Daily Archives: December 14th, 2014

መድረክ በአዲስ አበባ የጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠናቀቀ

medrek1የ6 የፖለቲካ ድርጅቶች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ  ዴሚክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ)እሁድ ታህሣሥ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ፡፡ መድረክ ሰልፉን ያደረገው ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓትት ጀምሮ ሲሆን፤መነሻውን ከ4 ኪሎ ግንፍሌ ድልድይ አድርጎ በአዋሬ አልፎ  መዳረሻውን በየካ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው የጥምቀተ ባህር ታቦት ማደሪያ አካባቢ በሚገኘው ኳስ ሜዳ ላይ መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡

የግንባሩ መረጃዎች አንንደሚያመለክቱት በሰልፉ ላይ ከ8 ሺ በላይ የአዲስ ኣበባ ነዋሪዎች መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡ በሰልፉ ላይ ከተጋበዙ ፓርቲዎች መካከል የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ተክሌ ና የፓርቲው አመራርና አባላትን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡  የመድረኩ ሰላማዊ ሰልፍ በወጣቶች የመድረክ አመራር፣ የሴቶች ተወካይ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳና የወቅቱ የመድረክ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ ባሰሙት ንግግሮች መጠናቀቁን ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል።

MedrekRally-Dec-2014-4-Merera2ሰላማዊ ሰልፉ የኢህኣዴግ መንግስት ሊያርማቸው የሚገቡ፣ መመቻቸት ያሉባቸው ፖለቲካዊ ምህዳር፣ መወገድ ያለበት የፀረ ሽብር ህግ ፣የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ፍትሃዊ እንዲሆን ሊያደረጉ የሚገቡ ስራዎች እንዲሰሩ፣ በየቦታው እያጋጠመ ያለው አፈና፣ እስርና እንዲሁም ግድያዎች እንዲቆሙ በሰልፉ ላይ ከተሰሙ መፈክሮች በተጨማሪ የመድረኩ አመራሮች ጥሪ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ

udj2bestአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከታህሣሥ 3-4 ቀን 2007 ዓ.ም. ያደረገው አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ፡፡ ፓርቲው በተከታታይ ቀናት መዋቅሩን ከዘረጋባቸው ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች በመጡ አባላቱ ባደረገው ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተለያዩ አጀንዳዎችን በማፅደቅ ውሳኔዎችን ያሳላፈ ሲሆን፤ በተለይም የቀድሞው የፓርቲው ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የተመረጡትን ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱን ስልጣን ከነ ስራ አስፈፃሚዎቹ አፅድቋል፡፡ ሌላው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ቁጥር በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በአባላቱ ተወስኖና የፀደቀው ደንቡ ላይ ሰፍሮ ይቅረብልኝ ባለው መሰረት ተወስኖ እንዲሰፍር መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

udj4belayudjይህ በእንዲህ እንዳለ ከዋና አጀንዳዎቹ መጠናቀቅ በኋላ ፓርቲው በአመራር አባላቱ ለጠቅላላ ጉባኤ አባላት በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች(የአርሶ አደሩ ፤የከተማው ነዋሪ፤የባለሐብቱ ሁናቴ) በዳግማዊ ተሰማ፣ የተማሪውና የምሁሩ ነባራዊ ሁኔታ በጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ፣ የአንድነት የምርጫ ስትራቴጂ ግብ በፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ መቅረቡ ታውቋል፡፡
udj5girmaudjበመቀጠልም የስልጠናው ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት በመስጠት ስልጠና ተጠናቆ፣ በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይና የአንድነትፓርቲምክትል ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በምርጫ ስትራቴጂ ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡አባላቱ የፓርቲው የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳይ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ገበየሁ ይርዳው የአባላት መብትና ግዴታ ከፓርቲው ደንብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንጻር ስልጠና ከሰጡ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆኖ በስልጠናዎቹና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደረጉን የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

udj123tekleudjበመጨረሻም የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ የጉባኤውን የመዝጊያ ንግግር በማድረግ  አንድነት በብሔርም ሆነ በህብረብሔር ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት መዘጋጀቱንና ከአንድነት ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ላላቸው ፓርቲዎች ሁሉ የውህደት ጥያቄ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ተክሌ አንድነት ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. ምርጫን በአሸናፊነት ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝና አባላቱም በያሉበት ጠንክረው የበኩላቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ ጉባዔው በስኬት መጠናቀቁን ፓርቲው አስታውቋል፡፡

የታሰሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በመታወቂያ ዋስ ከእስር ተፈቱ

blueመንግሥት ያስተላለፈውን ጥብቅ ትዕዛዝ በመተላለፍ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጣስ ሙከራ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ከሰባት እስከ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ከዘጠኝ ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮችና አባላት፣ ታኅሣሥ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም በመታወቂያ ዋስ ከእስር ተፈቱ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲና የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ፣ በአምስት ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሰባት፣ አሥርና 14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው 84 እስረኞች በሁለቱ ቀናት ውስጥ የተፈቱ ሲሆን፣ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ለሰላማዊ ሠልፉ ወጥተው ታስረው የነበሩ ሰዎች ሁኔታቸው እየተጣራ ኅዳር 28 እና 29 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈታታቸውም ታውቋል፡፡

ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ለ24 ሰዓታት፣ የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊያደርግ ለነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ቅስቀሳ ወጥተው የታሠሩ ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ግን አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ማቲያስ መኩሪያ፣ የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ባህሩ እሸቱና አቶ ሲሳይ ዘርፉ ናቸው፡፡

ሦስቱ የፓርቲው አባላት የታሰሩት ለሰላማዊ ሠልፉ ቅስቀሳ ወጥተው በመሆኑ ሌሎቹ ሲፈቱ መፈታት ቢኖርባቸውም፣ ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆባቸው አለመፈታታቸው ተገልጿል፡፡

የታሰሩት የፓርቲዎቹ አመራሮችና አባላት በወቅቱ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና እንደተጎዱ የተገለጸ ቢሆንም፣ የሰማያዊ ፖርቲ አባላት ከሆኑት አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድና ወ/ሪት እየሩስ ተስፋው በስተቀር፣ ሌሎቹ ደህና መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሰውነታቸው ጉዳት እንዳለውና ሕመም እንደሚሰማቸው ከመናገራቸው ውጪ የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሺ ፈይሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡- ረፖርተር

%d bloggers like this: