በኦሮሚያ ክልል ከሰኞ የካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2010 ዓ ም በመላው ኦሮሚያ ክልል የተጠራውን ከቤት ያለመውጣትና የንግድ እቀባ ተከትሎ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ /መድረክ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፥ እና ሌሎች የፓርቲው አመራሮች በተለይም የፓርቲው ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፥ የወጣቶች ክንፍ ሥራ አሥፈፃሚ አባል አቶ አዲሱ ቡላላ እና የወጣቶች ክንፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ጉርሜሳ አያኖን ጨምሮ 7 የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል። እነ አቶ በቀለ ገርባ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ ም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል።
አቶ በቀለ ገርባ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ህዝባዊ አቀባበል ላይ ንግግር ሲያደርጉ
እነ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ከአዲስ አበኣ ጀምሮ ከፍተኛ ህዝባዊ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በተለይም በመኖሪያ ከተሞቻቸው ህዝባዊ አቀባበሉ እስከምሽት እንደነበር ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በአዳማ/ናዝሬት አቶ በቀለ ገርባ የተደረገ ህዝባዊ አቀባበል
አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎ ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ. ም. አዳማ/ናዝሬት በሚገኘው አበበ ቢቂላ ስታዲየም በርካታ ህዝብ አቀባበል ያደረገላቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም ለህዝቡ ንግግር አድርገዋል። አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በውህኒ ቤት እንደሚገኙና ሁሉም መፈታት እንዳለባቸው ያስታወሱት አቶ በቀለ፤ ከእስር እንዲፈቱ በመንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር ድጋፍ ላደረገው ለመላው ህዝብ ምሥጋናችውን አቅርብዋል።