(ዳጉ ሚዲያ)የአራት ፓርቲዎች ግንባር አባል የሆነው የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ የብአዴን ተወካይና ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በፊት በነበሩበት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ተወስኗል። በተለመደው የኢህአዴግ አሰራ መሰረት አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጪው ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ በመፈፀም በይፋ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዶ/ር አብይ አህመድ (ፎቶ፡ ወልስትሬት ጆርናል)
ገዥው ኢህአዴግ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው ዶ/ር አብይ አህምድ አሊ የተለያየ የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁሟሉ። ዶ/ር አብይ በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፤ በመንግሥት የሥራ ድርሻ በመከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ደህንነት እና መገናኛ ኃላፊ በመሆን የሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ አላቸው። ከውትድርና ዓለም ከተሰናበቱ በኋላ የፌደራሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልቀት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር፥ የሀገሪቱ የስለላ ተቋም የሆነው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስራችና ምክትል ዳይሬክተር፥ የፌደራሉ የሳይንስና ቴኬኖሎጂ ሚኒስትር፥ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ፥ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት እና የኦህዴድ ዋና ጸሐፊ በመሆን ማገልገላቸው ታውቋል።
የ42 ዓመቱ ዶ/ር አብይ በትምህርት ዝግጅታቸው በኮምፒዩተር ሳይንስ ምህንድስና አዲስ አበባ ከሚገኘው ማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የመጀመሪያ ድግሪ፥ ድህረ ምረቃ በክሪፕቶግራፊ ከደቡብ አፍሪካው ማኪሄ ዳይናሚክስ ተቋም፥ ድህረ ምረቃ በለውጥ አመራ ከግሪንዊች ዩኒቨርሲ፥ ድህረ ምረቃ በንግድ አስተዳደር ከአሽላን ዩኒቨርሲ እንዲሁም ዶክተሬት ድግሪ በሰላም እና ደህንነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ አግኝተዋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከፖለቲካ ህይወትና ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በብዕር ስማቸው “እርካብ እና መንበር” የሚል መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ዶ/ር አብይ አህመድ ከወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር ትዳር በመመስረት የ3 ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ፤ በመጪው ሰኞ ሥልጣናቸው የሚያስረክቡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በመተካት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ ይጠበቃል።
ዶ/ር አብይ በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ ወደ አመራር ከመጡትና በህዝቡ ዘንድ ከፍተና ተቀባይነት ካገኙት የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን አባል ሲሆኑ፤ ከአገዛዙ መሪዎች ባልተለመደ መልኩ ንባብ፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፥ መማርና ማወቅ እንዲሁም ብሄራዊ የሀገር አንድነትና ውይይቶችን እንደሚያብረታቱ በተለያዩ መድረኮች ሲገልፁ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ አሁን በሚመሩት የኢህአድግ አገዛዜ በሀገሪቱ ያለውን የነፃ ፕሬስ፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፥ በሙያ የመደራጀት፥ የመሰብሰብ፥ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና መተግበር በተፃፈና ባልተፃፈ የድርጅታቸው ሕግ ገደብ የተጣለባቸው በመሆኑ፤ ሲናገሩ የነበሩትን ለመተግበር ከወዲሁ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል። በተጨማሪም የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው በተመረጡበት ወቅት በድጋሚ የታሰሩት ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾችና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በአስቸኳይ አዋጅ ስም ለእስር ተዳርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር አብይ መሪ ሆነው በተመረጡበት ወቅት ሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ፥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ወደመሪነት የመጡ ሲሆን፤ በተለይ በኦሮሚያ፥ በአማራ እና በከፊል በደቡብ ክልል ተከታታይ የሆነ ከፍተኛ የሆነ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል። 180 አባላት ባአሉት እና በዕለቱ 170 ብቻ በተገኙበት የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በርካታ ቀናት በፈጀ አለመግባባትና ውጥረት በኋላ በተደረገው ውድድር የድርጅቱ ሊቀመንበር ውድድር የኦህዴድ ተወካይና ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ 108 ድምፅ፥ የደኢህዴን ተወካይና ሊቀመንበር አቶ ሺፈራው ሽጉጤ 59 ድምፅ ሲያገኙ የህወሓት ተወካይና ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል 2 ድምፅ በማግኘት አሸናፊው ታውቋል። በወቅቱ የብአዴን ተወካይና ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ደመቀ መኮንን ምርጫው ሊጀምር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውም ተሰምቷል።
ምንም እንኳ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ የመልካም ምኞች የገለፁላቸው በርካታ ዜጎች ቢኖሩም፤ በተለይ የመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞችና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች በእስር የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፥ የአፋኝ ህጎች መሻሻል እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ለውጥ መደረግ በቅድሚያ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ሳይገልፁ አላለፉም። በተለይ የተለመደው የአገዛዙ አፋኝ ህጎች እና አምባገነናዊነት ካልተሻሻለ እንዲሁም በህግ የተሰጣቸው ሥልጣን ተጠቅመው የራሳቸውን አዳዲስ ካቢኔ አባላትን በራሳቸው አቋቁመው ሥራ ካልጀመሩ የእርሳቸው መምጣት ብቻውን ለውጥ አያመጣም የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ዜጎች በርካታ ናቸው።
በሀገሪቱ ካለው አፈና በተጨማሪ የሥራ አጦች ብዛት እየጨመር መሄድ፥ ሙስና፥ አድሏዊ አሰራር፥የፍትህ መጓደል፥ የዜጎች ነፃነት ማጣት እርምት የሚያሻቸው አንገብጋሚ ጉዳዮች ቢሆኑም የትኞቹን ቅድሚያ ሰጥው ሊተገብሩ እንደሚችሉ ሰኞ ከሚሰጡት መግለጫ እና እቅድ በተጨማሪ በተግባር የሚታይ ይሆናል።