በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለቀናት በአደራ እስር ላይ ይገኛሉ
(ዳጉ ሚዲያ) በቅርቡ የተደረገውን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ከዓመታት እስር በኋላ የተለቀቁ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ሌሎች የመብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ያለ በቂ ምክንያት ከመጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም.ጀምሮ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ከነበሩበት የምሳ እና የ “እናመሰግናለን” ግብዣ ላይ በነበሩበት ወቅት በድጋሚ ታስረዋል።
በድጋሚ ከታሰሩት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ አቶ አንዷለም አራጌ፥ ጦማሪ ዘላላም ወርቃገኘው፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ ጦማሪ ማህሌት ፍንታሁን፥ ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሀይሉ፥ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ አቶ ተፈራ ተስፋዬ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ልዩ ስሙ ጎተራ ፖሊስ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ከመደበኛ ሥራቸው ተይዘው ከታሰሩት መካከል የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋችና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዲሁም የመብት ተሟጋች እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደዓ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወህኒ ቤት ታስረው ይገናሉ።
በቅርቡ ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች መካከል በከፊል
በተያያዘ ዜና የአማራ ህዝብን ከአገዛዙ ጥቃት ለመከላከል በሚል በህጋዊ መንገድ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት በይፋ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የአካባቢ አስተባባሪዎች መካከል ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በጋራ በመሆን ሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ ም ባህርዳር ከተማ ተሰብስበው እራት ሲመገቡ በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ከታሰሩ በኋላ ድብደባ እንድተፈፀመባቸው ተጠቆመ። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በበእስር ላይ የሚገኙት ምሁራን፥ ፖለቲከኞች እና በዕለቱ በጓደኝነት እራት ግብዣው ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች በባህርዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ።
በባህር ዳር ከተማ ተይዘው ከታሰሩት መካከል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (ባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚደንት እና ተመራማሪ፣ ረዳት ፕሮፊሰር)፥ ጋሻው መርሻ (የአንጸባቂው ኮከብ መጽኃፍ ከታቢ፤ አዲስ አበባ በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛል)፥ የሱፍ ኢብራሂም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና በአሁንኑ ወቅት ጠበቃ)፥ ተመስገን ተሰማ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር፤የወሎ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መስራች፣ ረዳት ፕሮፊሰር እና አማራ ነን የሚለው መዝሙርም ገጣሚ)፥ በለጠ ሞላ ( ተባባሪ ፕሮፊሰር ፡አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር)፥ ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ (የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ(አርታኢ)፤ከ1997 እስከ 1999 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳት፤)፥ ጋዜጠኛ በለጠ ካሳ (የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ)፥ አቶ ሲሳይ አልታሰብ( ሲቪል ኢንጅነር)፥ አቶ ዳንኤል አበባው፥ አቶ መንግስቴ ተገኔ፥ አቶ ቦጋለ አራጌ፥ አቶ ካሱ ኃይሉ (የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መምህር፡የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ)፥ አቶ ተሰማ ካሳሁን፥ አቶ ድርሳን ብርሃኔ፥ አቶ በሪሁን አሰፋ፥ አቶ ፍቅሩ ካሳው፥ አዲሱ መለሰ (የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር)፥ አቶ ተመስገን ብርሃኑን ጨምሮ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ግለሰብም በእስር ላይ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ እና በባህርዳ ይታሰሩት ሁሉም ተከሳሾች ክስ እንዳልቀረበባቸውና የታሰሩበትም ምክንያት እንዳልታወቀ የተገኘው መረጃ አመልክታል። ይህንንም ተከትሎ ሐሙስ ምሽት መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ ም የተለያዩ ማኀበራዊ ሚዲያን በመጠቀም #ሁሉም_የፖለቲካ_እስረኞች_ይፈቱ የሚል ዘመቻ የተደረገ ሲሆን፤ ከአሰራቸው የመንግሥት አካል ግን የተሰጠ ምላሽ የለም።
አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጪው ሰኞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ሥራቸውን በይፋ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል
(ዳጉ ሚዲያ)የአራት ፓርቲዎች ግንባር አባል የሆነው የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ የብአዴን ተወካይና ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በፊት በነበሩበት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ተወስኗል። በተለመደው የኢህአዴግ አሰራ መሰረት አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጪው ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ በመፈፀም በይፋ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዶ/ር አብይ አህመድ (ፎቶ፡ ወልስትሬት ጆርናል)
ገዥው ኢህአዴግ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው ዶ/ር አብይ አህምድ አሊ የተለያየ የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁሟሉ። ዶ/ር አብይ በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፤ በመንግሥት የሥራ ድርሻ በመከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ደህንነት እና መገናኛ ኃላፊ በመሆን የሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ አላቸው። ከውትድርና ዓለም ከተሰናበቱ በኋላ የፌደራሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልቀት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር፥ የሀገሪቱ የስለላ ተቋም የሆነው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስራችና ምክትል ዳይሬክተር፥ የፌደራሉ የሳይንስና ቴኬኖሎጂ ሚኒስትር፥ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ፥ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት እና የኦህዴድ ዋና ጸሐፊ በመሆን ማገልገላቸው ታውቋል።
የ42 ዓመቱ ዶ/ር አብይ በትምህርት ዝግጅታቸው በኮምፒዩተር ሳይንስ ምህንድስና አዲስ አበባ ከሚገኘው ማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የመጀመሪያ ድግሪ፥ ድህረ ምረቃ በክሪፕቶግራፊ ከደቡብ አፍሪካው ማኪሄ ዳይናሚክስ ተቋም፥ ድህረ ምረቃ በለውጥ አመራ ከግሪንዊች ዩኒቨርሲ፥ ድህረ ምረቃ በንግድ አስተዳደር ከአሽላን ዩኒቨርሲ እንዲሁም ዶክተሬት ድግሪ በሰላም እና ደህንነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ አግኝተዋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከፖለቲካ ህይወትና ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በብዕር ስማቸው “እርካብ እና መንበር” የሚል መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ዶ/ር አብይ አህመድ ከወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር ትዳር በመመስረት የ3 ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ፤ በመጪው ሰኞ ሥልጣናቸው የሚያስረክቡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በመተካት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ ይጠበቃል።
ዶ/ር አብይ በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ ወደ አመራር ከመጡትና በህዝቡ ዘንድ ከፍተና ተቀባይነት ካገኙት የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን አባል ሲሆኑ፤ ከአገዛዙ መሪዎች ባልተለመደ መልኩ ንባብ፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፥ መማርና ማወቅ እንዲሁም ብሄራዊ የሀገር አንድነትና ውይይቶችን እንደሚያብረታቱ በተለያዩ መድረኮች ሲገልፁ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ አሁን በሚመሩት የኢህአድግ አገዛዜ በሀገሪቱ ያለውን የነፃ ፕሬስ፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፥ በሙያ የመደራጀት፥ የመሰብሰብ፥ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና መተግበር በተፃፈና ባልተፃፈ የድርጅታቸው ሕግ ገደብ የተጣለባቸው በመሆኑ፤ ሲናገሩ የነበሩትን ለመተግበር ከወዲሁ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል። በተጨማሪም የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው በተመረጡበት ወቅት በድጋሚ የታሰሩት ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾችና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በአስቸኳይ አዋጅ ስም ለእስር ተዳርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር አብይ መሪ ሆነው በተመረጡበት ወቅት ሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ፥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ወደመሪነት የመጡ ሲሆን፤ በተለይ በኦሮሚያ፥ በአማራ እና በከፊል በደቡብ ክልል ተከታታይ የሆነ ከፍተኛ የሆነ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል። 180 አባላት ባአሉት እና በዕለቱ 170 ብቻ በተገኙበት የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በርካታ ቀናት በፈጀ አለመግባባትና ውጥረት በኋላ በተደረገው ውድድር የድርጅቱ ሊቀመንበር ውድድር የኦህዴድ ተወካይና ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ 108 ድምፅ፥ የደኢህዴን ተወካይና ሊቀመንበር አቶ ሺፈራው ሽጉጤ 59 ድምፅ ሲያገኙ የህወሓት ተወካይና ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል 2 ድምፅ በማግኘት አሸናፊው ታውቋል። በወቅቱ የብአዴን ተወካይና ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ደመቀ መኮንን ምርጫው ሊጀምር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውም ተሰምቷል።
ምንም እንኳ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ የመልካም ምኞች የገለፁላቸው በርካታ ዜጎች ቢኖሩም፤ በተለይ የመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞችና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች በእስር የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፥ የአፋኝ ህጎች መሻሻል እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ለውጥ መደረግ በቅድሚያ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ሳይገልፁ አላለፉም። በተለይ የተለመደው የአገዛዙ አፋኝ ህጎች እና አምባገነናዊነት ካልተሻሻለ እንዲሁም በህግ የተሰጣቸው ሥልጣን ተጠቅመው የራሳቸውን አዳዲስ ካቢኔ አባላትን በራሳቸው አቋቁመው ሥራ ካልጀመሩ የእርሳቸው መምጣት ብቻውን ለውጥ አያመጣም የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ዜጎች በርካታ ናቸው።
በሀገሪቱ ካለው አፈና በተጨማሪ የሥራ አጦች ብዛት እየጨመር መሄድ፥ ሙስና፥ አድሏዊ አሰራር፥የፍትህ መጓደል፥ የዜጎች ነፃነት ማጣት እርምት የሚያሻቸው አንገብጋሚ ጉዳዮች ቢሆኑም የትኞቹን ቅድሚያ ሰጥው ሊተገብሩ እንደሚችሉ ሰኞ ከሚሰጡት መግለጫ እና እቅድ በተጨማሪ በተግባር የሚታይ ይሆናል።
በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች በድጋሚ ታሰሩ
(ዳጉ ሚዲያ) እሁድ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወጣቶች በቅርቡ ከእስር ለተፈቱት ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞችን “እናመሰግናለን” በሚል በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ከነበሩት መካከል 11 ያህሉ በፖሊስ ታግተው መቆየታቸው ታውቋል። ፖሊስም ታጋቾቹን ከጋዜጠና ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በበርካታ የፖሊስ ኃይል በማጀብ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ስር በሚገኘው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዷችው ሲሆን፤ ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ጎተራ ወደ ሚገኘው ፖሊስ መምሪያ ወስደው እንዳሰሯቸው ለማወቅ ተችሏል።
አቶ አንዱዓለም አራጌ ኤና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
እንደምንጮች መረጃ ከሆነ፤ ለእገታው ምክንያት የሆነው በመርሃ ግብሩ ላይ የገዥው ስርዓት መለያ የሌለበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሎ በማየታቸው በተቆጡ የአገዛዙ ፖሊሶች በፈጠሩት አለመግባባት መሆኑ ተጠቁሟል። በተለይም በስፍራው የነበረው መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው ደርሰው የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ሰንደቅ ዓላማውን ከተሰቀለበት በግድ ነጥቀው በመውሰድ ድርጊቱን ስብሰባ አድርጎ በመቁጠር ለምን አላስፈቀዳችሁም በሚል ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ማናገር እንፈልጋለን በማለት ፖሊሶቹ ታዳሚውን ለማስፈራራት ሞክረዋል። ይህንንም ተከትሎ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የነበረው መርሃ ግብር የተለመደ የማኀበራዊ ወዳጅነት እንጂ ስብሰባ አይደለም፥ ለማኀበራዊ ወዳጅነት ፈቃድ እያስፈልግም ሲል ምላሽ በመስጠቱ በተለይ ሲያናግረው የነበረውን ፖሊስ እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችላል።
በጋዜጠኛው ምላሽ ደስተኛ ያልነበረው ፖሊስ ጉዳዩን በማክረር ኃላፊነቱን የሚወስዱ 3 ሰዎችን ማናገር እንፈልጋለን ወደሚል እልህ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ አቶ አንዱዓለም አራጌ ጉዳዩን ለማረጋጋት በሚል ፖሊሱን ለማግባባት ቢሞክርም፤ ፖሊሱ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በመጨረሻም አቶ አንዱዓለም አራጌ ለፖሊሱ ” ችግር አለ ብላችሁ ምታምኑት ነገር ካለ እና ማናገር ከፈለጋችሁ ሁላችንንም ወስዳችሁ ማናገር ትችላላችሁ፤ ከዛ ውጭ በተናጥል ኃላፊነት የሚወስድም ሆነ የሚያናግር የለም” የሚል ምላሽ ይሰጣል።
በተሰጣቸው ምላሽ ደስተኛ እና ፈቃደኛ ያልሆነው ፖሊስ በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል በወቅቱ በስፍራው የነበሩትን እንዳይንቀሳቀሱ በማስገደድ፤ በያዘው የፖሊስ መገናኛ ሬዲዮ ወደበላይ አለቆቹ በመደወል በአካባቢው ከፍተኛ ችግር እንዳለ እና ለዚህም በርካታ የፖሊስ ኃይል እንዲታዘዝለት ጥሪ ያስተላልፋል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም በተሽከርካሪ መኪና ተጭነው የመጡ በርካታ ፖሊሶች የጦር መሳሪያዎቻቸውን በመደገን አካባቢውን በመቆጣጠር በስፍራው በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት እና በወቅቱ የ “እናመሰግናለን” ሽልማት መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው የነበሩትና ከእስር ተለቀው የነበሩ 11 የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አቶ አንዱዓለም አራጌ፥ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፥ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉ፥ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፥ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፥ የመብት ተሟጋች ወጣቶች አቶ ስንታየሁ ቸኮል፥ አቶ አዲሱ ጌታነህ፥ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፥ አቶ ይድነቃቸው አዲስ እና አቶ ተፈራ ተስፋዬ በድጋሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ፖሊስ አግቶ ያሰራቸውን 11 ሰዎች ለምን እንደሆነ እስካሁን በይፋ የሰጠው ማብራሪያም ሆነ ምክንያት የለም። ይሁን እንጂ የታገቱት ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ታፍነው ተወስደውበት ከነበረው ጀሞ ፖሊስ ጣቢያ ማምሻውን ጎተራ ፊትለፊት ወደሚገኘው የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰሩ ለማወቅ ተችሏል። ጋዜጠኞቹ እና የመብት ተሟጋቾቹ በታሰሩብት ዕለት ቀደም ሲል በቅርቡ በሀገሪቱ ላለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ ያልተቋረጠውን የፀረ ጭቆና አገዛ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በቅርቡ ከእስር ከተፈቱት በርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጋር የሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋአጀው ተመሳሳይ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው ካጠናቀቁ በኋላ ተጨማሪ በሌሎች በጎ ፈቃድ ወጣቶች ባዘጋጁት መርሃ ግብርን አጠናቀው ርስ በርስ በመጨዋወት ላይ እያሉ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በአሁን ወቅት ሀገሪቱ ለ6 ወራት በሚቆይ የአስቸኳይ አወጅ ስር ሆና በወታደራዊ ዕዝ ቁጥጥር ስር መውደቋ ይታወቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በእስር ቤት ተጠርጣሪዎችን ያሰቃዩ እንደነበር ተጋለጠ
ጌታቸው ሺፈራው
ተከሳሹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ አቶ መለሰ አለም ድብደባ እንደፈፀሙበት ለፍርድ ቤት ገለፀ
~ “ጉራጌ በመሆኔ ብቻ ዘሬ እየተጠቀሰ ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስብኝ ነበር”
~” ከደበደቡኝ ሰዎች መሀል የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለሰ አለም አንዱ ናቸው”
( በእነ ጌታሁን በየነ ክስ መዝገብ ተከሳሽ የሆነው ሰይፈ አለሙ መከላከያ ምስክር ከማሰማቱ በፊት ለፍርድ ቤት የሰጠውን ቃል ፍሬው ተክሌ እንደሚከተለው ፅፎታል)
“በማዕከላዊ ከመርማሪዎች ጋር ሳይሆን ጥቃትን ከሚያደርሱ አካላት ጋር ነበርኩ። እኔ የተያዝኩት አርባምንጭ ሆቴል ውስጥ ነው። የያዘኝም ደህንነት ነው። ይዞም ማዕከላዊ የሚባል ሲኦል ውስጥ ነው የከተተኝ የተረከበኝም ኮማንደር ተክላይ ነው። ይደበድቡኝ የነበሩት በጣም ብዙ ናቸው ሴቶችም አሉበት፥ ከኮማንደር ተክላይ ጋር ሰክረው ነበር የሚደበድቡኝ። ከሚደበድቡኝ ሰዎች መሀከል የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለሰ አለም አንዱ ነበር። በማዕከላዊ ጥቃት ይደርስብኝ የነበረው በቤሄሬ ነው ጉራጌ ሌብነት እንጂ ፖለቲካን የት ያውቃል እየተባልኩ ምራቅ እየተተፋብኝ ነበር ስደበደብ የነበረው። ከዚህ በፊትም ማዕከላዊ ተይዘው የገቡ ብዙ ጉራጌዎች ተደብድበዎል ተኮላሽተዎል በዚህ ቤሄር ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ሊቆም ይገባል። ሰውነቴ ላይ የሚታዩት እነዚህ ጠባሳዎች ከእናቴ ማህፀን ስወለድ ያገኘሆቸው ሳይሆኑ በማዕከላዊ በደረሰብኝ ድብደባ ምክንያት ሰውነቴ ላይ የቀሩ ናቸው። ይሄ ሁሉ ድብደባ ደርሶብኝ ሰውነቴም መግሎብኝ ህክምና እንኮን አለገኘሁም ነበር። በጊዜው አብረውኝ የነበሩ እስረኞች ህክምና ያግኝ ብለው የረሀብ አድማ አድርገው ነበር ሀላፊዎቹም ህክምና ይደረግለተል ብለው ቃል ከገቡ በሆላ እኔን ጠርተው አንተን አናክምህም ብለው ማስታገሻ ብቻ ሰተውኛል። ስደበደብ የነበረውም የግንቦት ሰባት አመራር ነህ ተብዬ ነው።” ሲል የተከሳሽነት ቃሉን የሰጠ ሲሆን ሶስት የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ አሰምቶል።
በወቅቱ መከላከያ ምስክሮቹም ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ጣቢያ አብረው መታሰራቸውን ገልፀዋል። ምስክሮቹም አቶ ሰይፉ አለሙ ላይ ይደርስ የነበረውን ሰቃይ በድብደባ ምክንያት ሰውነቱ ላይ ይታዩ የነበሩ ቁስሎችን እና የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ የረሀብ አድማ ማድረጋቸውን ገልፀው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዎል። ፍርድ ቤቱም በመከላከያ ምስክሮች ላይ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሽብር ወንጀል የተከሰሱት የነ መሪ ጌታ ዲበኩሉ አስማረ የፍርድ ቤት ውሎ
ቴዎድሮስ አስፋው
“እየተመገብንና እየጠጣን ያለው አሸዋ ነው” ተከሳሾች
~”ስሜ መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረ እንጂ ወይዘሪት ዲበኩሉ አስማረ አይደለም”
~የመቃወሚያ ብይን ለመስጠት 9 ወር ፈጅቷል
በፀረ ሽብር አዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 1 ተጠርጥረው በነ አቶ ክንዱ የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 8 ተከሳሾች መጋቢት 3 ቀን 2010ዓ.ም የክስ መቃወሚያ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 6 ቀን 2010ዓ.ም ተቀጥሮ በነበረው መስረት ተከሳሾች የሚመለከታቸው አካላት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ችሎቱ በሚካሄድበት የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት አዳራሽ ውስጥ የተገኙ ቢሆንም ችሎቱ ግን ዘግይቶ 5 ሰዓት ላይ ነው የጀመረው።
የመሀል ዳኛው ዳኛ በመጓደሉ ምክንያት መዘግየታቸውን ገልፀው ዘግይተው በመጀመራቸው ይቅርታ በመጠየቅ ከሳሽ ዐቃቤ ህግ የተከሳሽ ጠበቆች እንዲሁም ተከሳሾች መኖራቸው በስም ጥሪ በሚያረጋግጡበት ግዜ 6ኛ ተከሳሽ መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረን ወይዘሪት ዲበኩሉ ሰመረ ብለው በመጥራታቸው ተከሳሹ ስሜ መሪጌታ ዲበኩሉ ሰመረ እንጂ ወይዘሪት ዲበኩሉ አስማረ አይደለም በማለት ስማቸው እንዲስተካከልለት ጠይቀዋል።
በዚህም መሰረት ዳኛው መዝገቡ ላይ ወ/ት ተብሎ መመዝገቡን ገልፆ ለስህተቱ ይቅርታ ጠይቋል። በመጨረሻም የክስ መቃወሚያ ብይኑን በዳኛ መጓደል ምክንያት እንዳልሰሩት በመግለፅ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት የተከሳሽ ጠበቆችና ተከሳሾች አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ከ2ኛ እስከ 6ኛ እና የ10ኛ ተከሳሾች ጠበቃ መዝገቡ በዚህ ሳምንት ብቻ ብይን ለመስጠት ለ3ኛ ግዜ መቀጠሩን በመግለፅ የአሁኑ ቀጠሮ የመጨረሻ እንዲሆን ጠይቀዋል። 7ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ እንየው መዝገቡ እየተጓተተ ያለው በኔ የመቃወሚያ ብይን ነው ይህም 9 ወር መፍጀቱ አሳዛኝ ነው ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ 10ኛ ተከሳሽ ለገሰ ወልደሃና በማረሚያ ቤቱ የሚቀርብልን ምግብና መጠጥ አሸዋ ያለበት በመሆኑ በተደጋጋሚ ግዜ እንዲስተካከልልን ለአስተዳደሩ ብናቀርብም መልስ ማግኘት ስላልቻልን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይስጥልን ሲል አቤቱታውን በጽሁፍ ጭምር አቅርቧል።
የመሀል ዳኛው ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤቱ የውስጥ አስተዳደር ጣልቃ የማይገባ ቢሆንም የምግብና የመጠጥ አቅርቦቱን በሚመለከት አስተዳደሩን ጠርተን እናናግራለን ዛሬ ከሰዐትም አጠቃላይ የፍትህ አካላት ውይይት ያለ በመሆኑ በዚሁ አጋጣሚ መልስ እንደሚያገኝ ገልፀዋል። ቀጠሮውንም በሚመለከት ለቀጣዩ ሳምንት ለመጋቢት 13 ጠዋት ላይ እንዲሆን በመወሰን የመጨረሻ እንደሚሆን ገልፀዋል።
የተከሳሾች ስም ዝርዝር
1ኛ. ክንዱ ዱቤ
2ኛ. ዘመነ ጌጤ
3ኛ. ደበበ ሞገስ
4ኛ. ዘራይ አዝመራው
5ኛ. ገብረስላሴ ደሴ
6ኛ. መሪጌታ ዲበኩሉ ሰመረ
7ኛ. ሀብታሙ እንየው
10ኛ. ለገሰ ወልደ ሃና ናቸው
8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች ክሳቸው መቋረጡ በፍርድ ቤቱ ተገልፆል።