አቶ ፈቃደ ሸዋቀና አረፉ
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስነ ምድራዊ ጤና መምህር የነበሩት አቶ ፈቃደ ሽዋቀና ባጋጠማቸው የጤና ችግር ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በስደት ይኖሩ ከነበረበት አሜሪካ ህይወታቸው አልፏል።
አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ህወሓት/ኢህአዴግ ግንቦት 1983 ዓ ም አዲስ አበባ ገብቶ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ወዲያ 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን በሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜና ትዕዛዝ ከተባአረሩ አንዱ ነበሩ።
አቶ ሸዋቀና ከስራቸው እንዲባአረሩ ከተደረጉ ብሏላ ወደ አሜሪካ በመሰደድ በሙያቸው የአንድ SCG ኩባንያ የስነምድር ጤና ተንታኝ በመሆን ለ25 ዓመታት አገልግለዋል። ከሙያቸው በተጨማሪ በይበልጥ በተለያዩ ፅንፍና ጠርዝ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ መሐል ለማምጣት ባደረጉት የአስታራቂነት ሚና እና ጥረት በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እምነትና ከበሬታን ማግኘት የቻሉ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
የቀብር ስነ ስርዓታቸውም በስደት ዓለም በቆዩባት አሜሪካ እንደሚፈፀም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የመድረክ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ተለቀቁ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የቀድሞው የኦሮሞ ፌደራሊስት ንቅናቄ፣ የአሁኑ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ/መድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ከነሐሴ 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ከቆዩ በኋላ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለቀዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ መንግሥት በዜጎች ላይ በፈፀማቸውና እየፈፀማቸው ባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ከአምንስቲ ኢንተርናል ጋር ቃለ መጠይቅ ካደረጉ በኋላ የኦነግ አባል ናቸው በሚል በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት 8 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተከላካይ ጠበቆቻቸውና አቶ በቀለ የታሰሩት ያለምንም ወንጀል እንደሆነ፣መንግሥት የኦነግ አባል ብሎ የመሰረተባቸው ክስ እንደማይመለከታቸው፣ እሳቸው በወቅቱ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለው የኦፌዲን/መድረክ አመራር መሆናቸውን በማስረጃ ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው በመቅረቱ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
እነ አቶ በቀለ ገርባ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ካሉ በኋላ የ8 ዓመቱ ፅኑ እስራት ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር የተቀነሰ ሲሆን፤ ይሄንንም ይግባኝ ብለው ወደ ፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢሄዱም የ3 ዓመት ከ7 ወር ፍርድ በመፅናቱ በእስር ቆይተዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ በህጉ መሰረት በአመክሮ ከእስር መፈታት የነበረባቸው ከአንድ ዓመት በፊት ጥር 2006 ዓ.ም. ቢሆንም፤ ዝዋይ የሚገኘውም ሆነ አቃቂ ቂሊንጦ የሚገኘው ወህኒ ቤት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው 4ኛ ዓመት ድረስ በእስር ሊቆዩ ችለዋል፡፡ መረጃዎች እንደጠቆሙት ከሆነ አቶ በቀለ ገርባ የተለቀቁት ከነበሩበት እስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ሐና ጋር እየተጓዙ ከእስር ቤቱ ብዙም ሳይርቁ፤ በወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች ቆይ ሌላ የሚጣራ ጉዳይ አለ በሚል ተመልሰው እስር ቤት ካስገቧቸው በኋላ በጭለማ ሞጆ ከተማ አካባቢ ተወስደው መለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ በቀለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከማስተማራቸው በተጨማሪ የዶክተሬት ዲግሪ ማጠናቀቂያቸው ላይ መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁን ወቅት የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ ኦልባና ሊሊሳን፣ የአድነት ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስንክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
“ተወይኖብኛል… በዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ተልዕኮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባርሬአለሁ”
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሦስት አሥርት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሚሌኒየሙ መባቻ ወደ አገራቸው ተመልሰው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማስተማር ሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡ ምሁሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ቢኾኑም በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም አስተምረዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በተለያየ ጊዜ ሲያስተምሩ ቢቆዩም ከጠየቁት የዓመት ዕረፍት (sabbatical leave) ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርስቲው መሰናበታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በእርስዎ መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ጋር በኹለት ጥያቄዎች ዙሪያ የማይታረቅ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግና የቅጥር ውሌ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው÷ አንድ መምህር ለስድስት ዓመት በተከታታይ ከአስተማረ፣ ለአገለገለበት ዘመን የአንድ ዓመት የጥናትና ምርምር ዕረፍት (sabbatical leave) እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡ ኾኖም ግን ዩኒቨርስቲው ‹‹የጡረታ ሥርዓተ – ሒደቱን አላሟላኽም›› በሚል በሕጉ ፊት የማይጸና ሰበብ ፈጥረው ይገባኻል ብለው ከፈቀዱልኝ በኋላ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ለማንኛውም መምህር ሥርዓተ ሒደቱን የማስፈጸም ሓላፊነት የሰው ሀብት አስተዳደሩ ድርሻ ኾኖ ሳለ፣ እኔን ተጠያቂ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሟል::
በነገራችን ላይ የጥናት ዕረፍት ፈቃዴን የጠየቅኹት ከሦስት ዓመት በፊት፣ ስድሳ ዓመት ሳይሞላኝ ነበር፡፡ በየሰበቡ ሲጓተት ስለቆየ ወደ ስድሳ ዓመቱ ገደብ ደረስኹ፡፡ ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ከመሔዱ አስቀድሞ ውስጣዊ ተቋማዊ መፍትሔ ለማበጀት ወደ ዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ቀርቦ ምላሽ ስጠባበቅ ከሦስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡
የሥራ ውሌን በተመለከተ፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የእኔን የአገልግሎት ቆይታ እንደሚፈልግና በተለይም በቅርቡ ለሚጀምረው የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተሳትፎዬ እንደሚጠቅም በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ በመወሰኑ ውሌ እንዲራዘም ለማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኮሚሽን ጽፎልኝ ነበር፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሓላፊዎች በተሰበሰቡበት፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ ከተወያየበት በኋላ የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉን ጥያቄ ዳግመኛ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶበት፣ ውሳኔው በማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ በፕ/ር ወልደ አምላክ በዕውቀት በኩል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይኹንታቸውን እንዲሰጡበት(እንዲያጸድቁት) ተጠይቆ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ከአራት ወራት ያኽል ቸልተኝነት በኋላ ‹‹ወረቀቱ ይመጣለታል›› በሚል ለተከታዩ ሴሚስተር እንዳልደለደል በአዲሱ ዲን በኩል ለትምህርት ክፍሉ ሊቀ መንበር መመሪያ አስተላለፉ፡፡ መመሪያው የእኔን መሰል ጥያቄ ባቀረቡ ሌሎች መምህራን ላይም የተላለፈ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በላይ ደመወዜን ይዘው መክፈል ከአቆሙ በኋላ ‹‹ለሚመጣው ሴሚስተር አትመድቡት›› ማለት በአካዳሚያ ቋንቋ ግለሰቡ ተሰናብቷል ማለት ነው፡፡
በመሠረቱ፣ የትምህርት ክፍሌና አካዳሚክ ኮሚሽኑ የሥራ ውሌን መራዘም ተስማምተው ላቀረቡት ጥያቄ ሲኾን እንደወጉ ማጽደቅ አልያም በአስቸኳይ ውሳኔን ማሳወቅ ሲገባ፣ ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ወራት በላይ ማቆየታቸው ኢ-ሕጋዊ ነው፤ ሕጉን ጠብቆ በወጉ ለቀረበ ጥያቄ ከሦስት ወራት በላይ ምላሽ አለመስጠት እብሪት፣ ትዕቢትና ማናለብኝነት እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም፤ በተመሳሳይ ወቅት አንድ ዐይነት ጥያቄ በደብዳቤ ከአቀረብነው መምህራን መካከል፣ ለምሳሌ ከኛው ትምህርት ክፍል ዶ/ር በቀለ ጉተማ በሥራው እንዲቀጥል በቃል ትእዛዝ ፈቅደው፣ ለእኔ በአግባቡ ውሳኔ ሳይሰጡ ‹በሚቀጥለው ሴሚስተር እንዳትመድቡት’ ማለት የአድልዎ አቀራረብ ብቻ ሳይኾን በዘፈቀደና በግፊት የሚካሔድ አመራር መኾኑን ያረጋግጣል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አድማሱ ዩኒቨርስቲውን ለመምራት ያላቸውን ብቃት ከዚህ ቀደም በአደባባይ ስለጠየቅኹ በቂም በቀልና ኹን ብለው እኔን ለመጉዳት የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡
የጥናትና ምርምር ዕረፍት(sabbatical leave) በተመለከተ በጊዜው የኮሌጁ ዲን የነበሩት ዶ/ር ገብሬ ይንቴሶ፤ የፕሬዝዳንቱን ፍላጎት ተከትለው ከላይ እንደጠቀስኹት የሰጡኝን ፈቃድ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከማምራቴ በፊት፣ የፕሬዝዳንቱን ምላሽ ከወዲኹ ባውቀውም አቤቱታዬን የግድ ለእርሳቸው ማቅረብ ነበረብኝ፡፡
በኮሌጁ የቀድሞ ዲን ውሳኔ ላይ ከዐሥር ገጽ ያላነሰ አባሪ ሰነዶች አያይዤ ጠዋት ላቀረብኹት አቤቱታ፣ ከቀትር በኋላ ‹‹በጥልቅ መርምረን›› በሚል በአንድ መሥመር የኮሌጁ ውሳኔ እንደማይሻር የሚገልጽ ፌዝና የቀልድ ምላሽ ነው የተሰጠኝ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፕሬዝዳንቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራን ከበሬታ የሌላቸውና አመራራቸውም ከሞራላዊነት የተራቆተ መኾኑን ነው፡፡ እኔ ግን ታዋቂው አርበኛ አበበ አረጋይ በአንድ ወቅት በፋሽስት ጣልያንና በባንዳ ለተከቡበት የተራቡ ጭፍሮቻቸው ‹‹ሞተን አንጠብቃቸውም፤ ተረጋግታችኹ ብሉ›› እንዳሉት፣ ከማባረር ያልተናነሰ የዘገየ አንድ ብጣሽ ወረቀት ገና ለገና ይመጣል ብዬ ሞቼ አልጠብቃቸውም፡፡
ከዚህ ቀደም የጡረታ ጊዜያቸው ደርሶ ለማራዘም የተፈቀደላቸው መምህራን አሉ ? ማለትም በዩኒቨርስቲው አሠራር የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ መምህራን ውላቸውን ማራዘም ይችላሉ?
በተለምዶ ስድሳ ዓመት የሞላቸው መምህራን የውል ማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ እኔ የማውቃቸውና በተደጋጋሚ የተጨመረላቸው መምህራንም አሉ፡፡ በጣም አስገራሚና በግቢው አነጋጋሪ የኾነው የእኔና የዶ/ር መረራ ጉዲና የውል ማራዘሚያ ጊዜ መከልከሉ ነው፡፡
ግን የዚህ ኹሉ መነሻ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?
ከኹሉ በፊት የእኔ መከልከልና መሰናበት ከፖሊቲካ እይታ አኳያ የመነጨ መኾኑ የታወቀ ነው፡፡
ማለት…
በዩኒቨርስቲው በማስተማር ሥራ በቆየኹባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች የማደርጋቸው የዐደባባይ አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች አልተወደዱም፡፡ እንዲያውም ለሹመኞች ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳጫወቱኝ፣ ‹‹ዳኛቸው፣ ዩኒቨርስቲውን እንደ ደጀንና ገዥ መሬት ተጠቅሞ መድፍ ሲተኩስብን ቆይቷል›› ተብዬአለኹ፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ አቋም ከተወሰደ በኋላ በሥራ ገበታዬ እንድቀጥል አለመደረጉ አይገርመኝም፡፡
ከዩኒቨርስቲው በዚኽ መልኩ ሲሰናበቱ ምን ተሰማዎ?
እንደ እውነቱ ከኾነ የተደበላለቀ ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ነገር ከሰባት ዓመት በኋላ መኾኑ አስደስቶኛል። ይኸውም የመጣኹበትን የማስተማር ዓላማ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመኾን ለመስኩ ተተኪና ምሉዕ የኾኑ ተማሪዎች ለማፍራት በመብቃታችን አስደስቶኛል፡፡ ይህ ክልከላና ስንብት በቂ ምሩቃን ባላፈራንበት ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት ቢከሠት ኖሮ አዝን ነበር፡፡ በኹለተኛ ደረጃ፣ ‹የዓመት ዕረፍት(ሳባቲካል) አይሰጥኽም፤ ከእንግዲኽ ማስተማርም አትችልም› ስባል ለራሴ በጥልቀት ተሰምቶኝ ያልኹት፣ ‹‹አኹን ገና ኢትዮጵያዊ ኾንኩ፤ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የሚረገጥ ማለት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚኽ ሰባት ዓመት ቆይታዬ ከአሜሪካ ሳልፈታ ይዠው የመጣኹት የነፃነትና የመብት አቅዋም፣ ከአገራችን ፖሊቲካዊ ነባራዊ ዕቀባ በተፃራሪው እንደ ልቤ እንድተችና ያለገደብ እንድናገር አስችሎኝ ነበር፡፡ አኹን ግን ሥርዓቱ ‹ይኼ አሜሪካ አይደለም፤ እንደ ጎረቤትኽ ሳይኾን እንደቤትኽ እደር› ብሎኛል፡፡ ይህን ስል ግን፣ እኔ በዕድሜዬ የምወልዳቸው ልጆች በኾነ ባልኾነ ክሥ ወኅኒ ቤት ተወርውረው ባሉበት ኹኔታ ከሥራ አባረሩኝ ብዬ የማለቅስ ሰው አይደለኹም፡፡ በእኒኽ ብሩህ ተስፋ ባላቸው ወጣቶች ላይ ከደረሰው አንጻር ሲታይ መብቴ መረገጡ እውነት ቢኾንም፣ የአገራችን ተረት ‹‹እናቱ ውኃ ልትቀዳ የወረደች ልጅና እናቱ የሞተችበት ልጅ አንድ ጋር ቆመው ያለቅሳሉ›› እንደሚባለው ይመስልብኛል፡፡
በመጨረሻም በአንድ በኩል፣ በውጭ ለብዙ ዓመት ቆይቼ ስመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የት ከረምክ ሳይለኝ፣ ችሎታዬ በሚፈቅድልኝ ቦታ ሥራ ሰጠኝ፡፡ ለዚኽ ትልቅ ምስጋና ነው የማቀርበው፡፡ ኾኖም በሌላ በኩል የውስጥ አስተዳደሩና የውጭ የፖሊቲካ ኃይሎች በመተባበር መክረው ከሕዝብ ባገኘኹት ቸርነት ላይ ወይነውብኛል!
ከዚኽ በኋላስ ምን ዓይነት ሥራ ላይ ለማተኮር ያስባሉ?
ይህን ጥያቄ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ብትጠይቀኝ ኖሮ፣ ጉዳዩ በራሴ የሚወሰን በመኾኑ አኹኑኑ እመልስልኽ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ቤትኽ እደር ተብዬአለኹና የጥያቄው ምላሽ በእኔ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥያቄው በአንድ ወቅት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሉ የተባለውን ያስታውሰኛል፡፡ አንድ ሹም ጃንሆይ ፊት ቀርበው የንጉሡ ትችትና ተግሣጽ ሲገጥማቸው፣ ‹‹እንዲያውም ግርማዊ ሆይ፣ የሰጡኝ ሹመት ይቅርብኝ፤ የአባቴን ርስት እያረስኩ እኖራለኹ›› አሏቸው፡፡ ጃንሆይም ወዲያው ‹‹እርሱንም እኛ ስንፈቅድ ነው…›› አሉ ይባላል፡፡
እኔም እንደ አቅሜ ለመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም፣ በቀጣይ ምን መሥራት እንደምችልና እንደማልችል ብያኔው በመሠረቱ ከእኔ ውጭ ነው፡፡ በተቻለኝ መጠን ግን በአለችኝ ቀሪ ዕድሜ አገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡ በዚኹ አጋጣሚ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበትን ተቋማዊ ኹኔታ በተመለከተ አንድ ጽሑፍ እንደማቀርብ ከወዲኹ ለማሳወቅ እወዳለኹ፡፡
ምንጭ፡-አዲስ አድማስ ጋዜጣ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ይፋ አደረጉ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማኀበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊቀመንበር ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ይፋ አደረገ፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ከትምህርት ክፍሉ ሊቀመንበርነት ራሳቸውን ለማንሳት የተገደዱት፤ በትምህርት ክፍሉ ከ28 ዓመታት በላይ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና የስራ ውል በዩኒቨርስቲው አስተዳደር መቋረጡን ተከትሎ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን የዶ/ር መረራ የጡረታ ጊዜ እንዲራዘም ያስገቡት ጥያቄ በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ውድቅ መደረጉ እና ከዚያም የትምህርት ክፍሉ ስለሚፈልጋቸው በራሱ የኮንትራት ውል አስፈርሞ ለሰባት ወራት ያሰራበት ክፍያ አለመፈፀሙን ተከትሎ ከመጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ለዩኒቨርስቲው አስተዳደር ማስገባታቸው ታውቋል፡፡
በተለይ እንደ አሜሪካ ድምፅ ዘገባ ከሆነ፤ ዶ/ር ካሳሁን በዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኩል በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የተወሰደውን ርምጃ ተከትሎ “ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ለትምህርት ክፍሉ ጥያቄና ፍላጎት ምላሽ ባለመስጠቱ፤ የትምህርት ክፍሉን እያስተባበርኩ መቀጠል ከሞራልም አኳያ ተቀባይነት እንደሌለው ይሰማኛል፡፡” በማለት ከትምህርት ክፍሉ ሊቀመንበርነት ለመልቀቅ መወሰናቸውን የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡ ዶ/ር መረራ በበኩላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት አስታውቀዋል፡፡ በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጡረታ ጊዜያቸው እንዲራዘም ጠይቀው የተፈቀደላቸውና እየሰሩ የሚገኙ በርካታ መምህራን እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ባልተገለፀ ምክንያት የዶ/ር መረራ ጉዲና የስራ ጥያቄ ብቻ ተቀባይነትን ሊያገኝ አለመቻሉ ታውቋል፡፡
ዶ/ር መረራ ከዚህ ቀደም ለሙሉ ፕሮፌሰርነት የሚያበቃ በርካታ ጥናቶችን አጠናቀው ማዕረጉን ለማግኘት ያቀረቡት ማመልከቻ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ተቀባይነት እንዳላገኘ የሚታወቅ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን የተወሰደባቸው እርምጃ በተቃውሞ ፖለቲካ ባላቸው ተሳትፎ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፤ በአሁን ወቅትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው በተጨማሪ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ሊቀመንበር እና የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) ምክትል ፕሬዘዳንት እና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ስራቸውን ለመቀጠል የሚያስችል ውል መጨረሻው የሚወሰነው በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሲፀድቅ እንደሆነ ገለፁ
ታዋቂውና ስመ ጥር የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በመንግስት መደበኛው በስራ በቆያ ዕድሜያቸው በመጠናቀቁ ስራቸውን በሚታደስ ውል ስራቸውን እንዲቀጥሉ የትምህርት ክፍሉ ፈቃደኝነታቸውን በጠየቀው መሰረት ውል ፈርመው በስራ ገበታቸው ላይ እንደሆኑ አስታወቁ፡፡
ዶ/ር መረራ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ እንደገለፁት ከሆነ፤ በዩኒቨርስቲው በማስተማርና በምርምር ከ25 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉና አሁን ዕድሜያቸው 60 ዓመት ስለሞላቸው የጡረታ ጊዜያቸው በመሆኑ፤ በእሳቸውና በዩኒቨርስቲው መካከል በሚታደስ አዲስ የኮንትራት ውል ስምምነት መሰረት ስራቸውን ለመቀጠል ከዚህ ቀደም ከሚያስተምሩበት ትምህርት ክፍል እና ከዩኒቨርስቲው ማኀበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር መፈራረማቸውን እና ስራቸውንም መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው በኮንትራት መልክ የሚታደሰው አዲሱ የውል ስምምነት ሊፀና የሚችለው በእሳቸውና በትምህርት ክፍሉ ስራውን ለመቀጠል የሚያስችል ፈቃደኝነት ስምምነት በዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኩል ሲፀድቅ መሆኑንም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡
አዲስ ሚዲያም በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዶ/ር መረራ ከሚሰሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባረሩ የሚል ዜና ተሰምቷልና እውነት ነው ወይ ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ እስካሁን የደረሰኝ መረጃ የለም፣ መደበኛ ስራዬን እየሰራሁ ነው፣ ነገር ግን አንዳንድ ወሬ እኔም እሰማለሁ እንጂ እሳካሁን የደረሰኝም የእግድ ደብዳቤም ሆነ መሸኛ የለም፣ አዲስ ነገር ካለ ወደፊት አብረን የምንሰማው ነው ሚሆነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዶ/ር መረራ ስራ ጋር በተያያዘ ስለተወራው ነገር ለማጣራትና ምላሽ ለማግኘት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ክፍል ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የኦፌኮ ሊቀመንበርና በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡