የአዲስ አበባው “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ” ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፍ እና ክስተቶቹ
ብስራት ወልደሚካኤል
ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ ም ከጠዋቱ 1፡0 ጀምሮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሁሉን ያሳተፈ ታሪካዊ ሰልፍ ተከናውኗል። ህዝባዊ ሰልፉም በኢትዮጵያ ታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ፥ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወይም የሲቪክ ተቋም ውጭ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እየወሰዷቸው ባሉ በጎ የለውጥ ርምጃዎች ደስተኛ በሆኑ እና ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚፈልጉ ግለሰቦች ተነሳሽነት የተጠራ ህዝባዊ ሰልፍ ሲሆን፤ መሪ ቃሉም “ለውጥን እንደግፍ፥ ዴሞክራሲን እናበርታ” በሚል በሪ ቃል የተዘጋጀ ህዝባዊ ትዕይንት ነበር።
ዶ/ር አብይ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰልፍ በከፊል (ፎቶ፡ ከዕለቱ ማኅበራዊ ገፆች የተወሰደ)
በሰልፉ ላይ ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን ተሳታፊዎች ሊገኙ ይችላሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ እንደ አዲስ አበባና ፌደራል ፖሊስ ግምት ግን ከ4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደታደመበት ሙያዊ ግምታቸውን ሰጥተዋል። ይህም ከተጠበቀው በላይ መሆኑ ነው። ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉም ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተጨማሪ የአጎራባች ከተሞች ነዋሪዎችም ታድመውበታል። በሰልፉ ላይም ህዝቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚቆም በተለያዩ መፈክሮች እና ህብረ-ዜማዎች በመግለፅ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፋቸውን ሲቸር ታይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ህዝባዊ ድጋፉ ለስራቸው ተጨማሪ ጉልበትና አቅም እንደሚፈጥርላቸውና በድጋፉ ሳይታበዩ ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት እንደሚያገለግሉ በመግለፅ ትህትናን በሚያሳይ መልኩ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ለህዝቡ ያላቸውን አክብሮት ሲያሳዩ ተስተውሏል። የጠቅላይ ሚኒስትሩና በጎ የለውጥ ርምጃቸው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትና ፍላጎት ባላቸ አካላትንም ጭምር በማካተት የተደረገ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝቡ ያደረጉት ንግግር እና ያሳዩት ትህትና፤ በታዳሚው ዘንድ የተቸራቸው የአደባባይ አድናቆትና ድጋፍ በኢትዮጵያ ያልተለመደ አዲስ ክስተት ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መስቀል አደባባይ ለህዝቡ ምስጋና እና አክብሮቱን ሲገልፅ
የአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰልፍ በከፊል (ፎቶ፡ ከዕለቱ ማኅበራዊ ገፆች የተወሰደ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ገና 82ኛ ቀናቸው ቢሆንም በየዕለቱ በሚተገብሯቸው ስራዎችና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ላለፉት 27 ዓመታት በርካቶችን ለእስር፥ግድያ፥ ስደትና መከራ የዳረገውን የሚመሩት ኢህአዴግ ድርጅት ተፎካካሪዎችን ሳይቀር ይሁንታ ያገኘ ያልተለመዱ በጎ ርምጃዎች ለድጋፉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የሀገሪቱን መሪነት ከተረከቡ ጀምሮ በተለይ በአዲስ አበባ ፥ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል የታሰሩ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ተደርጓል። በተለይ የርስ በርስ ሽኩቻና ግጭቶችን በይፋ በማውገዝ ከመከፋፈል ና ልዩነት ይልቅ “መደመር” በሚል የሚታወቁበት አብሮነት ቃል ፍቅር፥ ይቅርታ፥ ሰላምና ኢትዮጵያዊ አንድነት ጥሪያቸው የህዝቡን ቀልብ የሳቡ ንግግሮቻቸው ተጠቃሽ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳ ላለፉት 27 ዓመታት ገዥ የነበረው ኢህአዴግ አመራር ሆነው የመጡ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም በነበሩ የገዥው አመራሮች ሲፈፀሙና ሲቀነቀኑ የነበሩና በህዝቡ የተወገዙ ተግባራት፥ የሀገሪቱን እና የህዝቡን አንድነት የሚፈታተኑ እጅግ ለጆሮ የሚቀፉ ቃላቶችና ትርክቶችን ሁሉ በመተው በአዲስ ማንነት ራሳቸውን ሆነው በመምጣት መልካም የሚባሉና በህዝቡ የተወደዱ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎችን ማከናወናቸው ለድጋፉ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በርግጥም ከ3 ወር ላልበለጠ የሥልጣን ጊዜያቸው ይበል የሚያሰኙ በጎ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑ እሙን ነው።
ዶ/ር አብይ ካከናወኗቸው በጎ ሥራዎች መካከል በፖለቲካዊ አመለካከታቸውና ሐሳባቸው፥ በነፃነት በመግለፃቸውን እና መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በአስከፊ እስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች፥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የኢንተርኔት ጦማሪዎች እንዲሁም ገዥውን ሥርዓት ሲያገለግሉ የነበሩና የመንግሥትን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አድሏዊ የሆነ ብልሹ አሰራርን በመቃወማቸው የታሰሩ የጦር መኮንኖች ለዓመታት በግፍ ከሚማቅቁበት ወህኒ ቤቶች ከእስር በነፃ እንዲለቀቁ ማድረጋቸውን እና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ ገደብ የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ማድርብጋቸው በበጎ ጎን ማንሳት ይቻላል። ሌላው ላለፉት 27 ዓመታት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እና በቅርቡ ሥልጣናችውን በለቀቁት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ሲከናወኑ የነበሩ የመብት ጥሰቶችን በማመን እና ድርጊቱን በመኮነን ህዝቡን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ፤ መንግሥት በህዝቡ ላይ የሽብር ተግባር ይፈፅም እንደነበር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመረጃ ናሙና በመግለፅ አረጋግጠዋል። ለዚህም ህዝቡን በድጋሚ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ሌላው በህዝብ ላይ ላለፉት 27 ዓመታት በደል ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ የነበሩ አመራሮችን ከሥልጣን አሰናብተዋል። ለዓመታት በሀገር ውስጥና እንዳይነበቡና እንዳይደመጡ ታፍነው የነበሩ 246 የኢትዮጵያውያን የመረጃ ድረ-ገፆች እና ብሎጎች እንዲለቀቁ እና አማራጭ የመረጫ ምንጭ ሆነው እንዲያገለግሉ አድርገዋል። ከዚህ በፊት የመንግሥትን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ብልሹ አሰራር የሚኮንኑትን በመወንጀል፥ የተሳሳተ መረጃ ለህዝቡ በማሰራጨትና የባለሥልጣናትን ገመና ለመሸፈን ሲውሉ የነበሩ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን አሁን ሙያዊ ስነምግባርን የተከተለ ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ እንዲያሰራጩ አድርገዋል። ላለፉት 18 ዓመታት ሻክሮ የነበረውን እና በኢትዮጵያ ታሪክ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ያለቁበት አስከፊ ደም አፋሳሽ ጦርነት መንስኤ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት አልባ ጦርነት ያሉት የኢትዮጵያና እርትራ ግንኙነት እልባት እንዲያገኝ የወሰዱት የሰላም ርምጃ ህዝቡን ካስደሰቱት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
የአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰልፍ በከፊል (ፎቶ፡ ከዕለቱ ማኅበራዊ ገፆች የተወሰደ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እየወሰዷቸው ካሉ በጎ ርምጃዎች በተጨማሪ የዴሞኬራሲ የሰብዓዊ መብት አጠባብቅ በተግባር እንደሚረጋገጥ፥ በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ማንም ኢትዮጵያዊ አሳዳጅና ተሰዳጅ እንደማኖር፥ የዜጎች እኩልነት፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት፥ በነፃነት የመሰብሰብና የመደራጀት እናንዲሁም ዴሞክራሲ መብቶች እንደሚያረጋገጡ ቃል በመግባት ተግባራዊ ርምጃዎችን መውሰድ በመጀመራቸው ህዝቡን እያስደሰተው እንደሆነ ይስተዋላል። በተቃራኒው ያለፉት 27 ዓመታት ህዝቡን ለመከራ፥ ሀገሪቱን ለከፋ ውድቀት የዳረጉ የገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች ምክንያት የተበሳጨው ህዝብ አገዛዙና ሥርዓቱ እንዲወገድ በተለይም ላለፉት ሶስት ዓመታት በኦሮሚያ፥ በአማራ እና በከፊል በደቡብ ክልል በተነሳው ህዝባዊ ተከታታይ አስገዳጅ ተቃውሞ ምክንያት ከሥልጣን የተወገዱ አካላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ርምጃዎች ደስተኛ ባለመሆናቸው በጎ ርምጃዎቹ “የፓርቲውን ህገ ደንብ የተከተለ አይደለም፥ ሕገ መንግሥቱም እየተጣሰ ነው” በሚል ከሚነሳው ውስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻ እስከ አደባባይ የተቃውሞ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ የተጀመረው በጎ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና እንዳይደናቀፍ በመፈለግ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. “ለውጥን እንደግፍ ፥ ዴሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል የተደረገ ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ነው። በተጨማሪም በጎንደር፥ ደብረ ማርቆስ፥ ደሴ፥ ዱራሜ ከተሞች ተመሳሳይ የድጋፍ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፤ እሁድ ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ ም ደግሞ በድሬዳዋ፥ ሰመራ፥ አሳይታ እና ጅግጅጋ ከተሞች ተመሳሳይ የለውጡና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፎች ተከናውነዋል።
በተለይ የአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተደረገው ህዝባዊ ሰልፉ እጅግ የደመቀ፥ ብዙ ህዝብ የተገኘበት፥ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት እና ፍላጎች ያላቸው አካላት በአንድነት በመሆን የተለያዩ ሐሳቦች የተንፀባረቁበት ልዩ ህዝባዊ ሰልፍ በመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ክስተት ነው። ከዚህ ቀደም ዛሬም ድረስ ሥልጣን ላይ ያለውን እና በምርጫ ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቅደኛ ያልሆነውን ገዥውን ኢህአዴግን በመቃወም እና ተፎካካሪውን ፓርቲ ቅንጅት በመደገፍ የተደረገው የሚያዝያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. ሰልፍ በርካታ ህዝብ የተገኘበት ሆኖ የተመዘገበ ነበር። ይሁን እንጂ ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ ም የተደረገው ሰልፍ ግን በበጎ ፈቃድ ግለሰቦች ተነሳሽነት የተከናወነ፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ህዝብ የተሳተፈበት፥ የትኛውምን የፖለቲካ ፓርቲ ፍላጎት ምክንያት ወይም ተገን ያላደረገ፥ ይልቁንም ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያካተተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን በመደግፍ የተደረገ ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ በመሆኑ በሀገሪቱ ታሪክ ልዩ ሥፍራ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል። በሰልፉ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በዕለቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና ሌሎች ባለሥልጣናትም ተገኝተው ነበር።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለደጋፊዎቻቸው የሰልፉ ታዳሚዎች እንደወትሮ ህዝቡን ያስደመሙና ያስደሰቱ ንግግሮችን አድርገው ጨርሰው በተቀመጡ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ በቅርብ ርቀት የቦንብ ፍንዳታ ተሰማ። የቦንብ ፍንዳታው የተከሰተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሉብት መድረክ በስተቀኝ በአማካይ 40 ሜትር ርቀት አካባቢ እንደሆነ የዓይን እማኞች የገለፁ ሲሆን፤ ድርጊቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራ እንደነበር ታምኗል። በወቅቱም በፍንዳታው አቅራቢያ ሌላ ተጨማሪ ፍንዳታ ሊያከናውኑ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለት ሴቶች ራሳቸውን የአዕምሮ ህሙማን በማስመሰልና ራሳቸውን የጣሉ ሰዎች አለባበስ በመልበስ ተጨማሪ ቦንብ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደሚገኙበት መድረክ ለመወርወር ከቦርሳችው ውስጥ ቦንብ ሲያወጡ ከነፖሊስ የደንብ ልብስና የትጥቅ መያዣ በሰልፉ ታዳሚዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘው እንዳስጣሏችውና ደብድበው ለፖሊስ አሳልፈው እንደሰጧቸው እማኞች በፎቶና ቪዲዮ የታገዘ መረጃ አስደግፈው ይፋ አድርገዋል።
አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የአደጋው ተጠርጣሪዎች የፖሊስ ባልደረባ አካላት ነበሩበት በሚል በህዝቡ የተያዘና ጉዳት የደረሰበት የፖሊስ ተሽከርካሪ (ፎቶ፡ ከዕለቱ ማኅበራዊ ገፆች የተወሰደ)
ከአደጋው ጋር በተያያዘ ከተያዙ ሴቶች በተጨማሪ በተመሳሳይ ቦታና ሰዓት አንድ የፖሊስ ባልደረባ አባል ከመድረኩ በስተጀርባ ባለ ህንፃ ላይ በፍጥነት በመውጣት ተጨማሪ ቦንብ ሊያፈነዳ ሲሞክር አካባቢው ላይ ሰልፉን እንዲያስተባብሩ እና የህንፃውን መግቢያና መውጫ እንዲቆጣጠሩ በተመደቡ የአዲስ አበባ ወጣቶች መያዙ ታውቋል። በኤግዥቢሽን ማዕከል አካባቢ ደግሞ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ በወጣቶች ተይዞ ለሚምለከተው የፖሊስ አካል ተላልፎ መሰጠቱ ተሰምቷል። በሰልፉ በቅርብ ርቀት የነበረና የአንዱ ተጠርጣሪ ፖሊስ ይዞት የነበረው የፖሊስ መኪና ባልታወቁ ሰዎች ወዲያው እንዲቃጠል የተደረገ ሲሆን፤ ከውስጡም የቦንብና ፈንጅ ማስቀመጫ ሳጥን መሰል ሻንጣ በሰልፉ ታዳሚዎች መያዙ ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍንዳታው መድረኩ አቅራቢያ ከመከሰቱ አስቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሰልፉ ከመምጣታቸው በፊት ህዝቡ በብዛት ከሚገኝበት የአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ባለ የሰልፉ መግቢያ በር ላይ ከአንድ ወጣት ጋር የነበረች አንዲት ሴት ተለቅ ባለ የእጅ ቦርሳ ይዛ ያልተለመደ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ጥርጣሬ ባደረባቸው የሰልፉ ታዳሚ ወጣቶች ተይዛ ስትፈተሽ ቦርሳዋ ውስጥ ቦንቦችን የያዘ ሸራ ጋር ይዛ በመገኘቷ አብሯት ከነበረ ወጣት ጋር አንድ ላይ ለፖሊስ ማስረከባቸው ተጠቁሟል።
በዕለቱ ወደ ሰልፉ ስፍራ ለመግባት እንደከዚ ቀደሙ በሁሉም የአደባባዩ መግቢያ እያንዳንዱ ሰው በአማካይ ለሶስት ጊዜ ያህል በተለያየ ርቀት በፖሊስ ተደጋጋሚ ጥብቅ ፍተሻ እንደተደረገ የተገለፀ ሲሆን፤ አደጋውን ያደረሱ አካላት እንዴትና በምን ያንን ተደጋጋሚ ጥብቅ ፍተሻ አልፈው መድረኩ አቅራቢያ እንደተገኙ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል። ከዚህ ቀደም በዛ መድረክ በየዓመቱ መሪዎች በሚገኙበት የተለያዩ ፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ ዝግጅቶች ቢደረጉም፤ በሀገሪቱ ታሪክ ተመሳሳይ አደጋ ተከስቶ አያውቅም ነበር። በዕለቱ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ አደጋ እስካሁን የ2 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 135 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
የቦንብ ጥቃቱን ተከትሎም ከህዝባዊ ሰልፉ ውስጥ እጅ ከፍንጅ የተያዙትን ጨምሮ 6 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም፤ በተሳሳተ ጥቆማ አብሮ ተይዞ ነበር የተባለው ዲያቆን በፅሐ ለ10 ዓመታት በቄራ ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አገልጋይና በአካባቢው ሰዎች በመልካም ስነምግባሩ የሚታወቅ እንደሆነ በመግለፅ በተደረገ ምርመራ የተሳሳተ ጥቆማ መሆኑን በመጥቀስ ፖሊሴ ወዲያው ለቆታል። እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ የተገለፁት ቀሪዎቹ 5 ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ ከጥቃቱ ጋር ንክኪ አላላቸው በሚል እስካሁን 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላችውን የፌደራል ፖሊስ ዋና ኮሚሺነር ዘይኑ ገልፀዋል። ከአደጋው ጋር በተያያዘ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም በፖሊስ እየተፈለጉ እንደሆነም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከህዝባዊ ሰልፉ ጥበቃ ላይ ክፍተት አሳይተዋል በሚል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ 9 የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አቶ አህምድ ሸዴ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል። ዘግይቶ በወጡ መረጃዎች ከአደጋው ጋር በተያያዘ የብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት ምክንትል ኃላፊና የሀገር ውስጥ ጉዳይ የደህንነት ኃላፊም በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በአደጋው ቅንብር እጃቸው አለበት በሚል ሌሎች ተጠርጣሪዎች በተለይም ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ አስከባሪ አካላት በቁጥጥር ስር ሊውሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
በአደጋው ሰለባ ከሆኑ ሰኣላምዊ የሰልፉ ታዳሚዎች በስተቀር ጉዳት የደረሰበት ባለሥልጣን እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል። ከአደጋው የተረፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዕለቱ በቤተመንግሥት መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ከሁለት ሰዓታት ቆይታ በኋላም በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው በጥቅር አንበሳ፥ ዘውዲቱ እና ያቤፅ ሆስፒታል ህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኙ ተጎጂዎችን ሄደው ጎብኝተዋል። በተመሳሳይም እሁድ ሰኔ 17 ቅቀን 2010 ዓ.ም. የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾሙ የአደጋው ሰለባ የሆኑትን በየሆስፒታሉ በመገኘት ጎብኝተዋቸዋል።
አደጋውንም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ፥ በቅርቡ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አበይ አህመድ የተደረገውን የሰላም፥ የይቅርታና እርቅ ጥሪን ተከትሎ ሁለገብ ትግል ያደርግ የነበረውና ማንኛውንም የአመፅ እንቅስቃሴ በይፋ ማቆሙን ያወጀው ተቀናቃኙ አርበኞች ግንቦት 7 እንዲሁም ሰማያዊ ፓርቲን ድርጊቱን ኮንነው አውግዘውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ እና የኢትዮጵያ የሰላም፥ የፍቅር፥ የይቅርታና አንድነት ተስፋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫችው አስታውቅዋል። መንግሥት የአደጋውን ፈፃሚዎችና ተባባሪዎች ተከታትሎ ለህግ እንደሚያቀርብ በመግለፅ ወንጀሉ በማን እና ለምን ዓላማ እንደተቀነባበረ የፖሊስ ምርመራ ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል።
የተፈፀመውን የቦንብ ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሐፊ፥ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዘዳንትና ኮሚሽነር፥ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ቢሮ፤ የጅቡቲ፥ የኬንያ፥ የሶማሊያ እና የኤርትራ መንግሥታት በዕለቱ ድርጊቱን ኮንነው አውግዘዋል።