እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ 28 ቀን ቀጠሮ ተጠየቀባቸው
የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሆኑት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው ትናንት መጋቢት 21 አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው 28 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡ ፖሊስ እነ ብርሃኑ ተክለያሬድን ‹‹ለግንቦት 7 አባላትን መልምለው ወደ ኤርትራ በመላክና ቡድኑን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ተይዘዋል›› ብሏል፡፡
ጠበቃው እነ ብርሃኑ ተ/ክለያሬድ ለግንቦት ሰባት ሲመለምሉም ሆነ አባል ሲሆኑ የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ፖሊስ ‹‹ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምመረምራቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ሌሎች የምንይዛቸው ግብረ አበሮችም አሉ፡፡ መረጃ ያጠፉብናል፡፡›› በሚል ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ 28 ቀን ተፈቅዶለታል፡፡ ሚያዚያ 19 ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ፖሊስ ሌሎች ሰዎች ይዘውት የተነሱትን መሳሪያ በማሳየትም እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ እንደነበር ለማሳየት በመረጃነት አቅርቧል፡፡ ጠበቃው በበኩላቸው ‹‹የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምርመራ ለማድረግና መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጠርጣዎቹን ማሰር ተገቢ አልነበረም፡፡ ሌሎች ሰዎች የያዙትን መረጃ እነሱን ለመክሰስ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡›› ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ የታሰረበት ቤት መብራት ስለማይጠፋ አይኑ ላይ ለከፍተኛ ችግር እንዳደረሰበት ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ለ15 ደቂቃ ፀኃይ እንዲሞቁ ከሚፈቀድላቸው ውጭ ወደ ከታሰሩበት ቤት ውጭ መውጣት እንደማይፈቀድላቸውና ቤተሰቦቻቸውም እንዲጠይቋቸው እየተደረገ አለመሆኑን በቅሬታ አቅርበዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ለግንቦቱ ምርጫ 2007ዓ.ም. በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ
- “ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል” በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን “የሚያልፉት በዕጣ ነው” የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች “ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡” ተብሏል፡፡
ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡” ብለዋል
ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ማለታቸውን ጨምሮ ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከ200 በላይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ሰረዘ
- “ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ እንዲቆይ አይፈልግም” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ እንደተሰረዙበት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በመላ አገሪቱ በተለይም በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወላይታ፣ በቤንች ማጅ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በሲዳማ፣ በከምባታ፣ በጋሞጎፋ፣ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ጎንደርና ጉጅን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ አንድን ዕጩ ለመሰረዝ የሚያበቃ ምንም አይነት ህጋዊ ምክንያት ሳይኖር “ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ታዘናል” በማለት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ያስመዘገብናቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን በመሰረዝ ከምርጫው ውድድር ውጪ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሆነ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት አስረድተዋል፡፡
በየክፍለ ሀገሩ የተሰረዙት ዕጩዎች “ፓርቲው ትብብር የሚባል ህገ ወጥ አደረጃጀት መስርቷል፣ የሌሎች ፓርቲዎች አባላት ናችሁ” የመሳሰሉ ምክንያቶችና ደብዳቤ የተሰጣቸው ሲሆን በአንጻሩ በአዲስ አበባ የተሰረዙት ዕጩዎች ከምርጫ አስፈጻሚዎች ምንም አይነት ምክንያትና ደብዳቤ እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዕጩዎቹ “የተሰረዝንበትን ምክንያት ንገሩን፣ ደብዳቤ ልትሰጡን ይገባል” ቢሉም የምርጫ አስፈጻሚዎቹ “እኛ እናንተን ለመመዝገብ ችግር የለብንም፡፡ ግን ከበላይ አካል እንዳንመዘግብ ተነግሮናል፡፡ ደብዳቤም ልንሰጣችሁ አንችልም፡፡” የሚል መልስ እንደሰጧቸው ገልፀዋል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የቦርዱን ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃናን ለማግኘት ቢጥሩም “ከከተማ ውጭ ናቸው፡፡ አሁን አታገኟቸውም” የተባሉ ሲሆን ፕ/ር መርጋ የህወሓትን 40ኛ አመት ለማክበር መቀሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በትናንትናው ዕለት በጉዳዩ ላይ ከቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን አቶ ነጋ “ማመልከቻ አስገቡ” ከማለት ውጭ ዕጩዎቹ ለመሰረዛቸው ተጨባጭ ምክንያት መስጠት እንዳልቻሉ ኢ/ር ይልቃል ገልጸውልናል፡፡
“የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ያለ አግባብ የሚሰርዙት ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ ጫና መፍጠር ስለሚችል በሂደቱ እንዲቆ ስለማይፈልጉ ነው” ያሉት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤ ሆኖም ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ትክክለኛ እንደሆነ እንዳስረገጠላቸው፣ ይህን የነፃነት ትግልም አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የካቲት 22 ፓርቲያቸው ከትብብሩ ፓርቲዎች ጋር በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በ15 ከተሞች የሚያደርገው ሰልፍ የዚሁ የነጻነት ትግል አካል እንደሆነ መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱን እንዲለቅ ክስ ቀረበበት
• በወር 40 ሺህ ብር ኪራይና 250,000 ብር ለ‹‹ኪሳራ›› እንዲከፍል ተጠይቋል
ሰማያዊ ፓርቲ የካ ክ/ከተማ በቀድሞው መጠሪያው ቀበሌ 15 እንዲሁም በአዲሱ መጠሪያው ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 460 የሆነውን ጽ/ቤቱን 25000 ሺህ ብር ቅጣት ከፍሎ እንዲለቅ በአከራዮቹ በኩል ክስ ቀረበበት፡፡ በከሳሽ እነ አቶ ሚስጥረ ሽበሽ የተመሰረተው ክስ ‹‹ቤቱን ለቀው ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው …በወር ብር 40,000 (አርባ ሺህ ብር) ሒሳብ ከጥር 16 ቀን 2007 ጀምሮ ቤቱን ለቀው እስከሚያስረክቡ ድረስ ባልተነጣጠለ ኃላፊነት እንዲከፍሉን›› ያሉ ሲሆን ‹‹ከሳሽ ቤቱን ለማደስ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በገባነው ውል መሰረት የደረሰብንን 250 ሺህ ብር ኪሳራ እንዲተኩልን›› ሲሉ ከሰዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሚፈልግባቸው ጊዜያት የቀበሌ ካድሬዎች አከራዮቹና ደላሎቹ ለፓርቲው እንዳያከራዩ ሲያስጠነቅቁ የቆዩ ሲሆን በተለይ በጥር ወር 2007 ዓ.ም ይህ ጽ/ቤት እንዳይከራይ ግፊት የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የኦሕዴህ አባላት በሰማያዊ ምልክት ሊወዳደሩ ነው
- “ለአንድ አላማ እንታገላለን” አቶ ግርማ በቀለ
- “መሰባሰባችን ትግሉን ያጠናክረዋል” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ኦሕዲኅ) አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ምልክት ለመወዳደር መወሰናቸውን የኦሕዲኅ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጹ፡፡ ‹‹ጥቅምት 26/2006 ዓ.ም ፓርቲው ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አባላቱና አመራሩ ከአገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በውህደት መስራት እንዳለባቸውና በኦሕዲኅ ስም የሚደረገው የመጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሆን ወስነው ነበር›› ያሉት ሊቀመንበሩ የፓርቲው እጩዎች በሰማያዊ ፓርቲ ስምና ምልክት መመዝገባቸው አባላቱና አመራሩ ‹‹አገራዊ ፓርቲ ጋር በውህደት አሊያም በሌላ መንገድ አብረን መስራት አለብን፡፡›› በሚል በጠቅላላ ጉባኤው ያስተላለፉት ውሳኔ አካል ነው ብለዋል፡፡
አቶ ግርማ ፓርቲያቸው ከሰማያዊ ጋር ሆኖ ለመታገል የተነሳበትን ምክንያትም ‹‹አሉ ከሚባሉት 70 ያህል ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ የክልል ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የክልል ፓርቲዎች በአገራችን ፖለቲካ ፋይዳ ያለው ለውጥ እያመጡ አይደለም፡፡ የክልል ፓርቲዎች ሲጠናከሩም ቢሆን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ተረድተናል፡፡ በተቃራኒው አገር አቀፍ ፓርቲዎች ሲጠናከሩ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ግርማ አክለውም ‹‹እስካሁን የክልልና አገራዊ ፓርቲ ተባብለን ተበታትነን ቆይተናል፡፡ አሁን ግን የተሻለ ለውጥ ለማምጣት አንድ አይነት ጥያቄ አንስተን፣ በአንድ አላማ ለመታገል ወስነናል፡፡ አንድነት ኃይል በመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተሻለ ለውጥ እንደምናመጣ የሚል ትልቅ ተስፋ አለን›› ብለዋል፡፡
ፓርቲው ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ስምምነት በመፈረሙ አባላቱ በሰማያዊ ፓርቲ ስር ሆነው እንዲወዳደሩ ለምርጫ ቦርድ ባስገባው ደብዳቤም ‹‹የዚህ ስምምነት አላማ ፈራሚዎች ለ2007 ዓ.ም አጠቀላይ አገራዊ ምርጫ አባላትን በጋራ በአንድ የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረብ፣ ማለትም የአንዱ ፓርቲ አባልና አመራር በሌላው ፓርቲ ሥምና ምልክት የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ስምምነት ሲደረስም ተግባራዊ ማድረግ ነው›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የቀድሞ የአንድነት አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ መምጣታቸውን አስታውሰው አሁንም የኦሕዲኅ አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ስር ለመወዳደር በፓርቲው ጥላ ስር መሰባሰባቸው ሰላማዊ ትግሉን እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአንድነት መቆማችንና መሰባሰባችን ትግሉን ያጠናክረዋል፡፡ ኢህአዴግ የአንድነት አመራሮችና አባላት ወደ ሰማያዊ በመምጣታቸው፣ ሰማያዊም እጁን ዘርግቶ በመቀበሉ ከፍተኛ ፍርሃት ተፈጥሮበታል፡፡›› ብለዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል አክለውም ‹‹አሁንም ሌሎች ፓርቲዎች መቀላቀላቸው ለኢህአዴግ ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በቴሎቪዥንና በራዲዮ እጩ ያቀረቡ ፓርቲዎችን ሲያስተዋውቅ የሰማያዊን ስም ሳይጠቅስ ቀርቷል፡፡ በተቃራኒው በሬዲዮና በቴሊቪዥን ሰማያዊ ተቋማትን አይቀበልም እያለ በሀሰት እየወነጀለ ያለው የተቃውሞ ጎራው በአንድነት በመቆም እየተጠናከረ በመምጣቱ ነው፡፡›› ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በሰማያዊ ስር መሰባሰባቸው ያለውን ፋይዳ መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡




