አቃቤ ህግ እስማኤል ዳውድ ላይ ምስክሮቹን ሲያስደምጥ፤ የአቶ አለነ ማህፀንቱ የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
ኢዩኤል ፍስሃ ዳምጤ
የአንድነት ፓርቲ አባልና የሚሊየኖች ድምፅ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው ወጣት እስማኤል ዳውድ በዛሬው እለት በአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት ቀረበ፡፡
ወጣት እስማኤል፣ በፍርድ ቤት የቀረበው መዝገቡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማድመጥ በዛሬው እለት በተያዘው ቀነ ቀጠሮ መሠረት ነው፡፡ አቃቤ ሀግ በእስማኤል ላይ እንዲመሰክሩ ካዘጋጃቸው 4 ምስክሮች መሃል ሁለቱን ማስደመጡን የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ገበየሁ ይርዳው ገልፀዋል፡፡ አንደኛ ምስክር እስማኤል፣ ሰልፉ ላይ መገኘቱን ገልጾ ፈፀመ ስለተባለው ድርጊት እንደማያውቅ ማስረዳቱን ያወሱት አቶ ገበየሁ ሁለተኛው ምስክር በበኩሉ እስማኤል፣ መስቀል አደባባይ ተገኝቶ ድንጋይ ወርውሯል፣ እጁን በማነባበር ተቃውሞውን ገልጿል በማለት ምስክርነት መስጠቱን የተከሳሹ ጠበቃ አስረድተዋል፡፡ ጠበቃው የተለያዩ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ለሁለቱም ምስክሮች ማቅረባቸውን አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዚሁ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና የአንድነት ፓርቲ ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማህፀንቱ፣ ከጠዋቱ 3፡00 ሰባራ ባቡር የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትናውን ጉዳይ በሚመለከት ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ተሰይሞ እንደነበር የገለፁት አቶ ገበየሁ፣ ፍርድ ቤቱ የደምበኛቸውን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ አቃቤ ህግ ‹‹ተከሳሹ ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈፅም ስለሚችል›› የዋስትናው ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ ለፍርድ ቤቱ ያመለከት ሲሆን የተከሳሹ ጠበቃ በበኩላቸው ‹‹የአቃቤ ህግ መከራከሪያ በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳ በመሆኑ፣ አቃቤ ህግም ካስያዘው ጭብጥ ውጪ የሆነ መከራከሪያ ነጥብ በማቅረቡ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደመሆኑ መጠን አቃቤ ህግን ይህን መከራከሪያ ሊያቀርብ የሚችልበት የህግ አግባብ›› እንደሌለ ገልፀው የደምበኛቸው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ከህግ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለውና በድጋሚ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡ አቶ አለነ ማህፀንቱ፣ ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥ እንዲሁም ምስክሮቹን እንዲያስደምጥ የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር የጠበቃ ተማም አባቡልጉን የጥብቅና ፈቃድ ማገዱ ታወቀ
የታዋቂው ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የጥብቅና ሙያቸው የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የጥፋተኝነት ብይን በተላለፈበት ቀን መሰረዙ ታወቀ፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር የአቶ ተማም አባቡልጉን ጥብቅና ለአንድ ዓመት ከሰባት ወር የጥብቅና ፈቃዳቸው መታገዱ ታውቋል፡፡
የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና በተለያዩ የህግ ጉዳዮች ጠበቃ የሆነው ጠበቃ ተማም አባቡልጉ በፍርድ ቤት ላይ በሚያደርጋቸው ክርክሮች በተለይም መንግስት ከጅሃዳዊ ሀረካት ጀምሮ የሰራቸውንና ኢትዮጵያ ውስጥ የፍትህ ስርዓቱን ዝቅጠት በመረጃና በህግ በማጣቀስ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በማጋለጣቸው ምክንያት ከዚህ ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወቃ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ማስፈራሪያና ዛቻዎች ከመፈጸማቸው ሌላ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ይታወቃል፡፡ ይህ እስከ ተዘገበበት ድረስ የፈቃዱ መሰረዝ ምክንያት አልታወቀም፡፡
ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ተፈታች፤ መንግሥት የተወሰኑ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችን እና ተማሪዎችንም መፍታት ጀመረ
በፍትህ ሚኒስቴር በፌደራሉ አቃቤ ህግ በ”ሽብርተኝነት” ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው በርካታ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች፣ ፖለቲከኞች እና ተማሪዎች መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን ጨምሮ ጥቂቶች ተለቀዋል፡፡
ከእስር ከተለቀቁት መካከል የእርስ ጊዜዋን የጨረሰችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ በሚያዚያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በጅምላ ከታሰሩት ጋዜጠኞች እና የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮጊስ፣ኤዶም ካሳዬ፤ እንዲሁም የዞን 9 ብሎገሮች ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን ይገኙበታል፡፡
ከእስር ከተለቀቁት ተማሪዎች መካከል ከአዲስ አበባ አዲስ ማስተርፕላን ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ ከኦሮሚያ ክልል ከታሰሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩት አዱኛ ኬሶ፣ ቶፊቅ ራሺድ፣ሌንጂሳ አለማየሁ፣ አብዲ ከማል፣ መገርሳ ወርቁ፣ ቤሊሱማ ዳመነ እና ተሻለ በቀለ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ይህን እንጂ አሁንም ሆን በስፋት ከታወቁት የህሊና እስረኞች መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ, ውብሸት ታዬ እና የዞን 9ኙ በፈቃዱ ኃይሉን ጨምሮ 13 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች፣ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ ኦልባና ሌሊሳ ፣አብርሃ ደስታን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ከነበሩት የኦሮሚያ ተማሪዎች መካከል ተማሪ አስላን ሐሰን በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዳለ በደረሰበት ድብደባ ህይወቱ ማለፉም ተጠቁሟል፡፡
መንግሥት ቀደም ሲል ጋዜጠኞችን፣ ብሎገሮችን ፣ ፖለቲከኞች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን በተመሳሳይ “የሽብር ክስ ወንጀል” ቢመሰርትባቸውም ከተከሳሾች ጀምሮ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኀበረስ፤ የተመሰረቱት ክሶች የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ ከወንጀል ጋር የተያያዘ እንዳልነበር በመጠቆም ከፍተኛ ተቃውሞ ያስከተለ ሲሆን፤ ተቃውሞው አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ሰበር ዜና፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሶስት ጋዜጠኞችን እና ሁለት የዞን 9 ብሎገሮችን ከእስር መልቀቁን አስታወቀ
ከሚያዚያ አጋማሽ 2007 ዓ.ም. በፌደራሉ አቃቤ ህግ በ”ሽብርተኝነት” ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ እየታየ ከነበረው የዞን 9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች መካከል፤ ሶስቱን ጋዜጠኞች እና ሁለቱን ብሎገሮች ክሳቸው በፍትህ ሚኒስቴር ውድቅ ተደርጎ መፈታታቸውን የገዥው መንግሥት ደጋፊ የሆነው ሬዲዮ ፋናን ዋቢ በማድረግ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
ዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር የተፈቱት ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ፤ የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን እንደሆኑ ታውቋል፡፡
እንደሬዲዮ ፋና ዘገባ ከሆኑ ቀሪዎቹ የዞን 9 ብሎገሮች መካከል በእስር ላይ የሚገኙት በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እና በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ሶሊያና ሽመልስ የክስ ጉዳዩን እንደሚቀጥል የፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ ማስታወቁን ጨምሮ ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮች ቀደም ሲል በፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ በ”ሽብር ወንጀል” ተከሰው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለብይን ተቀጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ተባሉ
ከ35 ወራት የፍርድ ሂደት ቆይታ በኋላ ዛሬ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት በእስር ላይ ባሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴ አባላት በሆኑት በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የአቃቤ ህግን እና የመከላከያ ምስክሮችን ቃል በንባብ አሰምቶ ማጠናቀቁን ተከትሎ ዛሬ በ18 ተከሳሾች ላይ ፍርድ ሰጥቷል።
ከ1ኛ እስከ 9ኛ ያሉት ተከሳሾች በተከሰሱባቸው በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ አራት ላይ በተዘረዘሩት መቀስቀስ፣ ማነሳሳት እና ማሴር በሚሉ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለዋል።

ቀሪዎቹ ተከሳሾች በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ አራት ላይ በተጠቀሰው በመሳተፍ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሀምሌ 27 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተከሳሾቹ እና አቃቤ ህግ ከሀምሌ 27 ቀደም ብለውም የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡም አዟል።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ጠዋት ከከሳሽና ከተከሳሽ በኩል በተካሄዱ ክርክሮች አምስት ጭብጦችን መመርመሩ ነው የተመለከተው።
ከአምስቱ ጭብጦች መካከል መንግስት በእስልምና ሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል አልገባም? የሃይማኖቱ ተከሳሾችን ከፋፍሏል አልከፋፈለም? እና የመጅሊሱ ምርጫ ከህገ መንግስቱ ጋር ተጋጭቷል? አልተጋጨም? የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
ችሎቱ እነዚህን ጭብጦች ሲመረምር በተለያዩ ሃገራት ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚራመዱ አሰራሮችን ማየቱን በችሎት መግለፁ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ሰፊ ሃተታ በኋላ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አለመግባቱን፣ ተከታዮችን አለመከፋፈሉንና የመጅሊሱ ምርጫ ከህገ መንግስቱ ጋር ሳይቃረን በሃይማኖታዊ ስርአት መካሄዱን ከምስክሮችና ከማስረጃ ቃል በማገናዘብ አረጋግጫለሁ ማለቱን ተከትሎ ነው ከሰዓት በኋላ ፍርድ መስጠቱን ኤቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡





