በጎንደር የ17 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን መንግሥት ሲያምን፤ አንዱን የገደልኩት እኔ ነኝ ብሏል
በጎንደር ህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በእስር ቤት ላይ በደረሰ ቃጠሎ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተነገረ፡፡ መንግሥት ከቃጠሎው ወቅት አንድ ሰው መግደሉን ሲያምን ሌሎቹ 16 ሰዎች ህይወት የጠፋው በቃጠሎው ወቅት ከ እስር ቤቱ ለማምለጥ ሲጋፉ ነው ብሏል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ለመንግስት ሚድያ በሰጠው መግለጫው በህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ወህኒ ቤት ከቀኑ 7፡30 ሰዓት አካባቢ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ እስረኞች ከቃጠሎው ለመውጣት በተደረገው ግፊያ የ16 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ሊያመልጥ ሲል ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መገደሉን አምኗል፡፡

እንደ ዓይን እማኞች ከሆነ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር ከ42 በላይ እንደሚሆን እና መንግሥት ቁጥሩን ዝቅ በማድረግ በእጁ የጠፉትን ቁጥር ወደ አንድ ብቻ ማሳነሱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለፃ ከሆነ በቃጠሎው ወቅት መንግሥት በእስረኞች ላይ ጠከታታይ ተኩስ ከፍቶ እንደነበርና የእስረኞችንም ህይወት ለማትረፍ ማንም ወደ አቅራቢያው እንዳይጠጋ የጥብቃ ኃይሎች እና ፖሊሶች ማንም የውጭ ሰው እንዳይጠጋ ሲያስፈራሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ከሞቱት መካከል አብዛኛው በመንግሥት እጅ የተገደሉ እንጂ ከእስር ቤት ከእሳት ለማምለጥና ለመውጣት ሲጋፉ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪ በቃጠሎው በርካታ እስረኞች ጉዳት እንደደረሰባቸውና በጎንደር ሆስፒታል የህክምና እርዳታም እየተደረገላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ የቃጠሎውን መንስኤና የተጎዱትንም ሆነ የሞቱን በተመለከተ እስካሁን በገለልተኛ አካል የተጣራ ነገር አለመኖሩ ታውቋል፡፡
በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ከቃጠሎው በፊት ባሉት ቀናት የቅማንት ማኀረሰብ ባነሱት የመብት ጥያቄ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ እስካሁን በገለልተኛ አካልም ሆነ በመንግሥት ተጣርቶ ይፋ ባይደርግም በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና የተወሰኑትም ምስሎቻቸውም በማኀበራዊ ሚዲያ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
የወህኒ ቤቱ ኃላፊ በቃጠሎውም ሆነ በመንግሥት ኃይሎች እርምጃ የሞተ ሰው የለም በሚል ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ 16ቱ በቃጠሎው ወቅት በተፈጠረ መገፋፋት ሲሞቱ አንዱ ግን ሊያመልጥ ሲል በወህኒ ቤቱ ጥበቃ አባላት መገደሉን በማመን እስካሁን 17 ሰዎች መሞታቸውን አምነዋል፡፡ በተለይ በዞኑ ሰሜን ጎንደር መንግሥት በህዝቡ ላይ እየወሰደ ስላለው የኃይል እርምጃ እና በጎንደር ወህኒ ቤት በቃጠሎው እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር መደበቅና መቀነስ የተበሳጩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በተለይ ማራኪ እየተባለ በሚጠራው ግቢ የተማሪዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተሰምቷል፡፡ በአሁን ወቅትም ተቃውሞው ወደሌሎች የዩኒቨርስቲው ግቢ እና ወደ ሌሎች የክልሉ ተቋማት ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት ዩኒቨርስቲው በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ተከቦ ጥብቅ ቁጥር እየተደረገበት መሆኑንም የአዲስ ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የዞን 9 ብሎገሮች የ2015 የዓመቱን የፕሬስ ነፃነት ሽልማት ተቀበሉ
በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ዋና ቢሮውን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Committee to Protect Journalists) በዘንድሮው የ2015 የዓመቱ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 ብሎገሮች ሽልማት ተቀበሉ፡፡ በስፍራው ማክሰኞ ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ምሽት የዞን 9 አባላት መካከል እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል እና ሶሊያና ሽመልስ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡

ሀገር ቤት የሚገኙት ቀሪዎቹ የዞን 9 አባለት ከአንድ ዓመት እስር ቆይታ በኋላ ቢለቀቁም ከሀገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውና የጉዞ ሰነድ የተነጠቁም እንዳሉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሬስ ነፃነት በሀገሪቱ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅዕ ሲፒጄን ጨምሮ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም አቀፍ ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በዕለቱ በእንግድነት የተገኘችው በቅርቡ የተፈረደባትን እስር አጠናቃ ከእስር የወጣችው ርዕዮት ዓለሙ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል፡፡ በያዝነው ዓመት የሲፒጄ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 በተጨማሪ ሶሪያዊ እና ማሌዥያዊ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስቶችም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ ከ አምስት ዓመት በፊት የቀድሞው የአውራምባ ታየምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ሲፒጄ ዓለም አቀፍ የሃዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኞች ላይ የሚወስደውን አፈና አጥብቆ በመኮነን ይታወቃል፡፡
አዲሱ ማስተር ፕላን አሁንም ተቃውሞ ቀስቅሷል
አዲስ አበባን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚል በመንግሥት ይፋ ባደረገው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከትናንት ጀምሮ በድጋሚ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

በተለይ በምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ጊኒጪ እና ምዕራብ ወለጋ ተቃውሞው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በተቃውሞው ከተሰለፉት መካከል በመንግሥት በተወሰደ ርምጃ በምዕራብ ሸዋ ድሬ ኢንጪኒ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ተቃውሞን የቀሰቀሰው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ያከተተ በመሆኑ እና የዞኑን እና የክልሉን ጥቅም እንዲሁም ገበሬዎችን ያለምንም በቂ ካሳና ቦታ በማፈናቀል ለጎዳና ህይወት ይዳርጋል የሚሉ ሐሳቦች እንደሚገኙበት የተጠቆሙ ሲሆን፤ ይህንን ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነው ከኦህዴድ አመራር አባላት ከመፅደቁ ውጭ ወደ ህዝብ ያልወረደና ለምክክርም እንዳልቀረበ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የዚህ ማስተር ፕላን ተቋውሞው በ2006 ዓ.ም. በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ በርካታ ተማሪዎች እና የተቃውሞ ታዳሚዎች ግድያ ከቆመ በኋላ ድጋሚ ማገርሸቱ ተሰምቷል፡፡

በአንዳንድ ከተሞች የመኪና መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፤ በተቃውሞው የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም መካተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ምንም የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ አስተያየት የለም፡፡
እነ ሀብታሙ አያሌው ለጥቅምት 22 ተቀጠሩ
᎐ማረሚያ ቤት እነ ሀብታሙን አላቀረባቸውም

የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው የአንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት አምስት ተከሳሾች ለጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ማረሚያ ቤት ሳያቀርባቸው በሌሉበት ቀጠሮ የተሰጣቸው የፓርቲዎች አመራሮቹ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና አብሯቸው ይግባኝ የተጠየቀበት አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡
የቂሊንጦ እና የቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች እነ ሀብታሙን ፍርድ ቤት ያላቀረቡበትን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ሲጠይቅ፣ “ቃሊቲ በፕላዝማ ይታያል ስለተባለ አላመጣናቸውም፤ ከአይ.ሲ.ቲ ጋር ተነጋግረው ነው ያስቀሯቸው” የሚል መልስ ተሰጥቷል፡፡ ማረሚያ ቤቱ እነ ሀብታሙን ብቻ ሳይሆን በሌላ መዝገብ በተለያዩ ወንጀሎች ስር የተጠቀሱ ተከሳሾችንም አለማቅረቡ ታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የቃሊቲ ማረሚያ ቤትን መልስ ካደመጠ በኋላ፣ “ይሄ ቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚባል ነገር የሚሆን አይደለም፤ አቅርቧቸው ብለን አዝዘን ነበር፤ እኛ ነን የምናዝዛችሁ ወይስ ማን ነው? አሁንም ቀጣይ ቀጠሮ ላይ አቅርቧቸው” ሲል በእነ ሀብታሙ መዝገብም በሌሎች መዝገቦችም ላይ ዛሬ ላልቀረቡ ተከሳሾች ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም እነ ሀብታሙ አያሌው ሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም የተጠየቀባቸው ይግባኝ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ብይን ቀርበው ለመስማት ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ድርቅና ርሃብ ትናንት እና ዛሬ
ብስራት ወልደሚካኤል
በርግጥ ድርቅ በተፈጥሮ ሊከሰት የሚችል የአየር መዛባት አደጋ ውጤት ነው፡፡ ድርቅ ባለፀጋም ሆነ እንደኛ ባሉ ደሃ ሀገራት ሊከሰት ይችላል፡፡ የድርቁ መንስኤም ተፈጥሯዊ አሊያም ሰው ሰራሽ ሊሆን ይችላል፡፡
ርሃብ በምግብ እጥረት የሚከሰት ሲሆን፤ መንስዔውም የምርት አቅርቦት ማነስ አሊያም የምግብ ፍላጎት ከምርት አቅርቦት ጋር አለመጣጣም ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ፍላጎት እና አቅርቦትን አሊያም የሀገር ምርት ለማሳደግ ሀገሪቱ የምትከተለው ፖሊሲ ትግበራ ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያም በተለያዩ መንግሥታትም ሆነ ዘመን ድርግቅን ተከትሎም ይሁን ያለድርቅ ለተከሰቱት እና እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ዋነኛ መንስዔው ፖለቲካዊ የፖሊሲ ትግበራ ውጤት ነው፡፡
ርሃብ በተፈጥሮ የሚከሰት ሳይሆን የሀገሪቱ መንግሥት ስርዓት በሚከተለው የፖሊሲ ንድፍና ትግበራ ውጤት ነው፡፡ ደካማ ወይም ተፈጥሮንና የሀገሪቱን ህዝብ አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ፖሊሲ ትግበራ ባለበት ሀገር ድርቅ ከተከሰተ ምንጊዜም ርሃብ አለ፡፡ ርሃቡ ምንም እንኳ ድርቅን ተከትሎ የመጣ ቢሆንም ዋነኛ ምክንያቱ ግን የፖሊሲ ንድፍና ትግበራ ውጤት ነው፡፡
በሀገራችን በተከታታይ የተከሰተውም ርሃብ ዋነኛ ምክንያት ድርቁ ሳይሆን የደካማ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም ድርቅ የተከሰተባቸው ሀገሮች ሁሉ ርሃብ አይከሰትም፡፡ ደካማ ፖሊሲ ያለባቸው ሀገሮች ግን ድርቅ ካለ ምንም ጊዜም ርሃብ አለና፡፡
በዘመናዊ ኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ጎልቶ መታወቅ የጀመረው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን ቢሆንም እስከዛሬም ይህን ችግር የሚቀርፍ የመንግሥት ፖሊሲና ተግባር አልታየም፡፡ አሳዛኙ ነገር በዘመነ ዳግማዊ ምኒልክ የነበረውን ርሃብ ለዓለም ማኀበረሰብ አሳውቆ ተገቢውን ርዳታ ይቆ ለተጎጂዎች በማድረስ ህይወት ለማትረፍ ቴክኖሎጂው ችግር ነበረብን፡፡ ቢሆንም ግን ይህን ክፍተት ንጉሱን ጨምሮ ባለሟሎቹ (አመራሮቹ) የተፈጠረውን ርሃብ በድርቅ ላይ ሳያመሃኙ ወዲያው ለህዝቡ በማሳወቅ ወገን ለወገን በሚችለው አቅም እንዲረዳዳ እና የመንግሥት ካዝና (ለችግር ጊዜ የተቀመጠ የእህል ጎተራ) ሳይቀር በይፋ ተከፍቶ ለተጎጂዎች ወዲያው እንዲደርስ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ይህ በጎ አስተሳሰብ ቢሆንም ከነበረው የእህል ክምችት አናሳነት እና የትራንስፖርት ችግር አኳያ ለሁሉም ተጎጂ እኩል ማድረስ ባይቻልም መንግሥት ችግሩን አምኖ የህዝቡን ድጋፍ ጤቆ ተገቢውን ምላሽ አግኝቶ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ወገኖቻችንን በርሃቡ አጥተናል፡፡
በዘመነ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበረው በ1965/66 ዓ.ም. ርሃብ ግን ንጉሱም ህዝቡም እንዳያውቁ መኳንንቱ ለመሸፋፈን ሞክረዋል፡፡ በዚህም መኳንንቱ ጠግበው እየበሉ በርካታ ወገኖቻችን በወቅቱ በተከሰተው ርሃብ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይሄ በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍለክ እጅግ የከፋ የታሪክ ጠባስም ጥሎልን አልፏል፡፡
በዘመነ ደርግ በተለይ በ1977 ዓ.ም. የተከሰተውን ልብ ይሏል፡ የተከሰተውን ርሃብ የሀገሪቱ መራሄ መንግሥት መንግሥቱ ኃይለማርያምና ሁሉም ሹማምንት ቢያውቁም ከሀገሪቱ ህዝብ (ርሃብ ካልነካቸውን) እና ከዓለሙ ማኀበረሰብ ለመደበቅ ተሞክሯል፡፡ በዚህም ብዙ ወገኖቻችን በጊዜ ማዳን ሲቻል በሞት ተነጥቀናል፤የበለጠ ክብራችንም እንዲዋረድ በር ከፍቷል፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ ከአንዴም ሶሰት ጊዜ፤በተለይ በ1985ዓ.ም.፣ 1986/87 ዓ.ም. እና የአሁኑን የ 2007/08 ዓ.ም. ርሃብ መንግሥት ከሀገሬው ህዝብና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ለመደበቅ ሞክሯል፤ባይችልም፡፡ በቅርቡ በተለይም ባለፈው ክረምት በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተጀመረው ርሃብ ወደ ሰሜኑ እና መካከለኛው የሀገራችን ክፍል በፍጥነት ቢዛመትም መንግሥት በምግብ ራሳችንን ችለናል፣ ርሃብ አልተከሰተብ፣ …ወዘተ የሚለው ፈሊጥ አንድ ወር እንኳ አልሞላውም፡፡ ርሃቡ ልክ እንደሰደድ እሳት እና አውሎ ነፋስ ማዕበል ምስራቁን፣ ሰሜኑን እና ከፊል መሐከለኛ የሀገራችን አካባቢ በፍጥነት ተዛመተ፡፡ ርሃብ የለም፣ በምግብ ራሳችንን ችለኛል፣…የክፉዎች ወሬ ነው ሲባል የነበረው ርሃብ፤ አሁን መንግሥት በህዝብ ላይ እና በእንሰሳቶቻቸው ላይ ከፍተኛ እልቂ ከደረሰ በኋላ “ኢሊኖ በሚባለው ድርቅን ተከትሎ በነሳው ርሃብ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 5 ሚሊዮን አካባቢ ደርሷል፣ ከዓለም አቀፉ ለጋሽ ድርጅቶች እና ሀገራት አፋጣኝ እና በቂ ድጋፍ አላገኘንም,…” የሚል ይፋ ልመናዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡ የተራቡ ወገኖቻንን ቁጥር መገመትና መናገር ቢከብድም አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ግን ከ 10 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ሁሉም ስርዓቶች በተፈጥሮ ሃብትና በግብርና ላይ ያላቸው ፖሊሲ የአንዳቸው ከአንዳቸው የማይሻል፣ ያልተለየ ቢሆንም በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ግን ርሃብ ለመደበቅ አልተሞከረም፤ ይልቁንም ከመንግሥት ካዝና በተጨማሪ ህዝቡ እንዲረዳዳ የጠማፅኞ ጥሪ ተደረገ እንጂ፡፡ በኃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን ሹማምንቱ ከንጉሱ እና ርሃብ ካልደረሰበት ህዝብ ለመደበቅ ቢሞከርም መደበቁ አልቻሉም፡፡ የደርግና ኢህአዴግ ስርዓት ክፋት ግን ከበታች ሹም እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ ርሃቡን እያወቁ ለመደበቅ መሞከራቸው የፖሊሲ ችግራቸውን ለመደበቅ ከመሞከራቸው ይልቅ በሰብዓዊ ፍጡር ህይወት ላይ ያላቸውን ጭካኔ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ርሃብ ቀን አይሰጥምና፡፡ ርሃብ የሰውንም ሆነ የእንሰሳትን ህይወት ሲቀጥፍ ዳግም አናገኛቸውምና፡፡
አሁን ርሃቡ በዋነኛነት የተከሰተው ውሃ ቅዳ ውሃ መለስ የሆነው የመንግሥት ስርዓትና በመሪዎች ቸልተኝነት፤ የተፈጥሮ ሃብት፣ የመሬት፣ ስነ ህዝብ፣የምግብ እና የመረጃ ጥንቅር ፖሊሲ ችግር ነው፡፡ ባለፈው ከነበረው ችግር ለነገው አለመማራችን እና ለመማር አለመዘጋጀታችን ውጤትም ነው፡፡ ስለዚህ ርሃብን እና የተራበውን ህዝብ ቁጥር በመደበቅና በማዛበት ርሃብን ማቆም እንደማይቻል ልናውቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ በርሃብ የተጎዱ ወገኖቻችንን በተመለከተ የውጭ መንዛሪ እጠረት ለመሸፈን ባለመ የውጭ ለጋሽ ሀገሮችን ተማፅኞ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ወገኖቻችንን እንዲረዳዳ ዕድሉ ሊሰጥና በይፋ የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማሰባሰብ ስራ በማድረግ የወገኖቻችንን ህይወት መታደግ ይቻላል፡፡ ለዚህም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ ርሃብ ጊዜ አይሰጥምና፡፡
ከፖሊሲ ችግር አንዱ ከዝናብ ጥገኝነት ለመውጣት የሚያስችል መስኖ አለማስፋፋት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሜትሪዮሎጂ ተቋም ብቃት ባላቸው የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አለመዋቀር እና አለመጠናከር፣ መስኖ በሌለባቸውና ዓመታዊ የዝናብ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ቆላማ አካባቢዎች የተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ እንዲሁም በቂ የእንሰሳትና የሰው ህክምና እና የምግብ ቅድመ ዝግጅት ክምችት አለማድረግን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከአስቸኳይ ርስበርስ የመረዳዳት እና ዓለም አቀፍ ድጋፍ ጥየቃ እንቅስቃሴው እንዳለ ሆኖ፤ ለ24 ዓመታት ተሰርቶበት ለውጥ ያላመጣውን ፖሊሲም ማሻሻል አሊያም መቀየር ዋነኛው ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት፡፡ አለበሊያ በኢህአዴግ ዘመን ለ4ኛ እና 5ኛ ጊዜ መከሰቱ እንደማይቀር የአሁኑን ጨምሮ ያለፉት ጊዜያት ከበቂ በላይ አስተማሪዎች ናቸውና ከፖለቲካ ጋጋታ ትርፍ ይልቅ ሕይወት የማዳኑ ተግባር ሊፈጥን ይገባዋል፡፡

