Category Archives: Social and Culture

የት ሂዱ ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ዓለም ሁሉ ጠላን፤ በየትም አገር እየሄድን ‹‹የሙጢኝ!›› ከራሳችን መሬት በጉልበት እየተነቀልን፣ ከራሳችን ቤት እየተባረርን፤ ከተወለድንበትና ከአደግንበት አካባቢ እየተፈናቀልን፣ ጭራውን ቆልምሞ እንደሚሮጥ ባለቤቱ እንዳባረረው ውሻ በአገኘነው አቅጣጫ እየሮጥን፣ እጃችንን እያርገበገብን ‹‹የሙጢኝ!›› እንላላን፤ የፈራነውን ሞት በየመንገዱ እናገኘዋለን፤ ሞትን ሸሽተን ሞትን ያጋጥመናል፤ የሞቱ ልዩነት አይታየንም፤ በየመንገዱ የሚያጋጥመው ሞት የውርደት ሞት ነው፤ የብቸኛነት ሞት ነው፤ ዘመድ-ወዳጅ ለቀብር የማይገኝበት ሞት ነው፤ ሠለስት፣ አርባ፣ ሙታመት የማይወጣበት ሞት ነው፤ ባዕድ ምስጥ ያላሳደገውን አካል የሚበላበት ነው፤ የሞት ሞት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከአገር አስወጥቶ ባዶ መሬት ብቻ ይፈልግ ይመስል የወያኔ ሎሌዎች በማስፈራራት ሁሉም አገሩን እየተወላቸው እንዲሄድ ያቀዱ ይመስላል፤ ጥንት ኢሰመጉ በምሠራበት ጊዜ በየጊዜው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎችን በማስፈራራት ሰላማቸውን ለመረበሽ ወደስደት ወይም ወደወንጀል ተግባር የሚመሩ የወያኔ አባለች ነበሩ፤ አሁን እንደገና ብቅ ማለት ጀምረዋል፤ ሕጋዊ ሥርዓት እየላላ ጉልበተኞች በግላቸው ለዘረፋና ለቅሚያ እየተሰማሩ ይመስላል፡፡
ስለራሴ ላውራ፤ ከእኔ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የሚፈልጉት የምኖርበትን አፓርትመንት እንደሆነም አላውቅም፤ በእኔ ቤት ያለ ሀብት የሚባል ለወያኔ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለት የገብረ ክርስቶስ ስዕሎች ብቻ ናቸው፤ (በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስዕሎች ለመግዛት የሚፈልግ ያነጋግረኝ)፤ ከዚህ ሌላ ለወያኔ ዋጋ የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ስለዚህም አሁን በእኔ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እኔን ወደስደት ለመግፋት የሚደረግ ሙከራ ይሆናል፤ በ1992 ግድም ተሞክሮ ነበር፤ አልሠራም፤ ዛሬ ይበልጥ አይሠራም፤ ለማናቸውም ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ባልችልም በእኔ ላይ ዘመቻ መጀመሩን አንድ በቅርብ ከማውቀው ወያኔ በትክክል ተረድቻለሁ፤ ይህንን ዘመቻ በመምራት ላይ ያለውንም ሰው ማንነት ተነግሮኛል፡፡
ይህ አገር የአንድ ጉልበተኛ ቡድን ነው ብዬ አልቀበልም፤ የአባቶቼና የእናቶቼ፣ የኤቶቼና የቅድማያቶቼ አጥንትና ደም የገነባው አገር ነው፤ ማንም ለስደት አይዳርገኝም፤ ማንም አስፈራርቶ ኢትዮጵያዊነት መብቴን መግፈፍ አይችልም፤ አልፈቅድለትም፤ በግልጽ በማያጠራጥር ቋንቋ ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም፡፡
እኔን ለማጥቃት ላሰፈሰፉት ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው አንድ እውነት ልንገራቸው፤– በፈለጉትና በተመቻቸው መንገድ በእኔ ላይ በጉልበታቸው ግፍ ቢፈጽሙ ነገ በነሱ ላይ የባሰ ግፍ እንደሚደርስባቸው ይወቁት፤ ሁልጊዜም ከሕግ የወጣ ጉልበተኛነት ጉልበተኛነትን ያነግሣል፤ በመግደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ወያኔዎች ትንሽ ቆም ብለው ያስቡ፤ በመሞትም ድል ይገኛል፤ በመሞትም ማሸነፍ ይቻላል፡፡
በእኔ ላይ የዘመተው ወያኔ ወይም ሎሌ ማናቸውም ሥራ ውጤት እንዳለው ማወቅ አለበት፤ አንድ ነገር አድርጎ ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ ይህ የሳይንስ ሕግ ነው፤ For every action there is a reaction ይላል!

በኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ በአል-ሸዓባብ በተፈፀመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 147 ደርሷል

Garissa-University-College attack

በኬንያ ሰሜን ምስራቅ  በምትገኘው ጋሪሳ የሶማሊያው ታጣቂ አል-ሸዓባብ ሐሙስ ጠዋት መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ በመግባት በከፈተው ጥቃት ሁለት የዩኒቨርስቲው ጠባቂዎችን፣ሶስት የፖሊስ ኦፊሰሮችን እና 142 ተማሪዎች በአጠቃላይ 147 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጆሴፍ ነካይዘሪ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡ በጥቃቱ ከሟቾች በተጨማሪ 79 ተማሪዎች የቆሰሉ ሲሆን፤ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ በታጣቂው ኃይል ታግተው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በፖሊስ እጥረት ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል የለብንም በማለት ከፍተኛ የፖሊስ ቁጥር እንዲጨምርና ወደስልጠና እንዲገቡ  ትዕዛዝ መስጠታቸውን አደጋው በደረሰ ቀን ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡ የሶማሊው ታጣቂ አልሸዓባብ በኬንያ ንፁሃን ላይ የሚያደርሰው ጥቃት እየተበራከተ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በናይሮቢ ዌስትጌት የንግድ ማዕከል ውስጥ በፈፀመው ጥቃት 67 ሰዎች መግደሉ ይታወሳል፡፡ ከዛም በኋላ የሐሙሱን የጋሪሳ ዩኒቨረድስቲ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ጥቃቶችን መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ የጥቃቲ ኢላማዎችም ሙስሊም ያልሆነ ማንኛውም አካል ሲሆን፤ በተለይ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃቱ መጨመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እንደ ሀገሪቱ ፖሊስ መጃ መሰረት ከ2004 ዓ.ም. እስከ ታህሳሥ 2007 ዓ.ም. ብቻ የአልቃይዳ ክንፍ በሆነው በሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ አልሸዓባብ የተገደሉ ኬኒያውያን ቁጥር 312 ደርሶ ነበር፡፡ በጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተፈፀመውን የጅምላ ግድያ ጨምሮ በሶማሊያው ታጣቂ አል-ሸዓባብ የተገደሉ ኬንያውያን  459 ደርሷል፡፡

Garissa-University-College attack

በዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ተማሪዎች ላይ ታጣቂው  ከፈፀመው የጅምላ ግድያ በኋላ አራት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሲገደሉ፣ አምስት ተጠርጣሪ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር  መዋላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥ የተገደሉ ሰዎችን ማንነት ለመለየትና ወደ የቤተሰቦቻቸው ለመላክ አሰከሬናቸው ወደ ናይሮቢ መላኩም ታውቋል፡፡

ጋሪሳ ከናይሮቢ ሰሜን ምስራቅ 367 ኪሎ ሜትር ስትርቅ፤ ከኬንያ ሶማሊያ ድንበር ያላት ርቀት  ደግሞ 147 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የታጣቂ ቡድኑ በተመሳሳይ መልኩ በዩጋንዳ የትምህርት ተቋማት ላይ ጥቃት ለመፈፀም ዕቅድ እንዳለው ተጠቁሞ፤ የዩጋንዳ የደህንነትና ፀጥታ አካላት የሀገሪቱን ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በላቀ በተጠንቀቅ ላይ ሆነው እንዲጠብቁ መደረጉንም የዩጋንዳ ከፍተኛ ፖሊስ ኦፊሰርን ጠቅሶ የአውስትራሊያው ኤቢሲ ዘግቧል፡፡

በኬንያ መንግሥት ተፈላጊው መሐመድ መሐሙድ

በኬንያ መንግሥት ተፈላጊው መሐመድ መሐሙድ

በተለይ ከጥቃቱ በስተጀርባ ዋና አቀናባሪና በጋሪሳ ከተማ የእስላማዊ ትምህርት ቤት መምህር እንደነበር የተጠቆመው መሐመድ መሐሙድ የገደለ ወይም ያለበትን የጠቆመም እንዲሁም ይዞ ለሚያስረክብ የኬንያ መንግሥት ፖሊስ 215 ሺህ የአሜሪካን ዶላር (200 ሚሊዮን የኬንያ ሽንልንግ)እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል፡፡ ጥቃቱን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነ ፀሐፊ ባን ኪ ሙንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማኀበረሰቦች ያወገዙት ሲሆን፤ ታጣቂው አልሸዓባብ በበኩሉ ድርጊቱ የፈፀመው ከኬንያ ጋ ጦርነት ውጊያ ላይ ስለሆንን ነው ማለቱን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ 28 ቀን ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ከግራ ወደቀኝ  ፍቅረማሪያም አስማማው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድና ኢየሩሳሌም ተስፋው

ከግራ ወደቀኝ ፍቅረማሪያም አስማማው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድና ኢየሩሳሌም ተስፋው

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሆኑት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው ትናንት መጋቢት 21 አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው 28 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡ ፖሊስ እነ ብርሃኑ ተክለያሬድን ‹‹ለግንቦት 7 አባላትን መልምለው ወደ ኤርትራ በመላክና ቡድኑን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ተይዘዋል›› ብሏል፡፡

ጠበቃው እነ ብርሃኑ ተ/ክለያሬድ ለግንቦት ሰባት ሲመለምሉም ሆነ አባል ሲሆኑ የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ፖሊስ ‹‹ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምመረምራቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ሌሎች የምንይዛቸው ግብረ አበሮችም አሉ፡፡ መረጃ ያጠፉብናል፡፡›› በሚል ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ 28 ቀን ተፈቅዶለታል፡፡ ሚያዚያ 19 ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ፖሊስ ሌሎች ሰዎች ይዘውት የተነሱትን መሳሪያ በማሳየትም እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ እንደነበር ለማሳየት በመረጃነት አቅርቧል፡፡ ጠበቃው በበኩላቸው ‹‹የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምርመራ ለማድረግና መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጠርጣዎቹን ማሰር ተገቢ አልነበረም፡፡ ሌሎች ሰዎች የያዙትን መረጃ እነሱን ለመክሰስ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡›› ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ የታሰረበት ቤት መብራት ስለማይጠፋ አይኑ ላይ ለከፍተኛ ችግር እንዳደረሰበት ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ለ15 ደቂቃ ፀኃይ እንዲሞቁ ከሚፈቀድላቸው ውጭ ወደ ከታሰሩበት ቤት ውጭ መውጣት እንደማይፈቀድላቸውና ቤተሰቦቻቸውም እንዲጠይቋቸው እየተደረገ አለመሆኑን በቅሬታ አቅርበዋል፡፡

የዞን9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ ለሁለተኛ ቀን የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል

z9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በ19ኛው ወንጀል ችሎት እየታየ ያለው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ ለሁለተኛ ቀን ምስክሮችን አሰምቶ በአወዛጋቢ መልኩ ለሚቀጥለው መጋቢት 30 ቀጠሮ ይዞ ተጠናቋል፡፡

ከእለቱ ዋዜማ ቃለ መሃላ ፈጽመው ሳይሰሙ የቀሩት ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቃለ መሃላ በቀደመው ቀን በመግባታቸው ቀጥታ ወደ ምስክርነት ቃላቸው ተገብቷል፡፡ በሃያ ስድስተኛው የፍርድ ቤት ውሎ ተሰሙት ምስክሮች

7ተኛ ምስክር -ተስፋዬ መንግስቴ የመሰከሩት አቤል ዋበላ ላይ ሲሆን ከመንገድ ላይ ፓሊስ ሲፈትሹ አንዲታዘቡ ጠይቋቸው ቤቱ እና መስሪያ ቤቱ የተገኘው ሲዲ መጽሄቶች እና መጸሃፍት ላይ ሲገኙ አይቼ ፈርሜያለው አቤልም ፈርሟል ብለዋል፡፡

8ተኛ ምስክር- አቶ በረከት ጌታቸው በተመሳሳይ መንገድ ላይ ፓሊስ ታዘቡልኝ ብሎ የበፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ መታዘባቸውን በፍቃዱ የፈረመባቸው ነገሮች ላይም መፈረማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጽሁፎቹ አማርኛ እና አንግሊዘኛ ከመሆናቸው ውጪ የሚያስታውሱት ይዘት አንደሌለ ተናግረዋል፡፡

9ኛ ምስክር – አቶ አንድነት ስሜ ይባለሉ አጥናፍ ብርሃኔ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ቤቱ የተገኙ ወረቀቶች ላይ እሱም ፈርሟል አኔም ፈርሜያለው ብለዋል፡፡ የተገኙት ወረቀቶች አማርኛ እና እንግሊዘኛ ሲሆኑ ሴኩሪቲ ኢን ኤቦክስ የሚል መጽሃፍ አለበት ብለዋል፡፡ በይዘቱ ላይ አቃቤ ህግ አንዲመሰክሩ ቢጠይቅም ጠበቆች በይዘቱ ላይ ለመመስከር ስላልተመዘገቡ አንዳይመሰክሩ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲመሰክሩ ቢፈቅድም ምስክሩ ምንም ይዘት አንደማያስታውሱ ተናግረዋል፡፡

10ኛ ምስክር -አቶ ታምራት ዓለሙ የሚባሉ ሲሆን አቤል ዋበላ ቤት ሲፈተሽ እንደነበሩ በመግለጽ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል፡፡ አቤል የፈረመባቸው ነገሮች ላይ ፈርመናል ያሉ ሲሆን የነጻነት ጎህ ሲቀድ መጽሃፍ እስልምና በኢትዬጲያ የሚል መጽሃፍ አዲስ ጉዳይ መጽኄቶች አና እምነት እና ተስፋ በኢትዬጲያ የሚሊ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡ ሲዲም ተገኝቷል ብለዋል፡፡ የፍተሻውን ቀን ሚያዝያ 11 ነው ብለዋል፡፡ ( ጦማሪ አቤል የታሰረው ሚያዝያ 17 አንደሆነ ይታወቃል)

11ኛ ምስክር አቶ ፋሲል ግርማ ሲሆኑ በፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤት ውስጥ ተገኙት እቃዎች እና ሰነዶች ላይ ተከሳሹ ሲፈርም እኛም ፈርመናል ብለዋል፡፡ የተገኙትን ሰነዶች ብዛትና ይዘት እንደማያሰታውሱም ተናግረዋል፡፡

12ኛ ምስክር አቶ ደረጀ አበበ የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ባልደረባ ሲሆኑ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ቢሮ ሲፈተሽ ፓሊስ ታዘቡ ብሏቸው አንደነበሩ እና ተገኙት ወረቀቶች ላይ ፈርመው ቢሮውን ዘግተው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የፈረሙበትን ወረቀት ይዘት የማያስታውሱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

13ኛ ምስክር አቶ አክሊሉ ሃይለማርያም ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ስሙን ብቻ ነው የማስታውሰው በማለት ያዬትን ተናግረዋል፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዬን አካባቢ ያለው ቤቱ ሲፈተሽ የተገኙ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ጽሁፎች የግል ማስታወሻዎች ሲም ካርድ እና መጽሃፍት የተገኙ ሲሆን ሁሉም ላይ በፍቃዱም ሲፈርም እኔም ፈርሜያለሁ ብለዋል፡፡

በ14ኛ ምስክርነት አቶ የማነ ብርሃኔ የተባሉ ግለሰብ ቀርበው የነበር ቢሆንም አቃቤ ህግ ‹የተለየ ነገር አያስረዱልኝም› በሚል ምስክሩ ሳይደመጡ እንዲመለሱ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ምስክርነታቸው ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ አጠቃላይ 41 ምስክሮችን እንዳስመዘገበ በመጥቀስ ትናንት ካስመዘገባቸው 17 ምስክሮች ውጭ ሌሎቹን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳጣቸው በመግለጽ ማቅረብ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን 8ኛ፣ 9ኛ እና 27ኛ ላይ አቃቤ ህግ ያስመዘገባቸው ምስክሮች መጥሪያ ደብዳቤ ደርሷቸው እንዳልተገኙለት ገልጹዋል፡፡

Ethiopia-Federal-High-Court-300x194

ፍርድ ቤቱ የጠበቆችን (የተከሳሾችን) አስተያየት ጠይቆ ነበር፡፡ በዚህም ጠበቆቹ አሉ የተባሉትን ምስክሮች ፌደራል ፖሊስ ሌሎችን በአድራሻቸው ፈልጎ ማቅረብ ይገባው እንደነበር፣ እግዚቢት ላይ የተመሰከሩት ቃሎችን ፍ/ቤቱ እንዳይመዘግባቸው ማመልከት፣ እንዲሁም ያልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ምስክር መስማቱ ተገቢ እንዳልሆነ በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አቃቤ ህግ ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ካለበትም ምስክሮቹን በተሰጠው ቀን ( የማስረጃ መስማት ለሶሰት ተከታታይ ቀናት አንደተቀጠረ ይታወሳል) እንዲያቀርብ በማሳሰብ የደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በፍርድ ቤቱና በአቃቤ ህግ በኩል እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ባልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ይህን ያህል ጊዜ መውሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ጦማሪ ናትናኤል በበኩሉ ‹‹አቃቤ ህግ ያቀረበውን ሰምተናል፤ እኛ ብቻችንን አይደለም የታሰርነው፤ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችንም አብረውን ታስረዋል፡፡ በህሊና እና በኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰብን ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሁሉ ‹ውሳኔው ላይ አብሮ እንዲታይልን እናመለክታለን ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጠዋት ምስክር መስማቱን ሂደት አጠናቆ ለከሰአት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ከሰአት በኋላ ሁለት ጉዳዬች ብይን ሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው የምስክሮች ቃል ከመዝገቡ ጋር አንዲያያዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀሩ የተባሉት ሶስት ምስክሮች ታስረው ለመጋቢት 30 አንዲቀርቡ እና አቃቤ ህግ ተጨማሪ ምስክሮች አሉኝ ካለም አንዲያቀርብ ነው፡፡በዚህም መሰረት ለሶስት ቀን የታቀደው ምስክሮችን መስማት በአንድ ቀን ከግማሽ ተጠናቋል፡፡ ጠበቆች አቃቤ ህግ ቀድሞ በተወሰነው ቀን ምስክሮችን ሊያቀርብ ሲገባ ሌላ ቀነ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም በማለት ያቀረቡትን ተቃውሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮቹን በፌደራል ፓሊስ እያስፈለኩ ስለሆነ ተከሳሾ ማረሚያ ቤት እንዳሉ ለፍለጋው ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ነበር ፡፡

ጠበቆቹ አቃቤ ህግ የእግዚቢት ሰነዶችን በተመለከተ የመዝገብ ቁጥሩን ገልጾ እንዲቀርብ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ በትዕዛዙ መሰረት አቃቤ ህግ ዛሬ የመዝገብ ቁጥሩን ይዞ መቅረብ የነበረበት ቢሆንም፣ ጠበቆቹ ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ሲጠይቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልሰጠንም በሚል ክዷል፡፡

ምንጭ፡- ዞን 9 ማኀበራዊ ገፅ

ፍትህ መረገጡን በአደባባይ አስመስክረናል፤ሃላፊነታችንንም ተወጥተናል!

ተክሌ በቀለ  (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ተክሌ በቀለ (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ለኔ እዉነተኛው የአንድነት ፓርቲ ትናንት መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ውሳኔ ተቀብሯል፡፡ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል እንደሆነ ቀድም ሲል አውቀናል፡፡ ዳኛ ብርቱኳንም፣ ፍርህይወትም ዳግም አልተከሰቱም፡፡ እንደ ኢህአዴግ የምርጫ ውጤት 99.6 ከመቶ አመራሩና አባላቱ በምርጫ ቦርድ እንዲበተኑ የተበየነበት እንዲሁም በደጋፊዎች የተገዛ ንብረት ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በመንግስት ታጣቂ ፖሊሶች የተዘረፈበት አንድነት የፍትህ ተቋሙን ለመፈተሸ ምርጫ ቦርዱን መክሰሱ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድን መክሰሳችን አግባብ እንዳልሆነ አንቀጽ ተጠቅሶ ከማስፈራሪያ ጋር ክሱ ዉድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም ፍትህ መረገጡን ባደባባይ አስመስክረናል፤ሃላፊነታችንንም ተወጥተናል፡፡ ቀጣዩን በቀጣይ ሂደት የምናየዉ ይሆናል፤እንደሚፈልጉት ተበትነን አንቀርም፡፡ አንድነቶች በያለንበት እንረጋጋ!!

ታላቋ ምዕራብ አፍሪካዊት ሃገር ናይጀሪያ እዚህ የደረሰችዉ ዉድ ዋጋ ከፍላ ነዉ፡፡ ከናይጀሪያም በላይ ዋጋ ብንከፈልም በልተዉ በማይጠግቡ በሎች ትግሉ እየተነጠቀ ዛሬም እዛዉ ላይ ነን፡፡ ታላቅዋ የምስራቅ አፍሪካ ኮከብ ሀገረ ኢትዮጵያ በልማት ስም ክብሯ እንዲወርድ እየተደረገች ትገኛለች፡፡ እናም በዲፕሎማሲ፤በዲሞክራሲ፤በኢኮኖሚም ይሁን በሁለንተናዊ ልማት የአለም ማህበረሰብ በአፍሪካ ትኩረት ናይጀሪያ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈለገዉ ለክፍለ አሁጉሩ የደህንነት አጋርነት ብቻ ነዉ፡፡

የናይጀሪያ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና(የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ትብብርና ዉህደት ያስከተለዉን ዉጤትም ልብ ይሏል) የተወዳዳሪ ግለሰቦች ሚና ቀላል ባይሆንም ለናይጀሪያ ተስፋ የሆናት ግን ህዝቡ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያችንም የለዉጥ ተስፋ ህዝቡ ነዉ፡፡ በዚህ ወቅት የተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡