እናታችን ፋናዬና ጋዜጠኛ ተመስገን በዝዋይ…
ታሪኩ ደሳለኝ
(የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም)
ያቺ የስምጥ ሽለቆ ከተማ ይበልጥ መንደድ ከጀማመራት አንድ ወር አልፏታል:: በፍትህ መዛባት ስሜቱ የተጎዳ፣ በወገኖቹ ስቃይ መንፈሱ የታመመ፣ ሀገራቸውን ከስቃይ መታደግ በሚችሉበት እድሜያቸው በታሰሩ፣ በተሰደዱና በተገደሉ ወገኖቹ ልቡ ያዘነ፣ ለሀገሩና ለባንዲራው ያለው ፍቅር ጥልቅ የሆነ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በውስጧ ይዛለች፡፡ ዝዋይ፡፡
ከዚህች ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው የዝዋይ እስር ቤት ለመሄድ የአስፓልት ዱካ እንዳረፈበት በሚያሳብቀው ኮሮኮንቻማ መንገድ ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ከረጅም ዓመታት በፊት ተሰርቶ ዛሬ አስታዋሽ ያጣው ይህ ጎዳና እስረኞችን የመጠየቁን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከፀሐዩ ግለት ትይዩ ያለው የመሬቱ አቧራ በእግሩ ቆሞ ይሄዳል ብል አይበዛበበትም፡፡ ይህን አልፈን ግዞት ቤቱን እናገኛለን፡፡ የእስር ቤቱን መግቢያ ያለበሰው አቧራ ደግሞ ቅጥሩን በቁፋሮ የተገኘ ጥንታዊ ከተማ አስመስሎታል፡፡ የግቢው ገፅታ ለዕይታ በማይስቡ ነገሮች ቢከበብም፣ ተናፋቂውን ብዕረኛ ግን ደጋግሜ እንድጠይቀው ከወንድምነት የሚዘለው ጥንካሬው ይስበኛል፡፡
በአቧራውና በንዳዱ መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀድሞ ይልቅ በጠነከረ ፅናቱ ስለመኖሩ ሳስብ ደስተኛ እሆናለሁ፡፡ እናታችንስ ምን ታስብ ይሆን? የማይበርድ፣ የማይዳፈንና የማይጠፋ የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከአቧራውና ከንዳዱ በላይ መሆኑ ለእርሷ ምን ስሜት ያጋባባታል?
እናታችንና ተሜን ሲገናኙ…
ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 20/07 ዓ.ም ነው፡፡ እናቴ አብረዋት ከኖሩ ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን፣ ዝዋይ እስር ቤት ከከተመ አንድ ወር ያለፈውን ተመስገንን ልታየው ተሰናድታለች፡፡ ዝዋይ ከሄደ ወዲህ አይታው አታውቅም፡፡ እንደናፈቃት ግን የፊቷ ገፅታ ይመሰክራል፡፡ እንደ ልጅነቱ ፀጉሩን ባትደባብሰውም፤ እጁን ልትነካውና በዕርጅና አንደበቷ ‹እንዴት ነህ?› ልትለው ወደዚያው እያቀናች ነው፡፡ ጠዋት ወጥተው ማታ እንደሚገቡት፣ ክፍለ-ሀገር ሰንብተው እንደሚመለሱት እንደ ጓደኞቿ ልጆች ተመስገን እንደማይመለስ የተረዳችው እናታችን ልጇ ጋር እየሄደሰች ነው፡፡
ለሊት 11፡30 ከጀሞ ኮንዶሚኒየም የተነሳችው መኪና ዝዋይ የደረሰችው ከጠዋቱ 2፡20 ላይ ነበር፡፡ አስፋልት መሰል ፍርስራሽ መንገዱን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ዛሬ አልሰጠኝም፡፡ ፍተሻውን አልፈን እስረኛና ጠያቂ የሚገናኘበት ቦታ ላይ ደረስን፡፡ ከነበርነው ሰዎች ይልቅ እናታችን ጉጉት እንዳደረባት ለመናገር ሁኔታዋን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡
እናታችን ተመስገን በልጅነቱ ከዕኩዮቹ ጋር ተጫውቶ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ስራ ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፤ አንዳንዴም ሲያመሽ ደውላ ‹‹አልመሸም፤ የቀረው ለነገ ይቆይህ›› ትለዋለች፤ እርሱም ሁሌ እንደሰማት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ልጇን የምትጠብቀው ከትምህርት ቤት አልያም ከጨዋታ ወይም ከስራ አይደለም፡፡ ከእስር ቤት ውስጥ እንጂ!
እናታችን እስረኞች ከሚወጡበት በር ላይ ከተቀመጠችበት ደቂቃ ጀምሮ አይኗን አላነሳችም፡፡ በሩ ሲከፈት የወታደር ልብስ የለበሰ ወጣት ወጣ፡፡ ከወታደሩ በኋላ ተሜ እስካርፉን እንዳደረገ ተከተለ፡፡ እናቴ ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ ዐይኗቿ እንባ አዘሉ፡፡ በዕስረኛና በጠያቂ መሀል ያለውን አጥር ተደገፈች፡፡ ሌላ ጊዜ አጥሩን መደገፍ የሚከለክሉት ወታደሮች እናታችንን ግን ጥቂት ታገሷት፡፡ ምን ያድርጉ? እነሱም እኮ እናት አላቸው፡፡ ከተመስገን ኋላ ሌላ ወታደር አለ፡፡ በሁለት ወታደሮች መካከል ሆኖ ተሜ እናቱን አያት፤ ፈገግ አለ፡፡ እየቀረበ ሲመጣ ግን ፈገግታው ከፊቱ ላይ ጠፍቶ በሀሳብ ተተካ፡፡ እናቴን በዚህ እድሜዋ አንከራተትኳት ብሎ እንዳላሰበ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ከዚህ ይልቅ ስንትና ስንት እናቶች በየቦታው እየተንከራተቱና እየተሰቃዩ ስለመሆናቸው እያሰበ የተጨነቀ ይመስላል፡፡ እናትና ልጅ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ቆዩ፡፡ ምን አለ ባይለያዩ? እንዲሁ እንዳሉ ወደ ቤት ቢሄዱስ ምን ነበረበት?
ይሄ ግን አይሆንም፤ ይሄ ቦታ ተሜ ለሀገሩ የከፈለውን፣ እየከፈለ ያለውንና የሚከፍለውን መስዋዕትነት ማቅረቢያው ቦታ ነው፡፡ ተሜ ወደ ቤት አይሄድም፡፡
ተሜና እናቴ የተጫወቱት ብዙ ነው ፡፡ ሲገናኙ የነበረው ድባብ ጠፍቶ ሁለቱም ደስ ብሏቸዋል፡፡ ተሜ ትንሽ አይቷት ‹‹ከስተሻል›› ሲላት ፈገግ እንዳለች ‹‹አረ አልከሳሁም፤ አንተ ግን ጤናህ እንዴት ነው?››፤ ‹‹ደህና ነኝ››… እናቴ በየመሀሉ ጨዋታቸውን ገታ እያደረገች በስስት ታየዋለች፡፡ እናትና ልጅ የሆድ የሆዳቸውን እንዲያወሩ የፈቀዱት ወታደሮችም ሁለቱን በስስት የሚያዩ ይመስላሉ፡፡
ሳይታወቀን 6፡00 ሆነ፡፡ የመሰነባበቻ ጊዜ ደረሰ፡፡ እናቴ እየሳቀች አቀፈችው፤ ተሜም እየሳቀ ተሰናበታት፡፡ እንደ አመጣጡ በሁለቱ ወታደሮች መካከል ሲሄድ ከጀርባው ትክ ብላ አየችው፡፡ የሆነ ነገር ልትል የፈለገች ትመስላላች፡፡ ‹‹ተመስገን›› አለች፤ አልሰማትም፡፡ በሩን አልፎ ገባ፡፡ እሱ ፊት የደበቀችውን እንባ ማቆም አልቻለችም፡፡ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ከፈገግታዋ ጋር አለቀሰች፡፡
እሁድ ህዳር 21/07 ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት፡፡ እናቴ ልጇ እስኪፈታ አልጋ ላይ አልተኛም ብላ መሬት መተኛት ከጀመረች 1 ወር ከ17 ቀኗ ነው፡፡ የዛሬውን ለሌት እንዳለፉት ጊዜ አንዴም ተነስታ ‹አይ ልጄ› ወይም ‹እህህ….እህህ….› ሳትል በሰላም ተኝታ በማደሯ ሳልተኛ እያየኋት አደርኩ፡፡ ልክ 12፡10 ሲል ነቃች፡፡ ስታየኝ እያየኋት ነው፡፡ ‹‹ስንት ሰዓት ሆነ?›› ነገርኳት፡፡ አላመነችም፡፡ ተሜ ከታሰረ ጀምሮ እንደ ዛሬ ተኝታ አታውቅም፡፡ ተነሳች፡፡ ‹‹እስከዚህ ሰዓት ስተኛ ዝም ትላለህ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹እንዴት ዝም አልልም?›› አልኳት፡፡ ‹ዛሬ የዓመቷ ማሪያም ነች› አለችኝ፡፡ ፊቷ ላይ ድካም አይታይባትም፡፡ … ከደቂቃዎች በኋላ የሀገር ባህል ጥበብ ቀሚስ ለብሳ አየኋት፤ አምሮባታል፡፡ የደስታ ሲቃ ይዞኝ ‹ትላንት እንዴት ነበር?› አልኳት፡፡ በፈገግታ እያየችኝ ‹‹ልጄ ጀግና ነው፤ ጀግና›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም በመስማማት ራሴን ነቀነኩ፡፡ እናቴ በንጋት ፀሐይ ታጅባ የሀገር ባህል ልብሷን እንደለበሰች ስትሄድ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ይሄ ብርታቷ እስከመቼ እንደሚቆይ እያሰብኩ ነበር፡፡
ተሜ ለሀገሩ ሲልና ሀገሩ እንድትሆን የሚመኝላትን በመፃፉ በግዞት እስር ቤት በአቧራና በንዳድ መሀል እንዲሰነብት ተፈርዶበታል፡፡ ፍትህ የነገሰባት፣ ልጆቿ የማይገደሉባትና የማይሰደዱባት ኢትዮጵያ እንደምትመጣ በተቃጠለ ስሜት እያሰበ፣ በማለዳ የወጣችውን የንጋት ፀሐይ በፈገግታ እያያት እንደሆነ ሳስብ እኔም በደስታ ተሞላው፡፡
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለአዳሩ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ አስገባ
- ቦታው መስቀል አደባባይ እንዲሆን ወስኗል
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 28/2007 ዓ.ም ለሚደረገው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የእውቅና ደብዳቤ አስገባ፡፡
ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የገባው ደብዳቤ በሰማያዊ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ ተፈርሞ የገባ ሲሆን የእውቅና ደብዳቤውንም ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲና የትብብሩ ሊቀመንበር፣ የከንባታ ህዝቦች ሊቀመንበርና የትብብብሩ ም/ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርጌሎ፣ አቶ ግርማ በቀለ ከኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የትብብሩ ፀኃፊ እና የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙደሲር አስገብተዋል፡፡የትብብሩ አመራሮች ወደ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ በሄዱበት ወቅት የአቶ ማርቆስ ተወካይ ለሆኑት አቶ ፈለቀ አበበ ደብዳቤውን ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም ተወካዩ ‹‹የከንቲባ ጉዳዮች ጽ/ቤ ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የለም፡፡ እሱ ካልመራበት መቀበል አንችልም›› በሚል ደብዳቤውን አልቀበልም እንዳሏቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹ ወደ አቶ አሰግድ ቢሮ ቢያቀኑም እንዳላገኙዋቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የትብብሩ አመራሮች ደብዳቤ መስጠት እንጂ ደብዳቤ ማስመራት የሰራተኞቹ እንጂ የእነሱ ስራ እንዳልሆነ በመግለጽ ደብዳቤውን ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ታመዋል የተባሉት የአቶ ማርቆስ ተወካይ የሆኑት አቶ ፈለቀ ቢሮ በአራት ምስክሮች ፊት አስቀምጠው መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ አመራሮቹ የእውቅና ደብዳቤውን አቶ ፈለቀ ቢሮ አስቀምጠው ከመውጣታቸውም ባሻገር በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በፈጣን መልዕክት (ኢ ኤም ኤስ) በሪኮመንዴ ቁጥር eg157416502et መላካቸውን ገልጸዋል፡፡
የአዳር ሰላማዊ ሰልፉ ህዳር 27 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተጀምሮ ህዳር 28 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ቦታውም መስቀል አደባባይ ላይ እንደሚሆን መወሰኑ ታውቋል፡፡
የትብብሩ አመራሮች የእውቅና ደብዳቤውን ለማስገባት በሄዱበት ወቅት በቦታው የትብብሩ አመራሮች የሚያውቋቸው ደህንነቶች ባለ ጉዳይ በመምሰል ይመላለሱ እንደነበርና ፖሊሶችም ይከታተሉ እንደነበር መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የማያዳምጥና የማያነብ መንግስት እድሜው ስንት ነው?
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
“መንገዱ በዚህ ወር ይጠናቀቃል፤ ባቡሩ በዚህ ወር ስራ ይጀምራል” ይሉናል፡፡ መንገዱ ወዴት ያደርሳል? ባቡሩ ወዴት ይወስዳል? ልጆቻችን ወጥተው የማይገቡበት መንገድ፣ የማይሳፈሩበት ባቡር ምን ያደርጋል? መንገዱ ሲሰፋ፣ መጓጓዣው ሲበረክት የልጆቻችን ፍርሀት፣ የእኛ የወላጆች ጭንቀት ከመበርከቱ በቀር ትርፉ ምንድነው?
ቁሳዊ ልማት ብቻውን ማህበረሰባዊ እድገት አያመጣም፤ ቀውስ ካልሆነ በቀር፡፡ የማህበረሰብህን . . . የነገ ወራሽህን. . የወጣቱን አስተሳሰብና አሰራር ሳታለማ (ሳትለውጥ) ታክሲ ብታመጣ፣ ወንዝ ውሀ ስትቀዳ፣ ጫካ እንጨት ስትለቅም ትደፈር የነበረችውን ልጃገረድ፣ ታክሲ ውስጥ ታስደፍራታለህ፤ ነገም ባቡር ውስጥ (ዛሬ በህንድ ሀገር ባቡር ማለት ብዙ የማያስከፍል ፔንሲዮን ነው)፡፡ እኛ ሀገር ብዙ መንገድ ብዙ ወንጀል፣ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሰፊ ዝርፊያ፣ ትልቅ ባለስልጣን ትልቅ ዘራፊ ከማለት የተለየ ፍቺ የሚኖረው መቼ ነው?
“ልማታዊ መንግስት ነን፣ ኒዎ ሊብራሊዝምን እንቃወማለን” ይሉናል፡፡ በልማት ስም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችንን አንጠፍጥፈው ወሰዱት፡፡ ይበጃል ያልነውን ስንጽፍና ስንናገር ጸረ ልማት ይሉናል፡፡ ደፈር ብለን መብታችንን ከጠየቅን አሸባሪ ይሉናል፡፡ በየእስር ቤቱ ያጉሩናል፤ ድንበር አሻግረው ያሰድዱናል፡፡ መብታችንንና የመናገር ነጻነታችን ልማታዊ ላሉት መንግስት ጭዳ አደረጉት፡፡
“ልማታዊ አይደላችሁም! ኒዎ ሊብራል ናችሁ አንላቸዋለን፡፡ የምትኖሩበት ቤት፣ የምትነዱት መኪና፣ ልጆቻችሁ የሚማሩበት ትምህርት ቤት (ሀገር)፣ የምትገበያዩበት ሱፐር ማርኬት፣ የምትዝናኑበት ሪዞሪት. . . የልማታዊነት ሳይሆን የኒዎ ሊብራሎች መገለጫ ነው፡፡” እንላቸዋለን፡፡
“ዝም በሉ! የምንላችሁን አሜን ብላችሁ ተቀበሉ” ይሉናል፡፡ ማተሚያ ቤቱ የእነሱ ነው፤ ራዲዮና ኢቲቪው የእነሱ ነው፤ አዋጅና መመሪያ የሚጥልብን ፓርላማ የእነሱ ነው፡፡ አዋጅ ጣሳችሁ፣ አሸበራችሁ፣ እራለ የሚይዘን ፖሊስ የእነሱ ነው፤ ከፖሊሶቹ ተቀብሎ የሚፈርድብን ፍርድ ቤት የነሱ ነው፡፡ ያለ ወንጀሉ ተከስሶ የሚፈረድበት ዜጋ እሱ ራሱ የራሱ አይደለም፡፡ ራሳችንም የእነሱ ነን፡፡ የእኛ የሆነው ተስፋችን ብቻ ነው! ለሀገራችንና ለወገናችን ያለንን ብሩህ ተስፋ ምንም ሊያስረው አይችልም፡፡ የኔ ተስፋ ልጆቼ ውስጥ፣ ያልተወለደው የልጆቼ ልጆች . . . . . ውስጥ አለ፡፡ ተስፋ የሚታሰረው፣ የሚሞተው እርኩስ፣ ለሀገርና ለወገን የማይበጅ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
ዛሬ አትጻፉ ተብለናል፡፡ አትናገሩ ተብለናል፡፡ አንጽፍም፡፡ አንናገርም፡፡ ከተማው ጭር ብሏል፡፡ ሀገሩ ጭር ብሏል፡፡ መንግስትም ጭርታው ተስማምቶታል፡፡ እኛ ግን አንጽፍም እንጂ እንነበባለን፤ አንናገርም እንጂ እንደመጣለን፡፡ የማያነበንና የማያዳምጠን የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው፡፡ አንድ መንግስት ህዝቡን ሳያዳምጥና ሳያነብ ምን ያህል እድሜ ይኖራል? እንጃ! . . . . . አንድ ቀን መንግስት ህዝብን ማንበብ፣ ህዝብን ማዳመጥ ግዴታው ይሆናል፡፡ አቤት ታዲያ ያኔ የሚያነበው መአት! የሚያዳምጠው ቁጣ! ያኔ ማንም መንግስትን መሆን አይመኝም፡፡ እውነቴን እኮ ነው፣ አሁን 1983 ዛሬ ቢሆን ደርግን መሆን የሚመኝ አለ?
በርካታ የአንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት ታግተው መለቀቃቸው ተገለፀ
የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃምን ጨምሮ ከ40 ያላነሱ የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት መታገታቸው ተገለፀ፡፡
አንድነት ፓርቲ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ አመራሮቹና አባላቱ ወደ ቃሊቲ እስር አቅንተው ነበር፡፡ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝን ጨምሮ ከ40 ያላነሱ የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ባልታወቀ ምክንያት በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡
በተለይ እገታውን በተመለከተ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አስራት አብርሃም ተናገሩት እንደታለው ከሆነው ‹‹እነእስክንድርንና አንዷለምን መጠየቅ አትችሉም ተባልን፡፡ ከዚያም ‹‹ለምን?›› ብለን ስንጠይቅ በዋናው በር በኩል ኃላፊውን አነጋግሩ የሚል መልስ ተሠጠን፡፡ እኛም ይህንን አምነን ሄድን፡፡ ነገር ግን በተባለው በር ስንደርስ በቁጥጥር ሥር ውላችኋል ብለውን መታወቂያችንን ከመዘገቡ በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ ለጊዜው ታገተው እንደነበር ሚኒሊክ ሳልሳዊ ዘግቧል፡፡ በመጨረሻም በኮንቴይነር ውስጥ ታግተው የነበሩት እስረኛ ጠያቂዎች ከበድ ያለ ፍተሻ ተደርጎላቸው ከቃሊቲ ግቢ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ወጣት ትዕግስት ካሳዬ የተባለች የአዲስ አበባ የፓርቲው አመራር ግን ከእገታው እንዳልተለቀቀች ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
እስረኞችን ሊጠይቁ የሄዱ የአንድነት አባላት በዛሬው እለት በአከባቢው የጠበቃቸው የደህንነት ቡድን በእያንዳንዱ ላይ ፍተሻ በማድረግ በኪሳቸው የነበረውን የአንድነት ፓርቲ ወረቀት እንዲሁም አንዲት ሴት የአንድነት አባል ፎት ልትነሳ መሞከር በሚል በተፈጠረ ሰበብ እንዲሁም በአባላቶቹ እጅ የተገኙት የፍኖተ ነፃነት እትሞች መቀማታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህ የተፈፀመው በቶዮታ ነጭ ዲኤክስ መኪና ተጭነው የመጡት የደህንነት አባላት እስረኛ ሊጠይቁ የሄዱትን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ስም ዝርዝራቸውን መዝግበው በመውሰድ እንዲፈቱ ትእዛዝ ሰጥተው ደህንነቶቹ መመለሳቸውን እና ከአንዲት አባል በስተቀር ሌሎች መለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡
አመክሮና በቀለ ገርባ
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ምክትል ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ስራ አስፈፃሚ የነበሩት “ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የአሸባሪ ቡድን የሆነው ኦነግ አባል ሆነዋል” በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የ8 ዓመት እሥር የተበየነባቸው ሲሆን፤ ይግባኝ ጠይቀው እስሩ ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር ዝቅ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከ3 ዓመት ከ7 ወር የእስር ጊዜ ውስጥም 3ቱን ዓመት በመጨረሳቸው በአመክሮ ይፈቱ ዘንድ ለማረሚያ ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ማረሚያ ቤቱም ‹አመክሮ መስጠትም አለመስጠትም መብታችን ነው› በማለት እስከአሁን ሊፈታቸው አልቻለም፡፡ ይህም ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡
አንዳንድ ህጋዊ ሁኔታዎች ስለጉዳዩ፡
አመክሮ ምንደር ነው?
ሌላውን ትርጉም ትተን የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ‹በተወሰነ ጊዜ በአመክሮ መፈታት› በሚለው ክፍል በተለይም በአንቀፅ 202 እንደደነገገው፡
“ተቀጭው ከተወሰነበት የእስራት ጊዜ ከሶስት እጅ ሁለቱን እጅ ወይም ፍርዱ የእድሜ ልክ እስራት ሲሆን ሀያ ዓመት በፈፀመ ጊዜ አግባብ ባለው አካል ወይም በጥፋተኛው አሳሳቢነት ጥፋተኛውን ከቅጣቱ ነፃ ያወጣዋል፡፡” ይህም ማለት አመክሮ 2/3ኛውን የቅጣት ጊዜውን የጨረሰ ታራሚ ከእስር የሚፈታበት አሰራር ነው፡፡
አመክሮ ለማግኝት ምን መስፈርት ማሟላት ያስፈልጋል?
የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከላይ በጠቀስነው አንቀፅ 202 ላይ አመክሮ ለማግኝት አንድ እስረኛ ማሟላት የሚያስፈልገውን መስፈርቶች ይዘረዝራል፡፡ ይህም፡
– ‹ታራሚው በስራ ጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል አሳይቶ እንደሆነ…›
– ‹ካሳ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበት ከነበረና ካሳውን መክፈሉ የተረጋገጠ እንደሆነ…›
– ‹አመሉና ጠባዩ መልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለውና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የታመነ እንደሆነ..›
ነው ብሎ ይደነግጋል፡፡
ማረሚያ ቤት ወይስ ፍርድ ቤት?
ታራሚን በአመክሮ የመልቀቅ የመጨረሻው ስልጣን የፍርድ ቤት፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ማረሚያ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በታራሚው አሳሳቢነት ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ ነው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚሰጠው፡፡ እዚህ ላይ ማረሚያ ቤቱ ትልቁን ስልጣን ይዞ እናገኛለን፡፡ ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ካልፈለገ ሊተወው የሚችልበት አግባብ አለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ በሕግ ስር ያለ አካል እንደመሆኑ መጠን በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 202 ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን ላሟላ ታራሚ አመክሮ ሊከለክል አይችልም – የታራሚው መብት ነውና!
በቀለ ገርባስ?
አቶ በቀለ ገርባ ከተፈረደባቸው የአምስት ዓመት እስር ውስጥ 2/3ኛውን ወይም 3 ዓመት የሚሆነውን ጨርሰው የአመክሮ ጥያቄያቸው በማረሚያ ቤቱ በኩል ለፍርድ ቤት እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ ‹አመክሮ መስጠትም አለመስጠትም መብታችን ነው› የሚል መልስ እንደሰጣቸው ተሰምቷል፡፡
1ኛ. አመክሮ መስጠት የማረሚያ ቤት መብት ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ መስፈርቱን ያሟላ ታራሚ አመክሮ የማግኝት መብት ያለው መሆኑ በሌላ በኩል አመክሮ ሰጭውን አካል ላይ ግዴታ ይጥላልና፡፡
2ኛ ሌላው አቶ በቀለ ገርባ መስፈርቱን አሟልተዋል ወይስ አላሟሉም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ 2/3ኛውን የእስር ጊዜ መጨረስ የሚለውን Objective መስፈርት እንዳሟሉ ግልፅ ሲሆን፡፡ ችግሩ የተፈጠረው Subjective መስፈርቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ይህም ማለት በእስር ወቅት መልካም ፀባይ አሳይተዋል ወይስ አላሳዩም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ታራሚ በእስር ወቅት ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ካሳየ የቅጣት ማስጠንቀቂያ ከመፃፍ እስከ ብቻውን ማሰር (Solitary Confinement) ድረስ ያሉ እርምጃዎች በማረሚያ ቤቱ ሊወሰዱበት ይችላሉ፡፡
አቶ በቀለ ገርባ ከፀባያቸው ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ቅጣት ያልተወሰደባቸው ከመሆኑም ሌላ መልካም ፀባይ እንዳሳዩ ከማረሚያ ቤቱ እንደተነገራቸው ራሳቸው ገልፀዋል፡፡ በቀለ ገርባ ምም መስፈር አሟልተዋል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሆን አቶ በቀለን በአመክሮ ከመፈታት ያገዳቸው?
አንዳንድ ነገሮች…
ባለው አካሄድ አብዛኛው ታራሚዎች በአመክሮ ይፈታል፡፡ ከሌባ እስከ ሙሰኛ፡፡ High Profile በሆኑ ክሶች የተከሰሱ ሰዎች ሳይቀሩ በአመክሮ ሲፈቱ እንደነበር እናስታውሳለን ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ 24 ወራት ተፈርዶበት 16 ወራትን ጨርሶ በአመክሮ ተፈቷል፡፡ አቶ አሰፋ አብርሃ 9 ዓመት ተፈርዶባቸው ሰባት ዓመታት ታስረው ከብዙ ውዝግብ በኋላ በአመክሮ ተፈተዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅንጅት ክስ ስር ተከሰው የነበሩት አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ 30 ወራት የተፈረደባቸው ሲሆን 20 ወራትን በእስር አሳልፈው አመክሮ ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ ‹ፍርዳችሁን ጨርሳችሁ ውጡ› በሚል ምክንያት አመክሮ ከልክሏቸው ነበር፡፡
እንግዲህ አቶ በቀለ ገርባ በሕጉ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው እያለ በአመክሮ የመፈታት መብታቸው አልተከበረም ወይም ማረሚያ ቤቱ ግዴታውን ሊወጣ አልፈለገም!
ምክንያት: በጉልበተኞች የምትተዳደር ሀገር ዜጋ ስለሆኑ!
ልዩ ማስታወሻ፡-ይህ ባለፈው ጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም. የዞን 9 ብሎገርና የአምቦ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ዘለዓለም ክብረት ከመታሰሩ በፊት የፃፈው ቢሆንም፤በአሁን ሰዓት እሱ ራሱ በግፍ እስር አቃቂ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛል፡፡
#FreeBekeleGerba