የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
ቀን 02/06/2007 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡ የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡
ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡
በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡
ግልባጭ
_ ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
_ የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
_ ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት
_ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)
_ ለእምባ ጠባቂ
_ ለአሜሪካ ኢምባሲ
_ ለእንግሊዝ ኢምባሲ
ከሰላምታ ጋር
ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት በደረሰባቸው ችግር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
የህዳር 27 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የጠራው የአዳር ሰልፍ ወቅት ተይዘው በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ እና ለሶስት ቀን የስኳር በሽታ መድሃኒት እንዳይገባላቸው በመከልከላቸው ለህመም የተዳረጉት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ፀኃፊ መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ ከእስር ከተፈቱበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወር ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ይዘውት የነበረውን የስኳር በሽታ መድሃኒታቸውን በመቀማታቸው፣ እንዳይገባላቸው በመከልከላቸውና በወቅቱም ህክምናም ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ህመም በመዳረጋቸው ለሁለት ወር ያህል ዘውዲቱ ሆስፒታል ቆይተዋል፡፡
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ዘውዲቱ ሆስፒታል ከገቡበት ታህሳስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም በቦሌ ሚካኤል እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በፊት ከኬንያ በህወሓት ደህንነት ታፍነው አዲስ አበባ ቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት ታስረው በህወሓት ፖሊሶችና ደህንነቶች በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ድብደባ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ያላወጣቸው የተለያዩ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ይታወቃል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ሚዲያ አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊ አለመሆኑን አስታወቀ
ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድ ያወጣው ረቂቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን አስታወቀ፡፡
ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎችን በረቂቅ የሰዓት ድልድሉ ላይ ጊዮን ሆቴል ጋብዞ ውይይት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ኃላፊዎች ረቂቁን ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና ሌሎች ኃላፊዎችም በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡
የኢብኮ/ኢቴቪ ኃላፊዎች ባቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀም ረቂቅ ድልድል መሰረት 55 ፐርሰንት በፓርላማ መቀመጫ ወንበር ላላቸው ፓርቲዎች፣ 20 ፐርሰንት ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ብዛት እንዲሁም ቀሪ 25 ፐርሰንቱ ለሁሉም ፓርቲዎች በዕኩል የሚከፋፈል እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጹት፣ ረቂቅ የሚዲያ አጠቃቀሙ ድልድል ሲወጣ እንደ መስፈርት የተጠቀሙባቸው ነጥቦች ችግር ያሉባቸው ናቸው፡፡
‹‹በእኛ እምነት መስፈርቱም ልክ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የሚዲያ ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ሲወጣ ሁለት መስፈርቶች በቂና ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እነዚህ ነጥቦች በሚቀርቡ እጩዎች ብዛት እና በእኩልነት የሚከፋፈል የድልድል መስፈርት መሆን አለባቸው›› ብለዋል አቶ ይድነቃቸው፡፡
በእርግጥ ረቂቁን ያቀረበው ኢብኮ እንደ መመዘኛ መስፈርት የተጠቀመው ‹‹እኩልነትና ፍትሃዊነት›› የሚሉ መርሆዎችን ነው፡፡ ‹‹ኢብኮ በቃላት ደረጃ የገለጻቸው ‹ፍትሃዊነትና እኩልነት› በተግባር ረቂቅ ድልድሉ ላይ አልታዩም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በእኩልነትና ፍትሃዊነት መርሆዎች ላይ ችግር የለበትም፡፡ መርሁን መሰረት አድርጎ ወጣ የተባለው የሚዲያ ድልድል መጠን ግን በትክክል መርሁን የተከተለ አይደለም፡፡ ስለሆነም ለውጥ ሊደረግበት ይገባል›› ብለዋል አቶ ይድነቃቸው፡፡
አቶ ይድነቃቸው የሰዓት አጠቃቀም ድልድሉ ላይ ስንወያይ ነጻ ሚዲያ በሌለበት፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተገደበበት፣ ጋዜጠኞች በታሰሩበትና በተሰደዱበት፣ አማራጭ የሚዲያ ተቋማት በሌሉበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት ላይ በህዝብ ሀብት በሚተዳደሩ ሚዲያዎች ላይ የፍትሃዊነት ችግር ይዘን መወያያታችን አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሳንሱር በህገ-መንግስቱ ተነስቷል፤ ይሁን እንጂ ኢብኮ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት ለህዝብ የሚያስተላልፏቸው አማራጭ ሀሳቦችና ፖሊሲዎቻቸውን በቆርጦ ቀጥል ሲያዛባ እናስተውላለን፤ ይህ ሁኔታ መወገድ ያለበት ነው፡፡››
በውይይቱ ላይ ኢህአዴግ የድልድሉ መስፈርት ላይ እንደሚስማማ በመግለጽ፣ በፐርሰንቱ የተቀመጠው መጠን ላይ ግን መሻሻል እንዲደረግ እንደሚፈልግ መግለጹ ታውቋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በወሰኑብን ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ተነጥቀናል ያሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት› በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስታወቁ፡፡
በእነ በላይ ፍቃዱ አመራርነት አንድነት ፓርቲን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ዛሬ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከቀድሞ ፓርቲያቸው አንድነት ጋር የፕሮግራምም ሆነ የስትራቴጂ ተመሳሳይነት ወዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
መግለጫውን የ”ቀድሞው አንድነት ፓርቲ” አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔው አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝ እንዲሁም የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ሌሎችን በመወከል ሰጥተዋል፡፡
“የምናምነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላማዊ ትግል ለመምራት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ብቁ ነው ብለን በማመን ፓርቲውን ተቀላቅለናል” ብለዋል በመግለጫው ላይ የተወከሉት አዲሶቹ የሰማያዊ አባላት፡፡
በዚህ መሰረትም በርከት ያሉ አመራሮችና አባላት በይፋ የሰማያዊ ፓርቲ የአባልነት ፎርም ሞልተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ወደ ሰማያዊ ቢሮ ባቀኑበት ወቅት፤ፖሊስ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ በመግባት “በሰማያዊ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ ሰለሰማን ነው” በሚል ለፓርቲው አመራሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ከስፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል፡፡
አይካ-አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መቱ
በቱርክ ባለሃብቶች የተያዘው የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች ከጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምረው የስራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ኩባንያው በየ አመቱ በሚያደርገው የደመወዝ ጭማሬ መሰረት በዘንድሮው አመት የተሻለ የደመወዝ ጭማሬ እንደሚያደረግ የገለጸበትን ወረቀት ለሰራተኞቹ በትኖ የነበር ቢሆንም ቅዳሜ ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለሰራተኞቹ በተበተነው ሌላ ወረቀት የደመወዝ ጭማሬው ከተጠበቀው በታች ሆኖ በመገኘቱ ሰራተኞች ‹‹ስራ አንሰራም›› ብለው ፋብሪካው ግቢ ውስጥ ተቀምጠው ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ከሰኞ 25 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የድርጅቱ ሰራተኞች አድማውን አጠናክረው እንደቀጠሉ ታውቋል፡፡
ቅዳሜ ጥር 23/2007 ዓ.ም ሰራተኞቹ የደመወዝ ጭማሬውን ከሰሙ በኋላ “ስራ አንሰራም” በማለታቸው የፋብሪካው ኃላፊዎች “የአንድ ወር ገደብ ስጡንንና እናስተካክል” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰራተኞቹ በበኩላቸው “በሳምንት ጊዜ ውስጥ ይስተካከል” የሚል ሀሳብ አቅርበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም በሁለቱ መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ሰራተኞቹን እየነጠሉ ለማናገር ያደረጉት ሙከራም እንዳልተሳካላቸው ተገልጾአል፡፡
ቅዳሜ ጥር 23 ዓ.ም ዝቅተኛ ነው የተባለው የደመወዝ ጭማሬ ምክንያት ስራ ሳይገቡ መስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው የዋሉት የአይካ አዲስ ሰራተኞች ከትናንት ሰኞ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ መምታታውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አይካ አዲስ ከ8 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት የገለጸችው አንዲት የድርጅቱ ሰራተኛ ድርጅቱ ተመሳሳይ ስራ ላይ በተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች መካከል ደመወዝን ጨምሮ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለና በኢትዮጵያውያን ላይ መድሎ እንደሚፈጽም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡ ከዚህ በደል በተጨማሪ ፋብሪካው የገባውን ቃል አለመፈፀሙ ሰራተኞቹ ስራ እንዲያቆሙ ምክንያት እንደሆነም ሰራተኞቹ ገልፀዋል፡፡




