Monthly Archives: December, 2014

24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን ባህር ሰጥመው ሞቱ

yemen1ባለፈው ሰኞ ታህሣሥ 20 ቀን 2007 ኣ.ም. በጀልባ ወደ የመን ሊገቡ የሞከሩ 24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቻ በምትባል የየመን ወደብ ከተማ አቅራቢያ በደረሰባቸው የጀልባ መስጠም አደጋ መሞታቸውን የየመን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለፃ ከሆነ በጀልቧ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ በህይወት የተረፉ ስለመኖራቸውም ሆነ በአደጋው የሞቱትን በለመለየት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተደረገ ጥረት አለመኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በቅርቡ ህዳር 28 ቅን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ በየመን የወደብ ከተማ በሆነችው ሞቻ አቅራቢያ 70 ኢትዮጵያውያን በሚጓዙበት ጀልባ በደረሰ አደጋ ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ባህር አቋርጠው የምን ሊገቡ ሲሉ ህይወታቸው ላለፈው 94 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በአቅራቢያው ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንፅላ ፅህፈት ቤት አምባሳደሮች ያሉት ነገር የለም፡፡ በየ ዓመቱ የህንድ ውቅያኖስን እና ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው ወደ የመን ሊገቡ የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እየሞቱ ቢሆንም አደጋውን ለመቀነስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

yemenአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመንን ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር ለመሸጋገር የሚጠቀሙባት በመሆኑ የስተኞች ጣቢያ እንደማይመዘገቡና እገዛም እንደማይደረግላቸው ተጠቁሟል፡፡ የመን ባህር አቋርጠው ከሚገቡ አብዛኞቹ ስደተኞች መካከል ጥቂቶች ብቻ በተለይም በፈረንጆቹ 2014 መጨረሻ የመን በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን እገዛ የተደረገላቸው 9,500 ኢትዮጵያውን እነደነበሩ የድርጅቱ መረጃ አመልክቷል፡፡

ከመንግስት በሚደርስባቸው የፖለቲካ ጫና እና በሀገሪቱ ከተከሰተው የኢኮኖሚ ችግር በተፈጠረው የኑሮ ውድነት የተነሳ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር በየ ዓመት እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና ስራቸውን ለመቀጠል የሚያስችል ውል መጨረሻው የሚወሰነው በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሲፀድቅ እንደሆነ ገለፁ

dr.mereraታዋቂውና ስመ ጥር የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በመንግስት መደበኛው በስራ በቆያ ዕድሜያቸው በመጠናቀቁ ስራቸውን በሚታደስ ውል ስራቸውን እንዲቀጥሉ የትምህርት ክፍሉ ፈቃደኝነታቸውን በጠየቀው መሰረት ውል ፈርመው በስራ ገበታቸው ላይ እንደሆኑ አስታወቁ፡፡

ዶ/ር መረራ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ እንደገለፁት ከሆነ፤ በዩኒቨርስቲው በማስተማርና በምርምር ከ25 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉና አሁን ዕድሜያቸው 60 ዓመት ስለሞላቸው የጡረታ ጊዜያቸው በመሆኑ፤ በእሳቸውና በዩኒቨርስቲው መካከል በሚታደስ አዲስ የኮንትራት ውል ስምምነት መሰረት ስራቸውን ለመቀጠል ከዚህ ቀደም ከሚያስተምሩበት ትምህርት ክፍል እና ከዩኒቨርስቲው ማኀበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር መፈራረማቸውን እና ስራቸውንም መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው በኮንትራት መልክ የሚታደሰው አዲሱ የውል ስምምነት ሊፀና የሚችለው በእሳቸውና በትምህርት ክፍሉ ስራውን ለመቀጠል የሚያስችል ፈቃደኝነት ስምምነት በዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኩል ሲፀድቅ መሆኑንም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

አዲስ ሚዲያም በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዶ/ር መረራ ከሚሰሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባረሩ የሚል ዜና ተሰምቷልና እውነት ነው ወይ ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ እስካሁን የደረሰኝ መረጃ የለም፣ መደበኛ ስራዬን እየሰራሁ ነው፣ ነገር ግን አንዳንድ ወሬ እኔም እሰማለሁ እንጂ እሳካሁን የደረሰኝም የእግድ ደብዳቤም ሆነ መሸኛ የለም፣ አዲስ ነገር ካለ ወደፊት አብረን የምንሰማው ነው ሚሆነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዶ/ር መረራ ስራ ጋር በተያያዘ ስለተወራው ነገር ለማጣራትና ምላሽ ለማግኘት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ክፍል ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የኦፌኮ ሊቀመንበርና በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና (ክፍል 2)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
(ከዝዋይ እስር ቤት)

temesegen dበዚህ አውድ ለማቅረብ የተገደድኩበትን ዘግናኝ ታሪክ፣ ወደር በሌለው አስከፊነቱ የተነሳ ለንባብ ባላበቃው በወደድኩ ነበር፡፡ ግና! ይህ መንግስታዊ የጭካኔ ተግባር፣ ዛሬም በምስኪን ዜጎች ላይ እየተፈፀመና ብዙዎችን ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ህዝቡ ይህን ሊሸሸግ እየተሞከረ ያለውን መከራ ተረድቶ ሥርዓቱን በአደባባይ ዓመፅ “ሃይ!” ይል ዘንድ ትርክቴን ለማጠናቀር ተገድጄያለሁ፡፡ ለእስር ያበቃኝ የጋዜጠኝነት ሙያዬም ተጨማሪ ዕዳ ጭኖብኛል፡፡

“ጄል-ኦጋዴን”

ጄል ኦጋዴን በሱማሌ ክልል ርዕሰ-መዲና የሚገኝ፤ ለ800 እስረኞች ታቅዶ በ1992 ዓ.ም የተገነባ እስር ቤት ነው፡፡ የግቢውን ዙሪያ ከከበበው አጥር በግምት 15 ሜትር ፈንጠር ብሎ ሌላ ተደራቢ የድንጋይ አጥር ተበጅቶለታል፡፡ እስከ ሚያዝያ 24 1999 ዓ.ም ድረስ እስር ቤቱ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ካሉ መሰል ማጎሪያዎች ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ በዚህ በተጠቀሰው ቀን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች፣ አቦሌ እና ሰንደሬ ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ፣ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቻይናውያን ባለሙያዎች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሰነዘሩትን ከባድ ጥቃት ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞች ብቻ የሚታጎሩበት እስር ቤት ከሆነ ወዲህ ግን በዋይታ የሚናወፅና በደም ጅረት የሚጥለቀለቅ ምድራዊ ሲኦል ለመሆን በቅቷል፡፡ መንግስት በጥቃቱ ከዘጠኙ ቻይናውያን ጋር 74 ሲቪል ዜጎችና ወታደሮች መገደላቸውን ቢያምንም፤ የአካባቢው የአይን እማኞች ከሰራዊቱ ብቻ እስከ 300 እንደተሰዉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦብነግ እንደ አል-ቃይዳ እና አል-ሸባብ የአባላቱን አስከሬን ትቶ የመሸሽ ልምድ ስለሌለው በቡድኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

የሆነው ሆኖ ከዚህ ጥቃት በኋላ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የሚመራ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የደህንነትና (ጄነራል ሳሞራ የኑስ እና ጌታቸው አሰፋ ያሉበት) የፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚከተሉትን (ዛሬም ድረስ እየተተገበሩ ያሉ) አስቸኳይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ‹‹ከጅጅጋ ውጭ ባሉ በክልሉ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ፣ ትዕዛዙን ጥሶ የተገኘ ከነጭነቱም ሆነ ተሳፋሪዎቹ በከባድ መሳሪያ እንዲመታ፤ አብዛኛውን ህዝብ በፍጥነት ከመኖሪያ ቀዬው በማፈናቀል ለቁጥጥር ወደሚያመቹ ከተሞች ማስፈር (በ2006 ዓ.ም መጀመሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን 2300 መንደሮችን ወደ ተመረጠ ቦታ ማስፈሩ እንደተሳካ መናገሩን ልብ ይሏል)፤ ወታደራዊ መኪና ላይ ምንም አይነት የደፈጣ ጥቃት ከደረሰ በአቅራቢያው የሚገኝ መንደርን ያለርህራሄ ማውደም (ለማሳያ ያህልም ፍልቼ፣ ቃሙዳ፣ ሳስባኒ፣ ሁለሌ፣ ለንካይርተ፣ ቻለሌን… የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን መጥቀስ ይቻላል) እና ከአንድ ሻምበል ያነሰ ኃይል ለአስቸኳይ ጉዳይም ቢሆን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ›› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላም ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በክልሉ የሚገኘውን የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ወታደራዊ አዛዦችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሰብስቦ ማብራሪያ ሰጥቶ ሲያበቃ ውሳኔውን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ እንዲያደርጉት በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ደቡብ ምስራቅ ዕዝ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (ከ1993 ዓ.ም) በኋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሰፈረ ሲሆን እስከ ታህሳስ 1999 ዓ.ም ድረስ በሜ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ከታህሳስ 1999 እስከ 2000 ዓ.ም ደግሞ ብርጋዴር ጄነራል ስዩም አስተዳድሮታል፤ በዚሁ ዓመት ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ ድረስ ባሉት ጊዜያትም በብ/ጄነራል ሙሉጌታ በርሄ ስር የቆየ ሲሆን፤ ከሚያዚያ 2000 ዓ.ም አንስቶ አሁን ድረስ እየተመራ የሚገኘው በሌ/ጄነራል አብርሃም ወ/ማርያም (ቅፅል ስሙ ‹‹ኳርተር››) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ዕዝ ውስጥ በዋናነት ሶስት ክፍለ ጦሮች (12ኛ፣ 13ኛ እና 32ኛ) ክልሉን ሶማሊያ ድንበር ድረስ እንዲቆጣጠሩት ተመድበዋል፡፡ ሰፈራቸውን ነገሌ ቦረና ያደረጉት 43ኛ እና 44ኛ ክፍለ ጦሮችም፣ ኦጋዴን ድረስ እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአናቱም የአግአዚ ኃይል በቀድሞ ምክትል አዛዡ ብ/ጄኔራል ገ/መድህን ፈቀደ (‹‹ወዲ ነጮ››) ስር ሆኖ አልፎ አልፎ በተደራቢነት እየተላከ በነዋሪዎቹ ላይ በደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ እና ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፈ ስለመሆኑ ከወታደራዊ መረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ለደረሱ እልቂቶችና ጭፍለቃዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ ተደርገው የሚጠቀሱት ከጄነራል ሳሞራ፣ ከጀኔራል ‹‹ኳርተር›› እና ከክልሉ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ በብ/ጄነራል በየነ ገ/እግዚአብሔር (‹‹ወዲ አንጥር››) የተመራው 12ኛ ክ/ጦር እና በብ/ጄነራል ፀጋዬ ገ/ጨርቆስ (‹‹ጀብጀብ››) ዕዝ ስር የነበረው 13ኛ ክ/ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኦብነግ በስፋት ይንቀሳቀስባቸዋል ተብለው የሚታሰቡት፡- ደገሃቡር፣ ቀብሪደሃር፣ ዋርደር፣ ጎዴ እና ቪቅ ከተሞች መደበኛ የጦር ቀጠናዎች ከሆኑ 15 አመት ያለፋቸው በመሆኑ፣ ከሌሎች የክልሉ አውራጃዎች በተለየ ሁኔታ የችግሩ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የሚፈፅማቸውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊቶች ለመሸፈን እንደ ቀይ መስቀል፣ ዓለም-አቀፍ ሚዲያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መሰል ተቋማት ከጅጅጋ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ በኃይል አግዷል፡፡ ይህ ኩነትም በ ዙ-23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ተደብድበው ከምድረ-ገፅ የጠፉ መንደር ነዋሪዎች፣ የቤት እንስሳት እና ቁሳዊ ንብረቶች በአንድነት ተቃጥለው መውደማቸውን ዛሬም ድረስ በምስጢርነት ሸሽጎ ለማቆየት አስችሎታል፡፡

የሆነው ሆኖ የመከላከያ ሰራዊቱ እና በክልሉ ከ70-80 በመቶ በሚሆኑ አካባቢዎች ላይ መንቀሳቀስ የቻለው ኦብነግ፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከባድ ውጊያ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ግጭቱ አሁንም ሳያበራ የመቀጠሉ ምክንያት አማፂው ቡድን ያን ያህል ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የጄነራሎቹ እጅ በዘወርዋራ ስላለበት መሆኑን ወታደራዊ ምንጮቼ ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹የኦብነግ ህልውና በተለይም ለከፍተኛ መኮንኖች ዋነኛ ንግድ (ቢዝነስ) ነው›› ይላሉ፡፡ የክልሉ መንግስት ‹‹የመረጃ እና ፀጥታ ባጀት›› በሚል ሽፋን በዓመት የሚመድበውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ሀብት እንዲያወራርዱ አዛዦቹ አይገደዱም፡፡ መከላከያ ራሱም ‹‹የመረጃ እና የበረሃ ፍሳሽ›› በሚል የሚበጅተው አመታዊ ወጪ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በጀት እስከ ኃይል አመራሮች ድረስ ወርዶ እንደየድርሻቸው መጠን የሚመዘበርበት አሰራርም ተዘርግቶለታል፡፡ እናም ጀነራሎቹ ኦብነግ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ የገቢ ምንጫቸው እንዳይደርቅም ሆነ፤ ከአቅም በላይ ተጠናክሮ በብቃት ማነስ እንዳያሳጣቸው (እንዳያስወቅሳቸው) ተቆጣጥረው ለመዝለቅ የቻሉበትን ቀመር እንዲከተሉ ይህ የገቢ ምንጭነት ገፊ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ በቀጥታ የክልሉ አስተዳደር የሚያዝዘውና ‹‹ልዩ ኃይል›› ተብሎ የተቋቋመው ታጣቂ ቡድን ዛሬም ድረስ የሎጅስቲክ አቅርቦቱን ያለጨረታ ጠቅላላ የያዘችው የሜ/ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ (በአሁኑ ወቅት ጀነራል አበባውን ተክቶ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነው) ባለቤት ሃዋ መሆኗ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ክልሉን የሚያስተዳድሩት በህዝብ የተመረጡት ሳይሆኑ ‹‹የፀጥታ አማካሪ›› በሚል በየወረዳው የተመደቡ የሻለቃ ወይም የሻምበል አዛዦች ከጀርባ ሆነው ነው፡፡ ለነርሱ ያልተመቸ ኃላፊን በሌላ እስከመቀየር ድረስ የሚንጠራራ ስልጣን አላቸው፡፡ የፕሬዚዳንት አብዲና እና የጄነራል ‹‹ኳርተር››ን የ‹‹ሥራ ግንኙነት›› መመልከቱ ጉዳዩን ፍንትው አድርጎ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በርግጥም አስራ ሦስት ፕሬዚዳንቶች የተፈራረቁበት ክልል ዛሬ እንዲህ በጨካኙ አብዲ መርጋት መቻሉ እንቆቅልሽ ሊሆን አይችልም)፡፡

‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ከደረቅ ወንጀለኞች ማረሚያነት፣ በኦብነግ አባልነት የሚጠረጠሩ ንፁሃንን ወደማሰቃያ እስር ቤት እንዲቀየር የተደረገበት መግፍኤ ከላይ የጠቀስኩትን (የ1999 ዓ.ም የኃይል ጥቃትን) ተከትሎ ሟቹ አምባ-ገነን ጠ/ሚኒስቴር በደህንነት ኮሚቴው ስም የሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ መቼም ዕድል ፊቷን አዙራበት ወደዚህ ግቢ የተላከ ምስኪን፣ በቀን አንድ መናኛ እንጀራ እየተወረወረለት፣ በ‹‹ምርመራ›› ስም የተወለደበትን ቀን ከመርገም አልፎ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚያጎናፅፈው መልአከ-ሞት ቶሎ መጥቶ እንዲገላግለው እስከመናፈቅ ለሚያደርስ ስቀየት (ቶርቸር) ይዳረጋል፡፡ እስር ቤቱ የተገነባው 800 ታሳሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ ወደምድራዊ ገሃነም ከተቀየረ ወዲህ ግን ከ5000 በላይ ሰዎች የሚታጎሩበት የሰቆቃ ግቢ ሆኗል፡፡ ሁሉም ታሳሪዎች ከጠዋት 2፡30 እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ አንድ ቦታ ተሰብስበው ክብርን፣ ሞራልን እና ሰብዕናን የሚያጎድፍ ግፍ ይፈፀምባቸዋል፡፡

ogadenበተለይም ሴት እስረኞች በየተራ እንዲቆሙ ይደረግና ወንዱ አንድ በአንድ እየተነሳ ሴተኛ አዳሪ መሆኗን፣ እሱ እና ጓደኞቹ ከእርስዋ ጋር ግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀማቸውን፣ ወዘተ እንዲናገር ይገደዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኖ ካልተገኘም በጨካኝ ታጣቂዎቹ ፍዳውን ይበላል፡፡ ሁኔታውን መራር የሚያደርገው ደግሞ ‹‹ስብሰባው›› ሲጠናቀቅ፣ ሰብሳቢው እስረኞቹ ወደየክፍላቸው እንዲገቡ ትዕዛዝ የማይሰጥ መሆኑ ነው፤ ይልቁንም ወፋፍራም ዱላ ጨብጠው ዙሪያውን ለከበቡት ፖሊሶች በአይኑ ምልክት ያስተላልፋል፤ ይሄኔ በያዙት ቆመጥ ከአቅራቢያቸው ያገኙትን ሁሉ መቀጠቀጥ ይጀምራሉ፤ እስረኛውም ከዱላው ውርጅብኙ ለማምለጥ ባገኘው አቅጣጫ ይተራመሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በየቀኑ የተለመደ በመሆኑ የዕለቱ ፕሮግራም ሊገባደድ በተቃረበ ቁጥር፣ ሁሉም ለመሸሽ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቃል፤ ከድብደባው ማምለጡ ግን ብዙም የሚሳካ አይሆንም፡፡

በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈር፣ ሙዝ ልጦ እንደመብላት ቀላል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም በርካቶች በየጊዜው ለውርጃ ወደሆስፒታል ሲላኩ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ እዚያው ለመውለድ የሚገደዱ እህቶችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሴት እስረኞች ፀጉራቸውን ከማሳደግ ይልቅ መላጨትን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈፀምባቸው ስቅየት የበሰበሱ ቆሻሻዎችንና ፈሳሽ-ሰገራዎችን ፀጉራቸው ላይ መደፋትን ስለሚያካትት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ቦታ ሴቶች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እና ልብሶቻቸውን እንዲያወልቁ ከተደረገ በኋላ እርቃናቸውን የሚገረፉበት ጊዜም እንዳለ ከአይን እማኞች ሰምቻለሁ፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ንፅህናን ካለመጠበቅና በምግብ እጥረት የሚነዛው ወረርሽኝ ነው፡፡ በ2004ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በሽታው ተከስቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ 700 ያህል ሰዎች በሞት መቀጠፋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ አስከሬን ቶሎ ስለማይነሳ እስረኞቹ ከአስከሬኑ ጋር እስከ 3 ቀን ድረስ ጋር ለመቆየት ይገደዱ ነበር፡፡

በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ግቢ ከሚገኙ ማጎሪያዎች መካከል 3ኛ፣ 4ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ‹‹የቅጣት ቤት›› ሲሆኑ፤ አሰራራቸውም ሶስት በሶስት ሜትር የሆነ እጅግ በጣም ጠባብ፤ ውስጣቸውም ሃምሳ ሳንቲ-ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ የተሞላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍልም የግድ ከ25 እና ከዚያ በላይ እስረኞች እንዲይዝ ስለሚደረግ ለቅጣት ወደግቢው የተላከ እስረኛ ለሳምንት ያህል እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ለመሰንበት ይገደዳል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደዚህ ግቢ እየተላኩ ስቅየትም ሆነ ግድያ እንደሚፈፀምባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በግቢው ለአራት ወራት ገደማ ያሳለፈው ሀሰን፣ በውል በማያስታውሰው በአንድ የተረገመ ቀን 3 ወታደሮች ሲረሸኑ ማየቱንና ከመካከላቸው አንዱም ‹‹እባካችሁ አትግደሉኝ! የ3 ልጆች አባት ነኝ!›› እያለ ሲማፀን መስማቱን ያስታውሳል፡፡

እስረኞቹ ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ከዚህ ቀደም ‹‹አል-ኢትሀድ አል-ኢስላሚያ›› በሚል ስም ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ፤ በኦብነግ ተሸንፎ ከኦጋዴን የተባረረው አማፂ ቡድን አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግስት ምህረት አድርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት ከተመለሱ በኋላ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዛኛውን አሰባስቦ ‹‹ልዩ ኃይል›› ብሎ አደራጅቷቸው ሲያበቃ፤ ከኦብነግ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ እስረኞች ላይ ያሻቸውን እንዲፈፅሙ ባልተፃፈ ሕግ ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም የቀድሞ ሽንፈታቸውን ለመበቀል እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በክልሉ ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ የእስር ቤት ግቢዎች ውስጥ የጅምላ መቃብር መመልከት አስገራሚነቱም አስደንጋጭነቱም እየቀረ የመጣው ከዚህ አኳያ ይመስለኛል፡

ኢትዮጵያዊውን የገደለው ቻይናዊ “ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት” ሲባል ክሱ እንዲቋረጥ ተደረገ

በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ውስጥ ኢትዮጵያዊውን የገደለው ዠንግ ቢንዥንግ የተባለ ቻይናዊ ‹‹በቸልተኝነት ሰው በመግደል›› ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የነበር ቢሆንም ‹‹ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት›› በሚል ትዕዛዝ ክሱ መቋረጡን ከክልሉ ፍትህ ቢሮ የተገኘው ሰነድ አጋለጠ፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለአቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተከሳሹ ካሳ ከፍሎ መውጣቱ ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት እንደሚበጅ በጻፈው ደብዳቤ ክሱ እንዲቋረጥ መደረጉን ‹‹በአማራ ፍትህ ቢሮ የምዕራብ ጎጃም ዞን የፍትሕ መምሪያ የወንጀል መዛግብት መርምሮ መወሰንና ተከራክሮ ማስወሰን የስራ ሂደት›› ለሰሜን አቸፈር ፖሊስ ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ተመልክቷል፡፡ በትዕዛዙ መሰረትም ክሱ ቀሪ ሆኖ የምርመራ መዝገቡ ተመላሽ መደረጉን በደብዳቤው ላይ መገለፁን ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

በ2004 ኣ.ም. በአርሲ በቻይና ኩባን ተቀጥረው የሚሰሩ ዘጎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በቻይኖች ተፈፅሞባቸው አቤቱታ ቢያቀርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ተበዳዮቹንና አቤቱታ አቅራቢዎቹን ለመግደልና ለማሰር በመሞከሩ የሰራተኛ ማኀበሩ አመራሮች ሀገር ጥለው መሰደዳቸው አይዘነጋም፡፡news pic

በኢትዮጵያ የሚካሄድው መጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. እና ተፅዕኖው

ብስራት ወልደሚካኤል

addismediab@gmail.com

የፖለቲካ ምርጫ ህዝብ የስልጣኑ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጥበትና ለዚህም ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበት አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት አካል ነው፡፡ ሂደቱ የሚከናወነውም ሁለትና ከዛ በላይ በሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በተዘጋጀላቸው እኩል መድረክ ተወዳድረው አማራጫቸውን ለህዝቡ በማቅረብ የመንግስት ስልጣን ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የፖለቲካ ምርጫን ከጀመረች የቆየች ቢሆንም፤እስካሁን በህዝቡ ተቀባይነትና መተማመን ላይ የደረሰ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውጤት ላይ ለስልጣን የበቃ የመንግስት ስርዓት ለማየት እንዳልተቻለ ይነገራል፡፡

ELECየፖለቲካ ምርጫ ዓላማ፣ጠቀሜታና አስፈላጊነት ዜጎችን የሀገራቸው ስልጣን ባለቤት ከማድረግ ጎን ለጎን ሀገሪቱን የመምራት ዕድል ባጋጠማቸውና በህዝቡ መካከል መተማመን ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖራቸው የነቃ ተሳትፎ የሚደርስባቸውን ግድያ፣ እስር፣ ስቃይ፣ ስደት፣አድሎና መገለልን ለማጥፋትና ለመቀነስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ስልጣን ምርጫ በቀረበ ቁጥር መብቶቻቸውን የሚጠይቁ ዜጎች ላይ የሚወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እምርምጃ ተባብሶ የሚቀጥል በመሆኑ፤በገዥው ስርዓት በሚወሰዱ ወታደራዊ የኃይል እርምጃዎች መቀነስ ሲገባቸው ይበልጥ ተጠናክረው በመቀጠል በርካታ ንፁሃን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ፡፡ በሚፈጠሩ ስህተቶችም የድርጊቱ ፈፃሚዎችም ሆኑ አዛዦቹ ኃላፊነት ወስደው አያውቁም፤ ሲወስዱም አይታይም፡፡

ምርጫ በቀረበ ቁጥር ሌላው የሚስተዋለው ችግር የፍትህ ስርዓቱ በህዝብ ያለው ተቀባይነትና አመኔታ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ በተለይም ከገዥው ስርዓት ተቃራኒ ሐሳብ ያነሱት ላይ የሚመሰረተው ክስ፣ የፍርድ ሂደት እጅግ መዘግየትና ፍርዱ ምርጫ ሲመጣ ከመቼውም ቀናት በላቀ ፍርሃት ሲነግስበት ይታያል፡፡ ይሄ በገዥውም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በህዝቡ የሚስተዋል አውነታ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በስልጣን ላይ ያለው አካል የራስ መተማመን ያለመኖርና የህዝብ አመኔታና ቅቡልነት አለኝ ብሎ ባለማመኑ በሚፈጠር ፍርሃት ነው በሚል ሲተች ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ምርጫ ሲቀርብና ሲመጣ ከበጎ ጎን ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹ ጎልተው ይወጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ

ኢትዮጵ ውስጥ የፖለቲካ ምርጫ መካሄድ የጀመረው በ1911 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህም የዘውድ ምክር ቤት በሚል የንጉሱ አማካሪዎች ምርጫ እንጂ የህዝብ የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት የሚሆንበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልነበረም፡፡ ተመራጮችም የህዝብ ወኪሎች ሳይሆኑ የዘውድ አማካዎች ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ በመቀጠልም በ1923 ዓ.ም. በሀገሪቱ የተፃፈ የመጀመሪያው ህገ መንግስት በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን መፅደቁን ተከትሎ እኩል ቁጥር ያለው ሁለት ምክር ቤት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ምክር ቤቶቹም የህግ መወሰኛ እና የህግ መምሪያ የሚባሉ ሲሆን፤ አባላቱ የተመረጡት በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሳይሆን በንጉሰ ነገስቱና በመኳንንቱ ነበር፡፡ ምክር ቤቶቹም ከ1923-1928 ዓ.ም. የጣሊያን ወረራ ድረስ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ከወረራው ድል በኋላ በ1935 ዓ.ም እንደገና የህግ መምሪያና የህግ መወሰኛ  ምክር ቤቶች ያሉት ፓርላማ ተቋቋመ፡፡ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም በንጉሠ ነገሥቱ የተመረጡ ሲሆን የህግ መምሪያ አባላት ግን እንደቀድሞው በንጉሡና በባለሟሎቻቸው አማካይነት የተመረጡ መሆናቸው ቀርቶ የአገር የሽማግሌዎች በየወረዳቸው ተሰብሰበው የሚመርጡዋቸው ባላባቶች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ እነዚህ የምርጥ ምርጥ ተወካዮች ከ1935 እስከ 1948 ዓ.ም ድረሰ ሳይለወጡ ለ15 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ህዝቡ ራሱ ወኪሎቹን በቀጥታ እንዲመርጥ ተፈቀደ፡፡ በዚህም መሰረት ከ1948-1967 ዓ.ም በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱም ምርጫውን የሚያካሂደው የምርጫ ቦርድ የተቋቋመ ሲሆን፤ስራውም ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይሰራ ነበር፡፡

በ1967 ዓ.ም. በሀገሪቱ በወታደራዊ ኮሚቴ “ደርግ” በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሥልጣኑን ጨበጠ፡፡ በሥራ ላይ የነበረው ፓርላማ ተበትኖ በምትኩ በ1967 ዓ.ም በጥቅምት ወር ከልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎችና መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ 6ዐ ሰዎችን ያቀፈ የመማክርት ጉባኤ ተመሠረተ፡፡ ይህ የመማክርት ጉባኤ እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ሲሰራ ቆይቶ ተበተነ፡፡

በኋላም በ1979 ዓ.ም 835 አባላት ያሉት የሥራ ዘመናቸውም አምስት ዓመት የሆኑ ባለ አንድ ሸንጎ ምክር ቤት በምርጫ ተሰየመ፡፡ በወቅቱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገሪቱ ቢኖሩም፤ዕጩ ተወዳዳሪ የሚጠቁመውምና የሚያስመርጠው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ “ኢሠፓ” ነበር፡፡ ኢሠፓ ይከተለው የነበረው የሶሻሊስት ርዕዮት ዓለምን በመሆኑ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ዝግጁነቱም ሆነ ፈቃደኝነቱ አልነበረውም፡፡ ስለሆነም በነበረው ምርጫ ጠቋሚው፣ አስመራጩ እና ተመራጩ ራሱ “ኢሠፓ” ነበር፡፡

በግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በትጥቅ ትግል ኢሠፓን በኃይል ከተወገደ በኋላ ወደ ሥልጣን በወጣው ኢህአዴግና አጋሮቹ የሽግግር መንግስት ተመሰረተ፡፡ በሽግግር መንግስቱ በየካቲት 1984 ዓ.ም የወረዳና የቀበሌ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት ምርጫመደረጉን እና ብዙ ሳይቆይ በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም ሀገር አቀፍ፣ ክልላዊ፣ የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ መደረጉን የአሁኑ የምርጫ ቦርድ ድርሳን ያመለከታል፡፡

በወቅቱ የነበረው ምርጫ ኮሚሽን ሥራውን አጠናቆ ሲጨርስ በምትኩ የዛሬው “ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ” በአዋጅ ቁጥር 64/1985 ዓ.ም መሠረት ተቋቋመ ፡፡ በተለይ በህዳር 1987 ዓ.ም. በሀገሪቱ ታሪክ 4ኛ ተደረጎ የሚወሰደው ህገ-መንግስት ከፀደቀ በኋላ ቀደም ሲል በአዋጅ የተቋቋመው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ” በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 1ዐ2 መሠረት ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቋቋመ ሲቪል ተቋም ነው ቢልም፤ ዛሬም ድረስ ከገዥው ስርዓት በስተቀር በህዝቡም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃና ገለልተኛ አይደለም በሚል ይተቻል፡፡

ቦርዱ ከተሠየመበት ከህዳር 1986 ዓ.ም ጀምሮ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች ተከትሎ በተፈጠሩ ቅሬታዎች መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ሐሳቦችን አካቷል በሚል የምርጫ አዋጁ አምስት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ይሁን እንጂ ችግሩ በተለይም ቦርዱ ነፃና ገለልተኛ አይደለም፣ የገዥው ስርዓት አንዱና ዋነኛው መሳሪያ ነው የሚሉ በርካታ ቅሬታዎች ከማስረጃ ጋር ቢቀርብም፤ ቦርዱ ራሱን ነፃና ገለልተኛ ነኝ በሚል ዛሬም ቀጥሏል፡፡

በተለይ በዘመነ ኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የተቋቋመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በስምና በስልት ካልሆነ በግብር ከቀደሙት ብዙም የተለየ አይደለም በሚል ቢተችም፤ በሀገሪቱ የነበረውን የምርጫ ታሪክ ወደ ጎን በመተው፤ ራሱን ቀዳሚ በማድረግ 1ኛው ምርጫ ብሎ የሚጀምረው በግንቦት1987 የተደረገውን ነው፡፡ በመቀጠልም 2ኛው በግንቦት 1992፣3ኛው በግንቦት 1997፣ 4ኛው በግንቦት 2002ዓ.ም. ብሎ 5ኛውን የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለማካሄድ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ቦርዱ አከናወንኳቸው በሚላቸው ያለፉት አራቱም ምርጫዎች አስፈፃሚዎች፣ የህዝብ ታዛቢዎችና የቦርዱ አባላት ከአባልነት ጀምሮ ለገዥው ስርዓት ወገንተኝነት ስላለ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አልነበረም በሚል ወቀሳ የቀረበበት ሲሆን፤በተለይ በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ግን ያልተጠበቁ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ ከነበሩ ክስተቶች መካከልም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ያልተጠበቀ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው፣ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ በንፁሃን ሲቭሎች ላይ የተፈፀመው ግድያና እስራት እንዲሁም ስደት የማይረሳ ክፉ ትዝታን ጥሎ አልፏል፡፡

ELECT2ቦርዱ በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የነበረውን የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በምርጫ ቦረድ፣በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በዋነኞቹ ተፎካካሪ በነበሩት ቅንጅት እና ህብረት ከፍተኛ ቅራኔ ተፈጠረ፡፡ በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞች ሲሰሙ፤በተለይም በአዲስ አበባ በመንግስት የመከላከያና ፖሊስ አባላት ህፃናትን ጨምሮ ከ160 በላይ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ የአሁኑ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የመጨረሻ ውጤት መሰረት ከ547 የህዝብ ተወካዮች (ፓርላማ) መቀመጫዎች መካከል ኢህአዴግ 327፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች 174 (ቅንጅት 109፣ ህብረት 52፣ ኦፌዴን 11)፣ የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች የሚባሉት 45 እና 1 የግል ተወዳዳሪዎች መቀመጫ ማግኘታቸውን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ በምዕራብ ወለጋ ደምቢዶሎ የግል ተወዳዳሪ ሆነው ያሸነፉት ደግሞ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡

በግንቦት 2002 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ደግሞ ተስፋ ሲጣልበት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር መውደቁ ራሱ ገዥው ኢህአዴግንም እጅግ ያስደነገጠ ነበር፡፡ ይህም ገዥው ስርዓት በሚከተለው አሰራር ከቢሮ ጀምሮ የመንግስትን ንብረት ከህግ አግባብ ውጭ በይፋ ከመጠቀም አልፎ ከራሱ ውጭ መገናኛ ብዙኃን ጉልህ ሚና እንዳይኖራቸው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በገዥው ፓርቲ ጥብቅ ቁጥጥርና መልካም ፈቃድ ካልሆነ ተፎካካሪዎች አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውንም ሆነ የአደባባይ የፖለቲካ ምክክርና ክርክር እንደ 1997 ዓ.ም. እንዳያደርጉ በርካታ የእጅ አዙር አሉታዊ ገደቦች የተጣሉ ተጣሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በቴሌቪዥን መስኮት ለህዝቡ ፊትለፊት የሚደረግ ክርክር ቀርቶ በስቱዲዮ ተቀርፆና ተቀንሶ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡ በዚህም መሰረት በዓለም ላይ በመድበለ የፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት ታይቶ የማይታወቅ በግንቦት 2002 ዓ.ም.በተደረገው ምርጫ ከ547 የፓርላማ መቀመጫ ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ 545 መቀመጫ ድምፅ ሲያገኙ፣ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 1 ተወዳዳሪ ከአዲስ አበባ የአንድነት/መድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ፣ ከደቡብ ክልል ልዩ ቦታው ከፋ ቦንጋ በሚባል አካባቢ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የሚባሉ 1 የግል ተወዳዳሪ ሆነው ብቻ ማሸነፋቸውን ቦርዱ ይፋ አደረገ፡፡ ከዛ ውጭ ያለውን 99.6 በመቶ የሚሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በአንድ ፓርቲ ሐሳብና ድምፅ ውክልና ተዋጠ፡፡

 መጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. እና ሰብዓዊ መብቶች

ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በሀገሪቱ አንፃራዊ ሐሳብን የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት ሙከራ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ 1997 ዓ.ም. ተከትሎ በተወሰዱ ስልታዊ እርምጃዎች 101 የነበሩ የህትመት መገናኛ ብዙኃን በ2007 ዓ.ም. ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ ያሉት ጋዜጦችና መፅሔቶች በአጠቃላ ከ25 አይበልጡም፡፡ ከነዚህም 16 ያህሉ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኀበራዊ ላይ ትኩረት አድርገው ይሰሩ ከነበሩት ውስጥ 8ቱ መንግስት በመሰረተው ክስና ስልታዊ እርምጃ ከአንባቢው ውጭ ሆነዋል፡፡ የብሮድካስ ሚዲያ በተለይ ከጥቂት መዝናኛ ላይ ትኩረት ከሚያደርጉ ኤፍ ኤም ጣቢያዎችና ንብረትነታቸው የገዥው ፓርቲና የመንግስት ከሆኑት ውጭ አጭርና መካከለኛ የሬዲዮ ሞገድ ስርጭት ጣቢያ እስካሁን አልተፈቀደም፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ እስካሁን ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ አንድም የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የለም፡፡ ይህም ምርጫ 1997 ዓ.ም. ለነበረው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና የነበራቸው በመሆኑ ገዥው ስርዓት እንዲቀጥሉ ባለመፈለጉ የተወሰዱ እርምጃዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡በተለይ ከምርጫ 1997 ዓ.መ. በፊት አዲስ ብሮድ ካስቲንግ ካምፓኒ የሚባል የሬዲዮ ጣቢያ የስራ ፈቃድ ወስዶ ለስርጭት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ቢያስገባም፤ኩባንያው ስርጭት ሳይጀምር ከምርጫ  በኋላ መሳሪያዎቹ እንዲወረሱና ፈቃዱም እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ ይሄም አንዱ ያለፈው ምርጫ አሉታዊ ተፅዕኖ ውጤት ነው፡፡

የነበሩት የጋዜጦችና የመፅሔቶች መጠን በእጅጉ መቀነስ ዋነኛው ምክንያት ያ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ያ እንዳይቀጥል የተለያዩ አዋጆች ተከታትለው የወጡ ሲሆን፤በዋነኝነትም የፕሬስ ነፃነት አዋጅ፣ የብሮድካስት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጆች ይጠቀሳሉ፡፡ አዋጆቹም በቀጥታና በተዘዋዋሪ የፕሬስ ነፃነት እና ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የፕሬስ ነፃነትና የሲቪክ ተቋማትን መጎልበት አሽመድምደውታል፡፡  በተለይ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ ነፃ ፕሬስ መመስረትና ነፃና ገለልተኛ የሲቪክ ተቋም (የሙያ ማኀበርም ሆነ የብዙኃን ማኀባር) ማቋቋም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የምርጫ ውጤትን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ ሲሆን፣ ለዚህም እርምጃ ህጋዊነት ለማላበስ ተቋማቱ ከገዥው ስርዓት ቁጥጥር እና ፍላጎት ውጭ እንዳይሆኑ የሚያስችል አዋጅ ከመደንገግ በተጨማሪ መዋቅር ዘርግቶ ተቋም እስከመመስረት ተደርሷል፡፡ የዚህም ውጤት ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጣሱ ሰፊ እድል መፍጠሩ ቢታወቅም፤ በመንግስት በኩል ግን እስካሁን የተወሰደ እርምት የለም፡፡

በተለይ በ2001 ዓ.ም. የወጣው የፀረ-ሽብርተንነት አዋጅ የሀገሪቱን እና ህዝቧን ደህንነት ለመጠበቅ በሚል የወጣ አዋጅ ነው ቢባልም፤ በተግባር እየታየ ያለው ግን የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም አዋጁ ህገ መንግስቱን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥሱ አንቀፆች ያሉበት በመሆኑ ሐሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሞከሩና በህዝቡ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች የአዋጁ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ አዋጁን ተከትሎ 17 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች እንዲሁም ከ200 ያላነሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ለከፍተኛ ስቃይና እስር ተዳርገዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይፋ እያወጧቸው ያሉና ይፋ ያልወጡ በየ አካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ እንደታሰሩ፣ ፍርድ ቤት ያልቀረቡና ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎችም ቀላል አይደሉም፡፡ በዚህም የዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውና አካላቸው ያለመደፈር መብትን ጨምሮ የዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መነፈጉ ይነገራል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተደርጎ ቢወሰድም፤ በግንቦት 16 ቀን ለሚካሄደው መጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡

ELCT1ተፅዕኖውም ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት ገልፀው በሚፈልጉት የፖለቲካም ሆነ ማኀበራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉና ገዠው ስርዓት በሚያከናውናቸው አሉታዊ ድርጊቶች ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እስር እንደሚጠብቃቸው በመገመት በፍርሃት እንዲቀድቁ ምክንያት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ገዥው ስርዓት ካላዘዘና ካልፈቀደ በስተቀር በፖለቲካው፣ በማኀራዊ እና በኢኮኖሚው ላይ ነፃ ተሳትፎ እንዳይኖር ተጨማሪ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ብለው የሚከራከሩም አልታጡም፡፡

ቀደም ሲል በተወሰዱ እርምጃዎች መጪው ግንቦት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ከወዲሁ የፍርሃት ድባብ እንዳጠላበት በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ለአብነትም ከሚያዚያ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፖለቲካውና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ አላቸው ተብለው የሚታመኑ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መታሰራቸውና በርካታ ጋዜጠኞች መሰደዳቸው ሌላው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ በስልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ጉጉት የተነሳ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱና እንዳሉና፤ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል፡፡ለዚህመ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የስርዓት ለውጥ ፍላጎቶች፣ የኑሮ ውድነት፣ በገዠው ስርዓት የሚፈፀሙ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ውጤቱንም ሆነ ሂደቱን በፍርሃትና በጉጉት እንዲጠበቅ አስችሎታል፡፡

በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና በመራጩ ህዝብ በኩል አሁን ያለው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎችም ሆኑ የህዝብ ታዛቢ ተደርገው የሚቀመጡ ሰዎች ነፃናት ገለልተና ሳይሆኑ ለገዥው ስርዓት ወገንተኝነት የሚታይባቸው ናቸው ተብለው ቅሬታ ቢቀርብባቸውም በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻለም፡፡ እንደ ምርጫ 1997 ዓ.ም. የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካና ሌሎች ነፃና ገለልተኛ ናቸው የሚባሉ በርካታ የሲቪክ ተቋማት ከሀገሪቱ እንዲባረሩ በመደረጋቸው ምርጫ 2007 ዓ.ም. እንደማይታዘቡ መረጃዎች የጠቀሙ ሲሆን፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካ ህብረት ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ምርጫው ከወዲሁ የፍርሃት ድባብ ያጠላበት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ምናልባትም የፍርሃት ድባቡ ወደ እውነት የሚቀየር ከሆነና መንግስት ካለበት ውስጣዊና ውጫዊ ችግር በማንኛውም መንገድ ራሱን በስልጣን ለማቆየት ካለው ፍላጎት አንፃር እንደ ከዚህ ቀደሙ የኃይል እርምጃን የሚጠቀም ከሆነ፤ በሀገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ከፍተኛ የፖለቲካና ማኀበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይም ምርጫውን አስመልክቶና ተከትሎ ሰብዓዊና ዴሞክራሲም መብቶች መጣስ በቀጠናወም ላይም የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍጠር በማኀበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም መጪው ምርጫ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብት አንፃር ከአዎንታዊ ጎኑ ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖው ሊወጣ ይችላል በሚል ከሀገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ትኩረት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

%d bloggers like this: