከመቀመጫቸው በመነሳት፣ ‹‹በእሳት ቃጠሎው ወቅት ህይወታቸውን ላጡ በእስር ላይ የነበሩ ወንድሞቻችን የህሊና ጸሎት እናደርጋለን›› በማለት ጸሎት አድርገው መቀመጣቸውና በወቅቱ ለደረሰው ቃጠሎም ተጠያቂው ያሰራቸው አካል መሆኑን መናገራቸው አሁን ላይ በጨለማ ክፍል ለመታጎር እንደዳረጋቸው ቤተሰቦቻቸው እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የተከሳሽ ቤተሰቦች በተከሳሾች ላይ እየደረሰ ያለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲቆም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ቢያነጋግሩም፣ ‹‹ጉዳያችሁን ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ውሰዱ›› የሚል መልስ እንዳገኙ ታውቋል፡፡ በዚህም የተከሳሽ ቤተሰቦች ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማምራት ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባየንና ምክትል ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ወ/አገኝን አነጋግረዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ለተከሳሽ ቤተሰቦች ‹‹ጉዳያችሁን በጽሁፍ አቅርቡ›› በማለት አቤቱታቸውን በጽሁፍ የተቀበሉ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ታህሳስ 21 ቀን 2009 ዓ.ም ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥተው ነበር ፡፡ ነገር ግን ከቀናት በኋላም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ ነው የሚል ሰበብ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የተከሳሾችን አቤቱታ ከታች ይመልከቱ
ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት