Daily Archives: March 4th, 2018

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት ተባብሷል፤ መንግሥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ እወሰደ ያለው የኃይል ርምጃም ቀጥሏል

(ዳጉ ሚዲያ) የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱን በመደበኛው ህግ ስርዓት ፀጥታ መጠበቅም ሆነ ማስጠበቅ አልቻልኩም በማለት ከባለፈው የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህግ ተግባራዊ አድርጓል። ይሁን እንጂ አርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ ም በተደረገው ድንገተኛ የአስችኳይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ አዋጁ በአወዛጋቢ ሁኔታ መፅደቁን ፓርላማው አስታውቋል።

አፈ ጉባዔው አቶ አባዱላ ገመዳ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ 547 መቀመጫ ካሉት የፓርላማው አባላት መካከል 8ቱ በህይወት እንደሌሉ በመግለፅ፤ ቀሪዎቹ “539” የፓርላማ አባላት እንዳሉ አስታውቀዋል። ከነዚህ ውስጥ አዋጁ በህገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት እንዲፀድቅ ከፓርላማው 2/3 ኛ ድምፅ ድጋፍ ማግኘት እንዳለበት በመጠቆም፥ አዋጁን ለማፅደቅ 2/3ኛ ድምፅ 339 ድምፅ ብቻ እንደሚያስፈልግ፥ የተሰጠው የድጋፍ ድምፅ ግን 346 እንደሆነና ይህም ከሚጠበቀው በላይ ድምፅ ድጋፍ እንደተገኘ፥ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምፀ ተዓቅቦ አዋጁ መፅደቁን አስታውቀው ነበር። ይሁን እንጂ አፈ ጉባዔው በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለፓርላማ አባላቱና ለህዝቡ እንደገለፁ በዕለቱ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

በአፈ ጉባዔው ከተላለፉአት የሐሰት መረጃዎች መካከል በዕለቱ በፓርላማ የተገኙ አባላት ቁጥር 539 ሳይሆን 441 እንደሆነ የፓርላማው ህዝብ ግንኙነት ክፍል ወዲያውኑ በድህረ ገፁ በሰጠው እርማት ያጋለጠ ሲሆን፤ በዕለቱ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የፓርላማ አባላት በዕለቱ ያልተገኙ እንደነበር፥ ከፓርላማው 2/3ኛ ድምፅ ለማግኘት ቢያንስ 365 ድምፅ ድጋፍ ማግኘት የሚገባ ሲሆን በዕለቱ የተገኘው የድጋፍ ድምፅ 346 ብቻ መሆኑ ቀድሞ በአፈጉባዔው መገለፃቸው አዋጁ በህጉ አግባብ እንዳልፀደቀ መረጃዎች አመልክተዋል። ይሄንንም የፓርላማው አባላት ከተበቱ በኋላ የነበረውን ስሀተት ለማረም የገዥው ስርዓት ደጋፊ የሆኑትን ጨምሮ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም ተደጋጋሚ የቁጥር መሰረዝና ማስተካከል ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ይህንንም ተከትሎ አዋጁ ባለፈው ዓመት ምስከረም 2009 ዓ ም ጀምሮ ለ10 ወራት ከቆየው የአስቸኳይ አዋጅ በባሰ ህገ መንግሥቱን የሚፃረሩ፥ የዜጎችን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥሱ አፋኝ ድንጋጌዎችን ይዟል በሚል በህዝቡ ዘንድ ተቃውሞ ቢደረግበትም፤ አዋጁ ከህግ አግባብ ውጭ በአወዛጋቢ ሁኔታ ፀድቆ ስራ ላይ መዋሉ ታውቋል። ይህንንም ተከትሎ በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ የዋጁ አስፈፃሚ ተደርጎ ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው ወታደራዊ ዕዝ “ኮማንድ ፖስት” በጥቂቱ ከ8 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ተጠቁሟል።

በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞን፥ ደንቢ ዶሎ፥ ጊንቢ፥ ሻምቡ፥ነጆ፤ ነቀምት፥ በምዕራብ ሽዋ አምቦ፥ ጊንጪ ከተገደሉት በተጨማሪ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በተተኮሰባቸው ጥይት መቆሰላቸውን ከስፍራው የተገኙ የዓይን እማኞች ገልፀዋል። ከተገደሉ ዜጎች መካከልም በኃይማኖት የአምልኮ ሥፍራ የነበሩ የኃይማኖት ሰባኪ “ፓስተር” እና በ80 ዎቹ የዕድሜ ክልል ያሉ አዛውንት ይገኙበታል።

መንግሥት እየወሰደ ያለውን የኃይል ርምጃ ተከትሎ ህዝባዊ ቁጣው ከምዕረብ ኢትዮጵያ ወሌሎች አካባቢዎች እየተዛመተ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አዋጁን እና የመንግሥትን ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በሚቃወሙ አካላት ከነገ ሰኞ የካቲት 26 እስከ ረቡዕ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ ም ከቤት ያለመውጣት፥ የንግድና የሥራ እንቅስቃሴ እቀባ መጠራቱ ታውቋል። ከነገ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምንም ዓይነት መደበኛ የትራንስፖርት እና ንግድን ጨምሮ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይኖር፥ ህዝባዊ እቀባውን ጥሶ የሚገኝ አካልም በየ አካባቢው በሚገኙ የተቃውሞ አስተባባሪዎች ርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል ተጠቁሟል። ነገር ግን የጤና ተቋማትና አምቡላንሶች የተለመደ ሥራቸውን መስራት እንደሚችሉና በተቃውሞ አስተባባሪዎቹ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል። የአስቸኳይ አዋጁ ውድቅ እስካልተደረገ ድረስ ህዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በተለያየ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል። ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል ግን አዋጁን በተግባር ከማስፈፀም ውጭ የተሰጠ ሌላ ምላሽ የለም። ስለሆነም ይህ እስከተዘገበበት ድረስ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል።

%d bloggers like this: