Monthly Archives: August, 2017

የእነ አቶ በቀለ ገርባ መከላከያ የመስማት ሂደት አቃቤ ህጉ እርቦኛል በማለቱ ምክንያት ተቋረጠ

ጌታቸው ሺፈራው

አቃቤ ህግ ለሚያቀርበው ጥያቄ ተደጋጋሚ መቃወሚያ የቀረበበት ሲሆን መሃል ላይ “አርብ እንደመሆኑ እኛ ለምሳ መውጣት ያለብን 5:30 ላይ ነው። የምሳ ሰዓታችን ይከበር” ብሎ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መጠነኛ ክርክር ተደርጓል።

ሌላ አቃቤ ህግ ስለነበር ፍርድ ቤቱ ሌላኛው አቃቤ ህግ ራበኝ ያለውን ተክቶ የሚሰራበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ቢጠይቅም ራበኝ ያለው አቶ አንተነህ የተሰየመው እሱ ብቻ መሆኑን ገልፆአል።
” እኔም ከጤናዬ አንፃር ሊታሰብልኝ ይገባል።ጨጓራ አለብኝ። መብላት አለብኝ” ብሏል አቶ አንተነህ።

የቀኝ ዳኛው አቃቤ ህጉ ያነሱት ጥያቄ መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጀመር ቢሆን ኖሮ ተገቢ ይሆን እንደነበር ገልፀው መታገስ እንደሚገባ በመጠቆማቸው አቃቤ ህጉ ” ትክክል ነው። ታግሼ መስራት እንዳለብኝ አውቃለሁ። እዚህ ቦታ ላይ ቆሜ የምሰራው ጤና ሲኖረኝ ነው። ህመሜን እያዳመጥኩ ልጠይቅ አልችልም።” ብሎ የምሳ ሰዓቴ ይከበር የሚለውን ጥያቄ ገፍቶበታል።

አቶ በቀለ ገርባ በበኩሉ ” ይህ ከዚህ ትልቅ ተቋም የሚጠበቅ አይደለም። እኛ እየተራብን፣ ብዙ መከራ እያየን ነው ያለነው። ህዝቡም የፍትህ ሂደቱን እንዲያይ ነው። አቃቤ ህግ ከተለየ አካል ትዕዛዝ ሊቀበል ካልሆነ በስተቀር ይህ በምክንያትነት ሊቀርብ አይገባም” ብሏል።

መሃል ዳኛው” ከዚህ ወንበር ተቀምጠን ትዕዛዝ መስጠት አለብን። ሁለት አቃቤ ህጎች ስላሉ አንዱ ተክቶ ሊሰራ እንደሚችል እንረዳለን። ይህ የትዕዛዝ ጉዳይ አይደለም።” ቢልም ሂደቱ ተቋርጦ ለምሳ ተወጥቷል።
ይህ የምሳ ሰዓት ይከበር ጥያቄና ክርክር በታዳሚውና ተከሳሾች ሳቅ የታጀበ ነበር።

በሌላ በኩል በእነ ጉርሜሳ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ነሃሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሳ እንዳይበሉ የተከለከሉ ሲሆን በወቅቱ የከለከሉት አመራሮች ተጠይቀው በማረሚያ ቤቱ ደንብ መሰረት መከልከላቸውን ገልፀው ነበር። ይሁንና ደንቡ ለእስረኞች የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያቀርብና፣ ፍርድ ቤት ለሚውሉ እስረኞች ምሳ ተብሎ የሚቀርበው አንድ ደረቅ ዳቦ ያለማወራረጃ በመሆኑ ደንቡ ጋር የማይሄድ ስለሆነ የከለከሉት አዛዦች ጥፋተኛ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ወስኗል።በዚህም መሰረት አዛዦቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ይቅርታ ጠይቀው ታልፈዋል።

ዛሬ አቃቤ ህጉ የምሳ ሰዓቱ እንዲከበር ከጠየቀ በሁዋላ እስረኞቹም ምግብ እንዲገባላቸው የጠየቁ ሲሆን ፍርድ ቤቱ “እንዲያውም እዚሁ ጥሩ ማስረጃ አለ። ሌላኛው ወገንም ተገቢውን ምግብ አግኝቶ መከራከር አለበት” ብሎ ለእስረኞች ምግብ እንዲፈቀድ ወስኖ ነበር። ይሁንና ፖሊሶች ተከሳሾቹ ምግብ እንዳይገባላቸው ከልክለዋል።

በባህር ዳር ከተማ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ በርካቶች እየታሰሩ ነው

ዘመኑ ተናኘ

አምና ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በነበረው ሁከት የሞቱ ሰዎችን ለማሰብ በተደረገው የመደብሮች መዝጋትና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቋረጥ ምክንያት፣ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

Bahir Dar city

ባህርዳር ከተማ

የሪፖርተር ምንጮች ሰሞኑን እንደገለጹት፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎችና ወጣቶች ታስረዋል፡፡ ከታሰሩት መካከል በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ካፒታል ያላቸው፣ በሆቴልና በሌሎች ትልልቅ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት እየታሰሩ ያሉ አካላት እንዳሉ ገልጾ እነማንና ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ተቃውሞ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡

‹‹አላስፈላጊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና የተለየ ዓላማ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ትክክለኛ ትምህርት እንዲወስዱ እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ስማቸውን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡

ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ተነስቶ የነበረው መደብሮችን የመዝጋትና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቃውሞ፣ ለሦስት ቀናት የዘለቀ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ተቃውሞው እንደገና መነሳቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡

አቶ ፀጋዬ እንደተናገሩት በክልሉ ውስጥ ባሉ አዋሳኝ ዞኖችና ወረዳዎች ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ተነስቷል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ ካሉ ወረዳዎች መካከል ስናን፣ ቢቡኝና ማቻከል ወረዳዎች ውስጥ ነጋዴዎች ለተከታታይ ሁለት ቀናት መደብሮችን በመዝጋት ተቃውሞ ማሰማታቸውን አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል፡፡

ተቃውሞው ደብረ ታቦር፣ ወልዲያና ኮምቦልቻ አካባቢዎችም እንደነበር አቶ ፀጋዬ ጠቁመው፣ ተቃውሞውም ከአንድ እስከ ሁለት ቀናት የዘለቀ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው ተቃውሞ ባህር ዳር ካለው ተቃውሞ ጋር እንደማይገናኝ አቶ ፀጋዬ ማስረዳታቸውን የሪፖርተር ዘገባ አመልክቷል፡፡

አቃቤ ህግ ለ‹‹ሽብር›› ተከሻሾች በነፃ የቆሙ ጠበቆችን ማስፈራራቱ ተገለፀ

‹‹አቃቤ ህግ ጠበቆችን በማስፈራራትና በመክሰስ ከፍርድ ስርዓቱ ለማራቅ እየጣረ ነው›› ጠበቆች

በጌታቸው ሺፈራው

አቃቤ ህግ የቂሊንጦ እስር ቤትን በማቃጠል፣ ንብረት ማውደምና የሰው ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ስር ከተከሰሱ 38 ግለሰቦች መካከል የነፃ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጠበቆች ሊከሰሱና የጥብቅና ፈቃዳቸው ሊነጠቅ እንደሚችል አስፈራርቷል፡፡ ጠበቆቹ ፍርድ ቤቱን በማስፈቀድና በማሳወቅ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ለተከሰሱት ግለሰቦች በነፃ ከመቆም በተጨማሪ ለበርካታ ተከሳሾች የቆሙትን አቶ ወንድሙ ኢብሳን በማገዝም እየተከራከሩ ቆይተዋል፡፡

ይሁንና ዛሬ ነሀሴ 4/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቃቤ ህግ ለተከሳሾች በነፃ የሚቆሙት ጠበቆች ከተከሳሾች ጋር የፈፀሙት ውል እስከሌለ ድረስ ተከሳሾችን ወክለው እንዳይቆሙ፣ የሚቆሙ ከሆነም ሊከሰሱና ፈቃዳቸውን ሊነጠቁ እንደሚችሉ ማስፈራሪያ አዘል አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ አቃቤ ህግ ያቀረበውን አቤቱታ ተቀብለው ለተከሳሾቹ የጥብቅና አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ ወይንም ለጥያቄው መልስ እንዲሰጡበት ምርጫ ባቀረበው መሰረት ጠበቆቹ መልስ በመሰጠት ተከሳሾቹን ወክለው እንዲቆሙ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ጠበቆቹ በአንድ ወንጀል የተከሰሰ ሰው የጥብቅና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው፣ እንዲሁም በአመት ቢያንስ 40 ሰዓት በነፃ የማገልግል ግዴታ እንዳለባቸው ገልፀው በነፃ የሚሰጥ አገልግሎትም ውል ሊፈፀምበትና ለፍርድ ቤትም ሊቀርብ እንደማይችል አሳውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ ጠበቃ ሊጠየቅ የሚችለው የሙያ ፈቃዱን እንጅ በነፃ በቆመበት ጉዳይ ውል መጠየቅ እንደማይገባ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ክሱ አንድ በመሆኑና አንድ ምስክር በርካታ ተከሳሾች ላይና ተፈፀመ የሚባለው ጉዳይ ላይ እየመሰከረ ባለበት ሁኔታ ጠበቆች ደንበኛቸው ባይሆንም ሌላ ደንበኛ ላይ የተመሰከረውን ጉዳይ ላይም በመከራከር ክሱን ውድቅ ማድረግ ስላለባቸው ሌሎች ተከሳሾች በማገዝ መከራከር እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ጠበቆቹ አቶ ወንድሙ ሌላ ችሎት ለሚቀርቡ ደንበኞቻቸው ሲቆሙ፣ እንዲሁም ጠበቃ የሌላቸውን ሲወክሉ ፍርድ ቤቱ አውቆና ፈቅዶ መሆኑን በመግለፅ አቃቤ ህግ ያቀረበውን አቤቱታና ማስፈራሪያ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡

አቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታና ማስፈራሪያ የህግም የሞራል ድጋፍ የለውም ያሉት ጠበቆቹ ‹‹አቃቤ ህግ ጠበቆችን በማስፈራራትና በመክሰስ ከፍርድ ስርዓቱ ለማራቅ እየጣረ ነው›› ብለዋል፡፡ የእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የምስክር ሂደት ጠንካራና የአቃቤ ህግን ክስ የሚያስተባብል ክርክር እየተደረገበት ያለ በመሆኑ እና አቃቤ ህግ ደግሞ ጠበቆችን በማራቅ ክሱ እራሱ በፈለገው መንገድ እንዲሄድለት በመፈለጉ አቤቱታና ማስፈራሪያውን እንዳቀረበ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ጠበቃ ገልፀዋል፡፡

አቃቤ ህግ አቤቱታና ማስፈራሪያውን ካቀረበ እና ጠበቆችም ምላሽ ከሰጡ በኋላ የፍርድ ቤቱን ብይን ሳይጠይቅ ‹‹በህጉ መሰረት አቤቱታችን አቀረብን እንጅ አላስፈራራንም›› ብሏል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን መርምሮ ለመበየን ጊዜ የሚወስድ መሆኑንና ችሎት ላይ መበየን እንደማይቻል ገልፆ፣ በገንዘብ ጠበቃ ማቆም ላልቻሉ ተከሳሾች በነፃ የሚቆሙና አቶ ወንድሙ ኢብሳን የሚያግዙ ጠበቆች ውል ሳይኖራቸው ሊቆሙ ይገባል አይገባም የሚለውን ለመበየን በአዳር ቀጠሮ ይዟል፡፡

በስኳርና በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሙስና የተጠረጠሩ ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

ታምሩ ጽጌ

በ184 ሚሊዮን ብር ሙስና የተጠረጠሩ ብርጋዴር ጄኔራል ተካተዋል
የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታሰሩ

በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር ማዋል የጀመረው ፌዴራል ፖሊስ፣ ከሁለት የስኳር ፋብሪካዎችና ከአንድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሦስት ተጠርጣሪዎችን አስሮ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር አውሎ ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ካቀረባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ፣ በ184,008,000 ብር የተጠርጣሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ ናቸው፡፡ ብርጋዴር ጄኔራሉ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለግላቸው በመዋላቸው ኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት እንዲዘገይ ማድረጋቸውንም አስረድቷል፡፡

ሌላው በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው ናቸው፡፡ በመንግሥት የተጣለባቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው ኦአይኤ ለተባለ ኮንትራክተር በትውስት አርማታና ሲሚንቶ መስጠታቸውን፣ ከሰጡ በኋላም ከተከፋይ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ባለመቀነሱ፣ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡

አቶ ዮሴፍ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ሌላም ጉዳት አድርሰዋል ያለው መርማሪ ቡድኑ፣ የአገዳ ምንጠራ ሥራ በአንድ ሔክታር 25,000 ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቶ እያለ ሥራውን ከባቱ በመንጠቅና በአንድ ካሬ ሜትር 72,150 ብር ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመስጠት፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በተመሳሳይ የአገዳ ምንጣሮ ላይ፣ ሥራው ሳይከናወን አሥር ሚሊዮን ብርና 20 ሚሊዮን ብር ለተለያዩ ግለሰቦች በመክፈልም ጉዳት ማድረሳቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ካሳዬ ካቻ ደግሞ 26,771,681 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡

ተጠርጣሪው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ለተባለ ኩባንያ ከመካኒሳ እስከ ዓለም ገና ለሚሠራ መንገድ፣ 400 በርሜል ወይም 23,456,481 ብር ግምት ያለው አስፋልት በውሰት መስጠታቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ አቶ ካሳዬ በውሰት የሰጡትን አስፋልት በሦስት ወራት ውስጥ ማስመለስ ሲገባቸው ባለማስመለሳቸው፣ በመንግሥት ላይ የ26,771,681 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

አቶ ካሳዬ በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ ለሳትኮን በትውስት የተሰጠው አስፋልት በባለሥልጣን ተፈቅዶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱም በወቅቱ ባለመመለሱ በፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶበት በሒደት ላይ መሆኑን በማስረዳት ሊጠየቁ እንደማይገባቸው ገልጸዋል፡፡ መጠየቅ አለባቸው ቢባል እንኳን በዋስ ሆነው በውጭ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ የጠየቁ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ተቃውሟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን የዋስትና መብት ጥያቄውን በማለፍ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬምና አቶ ዮሴፍ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ቀደም ብሎ ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ካሳዬ ላይ የተጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ፣ ለነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታን አቶ አለማየሁ ጉጆን ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳቱ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ አቶ ኪሮስ በኮርፖሬሽኑ የቤቶችና የመስኖ ዘርፍ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደሪፖርተር ዘገባ ከሆነ፤ በአጠቃላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር እስከ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ድረስ 51 ደርሷል፡፡

የመኢአድ አመራር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሱ

በታምሩ  ጽጌ

Mamushet Amare

አቶ ማሙሸት አማረ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራር የነበሩትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለሌሎች አመራሮች ጋር በተፈጠረ ልዩነት ከአባልነት የራቁት አቶ ማሙሸት አማረ፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

አቶ ማሙሸት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን ተላልፈው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማሴር መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. መልምለው ያደራጇቸውንና በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን አስተባብረው፣ በአማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች የሽብር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ማዘጋጀታቸውን በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት ኃላፊነት ወስደው እንቅስቃሴውን ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ለመምራት ኬንያ ለመሄድ ሞያሌ ከተማ እንደገቡ፣ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ ገልጿል፡፡

ተከሳሹ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አባል አማካይነት እንደተመለመሉ የሚገልጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ተልዕኮ በመቀበል ከቡድኑ በሚላክላቸው ገንዘብ የጦር መሣሪያ በመግዛትና ማሠልጠኛ በማመቻቸት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረውን ሁከት እንዲቀጥል ሲያደርጉ እንደነበር ገልጿል፡፡

በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በምርጫ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ማስወገድ እንዲቻል፣ በውጭና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር የሽብር ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አባላት በመመልመልና በማደራጀት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ እንዲልኩም ተልዕኮ እንደተሰጣቸው አክሏል፡፡

ተከሻሹ በ2007 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ለቡድኑ አባላትን መልምለውና ወታደራዊ ቤዝና ማሠልጠኛ ወዳላት ኤርትራ በሁመራ በኩል መላካቸውን፣ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ከተለያዩ አካባቢዎች 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሰብስበው መንግሥትን ከሥልጣን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝባዊ አመፅ መሆኑን፣ አመጽ ለመፈጸም ደግሞ የጦር መሣሪያ ስለሚያፈልግ እያንዳንዱ አባል ሌላ አባላት በመመልመል፣ በማደራጀትና በማስፋፋት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል አንዱን ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ ማድረግ እንዳለባቸው ተልዕኮ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

ተከሳሹ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ውስጥ ለሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ቤዝ የሚሆን ቦታ በመምረጥ፣ ከደብረ ብርሃንና አዲስ አበባ የተመለመሉ ዘጠኝ አባላትን ወደ ማሠልጠኛ በመላክ ሥልጠና ማስጀመራቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. አቶ ማሙሸት ዘመነ ምሕረቱ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አመራርና ለገሰ ወልደሀና ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመሰብሰብ፣ በጎንደር ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ሰሜን ሸዋ ጫካ ውስጥ በመግባት፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲደርስ ተልዕኮ መስጠታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ አቶ ማሙሸት የሽብርተኛነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የማቀድ፣ የመዘጋጀት፣ የማሴርና የማነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ቀረቦባቸዋል፡፡ ተከሳሹ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆኑ፣ በግላቸው ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር

%d bloggers like this: