Tag Archives: Ethiopian Journalists incident

በቅርቡ የተሰደደው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ ህይወቱ አለፈ

 

milion shurbieየማራኪ መፅሔት ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ በስደት በሚገኝበት ናይሮቢ ኬኒያ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በድንገት ህይወቱ ማለፉን ከማኀበራዊ ገፆች የተገኙ መረጃች እና ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በጅምላ ያደረገውን የመፅሔቶች እና ጋዜጣ ክስ እና የበርካታ ጋዜጠኞችን እና ብሎገሮችን እስርን ፍርሃት ተከትሎ በቅርቡ ከተሰደዱ ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ አንዱ ነበር፡፡

ጋዜጠኛው በስደት ኬኒያ ከሚገኝበት አንድ ናይሮቢ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቢቆይም ህይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ከኢትዮጵያ ከተሰደደ ገና ሁለት ወር እንኳ እንዳልሞላው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጋዜጠኛው ህይወቱ እስካለፈበት ድረስ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ከ12 ዓመታት በላይ  እንዳገለገለና የድርሰት ስራም እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

ጋዜጠኛ ሚሊዮን በተወለደ በ33 ዓመቱ በስደት ናይሮቢ ኬንያታ ናሽናል ሆስፒታል ቢያርፍም፤የቀብር ስነስርዓቱ እሁድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በትውልድ አካባቢው ይርጋ ጨፌ ከተማ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ ጋዜጠኛው የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡

አዲስ ሚዲያም በጋዜጠኛው ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ፤ ለጋዜጠኛ ሚሊዮን ፈጣሪ ነፍሱን በገነት እንዲያኖር፤ ለቤተሰቦቹ፣ለወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡

maraki magazine

%d bloggers like this: