Daily Archives: February 26th, 2017

ዶክተር መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ክስ ተመሰረተባቸው

(አዲስ ሚዲያ) ከ3 ወር በፊት በአውሮፓ ፓርላማ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተይዘው ለ 3 ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከታሰሩ በኃላ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ።ም በገዥው መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አማካኝነት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሰረተባቸው።

merera-gudina-and-berehanu-nega

ዶክተር  መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የነበሩት እና የኦፌኮ ሊቀመንበር እንዲሁም የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር መረራ ክስ የተመሰረተባቸው፥ በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ ተጋብዘው ሲመለሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር እና ሊቀመንበር ከሆኑት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ታይተዋል በሚል እንደነበር ይታወቃል።

በዶ/ር መረራ ስም የተከፈተው በዚሁ የክስ መዝገብ ፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሁለተኛ ተከሳሽ ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ ሶስተኛ ተከሳሽ በመሆን በልይሉበት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ሶስቱም ተከሳሾች የተከሰሱት በወንጀለኛ መቅጫ ህጉን የተለያዩ አንቀጾች በመተላለፍ ሲሆን አራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሽ የሆኑት የኢትዮጵያ ሳተላይ ቴሌቪዥን ( ኢሳት) እና ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ( ኢኤም ኤን) ሲሆኑ፥ ተቋማቱ የፀረ ሽብር ህጉን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ሌላ ተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተላፍ በሚል ክስ ተመስቶባቸዋል፡፡ የክሱ ጭብጥም ተከሳሾች በዋና አድራጊነት ሽብር ተግባር መፈጸማቸውን እና ለኦሮሚያ እና አማራ ክልል አመጾች ማነሳሳት እና ንብረት መውደም ተጠያቂ መሆናቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ክሱን ለማየት ለየካቲት 24 ቀን 2009 ዓ ም ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በተለይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ በፊት በሌሉበት በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆን፥ በነ አቶ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ደግሞ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን፥ የአሁኑ ከነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር የተመሰረተባቸው ክስ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ ም ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ፥ በአማራ ክልል እና በደቡብ ክልል ኮንሶ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ህዝባዊ አመፅን ተከትሎ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ወታደራዊ ኃይል ሲገደሉ፥ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሲታሰሩ ከ15 ሺህ ያላነሱ በተለያየ ጊዜ ከእስር መልቀቁን መንግሥስት ቢያስታውቅም አሁንም ድረስ ህዝባዊ አመፁን ተከትሎ የታሰሩና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሰ ያሉ ዜጎች መንግሥስት ከእስር ልቅቄያቸዋለሁ ክሚለው ቁጥር እንደሚልቅ ይግመታል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት ለህዝባዊ አምፁ ተጠያቂ ራሱ መንግሥት እና አመራሮች እንደሆኑ ቢይሳውቁም፥ ለግድያ፥ እስርና እንግልት የተዳረጉት ግን ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መግለፃቸው ይታወሳል።

%d bloggers like this: