ፍርድ ቤቱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ላይ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮዎችን ሰጠ
∙ለጥር 7 እና ለጥር 26/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡
ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ የስድስት ተከሳሾችን ሁለት ጉዳዮች ለማየት ነበር ችሎቱ የተሰየመው፡፡
አንደኛው ጉዳይ ተከሳሾቹ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ተከትሎ ማረሚያ ቤቱ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የሰጠውን ትዕዛዝ በተመለከተ መልስ ለመስማት ነበር፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርበው ስለነበር በክስ መቃወሚያቸው ላይ አቃቤ ህግ የሚሰጠው የመቃወሚያ መቃወሚያ ካለ ለመስማት ነበር፡፡
በመሆኑም አንደኛው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ በወረቀት ተገልብጦ ስላልደረሰ ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግን የተከሳሾች መቃወሚያ ላይ የቀረበ መቃወሚያን ተቀብሏል፡፡ በመሆኑም በተከሳሽ መቃወሚያ ላይ የቀረበውን የፌደራል አቃቤ ህግ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ
24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን ባህር ሰጥመው ሞቱ
ባለፈው ሰኞ ታህሣሥ 20 ቀን 2007 ኣ.ም. በጀልባ ወደ የመን ሊገቡ የሞከሩ 24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቻ በምትባል የየመን ወደብ ከተማ አቅራቢያ በደረሰባቸው የጀልባ መስጠም አደጋ መሞታቸውን የየመን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለፃ ከሆነ በጀልቧ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ በህይወት የተረፉ ስለመኖራቸውም ሆነ በአደጋው የሞቱትን በለመለየት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተደረገ ጥረት አለመኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በቅርቡ ህዳር 28 ቅን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ በየመን የወደብ ከተማ በሆነችው ሞቻ አቅራቢያ 70 ኢትዮጵያውያን በሚጓዙበት ጀልባ በደረሰ አደጋ ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ባህር አቋርጠው የምን ሊገቡ ሲሉ ህይወታቸው ላለፈው 94 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በአቅራቢያው ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንፅላ ፅህፈት ቤት አምባሳደሮች ያሉት ነገር የለም፡፡ በየ ዓመቱ የህንድ ውቅያኖስን እና ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው ወደ የመን ሊገቡ የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እየሞቱ ቢሆንም አደጋውን ለመቀነስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመንን ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር ለመሸጋገር የሚጠቀሙባት በመሆኑ የስተኞች ጣቢያ እንደማይመዘገቡና እገዛም እንደማይደረግላቸው ተጠቁሟል፡፡ የመን ባህር አቋርጠው ከሚገቡ አብዛኞቹ ስደተኞች መካከል ጥቂቶች ብቻ በተለይም በፈረንጆቹ 2014 መጨረሻ የመን በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን እገዛ የተደረገላቸው 9,500 ኢትዮጵያውን እነደነበሩ የድርጅቱ መረጃ አመልክቷል፡፡
ከመንግስት በሚደርስባቸው የፖለቲካ ጫና እና በሀገሪቱ ከተከሰተው የኢኮኖሚ ችግር በተፈጠረው የኑሮ ውድነት የተነሳ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር በየ ዓመት እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ስራቸውን ለመቀጠል የሚያስችል ውል መጨረሻው የሚወሰነው በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሲፀድቅ እንደሆነ ገለፁ
ታዋቂውና ስመ ጥር የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በመንግስት መደበኛው በስራ በቆያ ዕድሜያቸው በመጠናቀቁ ስራቸውን በሚታደስ ውል ስራቸውን እንዲቀጥሉ የትምህርት ክፍሉ ፈቃደኝነታቸውን በጠየቀው መሰረት ውል ፈርመው በስራ ገበታቸው ላይ እንደሆኑ አስታወቁ፡፡
ዶ/ር መረራ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ እንደገለፁት ከሆነ፤ በዩኒቨርስቲው በማስተማርና በምርምር ከ25 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉና አሁን ዕድሜያቸው 60 ዓመት ስለሞላቸው የጡረታ ጊዜያቸው በመሆኑ፤ በእሳቸውና በዩኒቨርስቲው መካከል በሚታደስ አዲስ የኮንትራት ውል ስምምነት መሰረት ስራቸውን ለመቀጠል ከዚህ ቀደም ከሚያስተምሩበት ትምህርት ክፍል እና ከዩኒቨርስቲው ማኀበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር መፈራረማቸውን እና ስራቸውንም መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው በኮንትራት መልክ የሚታደሰው አዲሱ የውል ስምምነት ሊፀና የሚችለው በእሳቸውና በትምህርት ክፍሉ ስራውን ለመቀጠል የሚያስችል ፈቃደኝነት ስምምነት በዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኩል ሲፀድቅ መሆኑንም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡
አዲስ ሚዲያም በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዶ/ር መረራ ከሚሰሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባረሩ የሚል ዜና ተሰምቷልና እውነት ነው ወይ ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ እስካሁን የደረሰኝ መረጃ የለም፣ መደበኛ ስራዬን እየሰራሁ ነው፣ ነገር ግን አንዳንድ ወሬ እኔም እሰማለሁ እንጂ እሳካሁን የደረሰኝም የእግድ ደብዳቤም ሆነ መሸኛ የለም፣ አዲስ ነገር ካለ ወደፊት አብረን የምንሰማው ነው ሚሆነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዶ/ር መረራ ስራ ጋር በተያያዘ ስለተወራው ነገር ለማጣራትና ምላሽ ለማግኘት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ክፍል ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የኦፌኮ ሊቀመንበርና በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያዊውን የገደለው ቻይናዊ “ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት” ሲባል ክሱ እንዲቋረጥ ተደረገ
በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ውስጥ ኢትዮጵያዊውን የገደለው ዠንግ ቢንዥንግ የተባለ ቻይናዊ ‹‹በቸልተኝነት ሰው በመግደል›› ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የነበር ቢሆንም ‹‹ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት›› በሚል ትዕዛዝ ክሱ መቋረጡን ከክልሉ ፍትህ ቢሮ የተገኘው ሰነድ አጋለጠ፡፡
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለአቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተከሳሹ ካሳ ከፍሎ መውጣቱ ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት እንደሚበጅ በጻፈው ደብዳቤ ክሱ እንዲቋረጥ መደረጉን ‹‹በአማራ ፍትህ ቢሮ የምዕራብ ጎጃም ዞን የፍትሕ መምሪያ የወንጀል መዛግብት መርምሮ መወሰንና ተከራክሮ ማስወሰን የስራ ሂደት›› ለሰሜን አቸፈር ፖሊስ ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ተመልክቷል፡፡ በትዕዛዙ መሰረትም ክሱ ቀሪ ሆኖ የምርመራ መዝገቡ ተመላሽ መደረጉን በደብዳቤው ላይ መገለፁን ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
በ2004 ኣ.ም. በአርሲ በቻይና ኩባን ተቀጥረው የሚሰሩ ዘጎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በቻይኖች ተፈፅሞባቸው አቤቱታ ቢያቀርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ተበዳዮቹንና አቤቱታ አቅራቢዎቹን ለመግደልና ለማሰር በመሞከሩ የሰራተኛ ማኀበሩ አመራሮች ሀገር ጥለው መሰደዳቸው አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች የጦር ሄሊኮፕተር ይዘው ስርዓቱን መክዳታቸውን መንግሥት አመነ
ባለፈው አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከድሬዳዋ የአየር ኃይል ምድብ የጦር ልምምድ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ የአየር ኃይል አብራሪዎች እና አንድ መካኒክ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት በመክዳት ኤም አይ-35 የሆኑ ሁለት ዘመናዊ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ይዘው ኤርትራ መግባታቸው ተረጋገጠ፡፡ ይሄንንም የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ታህሣሥ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ማመኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ አብሪዎቹ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ እና የሄሊኮፕተሩ ቴክኒሻን ፀጋብርሃን ግደይ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
አብራሪዎቹ ይዘዋቸው የጠፉት የጦር ሄሊኮፕተሮች የአንዱ ዋጋ 36 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ሲሆን፤በኢትዮጵ ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ እንደ ኢሳት ዘገባ ከሆነ የአርብ ዕለቱን ጨምሮ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ 11 የመከላከያ ሚኒስቴር የአየር ኃይል አብራሪዎችና ባለሟሎች ከድተው ስርዓቱን በኃይል ለመጣል ወደ ሚታገሉ ታጣቂዎች መቀላቀላቸው ተጠቁሟል፡፡