ኸረ ዛሬም በአጃቢዎች እየተጠበቁ ነው !

ብስራት  ወልደሚካኤል

afrosonb@gmail.com

አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት እያሉ የጥበቃ አጃቢዎችን ብዛት ላየ የምር የሚሞቱ አይመስልም ነበር፡፡ ግን የማይሞት የለ እንዲሉ አቶ መለስ ስንቱን ኢትዮጵያዊ በግፍ ጨካኝ አመራራቸው ሲያስጨንቁ 21 ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. መሞታቸው በአምላኪዎቻቸው ይፋ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ አምላኪዎቻቸው ነሐሴ ሞቱ ቢሉንም እሳቸው የሞቱት ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያንን ካስጨነቁ በኋላ በቤልጂየም ብራሰልስ ሴይንት ሉክ ሆስፒታል በሞትና በህይወት መካከል  ከተጨነቁ በኋላ ፓርቲያቸው ይቆዩልን ቢሉም ሳይሰናበቷቸው በጨበጣ ያለፈቃዳቸው የላይኛው ጥሪ በልጦ ላይመለሱ ሄደዋል፡፡ ያኔ ግን ትዝ ይላችኋል? ነሐሴ 15 ቀን 2004ዓ.ም. አቶ በረከት ስምዖን  የአቶ መለስን መሞት በጠዋቱ ሲያረዱን  “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባጋጠማቸው ኢንፌክሽን ትናንት ሐምሌ 14 ቀን 2004ዓ.ም.ከምሽቱ 4 ሰዓት ህይወታቸው አልፏል” አሉ፡፡ ግን አቶ በረከት  የሰውየውን መሞት ለማርዳት የፈጠኑ አልመሰሏችሁም? በድናጋጤ እንዳንሞት እንኳ አላዘኑልንም፤ ያው ኢህአዴግ በተፈጥሮው “ግልፅ, ዴሞክራትና ዘመናዊ አስተዳደርም” አይደል? ለዛ ነው ቶሎ የነገሩን ፤ቢዘገየም ብራቮ! አቶ በረከት ብያለሁ፡፡

የአምባገነኑን ጨካኝ ለኢህአዴግዎች ቅዱስ የሆኑት መሪ ሞታቸውን ዓለም ይወቅልን፣ ነፍሳትም ያንቡ፣ ህዝቡም ይሰናበታቸው፣.…ተብሎ እምባ ማይታክታት ሀገር ህዝቡ ከነጭፍሮቻቸው በፈፀሙት የግፍ አገዛዛቸው 21 ዓመታትን ማልቀሱ ሳያንሰው ሞታቸው ከተነገረ ጀምሮ  13 ቀናት ምድሯን በጥቁር ልብስ ገበያ ካደሩ በኋላ ምክንያቱ ሳይታወቅ አስከሬኑ ለህዝብ ሳይታይ ባማረው የውጭ ሳጥን ነሐሴ 27 ቀን 2005ዓ.ም ግብዓተ መሬታቸው  አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ግቢ ተፈፅሟል፤ ወዳጆቻቸው እንዳሉን ከሆነ፡፡ ምክንያቱም ደጉ ለሀገሪቱ ህዝብ አላስ…የሆኑት አምባገነን መሪያችንን አስከሬን እንደነ ክቡር  አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ፣ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌና አቡነ ጳውሎስ አስከሬኑ ለህዝብ አልታየማ! ባለማየታችንም ቢሆን ቅር አይለንም፣ አንኮነንም…”ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አይደል የሚለው ቃሉ? ደግሞስ እንኳን የእሳቸውን መሞት ቀርቶ የሀገራችንን ዕድገትስ በነገሩን ብቻ ያልኖርንበትን ሳናይ  11 በመቶ አድገናል ሲሉን እያመንን አይደል?….፤ታዲያ እሳቸው ከኢትዮጵያ በምን ያንሳሉ?…ምክንያቱም በህይወት እያሉ እራሳቸውን ብቻ ተቋምም፣ሀገርም ፣ህዝብ አርገው ይቆጠሩ ነበርና፡፡

አሁን ግን ግብዓተ መሬታቸው የተፈፀመበት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን በወጣቶች ስፖርትና መዝናኛ(ወወክማ) አቅጣጫ ባለው መካነ መቃብራቸው ቦታ ግዙፍ የማያልቁ ትላልቅ ሻማዎች እየበሩ(እሳቸው ግን ተፍተዋል) በሁለት የጦር መሳሪያ በታጠቁ መከላከያ ሰራዊት ዘወትር ይጠበቃል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ሰውዬው ሞተውም ይፈራሉ እንዴ? ወይ አምባገነን ለካ ሞቶም አያርፍ…..!

ሌላው ያስገረመኝ ጉዳይ ቤተክርስቲያን ሊሳለምና ፀሎቱን ሊያደርስ የሚሄድ ምዕመን ድንገት ዓይኑን አዲስ ወደ ሆነበት መካነ መቃብር አቅጣጫ መልከት ቢያደርግ አስከሬኑ ያረፈበት አጠገብ በተጠንቀቅ የተቀመጡት የመከላከያ ሰራዊቶቹ  ግልምጫና ፍጥጫ ምን እሚሉት ነው? ደግሞስ ለሙት የሚደረገው ጥበቃ እና እኒያ ግዙፍ አራቱ ሻማዎች በጀት ከማን ይሆን የሚሸፈነው? መቼም ጉድ እማይሰማ የለ! ከሀገሪቱ በጀት ነው እንዳይባል፣ አያደርጉትም አይባልማ! እንዲህ ከሆነማ በቁማቸው ሀገሪቷንና ህዝቡን የጋጡት የኢህአዴግ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሲሞቱ እንዲህ የሀገር በጀት የሚባክን ከሆነ ምን ቀረን…?

ግድ የለም ጎበዝ!…ከእንግዲህ ሞተውም በዛ ክፉ መንፈሳቸው ሀገር ማተራመስና ማራቆት ስለማያቆሙ አትሙቱብን፣ በቁማችሁ ጋጡና ጨርሱን ብለን እንፀልይላቸው ይሆን ወይስ…..?  ኦ…ኦ…የረሳሁት ትዝ አለኝ!…ግን መከላከያ ሰራዊቱ የሞተ አስከሬን እንዲጠብቁ የተደረጉት የአቶ መለስ አምላኪ ኢህአዴጋዊያን  አውጠተው የሙዚየሙን ስራ ያስተጓጉላሉ ተብሎስ  ይሆን? የሀገሪቱ ካዝና ይመስል ምናልባት ሼም ስለማያውቁ  ሊሆን ይችላል፤ አለበለዚያ ሰውዬው  በምድር ለሰሩት ግፍ ወደላይኛው ቅጣት እንዳይሄዱ/እንዳያርጉ ታስቦስ ይሆን? ኸረ መላ በሉን ጎበዝ! ሞተውና ተቀብረውም ስፍራው በመከላከያ ጦር መጠበቁ ለምን ይሆን?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: