በባህርዳር በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ የሰው ህይወት ሲጠፋ፤ በአዲስ አበባም ተቃውሞ ተደርጓል
ዛሬ አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 04 እየተባለ የሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የጥምቀት ባህር ታቦት ማደሪያ መንግስት ለባለሀብት ይሰጣል መባሉን ተከትሎ ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ ላይ ቢወጣም፤ የመንግስት ፖሊሶች በሰላማዊ ሰለፈኞቹ ላይ በከፈቱት ተኩስ እስካሁን 3 ዜጎች መገደላቸው ሲነገር፣ አዛውንት መነኩሴን ጨምሮ በርካቶች ከመንግስት በተተኮሰ ጥይት መቁሰላቸውን ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ ለተቃውሞ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ከመነሻው እየዘመሩ ወደ ጥምቀተ ባህር ታቦት ማረፊያ ሲሄዱ የመንግስት ፖሊሶች ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፉን ለማስቆም በሚል በወሰዱት የተኩስ ኃይል እርምጃ አማረ ያዜ የተባለ ወጣት ወዲያው ሲሞት፤ ሌሎች 2 ሰዎችም ሆስፒታል ደርሰው መሞታቸው ተጠቁሟል፡፡ እንደ ባህርዳር ሆስፒታል ምንጮች ጥቆማ ከሆነ የሟቾች ቁጥር ከ3 ወደ 5 እንዳሻቀበ የተገለፀ ሲሆን፤ ከ8 ያላነሱ ቆስለው የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል አስተዳደር የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውን የታቦት ማደሪያ ከፊሉን ለመንገድ ማስፋፊያ ቀሪውን ለባለሃብትና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች መስሪያ እንዲነጠቅ ማዘዙን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያኗ በተደረገ ጥሪ የተቃውሞ ሰልፉ መካሄዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን ለማስቆም ፖሊስ በወሰደው ሰልፍ በወጣው ምዕመናን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል፡፡ በመጨረሻም የአማራ ክል መስተዳደርና የባህርዳር ከተማ መስተዳደር በጋራ በተሸከርካሪ መኪና በመንቀሳቀስና ባርዳር በሚገኘው በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በተለይም በሬዲዮ በጥምቀተ ባህር ታቦት ማረፊያ ስፍራው ሊካሄድ የታሰበው የመንግድ ማስፋፊያ ቀርቷል ሲል ማወጁ ተጠቁሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል መንግስት በበኩሉ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቴቪ) ባሰተላለፈው ዜና በተፈጠረው ችግር አንድ ሰው ብቻ መሞቱን ሲያምን የሌሎች ሟቾችንና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በተመለከተ ያለው ነገር የለም፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለፀ ከሆነ የሟቾችና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚጨምርና በሰልፉ ላይ ከነበሩት መካከል ከ30 የማያንሱ ሰዎች በፖሊስ ታፍሰው ወዳልታወቀ ስፍራ ለእስር መወሰዳቸውን እማኞች ለአዲስሚዲያ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት በበኩሉ ቀደም ሲል በ2፡00 ሰዓት የዜና እወጃው ላይ ካስተላለፈው ዜና በተቃራኒ ስራው ሊከናወን የነበረው ከኋይማኖቱ አባቶች ጋር በተደረገ መግባባትና ስምምነት እንደሆነ እና የጥምቀተ ባህር ታቦት ማረፊያን እንደማይነካ ከየትኛው ደብርና ገዳም እንደሆኑ ያልተገለፁ የተወሰኑ ቀሳውስትን ምስል በማሳየት ስራው ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ በዜና እወጃው በሰልፉ የተገኙትንም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸውንም ሲወነጅል ተሰምቷል፡፡
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው ኑር (ቤኒ) መስኪድ ህዝበ ሙስሊሙ ድንገት በመንግስት ላይ ተቃውሞ ማሰማቱ ታውቋል፡፡ ለዓመታት የቆየው ህዝበ ሙስሊሙ የመንግስት በኃይማኖት ጣልቃ ገብነት በሰላማዊ መንገድ በተከታታይ ያሰማ የነበረውን ተቃውሞ ለተወሰነ ጊዜ ረገብ ያለ ቢመስልም ዛሬ አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የተለመደ ሰላማዊ ተቃውሞውን ማሰማት ቀጥሏል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ መንግስት በኋይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም ከጥር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ሰላማዊ ተቃውሞ ምላሽ ባለመገኘቱ ዛሬም ድንገት ሰላማዊ ተቃውሞ መቀጠሉ ታውቋል፡፡ መንግስት ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ተወካዮቻቸው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ሲደራደር ቆይቶ በመጨረሻ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹን በሙሉ አስሮ ክስ መመስረቱንና እስካሁንም እልባት እንዳልተገኘለት አይዘነጋም፡፡
እነ አብርሃ ደስታ ለታህሳስ 15 ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተሰጣቸው
∙ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል
በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች ለታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ሆኖም ግን 7ተኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን የሰጠው የተከሳሽነት ቃል ከክሱ ጋር ተያይዞ ለጠበቃው አለመቅረቡን ተከትሎ ጠበቃው የክስ መቃወሚያ ለማዘጋጀት ባለመቻላቸው የተከሳሽ ቃልን የያዘውን ዶክሜንት ከጽ/ቤት ወስደው መቃወሚያቸውን እንዲያስገቡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው በተለየ መዝገብ በመመዝገባቸው ከሌላው በተለየ ማሸማቀቅ እየተፈጸመባቸው ነው፡፡
ይህን በተመለከተ ለማረሚያ ቤቱ አቤት ቢሉም ሊሻሻል አለመቻሉን ተከሳሾቹ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸውን ተቀብሎ በቀጣይ ቀጠሮ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ስለጉዳዩ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-ነገረ-ኢትዮጵያ
ብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞቹ ተጨማሪ 20 ቀናት ቀነ ቀጠሮ ተሰጣቸው
∙ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየት ተሰጥቶበታል
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ተጨማሪ 20 ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለ13ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጦማርያኑና ጋዜጠኞች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ቀደም ብሎ ተሻሽሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆችም ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጠበቆቹ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ከማቅረባቸው በተጨማሪ በቃል ለችሎቱ ለማስረዳት ጠይቀው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹በጽሑፍ ካቀረባችሁ በቃል መድገም አያስፈልግም›› በሚል ሳይፈቅድላቸው ቀርቷል፡፡
ጠበቆቹ ‹‹ተሻሻለ የተባለው ክስ ምንም መሻሻል የለውም›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ቢሞክሩም፣ ችሎቱ ንግግራቸውን አቋርጦ ‹‹ክሱ በታዘዘው መሰረት መሻሻል አለመሻሻሉን መርምሮ የሚወስነው ፍርድ ቤቱ ነው›› ሲል አስረድቷል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠቦቆች የቀረበውን አስተያየትና ቀደም ብሎ ለአቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል የሰጠውን ትዕዛዝ በማገናዘብ ጉዳዩን መርምሮ ክሱ በምን አግባብ እንደተሻሻለ አይቶ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል የነገረ- ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡