ፖሊስ በወልቃይት ኮሚቴዎች ላይ አንድ ምስክር ለማቅረብ የበጀት እጥረት ገጥሞኛል አለ
በጌታቸው ሺፈራው
• ‹‹ደንበኞቻችን እየተንገላቱ ነው›› ጠበቆች
በእስር ላይ የሚገኙ የወልቃይት ኮሚቴ አባላት በከፊል
የፌደራል ፖሊስ በሽብር ተከሰው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ላይ በተደጋጋሚ ያልቀረበውን አንድ ምስክር አስሮ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት ታዞ የነበር ቢሆንም ምስክሩ የሚኖረው ትግራይ ክልል በመሆኑ እና በጀት ስላልተለቀቀልኝ ምስክሩን አስሮ የሚያመጣ አባል መላክ አልቻልኩም ሲል ዛሬ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት መልሱን በደብዳቤ ገልፆአል።
አቃቤ ህግም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አጋጠመኝ የሚለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ምስክሩን ይዞ እንዲያቀር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆአል። በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እስር ቤት ከመሆናቸውም ባሻገር ፖሊስ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ምስክሩ ታልፎ ለብይን እንዲቀጠርላቸው ጠይቀዋል። አቃቤ ህግ ለመመስከር የሚመጡትን ምስክሮች አልፈልጋቸውም ብሎ እያሰናበተ፣ የማይገኝና የሌለ ምስክር አመጣለሁ በማለት ደንበኞቻቸውን እያንገላታ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተውታል።
‹‹ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በአከባቢው የክልሉ ፖሊስ አለ። ፖሊስ ምስክሩን ማቅረብ ቢፈልገግ በቀላሉ ማቅረብ ይችላል ነበር።›› ሲሉ ፖሊስ ሆን ብሎ በደንበኞቻቸው ላይ በደል እየፈፀመ እንደሆነ ገልፀዋል። አቃቤ ህግና ፖሊስ ቀጠሮ በማራዘም ደንበኞቻቸው ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ያሉት ጠበቆቹ ‹‹የታሰረው ሰው ነው። ሰውን እስር ቤት አስቀምጠው ምስክሩን ለማቅረብ በጀት የለንም ማለት የተከሳሾችን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው። የቀረበው ምክንያትም አሳማኝ ባለመሆኑ ምስክሩ ይታለፍ›› የሚል አቤቱታ አቅርበዋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የሰጠውን ምክንያት ታሳቢ አድርጌያለሁ በሚል የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጥቶአል። እነ መብራቱ ለአራተኛ ጊዜ ለምስክር ተቀጥረው ምስክሩ ከመቅረቱም በተጨማሪ የዛሬው ቀጠሮ ለመጨረሻ እንዲሆን እና ፖሊስ ምስክሩን አስሮ ማምጣት ካልቻለ ምስክሩ ታልፎ መዝገቡ ተመርምሮ ብይን ለመስጠት ሊቀጠር ይገባ እንደነበር ገልፀዋል። ፖሊስ በበጀት ምክንያት ማቅረብ አልቻልኩም ያለውን ቀሪ አንድ ምስክር ለመስማት ለነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በሽብር የተከሰሰው ወጣት ህክምና ተከልክሎ እንደሞተ ተገለፀ
በጌታቸው ሺፈራው
• ‹‹አውቀው ነው የገደሉት፡፡ እኛንም ይገድሉናል!›› 1ኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፈ
• ‹‹ይህን የሚያደርገው መንግስት ከሆነ ቁርጡን አውቀነው እንሞታለን!›› 4ተኛ ተከሳሽ ይማም መሃመድ
አቶ አየለ በየነ
በእነ መልካሙ ክንፈ የክስ መዝገብ በሽብር ተከሶ ቂሊንጦ እስር ቤት ታስሮ የነበረው ወጣት አየለ በየነ ነገሰ ህክምና እንዳያገኝ ተከልክሎ እንደሞተ ተገለፀ፡፡ ወጣት አየለ በየነ ህክምና ተከልክሎ ለሞት እንደተዳረገ በአባሪነት የተከሱት ዛሬ ሀምሌ 18/2009 ዓ.ም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4 ወንጀል ችሎት ገልፀዋል፡፡
ተከሳሾቹ የፀረ ሽብር አዋጁ ከሚፈቅደው አራት ወር በተጨማሪ 5 ወር በአጠቃላይ 9 ወራትን ማዕከላዊ ታስረው እንደቆዩ የተገለፀ ሲሆን ሟች ለረዥም ጊዜ ታሞ ህክምና ቢጠይቅም ህክምና ሳይገኝ ቀርቷል ተብሏል፡፡ ህመሙ ከጠናበት በኋላም ከ10 ቀን በላይ ምግብ መብላት ባለመቻሉ ለእስር ቤቱ አስተዳደሮች በቀን ከሶስት ጊዜ ባላይ ህክምና እንዲያገኝ ጥያቄ ቢያቀርቡም መልስ ሳያገኙ መቅረታቸውንና በመጨረሻ ከእስር ቤቱ ውጭ እንዲታከም ቢታዘዝለትም በተቋሙ ቶሎ ህክምና ማግኘት ባለመቻሉ ህይወቱ ማለፉን ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡
ቀሪዎቹ ተከሳሾችም ህክምና ሊያገኙ ባለመቻላቸው ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸው አሰምተዋል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፈ ታሞ በየወሩ ህክምና እየወሰደ የነበር ቢሆንም መርማሪዎች የፈለጉትን መረጃ ስላልስጠ ህክምና መከልከሉንና የሟች እጣፈንታ ሊደርስበት እንደሚችል ስጋቱን ለፍርድ ቤት ገልፆአል፡፡ ‹‹አውቀው ነው የገደሉት፡፡ እኛንም ይገድሉናል፡፡›› ያለው 1ኛ ተከሳሽ ንፁህ በመሆናቸውና መረጃ ስላልተገኘባቸው ህጉ ከሚፈቅደው ውጭ ለ9 ወራት ማዕከላዊ መቆየታቸው ይህም ለንፁህነታቸው ማስረጃ እንደሆነ ገልፆአል፡፡ ማች ንፁህ በመሆኑም ክሱ እንዳይቋረጥ፣ ምስክሮችም ተሰምተው የፍርዱን ሂደት ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጾአል፡፡
ሌሎች ተከሳሾም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው የተገለፀ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ ይማም መሃመድ ‹‹ይህን የሚያደርገው መንግስት ከሆነ ቁርጡን አውቀነው እንሞታለን›› ሲል ገልፆአል፡፡ ‹‹አየለን ሞተ ማለት አልችልም፡፡ ተቀጠፈ ነው የምለው፡፡ የሞተው ዘመድ አጥቶ አይደለም፡፡ ጓደኛና ቤተሰብ አጥቶ አይደለም፡፡ የሞተው ህክምና የሚሰጠው አጥቶ ነው›› ሲልም አክሏል፡፡
ባለፉት ቀጠሮዎች ሟችን ፍርድ ቤት ሳያቀርብ የቀረውን ቂሊንጦ እስር ቤት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን የማያቀርብበትን ምክንያት እንዲገልፅ ወይንም ተከሳሹን እንዲያቀርብ በጻፈለት ትዕዛዝ መሰረት ሀምሌ 17/2009 ዓ.ም ተከሳሽ መሞቱን ቢገልጽም በምን ምክንያት እንደሞተ እንዳልገለፀ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ቂሊንጦ ሟች በምን እንደሞተና ለሞቱ ማረጋገጫ ባልላከበት ሁኔታ ግለሰቡ መሞቱን እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል እስር ቤቱ ለሀምሌ 26/2009 ዓ.ም ተከሳሹ ስለመሞቱ የሚያሳይ ማረጋገጫና የሞተበትን ምክንያት እንዲያመጣ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አየለ በየነ በመዝገቡ ስር 2ኛ ተከሳሽ የነበር ሲሆን ከኦነግ መሪ ዳውድ ኢብሳ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ሀገር ውስጥ ያሉ መረጃዎችን ሪፖርት አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡ የሟች ታናሽ ወንድም ቦንሳ በየነም በዚሁ ክስ መዝገብ ስር ክስ ተመስርቶበታል፡፡ በመዝገቡ ስር፡-
1.መልካሙ ክንፉ ተፈሪ
2. አየለ በየነ ነገሰ
3. ቦንሳ በየነ ነገሰ
4. ይማም መሃመድ ኬሮ
5. ለሜሳ ግዛቸው አባተ
6. ኩመራ ጥላሁን ዴሬሳ
7. መያድ አያና አቶምሳ
8. ሙሉና ዳርጌ ሩዳ የተከሰሱ ሲሆን ተመሳሳይ ችግር እየደረሰባቸው እንደሆነ ተገልፆአል፡፡