Monthly Archives: January, 2015

የአንድነት ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ

የአዲስ አበባ ፖሊስ የአንድነት ፓርቲ ዋና ጽ/ቤትን ሲቆጣጠር የሚያሳይ

የአዲስ አበባ ፖሊስ የአንድነት ፓርቲ ዋና ጽ/ቤትን ሲቆጣጠር የሚያሳይ

አዲስ አበባ ቀበና የሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዋና ጽህፈት ቤት በፖሊስ እና ደህንነቶች ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት በቁጥጥር ስራ የዋለው ምርቻ ቦርድ ለእኔ ይታዘዘኛል በሚል የፓርቲውን ስምና ህልውና ለነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ ማስረከቡን ተከትሎ ነው፡፡ ፖሊስ አርብ ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ጽህፈት ቤቱን ከመቆጣጠሩ በፊት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበርና በዕለቱ ከሰዓት በኋላ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ጉዳይ ለመምከር ወደ ጽህፈት ቤቱ ሲያመሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተረጋግጣል፡፡ በዕለቱ ጠዋት ስራ አስፈፃሚው በጉዳዩ ዙሪያ ከመከረና ከተወያየ በኋላ ለምሳ ወጥተው ለምክር ቤቱ ስብሰባ ሲመለሱ ወደ ቢሮው መግባት የተከለከሉ ሲሆን፤ ቢሮው በፖለስ ቁጥጥር ስር በመዋሉ ቀጠሮ የተያዘለት የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባም ሳይካሄድ መቅረቱ ታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች ለምሳ ሲወጡ ትተዋቸው የሄዷቸውን ተሸከርካሪም ሆነ ማንኛውንም ወረቀት ይዘው እንዳይወጡ ከታገዱ በኋላ ፖሊሶቹ በስልክ በተሰጣቸው ትዕዛዝ ስራ አስፈፃሚዎቹ መኪናቸው ብቻ ተፈትሾ እንዲወጣ መደረጉን የፓርቲው ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ግርማ ሰይፉ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ቢሮውን ሲቆጣጠር ከስራ አስፈፃሚው ውጭ በቢሮ ያሉ የፅህፈት ቤት ሰራተኞችና ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች ላልተወሰነ ጊዜ ከቢሮ እንዳይወጡ፣ከግቢ ውጭ የነበሩትም እንዳይገቡ መደረጉን የአይን እማኞች ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ ፖሊስ ቢሮውን በኃይል ሲቆጣጠር ምንም ዓይነት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመያዙ ታውቋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት በምርጫ ቦርድ እነ ትዕግስቱ አወሉ ከተመረጡ በኋላ አሁንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ ዜና አዲስ አበባ ቸርችል ጎዳና አካባቢ የሚገኘው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽህፈት ቤትም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቁሟል፡፡ ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፓርቲዎቹን ዋና ጽህፈት ቤት ለምን እንደተቆጣጠረ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም፡፡ የአዲስ ሚዲያ ፖሊስ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ፤ፖሊሶችም የፓርቲዎቹን ቢሮዎች ተቆጣጠሩ የሚል ትዕዛዝ ከመሰጠቱ በስተቀር ለምን እንደተቆጣጠሩ ራሳቸውም ምክንያቱን እንደማያውቁ ተጠቁሟል፡፡ ምርጫ ቦርድ መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ሂደትን ተክትሎ በዋዜማው ሁለት አንድነት እና መኢአድ ፓርቲዎችን በማፍረስ ሌላ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡ ቀደም ሲል “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” ከህወሓት/ኢህአዴግ የተሰጠውን ትዕዛዝ ከማስፈፀም ውጭ ነፃና ገለልተኛ አይደለም፣ቦርዱን የሚመሩት ስራ አስፈፃሚዎችም ተቋሙን ለመምራት የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነት ስለሌላቸው ለተቋሙ አይመጥኑም፣..በሚል በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አሁን ያለው የቦርዱ እንቅስቃሴ በቀጣይ ቀናትም ከምርጫው ዋዜማ እስከ ድህረ ምርጫ አዳዲስ ውሳኔዎችን እና እንቅስቃሴዎችን ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ሰበር ዜና፤ ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድን ፓርቲን ለእነ ትግስቱ አወሉና ለእነ አበባው መሐሪ ሰጠ

  • ‹‹እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው›› -ፕሮፌሰር መርጋ በቃና

nebe

ምርጫ ቦርድ አንድነትን ለእነ ትግስቱ አወሉ፣ እንዲሁም መኢአድን ለእነ አበባው መሃሪ መስጠቱን ዛሬ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቀ፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹የእነ በላይ በፍቃዱ ቡድን›› በጠቅላላ ጉባኤ እንዳልተመረጠ፣ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ አባላት እንዳልመረጠ፣ የተመረጡበትም 51 ሲደመር አንድ መርህ አለመሆኑን፣ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ ሪፖርት አለማድረጉንና ለአባላቱና ለፓርቲው ክብር የሌለው በመሆኑ ፓርቲውን ማስቀጠል እንደማይችል ገልጾአል፡፡

udj

በሌላ በኩል የትግስቱ አወሉ ቡድን መርህ ይከበር እያለ እየታገለ በመሆኑ፣ የኢ/ር ግዛቸው ካቤኔ አባላት ተገፍተው የወጡ በመሆናቸው፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ለቦርዱ ሪፖርት እንዳደረጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን›› ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንጂ እነሱ ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው እንዲሁም ለአባላቶቻቸውና ለፓርቲው ክብር ስላላቸው እውቅናውን ለእነሱ ሰጥቻለው ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹ምርጫ የሚገባ ፓርቲ በማስፈለጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን ፓርቲውን የሚያስቀጥለው ባለመሆኑና ፓርቲውን እንደ ፓርቲ እንዲቆይ ስለሚፈለግ ዛሬ ጥር 21 ቦርዱ ባደረው አስቸኳይ ስብሰባ እነ ትግስቱ አወሉ ወደ ምርጫ እንዲገቡ ወስኗል›› ብሏል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ ስለመሆኑ በምን ታረጋግጡልናላችሁ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ሁለቱም ችግር አለባቸው፡፡ እኛ ያየነው በአንጻራዊነት ነው፡፡ የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ችግር ቢኖርበትም ከዛኛው የተሻለ ነው፡፡ እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

aeup

በተመሳሳይ እነ ማሙሸት አማረ በጠቅላላ ጉባኤ ባለመመረጣቸው፣ ለተከታታይ 3 ወራት ወርሃዊ መዋጮ ያላወጣ አባል ከአባልነት የሚሰረዝ በመሆኑና ከፓርቲ አባልነትም ስለተባረሩ እንዲሁም ህገ ወጥ ማህተም በማሳተማቸው እውቅና እንዳልሰጣቸው ገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል 2005 ዓ.ም ላይ አበባው መሃሪ የተመረጡበት ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ እንዳልነበር ቢታመንም በተደረገ ምርመራ የተሟላ መሆኑ በመታወቁ፣ በትክክለኛው ማህተም ስለሚጠቀም፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ በተባለበት ወቅት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረጉና ሪፖርቱንም ስላቀረበ ወደ ምርጫው እንዲገባ ወስኛለሁ ማለቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ለመሳተፍ መወሰናቸውን ተከትሎ ህወሓት/ኢህአዴግ  በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ሊያፈርሳቸው የተለያየ ህገወጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፣ ቦርዱ ገለልተኛ እና ነፃ አለመሆኑን በድርጊቱ እየገለፀ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተቃውሞና ቅሬታ እያቀረቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ 94ኛ ዓመት የልደት በዓል ተከበረ

ሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ

ሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ

በጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት በ15ኛ አመታቸው ከፋሽስት ወራሪ ጦር ጋር በተለያዩ አውደ ግንባሮች ተፋልመው ከፍተኛ ጀብዱ የፈፀሙት እና ጣሊያን ከአገር ተሸንፎ ከወጣ በኋላም የአገር ዳር ድንበርን በማስጠበቅ ከፍተኛ ጀግንነት የፈፀሙት የሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ 94ኛ የልደት በዓል ዛሬ ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ተከበረ፡፡

በ1929 ዓ.ም ጣሊያን  ከ40 ዓመታት የአድዋ ሽንፈት በኋላ  ዳግም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ገና በ15 ዓመት ወጣትነት ዕድሜያቸው የራሳቸውን ጦር በማደራጀት ጠላትን የተዋጉት ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ በወቅቱ በተለያዩ የጦር ውሎዎች በጠላት ላይ ከፍተኛ ጀብዱን ተቀዳጅተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የአገርን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ቀበና አካባቢ በሚገኘው የልጃቸው የትምወርቅ ጃጋማ ቤት የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት 94ኛ አመት የልደት በዓላቸውን አክብረዋል፡፡ በጄነራል ጃገማ ኬሎ 94ኛ ዓመት የልደት በዓል ከታደሙት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችም ተገኝተው ማክበራቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ

ሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ

ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ከነበሩት ጀኔራሎች መካከል በአሁን ወቅት በህይወት ከሚገኙት ሁለት ጀኔራሎች (በውጭ ሀገር የሚገኙት ሌ/ጀነራል ወልደስላሴ በረካ እና ሀገር ውስጥ ያሉት የ94 ዓመቱ ሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ) አንዱ ሲሆኑ፤ጀነራሉ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆች፣ አምስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡

የሌ/ጀነራል ጃገማ 94ኛ ዓመት ልደታቸው ሲከበር

የሌ/ጀነራል ጃገማ 94ኛ ዓመት ልደታቸው ሲከበር

የሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ በህይወት እያሉ በደራሲ ፍቅረ-ማርቆስ ደስታ “ጃገማ ኬሎ የበጋው መብረቅ” ታሪካቸው የተፃፈ ብቸኛው ጀግናም ያደርጋቸዋል፡፡ ጀነራል ጃገማ በ15 ዕድሜያቸው ወራሪውን የጣሊያንን ጦር ለመዋጋት ከዘመቱበት የአርበኝነት ገድል ጀምሮ እስከመደበኛው የሀገሪቱ መካላከያ ጦር ድረስ ለኢትዮጵያ እና ለህዝቧ ነፃነት እና ክብር ሲሉ በርካታ የጦር ገድሎችን መፈፀማቸው ይታወቃል፡፡ አሁን ያላቸው የሌተናንት ጀነራል ማዕረግም በሀገሪቱ የወታደራዊ ማዕረክ ታሪክ የመጨረሻውና ከፍተኛ መሆኑም ይታወቃል፡፡

ፍርድ ቤቱ በብሎገሮቹና በጋዜጠኞች ላይ ተሻሻለ የተባለውን የአቃቤ ህግ ክስ ተቀበለ

z9

ባለፉት 9 ወራት በፖሊስ ቁትጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩት 6 የዞን 9 ጦማርያንና 3 ጋዜጠኞች ላይ አቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም. አሻሽዬ አቅርቤዋለሁ ያለውን የክስ ቻርጅ የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ተቀባይ አድርጎታል፡፡

በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ በአሸባሪነት ወንጀል እንደሚጠየቁና ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ዛሬ ጠዋት በነበረው የክስ ሂደት ወቅት ጠይቋቸው ጉዳዩን ለከሰዓት አስተላልፎት ነበር፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ሰዓታት በፊት በነበረው የክስ ሂደት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለ17ኛ ጊዜ ለሚቀጥለው ማክሰኞ ጥር 26 ቀን ቀጠሮ በመስጠት ተበትኗል፡፡

ስድስቱ የዞን 9 ጦማርያንና ሦስቱ ጋዜጠኞች ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የከረመ ቢሆንም የክስ ሂደቱ ላይ ግን በርከት ያሉ የህግ ሂደትን ያልተከተሉ ሁኔታዎች ሲስተዋሉ መቆየቱን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡

አንድነት ፓርቲ በድብደባ ትግሉን እንደማያቆም በመግለፅ በድጋሚ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የምርጫ ቦርድ በፓርቲው ላይ የሚያሳየውን ጣልቀ ገብነትና ፓርቲውን ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ነበር፡፡ በዕለቱም በደብረ ማርቆስ፣ በጋሞ ጎፋ ከንባ እና በሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ በአዲስ አበባ የሰልፉ ጅማሮ ላይ ከ26 በላይ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እና በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ የነበሩ የ70 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የዓይን እማኞች፣ የህክምና እና የምስል ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በዕለቱ በፖሊስ ከተፈፀሙ ድብደባዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ነፍሰጡር ሴት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው የዕለቱን ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ እንቋረጥ ቢደረገም ፤ ለጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. መነሻውን ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት አንስቶ በፒያሳ በዳረሻውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ አደባባይ በድጋሚ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ በተመሳሳይ ዕለትም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች  በደሴ፣ በባህርዳር ፣በደብረ ታቦርና በሌሎች የክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የጠርቷል፡፡

በተለይ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በፓርቲው አባላት፣ደጋፊዎችና ቤተክርስቲያን ለፀሎት የተቀመጡ አዘውንት ምዕመናን በፖሊስ የተፈፀመባቸውን ድብደባ በማውገዝ፣ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችንም በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ይህንንም ሰላማዊ ትግሉ በጭፍጨፋና በውንድብና ለማቆም መሞከር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው! ሲል አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከታች ይመልከቱ፡-

udj1

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
=============================
ሰላማዊ ትግሉ በጭፍጨፋና በውንድብና ለማቆም መሞከር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው!

ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
የተሰጠ መግለጫ
================================

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰልፍ መጥራቱ ይታወቃል። ነገር ግን ስርዓቱ ህገ ወጥ ሰልፍ ነው በማለት በአንድነት አመራሮችና አባለት ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ድብደባ ወደር የማይገኝለት ነው። እርጉዞች፣ ህፃናት፣ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ደማቸው ፈሷል፤ አጥንታቸው ተሰብሯል። ሰላማዊ ሰልፉ ስርዓቱ እንደሚለው ህገ ወጥ አልነበረም፤ ስልፍ እንደምናደርግ ደብዳቤ ስንልክላቸው አንቀበለም ብለው ሲያንገራግሩ ደብዳቤውን እዚያ አስቀምጠንላቸዋል፤ ይህ ብቻ አይደለም በሬኮማንድ በድጋሚ ተልኮላቸው ተቀብለዋል። ህጉ አስተዳደሩ በአስራ ሁለት ሰዓት ውስጥ መልስ መስጠት አለበት ቢልም ከሰባ ሁለት ሰዓት በኋላ በሚዲያ “ሰልፉ ህገወጥ ነው” የሚል መግለጫ ከማውጣት ውጪ በደብዳቤ የመለሱት ነገር አልነበረም። በመሰረቱ በስብሰባና በሰልፍ አዋጁ መሰረት አንድ ፓርቲ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለአስተዳዳሩ ማሳወቅ ነው ያለበት። አስተዳደሩ ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንጂ ሰልፍ መፍቀድም ሆነ መከልከል አይችልም።

አምባገነኑ የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱንም ጭምር በማበላሸት ጠንክራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ ላይ ታች እያለ ነው። በተለይ አንድነት ፓርቲ ላይ በምርጫ ቦርድ፣ በኢቲቪ እና በሬዲዮ ፋና የሶስትዮሽ ግንባር በመክፈት በህዝቡ ዘንድ ብዥታ እንዲፈጠር፣ ምርጫው ያለጠንካራ ተዋዳደሪ እንዲካሄድ በማድረግ የምርጫውን ዋጋ ቢስነት ከማረጋገጡም በተጨማሪ ፓርቲውን ለማፍረስ ቀን ከሌሊት እየሰራ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ስርዓቱና ምርጫ ቦርድ የጥቅም ምንደኞች በማዘጋጀት ተለጣፊ አንድነትን በመጠፍጠፍ ፓርቲውን ከእውነተኛ አባላቱና ደጋፊዎቹ ለመቀማት እጅግ አሳፋሪ የሆነ የሽፍትነት ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።

አሁንም ቢሆን አንድነት ይህን የህወሀት/ኢህአዴግ ሴራና ውንብድና በመቃወም ለሚቀጥለው እሁድ ጥር 24/2007 በአዲስ አበባና በሌሎች የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ሰልፍ ያድርጋል። በአዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው ሰልፍ በተለምዶ ኢትዮ ኩባ አደባባይ (ድላችን ሀወልት) ሲሆን በትናንትናው ጥር 18/2007 ለአስተዳደሩ በደብዳቤ አስገብተናል። ይህ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሰልፍ አስተዳደሩ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ ተለዋጭ የጊዜ ወይም የቦታ አማራጭ እስካላቀረበ ድረስ በምንም ሁኔታ የሚታጠፍ አይደለም። አንድነት ስብሰባና ሰልፍ የማድርግ ህገመንግስታዊ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ በህዝባዊ ንቅናቄና በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ይቀጥላል።

ድል የሕዝብ ነው!!
ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ስልክ ቁ. ዐዐ11-1- 22-62-88

ፖ.ሣ.ቁ 4222

%d bloggers like this: