የዶ/ር መረራ ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት ትእዛዝ ተሰጠ
የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መዝገብ ለዛሬ የተቀጠረው ከዚህ ቀደም በቀረበው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር። በመሆኑም ዛሬ – ሰኔ 30/2009 – ዶ/ር መረራ ጉዲና በተመሰረተባቸው 3ት ክሶች ላይ ያቀረቧቸው መቃወሚያዎች ላይ 19ኛው ወንጀል ችሎት ከፊል ብይን ሰጥቶበታል። ችሎቱ፣ ዶ/ሩ ያቀረቡትን ክሱ እንዳይንጓተት ከሌሎቹ በሌሉበት ከተከሰሱት ሶስት ተከሳሾች ይነጠልልኝ የሚለውን መቃወሚያ ጨምሮ ሌሎቹን መቃወሚያዎች በሙሉ ውድቅ ሲያደርግ አንዱን ግን ለትርጉም ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን ተናግሯል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና
በእነዶ/ር መረራ መዝገብ የተከፈተው ክስ ላይ አቃቤ ህግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ፣ የምስክሮች ሥም ሳይጠቀስ የቀረ ሲሆን፣ ይህ በሥራ ላይ ያለው የሥነ ስርዓት ሕግ ተከሳሾች የሚቀርብባቸውን ማስረጃ እና ምስክር የማወቅ መብት አላቸው ከሚለው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንዲተረጎም ወደፌዴሬሽን ምክር ቤት ተልኳል። የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው “እኛ የጠየቅነው፣ ደንበኛችን ባልተከሰሱበት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የምስክር ጥበቃው አንቀፅ ሊጠቀስባቸው አይገባም ብለን እንጂ ትርጉም ያስፈልጋል ብለን አይደለም” ብለው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ዶ/ር መረራም መልእክት አለኝ በማለት የሚከተለውን ለዳኞች ተናግረዋል፣ “የተመሰረተብኝ ፖለቲካዊ ክስ ነው። መንግስት ይዞ የተነሳው ተቃዋሚዎችን በራሱ የተበላሸ አስተዳደር ጥፋት ጉዳይ መወንጀል ስለሆነ እንጂ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በጠየቀበት ጉዳይ ነው የተከሰስኩት። የተከሰስኩት፣ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ለእኩልነት እና ሁላችንንም እኩል ለሚመለከት ስርዓት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ሀቀኛ የፍትህ ስርዓትና የፌዴራል ስርዓት እንዲኖር በመታገሌ ነው። ዳኞች እስካሁን ካላነበባችሁ፣ የአቤ ጉበኛን አልወለድም እና የበአሉ ግርማን ኦሮማይ አንብቡ። ሊወድቅ እየደረሰ መንግስት የሚሰራውን ሥራ የሚያስረዱ መፅሃፍት ናቸው።”
ዳኞች መዝገቡን ለሐምሌ 25/ 2009 የተቀጠሩ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ቀጠሮ ችሎቱ የምስክሮች ዝርዝር መገለፅ አለበት በሚል ክሱ እንዲሻሻል ወይም የለበትም በሚል የቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል።
EHRP