9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባና እስር ተቋረጠ
ዛሬ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በ9ኙ ፓርቲዎች ለትብብር ለ24 ሰዓት በመስቀል አደባባይ የተጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በደህንነት፣ ፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ድብደባና እስር ምክንያት መቋረጡ ተገለፀ፡፡ ሰልፉን ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩ በርካታ የፓርቲዎቹ አባላትና ደጋፊዎች ተደብድበው መታሰራቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በተለይም ከአመራሮች የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ አለሳ መንገሻ እና የከንባታ ህዝቦች ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ በፖሊስ ታግተው መታሰራቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ከዋና አመራሮቹ በተጨማሪ አቶ ወሮታው ዋሴ፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ኢየሩስ ተስፋው፣ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ፣ ወይንሸት ሞላ፣ ሳሙኤል አበበ፣ እያስፔድ ተስፋዬ፣ሜሮን አለማየሁ፣ ንግስት ወንዲፍራው፣ ወይንሸት ንጉሴ፣ ምኞት መኮንን፣ አቤል ኤፍሬም፣ ኤፍሬም ደግፌ፣ ኃይለማሪያም፣ ሜሮን፣ ኢብራሂም አብዱልሰላም፣ እና ሌሎችም የትብብሩ አመራሮችና አባላት ከፍተኛ ቁጥር ባለው ፌደራል ፖሊስ መያዛቸውን እና በታገቱበት ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደነበር የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ የታሰሩት አለመለቀቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት የታፈሱት አመራሮች ቂርቆስ ፖፖላሬ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከታሰሩት መካከል ወጣት አቤል ኤፍሬም በተፈፀመበት ከፍተኛ ድብደባ ራሱን ስቶ የካቲት 12 ሆስፒታል እንተኛ እና አቶ ይልቃል ጌትነትም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢ ኤን ሬዲዮን ጨምሮ የተለያዩ የማኀበራዊ ገፆች መረጃ አመልክቷል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ አሰግድ ጌታቸው ለከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ውስጥ የ24 ሰዓታት የአዳር ሰልፍ ለማካሄድ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበርና አስተዳደሩ ግን ፍቃድ አለመስጠቱን መናገራቸውን ድሬ-ቲዩብ ዘግቧል፡፡
የመንግስት ሹሙ ለሰልፉ ፈቃድ አልሰጠንም ቢሉም፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 30(1) ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ እንደሆነ እና ሰላማዊ ሰልፍን በተመለተ የወጣው አዋጅ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ለመውጣት ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ ድንጋጌ እንደሌለ ይታወቃል፡፡
ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ከሃገር እንዳይወጣ ታገደ
በአውሮፓና በተለያዩ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶቹን ለማቅረብ ወደ ባህር ማዶ ሊጓዝ የነበረው ታዋቂው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከሀገር እንዳይወጣ መታገዱ ተገለፀ። ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርቱን በፊንላንድ ሄልሲንኪ በነገው ዕለት ማቅረብ ይጀምራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ለዚህም የሙዚቃ ባንዱ አባላትና ማናጀሩ ዘካርያስ ጌታቸው እዛው ፊላንድ ቢገቡም፤ ቴዲ ከሃገር እንዳይወጣ በደህንነቶች በመታገዱ ምክንያት የነገው የፊንላንድ ኮንሰርት መሰረዙን አዘጋጆቹ ከፊንላንድ ሄልሲንኪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታው ቀዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ለቴዲ አፍሮ የበርካታ ወራት እስር በመንግስት በምክንያትነት የተገለፀችው ቢ ኤም ደብልዩ የቤት አውቶሞቢል ከገቢዎችና ጉሙሩክ ቀረጥ ጋር በተያያዘ ክፍያ ሳይፈፀም ወደ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ አስተላልፏል በሚል ክስ ተመስርቶበት በዋስ ከተለቀቀ በኋላ ወደ አሜሪካ ሊሄድ ሲል እንዲሁ በደህነንቶች ተይዞ በቦሌ ኤርፖርት ሲጉላላ ከቆየ በኋላ የተለመደ የኮንሰርት ስራውን ቀጥሎ ወደ ሀገሩ መመለሱ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. አርቲስቱ ከሀገር እንዳይወጣ ፓስፖርቱ በደህንነቶች ለጉዞ ዝግጅት ላይ እያለ ድንገት መነጠቁን እና ይህ እስከተዘገበበት ድረስም የጉዞ ሰነዱ እንዳልተመለሰለት መረጃዎች አመልክተዋል። ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ለምን ከሃገር እንዳይወጣ እንደታገደ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም:።
በሄል ሲንኪ ፊላንድ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመታደም ትኬቱን የገዙ በርካታ ታዳሚዎች በጉጉት ይጠባበቁ የነበረ ሲሆን፤ከአቅም በላይ በተፈጠረ ችግር ኮንሰርቱን በዕለቱ ማቅረብ ስለማይቻል መሰረዙን አዘጋጁ ቲ-ፕሮሞሽን ከሄልሲንኪ ፊንላንድ አስታውቋል ። ይሁን እንጂ አዘጋጆች ኮንሰርቱ በመሰረዙ ምክንያት ትኬቱን የገዙ ሰዎች ገንዘባቸው ክፍያ በፈፀሙበት መንገድ እንደሚመለስላቸው እና በቅርቡም የታሰበው ኮንሰርት እንደሚካሄድ በመጠቆም፤ ችግሩ የተፈጠረው ከአርቲስቱና ከአዘጋጆቹ አቅም በላይ በሆነ ችግር በመሆኑ አዘጋጁ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ለኮንሰርቱ መሰረዝ የሆነው ችግር እንደተፈታም የሙዚቃ ድግሱ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡