ታምሩ ጽጌ
ሰኔ 16 ቀን 2010ዓ.ም. መስቀል አደባባይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ላይ ግድያ ለመፈጸም፣ ቦምብ በመወርወር ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል በአምስቱ ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ረቡዕ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጻፈውና ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት ዓርብ መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው፣ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው አምስት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ተከሳሾቹ አቶ ግርማ ቶሎሳ፣ አቶ ብርሃኑ ጃፋር፣ አቶ ጥላሁን ጌታቸው፣ አቶ ባህሩ ቶላና አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ አራቱ ተከሳሾች የወንጀል ሕግ ቁጥር 32(1ሀ) 35 እና 38ን፣ እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በፈጸሙት የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ ከባድና ቀላል አካል ጉዳት ማድረስና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጥቃት ለማድረስ በፈጸሙት ሽብርተኝነት ድርጊት ወንጀል መከሰሳቸውን አስረድቷል፡፡ አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (12) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ የሽብርተኝነት ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ባለማሳወቅ ወንጀል መከሰሱንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ መንግሥት መኖር እንደሌለበት፣ በስመ ሕዝበኝነት የራሳቸውን ዓላማ የሚራምዱ መሆናቸውንና መገደል እንዳለባቸው መዶለታቸውን ያስረዳል፡፡ ጥቃቱ መፈጸም ያለበት ቀድሞ በተደራጀ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ስም በሚንቀሳቀሱና ቦምብ በመወርወር ጥቃት ማድረስ በሚችሉ አባላት መሆን እንዳለበትም፣ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር መመካከራቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኦሮሞ ብሔር ዘንድ የማይፈለጉ መሆኑን ለማሳየት በሚረዳ መንገድ ጥቃቱ መፈጸም እንዳለበት፣ የመኖሪያ አድራሻዋ ኬንያ መሆኑ በተገለጸው ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) አማካይነት ዕቅድ ወጥቶና ስምምነት ላይ ተደርሶ ተልዕኮው መተላለፉንና በዕቅዱ መሠረት ወደ ትግበራ መገባቱን ክሱ ያብራራል፡፡
ሰኔ 16 ቀን 2010ዓ.ም. መስቀል አደባባይ በነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ቦንቡ ከፈነዳ በኋላ
አቶ ጌቱ የተባለው ተከሳሽ ቀኑ ባልታወቀበት ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. ከቶለሺ ታምሩ ጋር በስልክ በመገናኘት፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሠልፍ መካሄድ እንደሌለበት መክረዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መሠረታዊ ለውጥ አለመምጣቱና ሠልፉን የጠራው ኢሕአዴግ መሆኑ እንደሆነ፣ የዓቃቤ ሕግ ክስ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም ኤችአር 128 የተባለውና የአሜሪካ ኮንግረስ ያስተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል የሚልም መሆኑንም ያክላል፡፡ በመሆኑም አቶ ጌቱ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአቶ ብርሃኑ ጃፋር ጋር ሱሉልታ ከተማ በመገናኘት ቦምብ እንዲዘጋጅና የሚወረውር ሰው እንዲያፈላልግ፣ ለሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ጥላሁን ጌታቸው ስልክ በመደወል ተልኮ እንደሰጡት ክሱ ያስረዳል፡፡
ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ብርሃኑ ሁለት ኤፍዋን እና አንድ የጭስ ቦምቦች ያሉት መሆኑን ለአንደኛ ተከሳሽ አቶ ጌቱ ነግሮት ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ሱሉልታ ከተማ በመገናኘት፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በድጋፍ ሠልፉ ቦታ ተገኝተው ጥቃቱን ለመፈጸም ከተስማሙ በኋላ፣ አቶ ብርሃኑ ቦምቡን የሚወረውር ሰው እንዲያዘጋጅ ለአቶ ጌቱ ተልዕኮ እንደሰጠውም በክሱ ተብራርቷል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ አቶ ጌቱ ለሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ጥላሁን ደውሎለት ቦምቡን እንዲወረውርና እንዲያፈነዳ ሲነግረው፣ አቶ ጥላሁንም ለአራተኛ ተከሳሽ አቶ ባህሩ ቶላ ደውሎ በድጋፍ ሠላማዊ ሠልፉ ላይ ቦምብ ለመወርወር ማቀዱን እንደገለጸለትና ለመመካከር በቡራዩ ከተማ በሚገኘው አምስተኛ ተከሳሽ አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ ቤት መገናኘታቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡ አቶ ደሳለኝ ቤት ሲመካከሩ ካደሩ በኋላ አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች ማለትም አቶ ጌቱና አቶ ብርሃኑ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት፣ አቶ ብርሃኑ በሚያሽከረክረው የሰሌዳ ቁጥሩ 02-26235 (አ/አ) በሆነ ተሽከርካሪ ሁለት ኤፍዋን ቦምቦችና አንድ የጭስ ቦምብ ለአቶ ጥላሁን ጌታቸውና ለአቶ ባህሩ ቶላ መስጠታቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሥል ያለበትን ቲሸርት ገዝተው በመልበስና ፍተሻውን በማለፍ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው በመግባት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አድርገው ሲጨርሱ ከመድረኩ በቅርብ ርቀት ላይ ቦምቡን ጥለው ማፈንዳታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
በደረሰው ፍንዳታም ሙሳ ጋዲሳና ዮሴፍ አያሌው የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከ163 በላይ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል፡፡ አንድ ኤፍዋን ቦምብ ግዮን ሆቴል መግቢያ አጠገብ ናኒ ሕንፃ ፊት ለፊት በሚገኘው ትንሹ ስታዲዮም ውስጥ ቢወረውርም ሳይፈነዳ መቅረቱን፣ አራተኛ ተከሳሽ ለአንደኛ ተከሳሽ በስልክ ሪፖርት ማድረጉም በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ተከሳሾቹ በቡድን በመደራጀት በግብረ አበሮቻቸው በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ላይ ጥቃት ለማድረስና ሠልፉን ለመበተን በወረወሩት ቦምብ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋትና አካል በማጉደል የሽብርተኝነት ድርጊት መፈጸማቸውንና ክሱን እንደመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ተረኛ ወንጀል ችሎትም ክሱን ለተከሳሾች በችሎት አንብቦላቸዋል፡፡ ክሱን ካነበበ በኋላ በራሳቸው ጠበቃ ማቆም ስለመቻላቸውና በክሱ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ለመስማትና የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡ ሁለት ተከሳሾችን በቤቱ ያሳደረው አምስተኛ ተከሳሽ አቶ ደሳለኝ የተከሰሰበት አንቀጽ ዋስትና እንደማይከለክል ተናግሮ የዋስትና መብቱ እንዲከበር ቢጠይቅም፣ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ዘገባው የሪፖርተር ነው።