Tag Archives: UDJ Party Ethiopia

በርካታ የአንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት ታግተው መለቀቃቸው ተገለፀ

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃምን ጨምሮ ከ40 ያላነሱ  የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት መታገታቸው ተገለፀ፡፡

አንድነት ፓርቲ  ለአንድ ሳምንት የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ አመራሮቹና አባላቱ ወደ ቃሊቲ እስር አቅንተው ነበር፡፡  የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም  እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝን  ጨምሮ ከ40 ያላነሱ የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ባልታወቀ ምክንያት  በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን  የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡

kalitiበተለይ እገታውን በተመለከተ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አስራት አብርሃም ተናገሩት እንደታለው ከሆነው ‹‹እነእስክንድርንና አንዷለምን መጠየቅ አትችሉም ተባልን፡፡ ከዚያም ‹‹ለምን?›› ብለን ስንጠይቅ በዋናው በር በኩል ኃላፊውን አነጋግሩ የሚል መልስ ተሠጠን፡፡ እኛም ይህንን አምነን ሄድን፡፡ ነገር ግን በተባለው በር ስንደርስ በቁጥጥር ሥር ውላችኋል ብለውን መታወቂያችንን ከመዘገቡ በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ ለጊዜው ታገተው እንደነበር ሚኒሊክ ሳልሳዊ ዘግቧል፡፡ በመጨረሻም በኮንቴይነር ውስጥ ታግተው የነበሩት እስረኛ ጠያቂዎች ከበድ ያለ ፍተሻ ተደርጎላቸው ከቃሊቲ ግቢ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ወጣት ትዕግስት ካሳዬ የተባለች የአዲስ አበባ የፓርቲው አመራር ግን ከእገታው እንዳልተለቀቀች ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

እስረኞችን ሊጠይቁ የሄዱ የአንድነት አባላት በዛሬው እለት በአከባቢው የጠበቃቸው የደህንነት ቡድን በእያንዳንዱ ላይ ፍተሻ በማድረግ በኪሳቸው የነበረውን የአንድነት ፓርቲ ወረቀት እንዲሁም አንዲት ሴት የአንድነት አባል ፎት ልትነሳ መሞከር በሚል በተፈጠረ ሰበብ እንዲሁም በአባላቶቹ እጅ የተገኙት የፍኖተ ነፃነት እትሞች መቀማታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህ የተፈፀመው በቶዮታ ነጭ ዲኤክስ መኪና ተጭነው የመጡት የደህንነት አባላት እስረኛ ሊጠይቁ የሄዱትን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ስም ዝርዝራቸውን መዝግበው በመውሰድ እንዲፈቱ ትእዛዝ ሰጥተው ደህንነቶቹ መመለሳቸውን እና ከአንዲት አባል በስተቀር ሌሎች መለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡

 

 

የነፃነቴ ዋጋ ነብሴ ነው!!

ግርማ ሰይፉ ማሩ
girma seifuመረጃ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ጠቃሚ ነው ብሎ መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡ የተሟላ መረጃ የሰውን ልጅ ሙሉ ያደርገዋል፡፡ መረጃን አጣሞ ማቅረብ ደግሞ የሰውን ልጅ ውሳኔ ለማጣመም ካልሆነ በስተቀር ግቡ ምን ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም፡፡ በሰሞኑ ሰው በላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥርሱም በጥፍሩም ዘመቻ የጀመረው እኔ ላይ ነው፡፡ ዓላማው ግልፅ ነው፡፡ በነፃነት የማሰብ መብቴን ለድርድር እንዳቀርብ ነው፡፡ ለነፃነቴ ያለኝን ዋጋ የማያውቁ ሰዎችን ይህንን ለማድረግ ቢሞክር ካላቸው የመረጃ እጥረት ወይም ማወቅ ባለመፈለጋቸው ነው፡፡ አንዳንድ ቅን ሰዎች ሰህተት እንደሰራው አድርገው ይቅርታ እንድጠይቅ፤ ይቅርም እንድባል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በቅን ልቦና ላደረጋችሁት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡

ነገር ግን በሰጠሁት አስተያየት ያልተስማማ ሰው በሃሰብ ልዮነት መለያየት እያለ ይቅርታ ጠይቄ፤ ይቅርታም ተደርጎልኝ ወደ እነሱ ሃሳብ እንድገበ መፈለጉ ምን ዓይነት ከፍተኛ ችግር ያለበት አስተሳሰብ እንደሆነ የተረዱት አይመሰለኝም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስገራሚ የሚሆነው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ደጋፊ፣ ለግለሰብ ነፃነት እንቆማለን የሚሉ ወገኖች መሆናቸው ነው፡፡ ለሃሳብ ነፃነት የማይቆም እንዴት አድርጎ ለመድበላ ፓርቲ ስርዓት ግንባታና የግለሰብ ነፃነት እንደሚያከብር አይገባኝም፡፡

ጫጫታ ወደ ፈጠረው አጃንዳ ስገባ፡፡ አንድነት ፓርቲ የምርጫ ግብረ ሀይል ማቋቋሙን ለህዝብ በይፋ ለማሳወቅ እና በቀጣይ ሳምንት ስለሚያደርገው የህሊና እስረኞች ስለሚታሰብበት ፕሮግራም መግለጫ በሰጠንበት ወቅት በፍፁም ጠቃሚ ያልሆነ የተቃዋሚ ጎራውን በተለይ በሀገር ውስጥ ለምንገኝ ሰዎች የማይጠቅም (በኢቲቪ ቢቀርብ የማይገርም) ጥያቄ ቀረበ፡፡ ጥያቄው በእስር ላይ የሚገኙ የቀድሞ አንድነት አባል የነበሩ ታሳሪ ስም ጠርቶ በአንድነት አቋም እኝህ ሰው የህሊና እስረኛ ናቸው ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ? የሚል ነበር፡፡ የሰጠሁት መልስ የማንንም ታሳሪ ስም ማንሳት ሳያስፈልግ የአንድነት ፓርቲ አባል ሆኖ የሌላ ፓርቲ አባል መሆን ትክክል እንዳልሆነ፣ ከአንድነት ጋር በትግል ስትራቴጂ ከማይመሳሰሉት ጋር ብቻ ሳይሆን በትግል ከሚመሳሰሉትም ጋር ቢሆን የተሻለ ወደሚለው መጠቃለል እንጂ ሁለት ቦታ መሆን ትክክል እንዳልሆነ አስረድቻለሁ፡፡ በማስከተልም “በፀረ ሽብር” ህግ መንግሰት እየከሰሰ የሚያስራቸው ሰዎች አንዳንዶቹ በወንጀል ህግ ሊያስጠይቅ የሚችል ሰህተት አልሰሩም የሚል ድምዳሜ እንደሌለኝ አሰረግጬ ተናግሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ በፈንጂ ስው የገደለ ሰው በወንጀለኛ ህግ መጠየቅ እና መቀጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እምቴ አሁን ፅኑ ነው፡፡ የ “ፀረ ሽብር” የሚባለውን ህግ በይፋ አሸባሪ ህግ ነው፡፡

ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች አሸባሪ እየተባሉ የሚታሰሩ ያሉት የአራት ኪሎን ወንበር ስለሚያሸብሩ ነው የሚል አቋሜን ከብዙዎቹ ተችዎቼ በላይ እና ከማንም በማያንስ መልኩ ሃሳቤን በነፃነት አራምጃለሁ፡፡ ይህን ሳራምድ ማንንም ለማስደስት ሳይሆን አምኜበት ነው፡፡ አንድነት የ “ፀረ ሽብር” የሚባለው ህግ እንዲሰረዝ የተገበረውን “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ዘመቻ በቁርጠኝነት ከመሩት አንዱ ስሆን፤ በተለይ በደሴ ከተማ የተደረገውን የሚሊዮኖች ድምፅ ዘመቻ በቦታው ተገኝቼ የመራሁት እኔ ነኝ፡፡ ይህን ሁሉ የምዘበዝበው በዚህ ህግ ላይ ያለኝን ግልፅ አቋም በድጋሚ ለማረጋገጥ ነው፡፡

በእኔ በኩል የአቋም ለውጥ ሳይኖር እሳት ጭረው ቤንዝን እያርከፈከፉ ያሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ለምን ተፈጠሩ? የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት የአንድነት በምርጫው የመሳተፍ ውሳኔ በትግል ስልታቸው ላይ የሚፈጥረው ጫና ስለሚያስጨንቃቸው ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምርጫ መሳተፍ ትክክል አይደለም ብሎ መሟገት ሲያቅታቸው የፈጠሯት ስልት ነች፡፡ አንድነት ምርጫ መሳተፍ ሲወስን በምንም መመዘኛ የመወዳደሪያው ሜዳ ምቹ ነው የሚል ግምገማ ላይ ደርሶ አይደለም፡፡ የፖለተካ ምዕዳሩ ጠበበ ብቻ ሳይሆን ዝግ ነው የሚል ግምገማ ላይ ደርሶዋል፡፡ ልዩነቱ ማስከፈቻ መንገዱ ምን ይሁን የሚለው ነው፡፡ በህዝብ ድምፅ የተዘጋው የፖለተኪ በር ይከፈታል ነው አንድነት ያለው፡፡ በዚህ ውሳኔ የማይስማማ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህ ደረጃ ወርዶ ግን በጥርስና በጥፍር ለመናከስና ለመቧጨር መሞከር ግን ያስተዛዝባል፡፡

የግል ሰሜቴን ለመግለፅ እሰከ ዛሬ ድረስ ለሚቀርብልኝ ሙገሳና የማጀገኛ ቃለቶችን ተመርኩዥ ልቤ አላበጠም፡፡ አንድ ቀን ያለአግባብ ከፍ አድርገው ከሰቀሉ ቦታ ላይ አውርዶ የሚከሰክስ ማህበረሰብ አባል መሆኔን አውቃለሁ፡፡ ያለ አግባብ በእራሳቸው ስሜት ሊወስዱኝ የፈለጉት ከፍታ ላይ ስለአልሄድኩኝ አሁን ሊያወርዱኝ አይችሉም፡፡ እደግመዋለሁ ለነፃነቴ የምሰጠውን ዋጋ የማያውቁ ሰዎች ምንም ሊሞክሩ ቢችሉም ነፃነቴን ለኢህአዴግ አሳልፌ አልሰጥም ስል በተቃዋሚ ጎራ ለተሰለፈ አሳልፌ እሰጣለሁ ማለት አይደለም፡፡ ለነፃነቴ የመደብኩት ዋጋ ነብሴን ነው፡፡ ስም፣ ዝና፣ ክብር፣ ገንዘብ፣ ወዘተ እንዳይመስላችሁ!!!!! ነብሴን ነው፡፡

አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል ዘመቻ ማዘጋጀቱን ይፋ አደረገ

udjአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል። በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም የዘመቻው ደጋፊና በሀገሪቱ ዴሞክራሲያው ስርዓት እንዲመሰረትና የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚሹ ሁሉ ከላይ ለተጠቀሱት ግልሰቦችና ተቋማትን ጨምሮ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ዛሬ ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ፓርቲው ከዚህ በፊት ከህዝቢ ከፍተኛ ድፍ ያስገኘለትን “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” እና “…ለመሬት ባለቤትነት” የሚሉ የተለያዩ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ማድረጉ ይታወቃል፡፡  የዛሬውን ሙሉ ዝርዝር መግለጫ ከታች ይመልከቱ፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

ምርጫ ሲባል አማራጭ ሳያሳጡ መሆን ይኖርበታል!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በሀገራችን ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚደረግ በመንግስት በኩል በከፍተኛ ደረጃ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተከናወኑት አራት ምርጫዎች ያየን እንደሆነ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ወደፊት ሊወስዱ እንዳልቻሉ እሙን ነው፡፡ ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ በተቃራኒው መንግስትና ገዢው ፓርቲ በፍፁም መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ተቀናጅተው ለአንድ ለአውራ ፓርቲ ግንባታ እየሰሩ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ተግባር ምርጫን ያለ አማራጭ እንዲሆነ እያደረገው እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡

በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዘመቻ በሚባል ደረጃ እየተካሄደ ያለው አፈናና እስር፤ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ክልከላውና ወከባው ተጠናከሮ መቀጠሉ፤ ገዥው ቡድን የምር ተቃዋሚ ፓርቲ ናቸው ብሎ የሚያስባቸው ፓርቲዎች ለማዳከምና ከምርጫው ውድድር ውጪ ለማድረግ ያለው ቁርጥ አቋም የሚያሳይ ነው። ይህ የገዢው ቡድን አካሄድ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመሰረት ፍላጎት እንደሌለው በደንብ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዲመርጥ እድል ሊጠሰው ሲገባ በሥርዓቱ በእኩል ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳያካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉበት የሚካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ትርጉም አልባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ የገዢው ቡድን ሀላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ በተግባር የሚደግፈው ከሠላማዊ ትግል ይልቅ የኃይልና የአመፅ መንገድ እንደሚሆን የተረዳ አይመስልም፤ ይልቁንም በሠላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፓርቲዎች ወደ አላስፈላጊ መስመር በመግፋት ሀገራችን ወደ ብጥብጥና ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንድትገባ የሚያደርግ ሁኔታ እየተከተለ ነው የሚገኘው። በሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በትክክል እንዳያዩ ጭፍን የሥልጣን ጥም ጋርዷቸዋል፡፡

በቀጣይ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚደረገው ምርጫም በመንግስት በኩል የመድበለ ፓርቲን ስርዓት ለማጎልበት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከአሁኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመደርደር ላይ ነው። የአንድነት አመራሮችና አባላት በግፍ በማሰር ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከፍተኛ የሆነ ጫና እየተደረገ ቢሆንም አንድነት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ህዝቡ እንዲሳተፍ በመቀስቀስና በማበረታታት የተዘጋውን የዴሞክራሲ በር በምርጫ ካርዱ ሊያስከፍት እንደሚችል ከፍተኛ እምነት አለው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደከዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን ብቻ በመራጭነት አስመዝግቦ ምርጫ የሚያደርግበት ሁኔታ ማብቃት ይኖርበታል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን በእኛ በኩል ደጋፊዎቻችን በመራጭነት እንዲመዘገቡ ከማበረታት ጀምሮ የህዝብና የፓርቲ ታዛቢ በመሆን የምርጫ ሂደቱን በሙሉ በንቃት እንዲከታተል እንዲሳተፍ የበኩላችንን ጥረት በማድረግ የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ከጅማሮው ህዝባዊ እንዲሆን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ይህ እርምጃም ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው የሚል እምነት አለን፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥው ቡድን መልካም ፍቃድ ወይም በማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደማይሰፋ ሊገነዘብ ይገባል። ምህዳሩ የሚሰፋውና ትክክለኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚኖረው ህዝቡ በጠቅላላ ከፍርሀት ቆፈን ተላቆ በሙሉ ልብ ለመብቱ ሲቆም፣ ለፓርቲዎች ተገቢው ድጋፍ ሲሰጥ፤ ከፍ ሲልም ወደ ትግሉ ሲቀላቀል መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በእኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ ነው። በዚህ ዘመቻ ላይ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

………..//………//…………

ኢህአዴግ በክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማሰርና መደብደቡን ቀጥሏል

የታሰሩ አመራሮች የአንድነት፣መኢአድ፣ ሰማያዊ እና አረና ፓር  እና የሲቪክ ተቋም አመራር ይገኙበታል፡፡  እነኚህም ከአንድነት  ከሰሜን ጎንደር  ምዕራብ አርማጭሆ አቶ አንጋው ተገኝ፣ አቶ አባይ ዘውዱ፣ አቶ እንግዳው ዋኘው እንዲሁም ከመተማ አቶ በላይነህ ሲሳይ እና አቶ አለባቸው ማሞ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም.፤ ከበመቀሌ የአንድነት አባል የሆነው አቶ ሺሻይ አዘናው ደግሞ ጥቅምት 26 2007 ዓም ተይዘው እስካሁን ባልታወቀ ስፍራ በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መሰወራቸው ተጠቁሟል፡፡

prisonበተመሳሳይ ወቅት ሌሎች የአንድነት አመራሮች ከወረታ አቶ አለበል ዘለቀ፣ከምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ አቶ ጥላሁን አበበ በመንግስት ፀጥታ ይሎች ታፍነው ወዳልታወቀ ቦታ መታሰራቸው ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ሌላው የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራሮች አቶ ማሞ ጎሙ፣ አቶ ወኖ መናሳ እና አቶ አልታዬ አቦታ በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና የህክምና ዕርዳታም እየተደረገላቸው እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ አንድነታ ፓርቲ ድርጊቱን በመቃወምና በማውገዝ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል፡፡

ከመኢአድ  የቀድሞው የፓርቲው ዋና ፀሐፊነ አመራር ተስፋዬ ታሪኩ ከጎጃም ደጀን በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸው እንዲሁም ከሰማያዊ  ፓርቲ ደግሞ  የሰሜን ጎንደር የዞን አመራር የሆኑት አቶ አግባው ሰጠኝ ጎንደር ከተማ ውስጥ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሰወሯቸው ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡ በተያያዘ ዜና ከአረና ትግራይ ፓርቲ ደግሞ በትግራይ ክልል የሚገኙ አመራሮቹና አባሎቹ ቀሺ ብርሃኑ ቀባዕ፣ኣቶ ኣያሌው ጣዕምያለው፣,አቶ ሓለፎም ገብረዝጊ እና ቀሺ ገብረእግኣብሄር ካሳዬ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.በተመሳሳይ በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ ከላይ የተጠቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮችን ማሰር፣ መሰወርና መደብደቡን አጠናክሮ መቀጠሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመግባባት፣ አንድነትና ሰላም (ሰላም) ማህበር የተሰኘው የሲቪክ ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ ጥቅምት 23 ቀን 2007 ዓ.ም.መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ፋንታሁን ማኀበራቸው በህግ የተፈቀደለትንና የቆመለትን ዓላማ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተይዘው መታሰራቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በተለይ የፓርቲዎቹ ወጣት አመራሮች ላይ በተከታታይ እየደረሰ ያለውን እስርና ድብደባ  ምክንያት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ  የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡ በተለይ ከሚያዚያ 2006 ኣ.ም. ጀምሮ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት  ጋዜጠኞችን፣ ብሎገሮችን እና ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጅምላ ማሰሩን አጠናክሮ መቀጠሉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የኢህአዴግ መንግስት በሰሜን ጎንደር የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ማሰሩ ተገለፀ

gon1በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከለሊቱ 11:00 ሰዓት ላይ በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አምርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንጋው ተገኝ እና የወረዳው ሌላ አመራር አባላት አቶ አባይ ዘውዱ እና አቶ እንግዳው ዋኘው የፌደራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪም ወደ ሌላ ቦታ እንዳይወስዷቸው ፖሊስ ጣቢያውን ከቦ እየጠበቀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በተያያዘ ዜና በዛው ሰሜን ጎንደር ዞን በመተማ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በላይነህ ሲሳይ በፖሊሶች በዛሬው ዕለት ከለሊቱ 11:00 ሰዓት በፖሊሶች ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በወላይታ ዞን የአንድነት አመራሮችም ከፍተኛ ድብደባና ወከባ እንደደረሰባቸው በፍኖተ ነፃነት የተዘገበ ሲሆን፤ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይም የአንድነት አመራሮች ላይ በኢህአዴግ የሚፈጠረው ጫና እንደቀጠለ መሆኑን የፓርቲው ልሳን ዘገባ ያመለክታል፡፡

gon2ከዚህ ቀደምም አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ የሺዋስ ይሁንዓለሙ፣ ሻምበል ዮሐንስ ተረፈ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው ፤በቅርቡ ደግሞ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከአረና እና ሰማያዊ
ፓርቲ አመራር ከሆኑት አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡