Tag Archives: EPRDF Democracy

የማያዳምጥና የማያነብ መንግስት እድሜው ስንት ነው?

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

bedlu“መንገዱ በዚህ ወር ይጠናቀቃል፤ ባቡሩ በዚህ ወር ስራ ይጀምራል” ይሉናል፡፡ መንገዱ ወዴት ያደርሳል? ባቡሩ ወዴት ይወስዳል? ልጆቻችን ወጥተው የማይገቡበት መንገድ፣ የማይሳፈሩበት ባቡር ምን ያደርጋል? መንገዱ ሲሰፋ፣ መጓጓዣው ሲበረክት የልጆቻችን ፍርሀት፣ የእኛ የወላጆች ጭንቀት ከመበርከቱ በቀር ትርፉ ምንድነው?

ቁሳዊ ልማት ብቻውን ማህበረሰባዊ እድገት አያመጣም፤ ቀውስ ካልሆነ በቀር፡፡ የማህበረሰብህን . . . የነገ ወራሽህን. . የወጣቱን አስተሳሰብና አሰራር ሳታለማ (ሳትለውጥ) ታክሲ ብታመጣ፣ ወንዝ ውሀ ስትቀዳ፣ ጫካ እንጨት ስትለቅም ትደፈር የነበረችውን ልጃገረድ፣ ታክሲ ውስጥ ታስደፍራታለህ፤ ነገም ባቡር ውስጥ (ዛሬ በህንድ ሀገር ባቡር ማለት ብዙ የማያስከፍል ፔንሲዮን ነው)፡፡ እኛ ሀገር ብዙ መንገድ ብዙ ወንጀል፣ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሰፊ ዝርፊያ፣ ትልቅ ባለስልጣን ትልቅ ዘራፊ ከማለት የተለየ ፍቺ የሚኖረው መቼ ነው?

“ልማታዊ መንግስት ነን፣ ኒዎ ሊብራሊዝምን እንቃወማለን” ይሉናል፡፡ በልማት ስም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችንን አንጠፍጥፈው ወሰዱት፡፡ ይበጃል ያልነውን ስንጽፍና ስንናገር ጸረ ልማት ይሉናል፡፡ ደፈር ብለን መብታችንን ከጠየቅን አሸባሪ ይሉናል፡፡ በየእስር ቤቱ ያጉሩናል፤ ድንበር አሻግረው ያሰድዱናል፡፡ መብታችንንና የመናገር ነጻነታችን ልማታዊ ላሉት መንግስት ጭዳ አደረጉት፡፡

“ልማታዊ አይደላችሁም! ኒዎ ሊብራል ናችሁ አንላቸዋለን፡፡ የምትኖሩበት ቤት፣ የምትነዱት መኪና፣ ልጆቻችሁ የሚማሩበት ትምህርት ቤት (ሀገር)፣ የምትገበያዩበት ሱፐር ማርኬት፣ የምትዝናኑበት ሪዞሪት. . . የልማታዊነት ሳይሆን የኒዎ ሊብራሎች መገለጫ ነው፡፡” እንላቸዋለን፡፡

“ዝም በሉ! የምንላችሁን አሜን ብላችሁ ተቀበሉ” ይሉናል፡፡ ማተሚያ ቤቱ የእነሱ ነው፤ ራዲዮና ኢቲቪው የእነሱ ነው፤ አዋጅና መመሪያ የሚጥልብን ፓርላማ የእነሱ ነው፡፡ አዋጅ ጣሳችሁ፣ አሸበራችሁ፣ እራለ የሚይዘን ፖሊስ የእነሱ ነው፤ ከፖሊሶቹ ተቀብሎ የሚፈርድብን ፍርድ ቤት የነሱ ነው፡፡ ያለ ወንጀሉ ተከስሶ የሚፈረድበት ዜጋ እሱ ራሱ የራሱ አይደለም፡፡ ራሳችንም የእነሱ ነን፡፡ የእኛ የሆነው ተስፋችን ብቻ ነው! ለሀገራችንና ለወገናችን ያለንን ብሩህ ተስፋ ምንም ሊያስረው አይችልም፡፡ የኔ ተስፋ ልጆቼ ውስጥ፣ ያልተወለደው የልጆቼ ልጆች . . . . . ውስጥ አለ፡፡ ተስፋ የሚታሰረው፣ የሚሞተው እርኩስ፣ ለሀገርና ለወገን የማይበጅ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ዛሬ አትጻፉ ተብለናል፡፡ አትናገሩ ተብለናል፡፡ አንጽፍም፡፡ አንናገርም፡፡ ከተማው ጭር ብሏል፡፡ ሀገሩ ጭር ብሏል፡፡ መንግስትም ጭርታው ተስማምቶታል፡፡ እኛ ግን አንጽፍም እንጂ እንነበባለን፤ አንናገርም እንጂ እንደመጣለን፡፡ የማያነበንና የማያዳምጠን የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው፡፡ አንድ መንግስት ህዝቡን ሳያዳምጥና ሳያነብ ምን ያህል እድሜ ይኖራል? እንጃ! . . . . . አንድ ቀን መንግስት ህዝብን ማንበብ፣ ህዝብን ማዳመጥ ግዴታው ይሆናል፡፡ አቤት ታዲያ ያኔ የሚያነበው መአት! የሚያዳምጠው ቁጣ! ያኔ ማንም መንግስትን መሆን አይመኝም፡፡ እውነቴን እኮ ነው፣ አሁን 1983 ዛሬ ቢሆን ደርግን መሆን የሚመኝ አለ?

 

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል በሰማያዊ ፓርቲ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ተገለፀ

  • “ማስጠንቀቂያውን እንደ ቁም ነገር አንቆጥረውም” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

    • “ስርዓቱ ምን ያህል ዝቅጠት ውስጥ እንደገባ ያሳያል” አቶ ግርማ በቀለ

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ ያስተባበረው የ9ኙ ፓርቲዎች የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ፀረ ህገ መንግስት በመሆኑና ነዋሪዎችን ሰላምና ፀጥታ በማወኩ በቀጣይ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ካደረገ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠነቀቀ፡፡

    አስተዳደሩ ትናንት ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ፤ ህዳር 6 ቀን “ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ለህዝብ የተሰራጨው በራሪ ወረቀት ህገ ወጥ መሆኑን፣ ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መሪነት ሊደረግ የነበረው አደባባይ ስብሰባ ህገ ወጥ እንደነበርና በወቅቱ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከፖሊስ ጋር ግብ ግብ ከመግጠማቸውም በተጨማሪ የአካባቢውን ህዝብ ሰላምና ፀጥታ አውከዋል ሲል ከሷል፡፡ አስተዳደሩ አክሎም ፓርቲው የአደባባይ ብጥብጥና ሁከት በመፍጠሩ እርምጃ እወስዳሉ ሲል ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ልኳል፡፡

    በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ በቀን ህዳር 5 ቀን 2007 ዓ.ም ለአስተዳደሩ የእውቅና ደብዳቤ ያስገባ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የሰማያዊ ፓርቲና የትብብሩ አመራሮች አስተዳደሩ የላከው ደብዳቤ ከገዥው ፓርቲ ፍርሃት የመነጨ በመሆኑ ከእንቅስቃሴያቸው እንደማይገታቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብርና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ደብዳቤው ስርዓቱ የደረሰበትን መጠነ ሰፊ የፍርሃት ደረጃና ትግሉን ይበልጥ አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን የሚያሳይ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

    pressreleaseማስጠንቀቂው የደረሰው ሰማያዊ ፓርቲና የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹የረዥም ጊዜ የመንግስት ታሪክ ባላት አገር የከተማ አስተዳደር ነኝ ያለ አካል እንዲህ አይነት ደብዳቤ መጻፉ ኢትዮጵያ ምን ያህል ውድቀት እንደገጠማትና እኛም እንደ ህዝብ የውርደት ካባ መከናነባችንን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ ሰማያዊ አሊያም የትብብሩ ሊቀመንበርነት ሳይሆን እንደ አንድ ይህን ያህል ውርደት እንደገጠማት አገር ዜጋ ሀፍረት ይሰማኛል፡፡›› ሲሉ አስተዳደሩ የላከው ደብዳቤ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

    ማስጠንቀቂያው በቀጣይ የፓርቲውም ሆነ የትብብሩ እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ችግር ካለ በሚል ለኢንጅነር ይልቃል ላነሳነላቸው ጥያቄም ‹‹ደብዳቤው የኢህአዴግ ፍርሃት ገደብ መልቀቁንና ትግሉም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴን ብቻ ሳይሆን የራሱን ጥላም አለማመን ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡ እኛ ይህን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደቁም ነገር አንቆጥረውም፡፡ ይበልጡንም ለትግሉ በተጠናከረ መንገድ እንድንነሳሳ ይገፋፋናል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

    በተመሳሳይ የትብብሩ ፀሐፊና የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ ‹‹ማስጠንቀቂያው ትብብሩ በየሳምንቱ ያቀዳቸውን መርሃ ግብሮች ለማደናቀፍ ያለመ ነው፡፡ ከአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት እንዲህ አይነት አሳፋሪ ደብዳቤ መጻፉ ስርዓቱ ምን ያህል ዝግጠት ውስጥ እንደገባ ያሳያል፡፡ ሆኖም ማስጠንቀቂያው ከእንቅስቃሴያችን አይገታንም፡፡ እንዲያውም ለዚህ የስርዓቱ ዝቅጠት የሚመጥን ስልት ነድፈን በጋራ እንድንሰራ ያደርገናል፡፡›› ማለታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ!

ግልጽ ደብዳቤ ”ለጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ

ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ!

ሠላም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!? እንዴት ነዎት? ያስታውሱ ከሆነ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢከፊሉ የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች ‘ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ’

“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎትን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሕገ መንግስታችንን ድንጋጌዎች እየጣሱ ነውና እርስዎም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 74/13/ መሠረት ሕገ መንስቱን የማስከበርና የማክበር ግዴታ ስላለብዎት ሕገ መንግስቱን ያክብሩ”በማለት አንዲት አጭር ደብዳቤ ፅፈንልዎት ነበር፡፡

ድንገት በተለያዩ ምክንያቶች የጻፍንልዎትን ደብዳቤ ካላነበቡት ወይም ማስታወስ ካልቻሉ ዛሬ ይሄን ማስታወሻ ስለምንፅፍልዎት ግለሰቦች አንድ ሌላ ማስታወሻ እንስጥዎ፡ ከ6ወራት በፊት /በሚያዚያ 2006 ዓ.ም/ ሶስት ጋዜጠኞችንና ስድስት ጦማሪያንን ‘ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ጠርጥሬያችኋለሁ’ በማለት መንግስትዎ ልማታዊ ርምጃ (አብዮታዊ ርምጃ እንደሚባለው) ወስዶ ነበር፡፡

እኛም የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች የዚህ ‘ልማታዊ ርምጃ’ ሰለባ የሆንን ግለሰቦች ነን፡፡በርግጥ ከሁለት ዓመታት በፊት ‘ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስቱን’ ያስከብሩልን በማለት ጥያቄ ያቀረብንልዎት ግለሰቦች ‘ከ6 ወራትበፊት ሕገ መንግስቱን ለመናድ ሞክራችኋል’ በማለት መንግስትዎ ሲያስረን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ጠይቀን ሕገ መንግስቱን ለመናድ በመሞከር ወንጀል ተጠርጥረን ስንታሰር እስሩ በጣም ግራ አጋብቶን ነበር፡፡በዚህ ያልቆመው መንግስትዎ ክሱን ‘ሕብረተሰቡንና ሀገሪቱን ለማሸበር አቅዳችኋል ሞክራችኋል አሲራችኋል…’ በማለት ወደ ‘ሽብርተኝነት’ያሳደገው ሲሆን እርስዎም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳብዎትን ሲሰጡ ስለተመለከትንዎ ትንሽ ቅሬታ ይዘን መጣን፡፡

በቅድሚያ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በትንሹ ብናስረዳዎት ቅሬታችንን ለመረዳት ያስችልዎታልና አንዳንድ ጉዳዮችን እንንገርዎት፡፡

zone9ይሄን ማስታወሻ በምንፅፍልዎት ወቅት ከታሰርን ከ 200 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፣ነገር ግንጉዳያችን ገና በቅድመ ክስ (Pre Trial) የክርክር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም መንግስትዎ እንኳን ለእኛ ለተከሳሾች ለከሳሽ አካልም ግልፅ ያልሆነ ክስ በማቅረቡ ነው፡፡ ይሄንንም ስንል ልትፈፅሙት ነበር የተባለው ‘የሽብርተኝነት ድርጊት’ ሳይጠቀስ ‘በቃ የሽብርተኝነት ድርጊት ልትፈፅሙ ነበር’ በማለት በጨበጣ ስለመጣብን ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንግዲህ የብዙ ድብደባ፣ ዛቻ እና ስድብ ሰለባዎች ከሆንን በኋላምየቀረበው ይሄ ክስ ነው ከ6 ወራት በኋላም ተከሳሾች ከሳሾቻችንምሳንረዳው በየቀጠሮው እየታሸ ነው የሚገኘው፡፡ ‘የተፋጠነ ፍትህ’ ሕገ መንግስትዊ መብት ነውና የተፋጠነ ፍትህ ይሰጠን፣ እርስዎምይሄን ሕገ መንግስታዊ መብት ያክብሩ እያልንዎት አይደለም ‘ሕገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ’በማለት ‘ጥፋት የሚያሳምን’ ( አንዱ የዚህ ደብዳቤ ጸሃፌ ጦማሪ ጥፋት ብሎ አንዲፈርም የተገደደው ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለህገመንግስቱ ይከበር ማለቴ ጥፋት ነው ብሎ መሆኑ መንግስትዎን መልክ ግልጽ አድርጎ ያሳያል) መንግስት አለዎትና ይህ ጥያቄ አንደሚበዛብዎትእናውቃለን፡፡

ይልቁንም ቀላልና ግልፅ ቅሬታን ነው ይዘን የመጣነው፡፡ ይሄውም የኢፌድሪ ሕገ መንግስትበአንቀፅ 20/3/ ላይ

‘የተከሠሡ ሰዎች[…] በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር[…]መብት አላቸው::’

በማለት የደነገገ ሲሆን፣ ይሄንን ሕገ መንግስታዊ መብትም ማንኛውም የመንግስት አካል እንዲሁም ግለሰብ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እርስዎና መንግስትዎም በተደጋጋሚ ‘ሕገ መንግስቱ ሳይሸራረፍ እናስከብራለን’ ይላሉና ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የምታውቁት ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ከታሰርን ወዲህ ስለእኛ የእስር ጉዳይ በተጠየቁባቸውጊዜያት ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ ‘ፍርድዎትን’ በተደጋጋሚ ሲሰጡ ታዝበናል፡፡ እናስረዳዎ፡- ሐምሌ 12/2006 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣሚ መግለጫ ላይ ስለእኛ እስር ጉዳይ ለቀረበልዎት ጥያቄ ሲመልሱ፡-

‘ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት ውስጥ አንዴከገቡ በኋላ ብሎገር ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ ማለት ዋጋ የለውም’

በማለት ብዙ ነገሮችን ተናገሩ፡፡ ይሔውልዎት ስህተትዎ፡-

1. የክሳችን ዋነኛ ጭብጥ በሃገርውስጥ ‘የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም ‘የሽብርተኝነት’ ተግባራትን ለመፈጸም አሲረዋል፡ አቅደዋል… የሚል እንጂ፣ እርስዎም እንደሚሉት ‘ሰንሰለት’ ምናምን አይደለም፣

2. እሺ አሸባሪዎችም ይበሉን፣ነገር ግን ሕገ መንግስቱ እንደሚደነግገው በፍርድ ቤት ‘ጥፋተኝነታችን’ እስሚረጋገጥ ቢጠብቁስ ምናለበት? ይህ የሚያመለክተው እርስዎም እንደ ማእከላዊ መርማሪዎች ነፃ ሆኖ የመገመት (presumption of innocence) መብታችንን እያከበሩልን እንዳይደለ ነው፡፡

ይሄ ነገር የሆነው በድንገት ሊሆን ይችላል ብለንዝም ብንልም እርስዎ ግን በድጋሚ ጥቅምት 6/2007 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባል ለቀረበልዎ ጥያቄሲመልሱ፡-

“የብሎገር ጭምብልአጥልቆና በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሸሽጎ ከተከሳሽነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ሽብርተኝነትን መዋጋታችን ይቀጥላል…” እያሉ እርስዎ ያሉትን የብሎገር ጭምብል አውልቀውና ተሸሸጉበት ያሉትን የጋዜጠኝነት ሙያመሸሸጊያ አፍርሰው ባንዴ ‘የአሸባሪነት’ ካባ ደረቡልን፡፡

ክቡር ጥቅላይ ሚኒስቴር፣ እያልን ያለነው የአንድ ሰው ‘አሸባሪነት/ወንጀለኝነት’ የሚረጋገጠው በፍርድ ቤት እንደሆነ ሕገ መንግስቱ ደንግጎ እያለ፣ እርስዎ ግን ነፃ ሆኖ የመገመት መብታችን ወደ ጎን ብለው እንደ ከሳሽም እንደፈራጅም በመሆን ‘አሸባሪዎች’… እያሉን ይገኛሉ ነው፡፡

ምናልባት ‘ስራ አስፈጻሚው ከሳሽ ነውና እኔም የስራ አስፈጻሚው አካል መሪ ስለሆንኩ የፈለኩትን አስተያየት የመስጠት መብት አለኝ’ ብለው ከሆነ፣ ሕገ መንግስቱን የማክበር ጉዳይ ‘ርስዎን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ላይ የተጣለ ግዴታነው፡፡ እርስዎ ‘L’e’tat, c’est moi’ ይሉት አይነት የራስ ግምት ውስጥዎ ከሌለ በስተቀር እንዲህ በግልፅ እየጠየቅንዎት ‘ሕገ መንግስትቱን አላከብርም’ በማለት ገና ዋነኛ ክርክሩ እንኳንያ ልተጀመረ ክስን (ዋነኛ ክርክር ካለው) መሠረት በማድረግ ከዚህ በኋላ እኛን ‘አሸባሪዎች’ አይሉንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ይህን ተመሳሳይ ምላሽ “በእርግጠኝነት አሸባሪ ናቸው” በሚል ቃና ለቢቢሲ ለኢንቢሲ ለመሳሰሉት አለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማትም መስጠትዎን ሰምተናል፡፡

ሌላው ልናስታውስዎ የምንፈልገው ጉዳይ እንደኛ አይነት የተራገበ( በሰፊው በታወቀ የአደባባይ)የፍርድ ጉዳይ ([un] popular case) ላይ የመንግስት አካላት አስተያየት (say) ያለውን ተፅእኖ እንዲያስቡት ነው፡፡እርስዎ በምክር ቤት ቀርበው የአሸባሪነት ፍርድ ከበየኑብን (አሁን እያደረጉት እንዳሉት) ፍርድ ቤትም ሆነ ሌሎች የመንግስትዎ አካላትምን ሊያስቡ እንደሚችሉ አስተውለውታልን?!

ይሄን ሁሉ ስንልዎ እንዲያው ሕጉን ያክብሩልን ለማለት ያክል ነው እንጅ፣ ከሽብርተኝነትጋር የሚያገናኘን ቅንጣት ያክል እውነት /A segment of fact/ እንደሌለና የሰው ልጆች መልካምና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸውከመመኘትና ለአገራችን ያገባናል ከማለት ያለፈ ሕይወትም ፍላጎትም እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን እርስዎና መንግስትዎም ያውቁታል፡፡ነገር ግን ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ጨዋታውን በግድ ካልተጫወታችሁ ተብለናልና እየተጫወትን ነው፡፡ የአሁኑ ጥያቄያችን ግን በጣም ቀላል ነው፣ ጨዋታው ገና በደንብ እንኳን ሳይጀመር ውጤቱን እይወስኑት ነው፡፡

እርስዎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ደረጃ በወጡ ሰሞን አብዛኞች የዚህ ማስታወሻፀሃፊዎች መጠነኛ ለውጥና ማሻሻዎች ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ሰንቀን “The First 100 Days” ወዘተ እያልን ብዙ ጠብቀንዎት ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በሚበልጥ ግዜ እንደተመለከትንዎ ግን ተስፋችን ፍሬ ሊያፈራልን አልቻለም፡፡ አሁንም አዲስ ተስፋ ሰንቀን ግን ፡- “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እባክዎትን ሕገ መንግስቱን ያክብሩ! የእኛንም መብት ያክብሩልን” እንላለን፡፡

‘’የብሎገር ካልሲ አድርጎ፣ የጋዜጠኝነት ጫማ ተጫምቶ የሽብረተኝነት ሰንሰለት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሕገ መንግስቱን ያክብሩልኝ ማለት ዋጋ የለውም!’’በማለት ተስፋችን ዋጋ እንደማያሳጡት ተስፋ አለን፡፡

ከአክብሮት ጋር

ጦማርያን ጋዜጠኞች

ጦማሪያን፡- ዘለዓለም ክብረት          ጋዜጠኞች፡-  ኤዶም ካሳዬ

ናትናኤል ፈለቀ                                ተስፋዓለም ወልደየስ

በፈቃዱ ኃይሉ                                   አስማማው ኃይለጊዮርጊስ

አጥናፍ ብርሃኔ

አቤል ዋበላ

ማህሌት ፋንታሁን

 

ምንጭ፡-  ዞን 9 (ኢትዮጵያ)

እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት ክሣቸው ተሰማ

  • ከአልሸባብና ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል
  • መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል

በጅሃድ ጦርነት እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም በጅማ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች፤ ሰሞኑን ፍ/ቤት ቀርበው ክሣቸው ከተሰማ በኋላ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ባለፈው ረቡዕ ክሣቸው በንባብ የተሰማው 7 ተጠርጣሪዎች፡- ጃፋር መሃመድ መሃሙድ ኑር፣ መሃመድ ሣኒ፣ መህዲን ጀማል፣ መሃሙድ አባቢያ፣ አንዋር ትጃኔ እና ሼክ ከማል አባጪብሳ ሲሆኑ በዋና ወንጀል ፈፃሚነት መሠረታቸውን ጅማ አካባቢ አድርገው፣ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድንና በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር ግንኙነት ነበራቸውም ብሏል – የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ጃፋር መሃመድ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ጦርነት ለማወጅና እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችለውን ስልጠና ከደቡብ አፍሪካ ወስዶ በመምጣት፣ ጅማ አካባቢ ለአላማው ማስፈፀሚያ ቦታ በመምረጥ አባላትን በመመልመል ሲንቀሳቀስ ነበር ተብሏል፡፡

123ተከሳሹ በደቡብ አፍሪካ ይገኛል ከተባለው አሸባሪ ቡድን የተላከለትን 80ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ተቀብሎ ለመሣሪያ መግዣ እንደተጠቀመበት የክስ መዝገቡ አመልክቷል፡፡ በጅማ አካባቢ ኮዳ በተባለ ጫካ ውስጥ የመለመላቸው ግለሰቦች ለ6 ቀናት ስልጠና እንደወሰዱና እንቅስቃሴው በፀጥታ ኃይሎች እንደተደረሰበት ሲረዳ፣ ወደ ሶማሊያ ሄዶ ከአልሻባብ ጋር ለመቀላቀል ሙከራ ሲያደርግ በግንቦት 2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡
በመዝገቡ የተካተቱት ቀሪዎቹ 6 ተጠርጣሪዎች አባል በመሆን፣ የሽብር ተልዕኮ በመቀበልና እስላማዊ መንግስት የመመስረት አላማቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ በፈፀሙት በሽብር ቡድን ውስጥ የመሳተፍ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤቱ ክሱን በንባብ ካሰማ በኋላ፣ የተከሳሾች ጠበቃ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለህዳር 10 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፡- አዲስአድማስ ጋዜጣ

ኢትዮጵያውያን በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት ፊትለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

europeዛሬ አርብ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ገዥው ስርኣት በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም የአውሮፓ ህብረት ዋና ፅህፈት በሚገኘው ቤልጂየም ብራሰልስ  ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ሰልፈኞቹ መንግስት በሽብር ስም አስሮ ክስ የመሰረተባቸውን እና የፈረደባቸውን የኢትዮጵያ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ፎቶ ግራፎችን በመያዝ፣ በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ በመንግስት የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በማሰብና በሀገሪቱ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግልፅ በመኮንን፤ የአውሮፓ ህብረት ሀገራትም እንዲህ ዓይነት ድርጊቱ በዜጎቹ ላይ ከሚፈፅም ስርዓት ጋር ትብብር ማድረጋቸው አቁመው ፖሊሲያቸውንና አቋማቸውን እንዲመረምሩ የሚጠይቅ ደብዳቤም ለህብረቱ ፅህፈት መግባቱን በስፍራው የነበሩ ምንጮች አስታውቃል፡፡

ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን በብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት ዋና ፅህፈት ካደረጉ በኋላ በከተማው ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመሄድ በሀገሪቱ እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማውገዛቸውን ተሰምቷል፡፡  የተቃውሞ ሰልፉን አስመልክቶ ከአውሮፓ ህብረትም ሆነ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘውን ዝርዝር ምላሽ በተመለከተ መረጃው እንደደረስን እናቀርባለን፡፡