Daily Archives: January 7th, 2015

የምርጫ ቦርድ ዉሳኔ- ሁለት በሉ…ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ!

            ተክሌ በቀለ (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ተክሌ በቀለ
(የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

አንድነት ፓርቲ የኢህኣዴግን ምንነት ላላመኑ ወገኖች ለማጋለጥ በትጋትና በስሌት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እየሰራም ነዉ፤እዚህ ደርሷል፡፡ “የሆደ ሰፊዉን ምርጫ ቦርድ” ሆድ በገሃድ አጋልጧል፡፡ በነ አሞራዉና ወዲ ቐሺ(በተጋሩ ሁሉ) ትግልና ሞት የሚቀልዱትን በህዝብ ፊት ወጥተዉ ዛሬም እንዲዋሹና ለኢትዮጵያችን የፖለቲካ ታሪክ እነማን ምን እንደሆኑ አንድነት ፓርቲ የበኩሉን ሚና ተጫዉቷል፡፡ ለኔ ከባድመ ዉሳኔና ልህዝቡ በወቅቱ ከተነገረዉ ጋር ይመሳሰላል፤ይጠጋጋል፡፡ ኢህኣዴግ ምርጫዉን እንደማይፈልገዉ፤ከፈለገዉም ለተለመደዉ ቀልዱ ከነማን ጋርና በምን ሁኔታ እንደሚፈልገዉ ፓርቲያችን ሶስተኛዉን (የአዉሮፓና አሜሪካ ታዛቢዎች የሌሉበት ምርጫ መሆኑን፤የህዝብ ታዛቢዎች የተበላሸ የምርጫ ሂደትና ፓርቲዎችን የማፈራረስ/የማዳከም ስራዎች) ነጥብ አስመዝግቧል፡፡

በዚህ ሂደት ላይ ሰፊ እዉነታ ለህዝብ ይቀርባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ከምርጫዉ ቦርድ መጋረጃ ካሉት ወገኖች ጋር በሃሳብ እየተሸነፈ ግን ተሳትፎዉ ያለተቋረጠ አንድ ከፍተኛ አመራር እንዳለ እናዉቃለን፡፡ ሁሉን ነገር በደንብና በመርህ የምንሰራዉ ለኢህኣዲግ/ምርጫ ቦርድ ካለን ፍርሃት ሳይሆን ለወደፊቱ ለምናስተዳድረዉ ህዝባችንና ለኢትዮጵያችን ፖለቲካ ክብር ስንል ነዉ፡፡ እናም ከደንብ ወጥተን የሰራነዉ ክዋኔም በግፍ የገፋነዉ አመራርም፤አባልም የለም፡፡ በመቻቻል መንፈስ ዲሰፒሊን ተጥሶም እንዲጓተት ተደርጓል፡፡ ይህንንም የኢህኣዴግ ተባባሪነት ለታሪክ አስቀምጠነዋል፡፡

ምርጫ ቅንጦት ሆኖብን፤የተከበሩ እየተባሉ ለመጠራት ሳይሆን እፊታችን ላይ ያለ እድልና ስልትም ስለሆነ አንድነት ፓርቲ መጪዉን ምርጫ የምር እንዲሆን ወስኗል፡፡ ኢህኣዴግ ደግሞ ማበላሸቱን ተያያይዞትል፡፡ ምርጫ በአምባገነን ቡድኖች ለሚገዙ አገራት ለለዉጥ እንዱ ስልት እንጂ ብቸኛዉ አለመሆኑ ይታመናል፡፡ፓርቲያችን ለለዉጥ ተደራጅም ይላል፡፡እዉነተኛ ፓርቲዎች ከምርጫዉ ባሻገር ላለዉ ግብ እንዲዋሃዱና እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርቧል፤ስልቶችን ለማቀራረብም እየጣረም ነዉ፡፡ የአንድነት ኣባላት በያለንበት ድርብ ሃላፊነት አለብን፡፡ ለአንድነት ሃይሎች ስልቶቻችን ሁሉ በማቀራረብ የተጀመረዉ የስልጣን ሃይሎችን እያራገፉ ትግሉን በሰለጠነና አንድነቱን በጠበቀ መልኩ የማስቀጠልና ልዩነቶችን በማቻቻል ሰፊ መሰረት የማንበር ሃለፊነት አለብን፡፡ ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ፤ፊታችንን ወደ ዋናዉ ግብ እናድርግ፤ከሃዲዱ አንወርድም!

የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት ተከሰሱ

በታምሩ ፅጌ

-79 ሰዎች መሞታቸውና 13,034 ነዋሪዎች መፈናቀላቸው በክሱ ተጠቅሷል

 

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ጋምቤላ ክልል በመሄድ በማዣንግ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በሕጋዊ መንገድ ሠፍረው ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩ የነበሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚሏቸውን በመግደል፣

ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በማድረስና በማፈናቀል የተጠረጠሩ፣ የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ 17 ባለሥልጣናትና ሌሎች 20 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ ተወላጆችና በደገኞቹ መካከል ያለውን የመሬት አጠቃቀም በሚመለከት ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2006 ዓ.ም.፣ ማዣንግ ዞን ጐደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ ውስጥ በተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሾች የወረዳ አመራሮችንና ኅብረተሰቡን በመሰብሰብ ውይይት ማድረጋቸውን የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠሩት ተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ፣ ‹‹ደገኞቹ በማዣንግ ዞን ውስጥ የያዙትን የእርሻና የቡና ተክል መሬት ለማዣንግ ብሔር ተወላጆች ሊያካፍሉ ይገባል፡፡ የማያካፍሉ ከሆነ ከአካባቢያችን ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል፤›› በሚል አጀንዳ ላይ ተወያይተው መመርያ ማስተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ክልሉ ሄደው የሠፈሩትና ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል የተባሉት በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚባሉት የሌላ ብሔር ተወላጆች፣ ተጠርጣሪዎቹ ያስተላለፉትን መመርያ ‹‹አንቀበልም›› ማለታቸውንም ክሱ ጠቁሟል፡፡

‹‹ደገኞቹ›› መመርያውን እንደማይቀበሉ ሲያሳውቁ የማዣንግ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ የዞኑ የፖሊስና የሚሊሻ ታጣቂ አባላትን በማደራጀትና በማስታጠቅ፣ ጥቃት እንዲፈጽሙ (በደገኞቹ ላይ) ትዕዛዝ በመስጠትና ራሳቸውም በመሳተፍ፣ ከሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት፣ በብሔሩ ተወላጆችና በ‹‹ደገኞች›› መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲከሰት ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በማዣንግ ዞን በተለይ በመንገሺና ጐደሬ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች ውስጥ ግጭቱ እንዲከሰት በመደረጉ፣ ክሱ እስከሚመሠረት ድረስ የታወቀው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 79 መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ 27 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ 273 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው ንብረትም መውደሙና 13,034 ዜጐች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪዎቹና ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው በማዣንግ ብሔር ተወላጆችና በ‹‹ደገኛው›› ማኅበረሰብ መካከል በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ክላሽኒኮብ፣ ጦርና የተለያዩ ሥለቶችን በመጠቀም ዜጐችን መግደላቸውን፣ አካል ማጉደላቸውን፣ ማቁሰላቸውንና ቤቶችን በማቃጠል ንብረት በማውደማቸው፣ በወንጀሉ ድርጊት በቀጥታ ተሳትፎ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የአምስትና የ12 ዓመት ሕፃናትን፣ ጐልማሶችንና ወጣቶችን በጥይት ደብድበው፣ በሥለት ወግተውና አርደው ከመግደላቸውም በተጨማሪ፣ የስምንት ወር ነፍሰ ጡርንና ሌሎች ነዋሪዎችን ወደ ቤት ውስጥ እንዲገቡ በማዘዝ፣ ቤታቸውን በእሳት በመለኮስ አቃጥለው የገደሏቸው መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ በዝርዝር ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በቡድንና በተናጠል 30 ክሶችን መሥርቶ ታህሳስ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ የክስ ዝርዝሩ ለተጠርጣሪዎች ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከክሱ ጋር የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ዝርዝር ተያይዞ በመቅረቡ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹ ዝርዝር ከተሰጠ ለደኅንነታቸው እንደሚያሠጋቸው በመግለጽ እንዳይሰጥ በማመልከቱ ነው፡፡

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ያዕቆብ ሸራተን ታኪካን፣ የማዣንግ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤል ራንጃን ኮንዜን፣ የጐደሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮናስ ማርቆስ፣ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ጌታቸው ደቢሊው ተልቲካ፣ የጐደሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አብዮት ሮኬት ኮርኮት፣ የማዣንግ ዞን ፖሊስ መምርያ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ዋና ኃላፊ ኢንስፔክተር ማቴዎስ ማጥኦት ሀኪ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የአስተዳደርና ማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አብርሃም ማይክል፣ የጐደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ያኬት ሪካ፣ የጐደሬ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ተፈራ፣ የዞኑ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይማም ፋሪስ፣ የሜጢ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የግዥና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ  ደንገቱ ረጳሽ፣ የጐደሬ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ አብረሃም፣ የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ስምዖን ኮኛንንና ሌሎችም ተጠርጣሪዎች በድምሩ 37 መሆናቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የግል የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈርሰው ከመንግስት ቻናል እንዲከራዩ ለማድረግ ታቅዷል

በኢንተርኔት የሚሰራጩ  ፅሑፎችን፣ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን ለመቆጣጠር ታስቧል

 ebaበኢትዮጵያ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭቶችን ለመቆጣጠር ከስምንት ዓመት በፊት በታወጀው ህግ ላይ አዳዲስ ቁጥጥሮችን የሚጨምርና እንዲሁም የኢንተርኔት ስርጭቶችንና ድረገፆችን የሚያካትት ህግ ተዘጋጀ፡፡

ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋር ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ውይይት የተካሄደበት ረቂቅ ህግ፣ ነባሩ አዋጅ ውስጥ የሰፈሩ የባለቤትነትና የፈቃድ አሰጣጥ ቁጥጥሮችን የሚዘረዝር ሲሆን፤ በኩባንያ መልክ እንጂ በግለሰብ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ድርጅት ማቋቋም እንደማይቻል ይጠቅሳል፡፡ የዝምድና ወይም የጋብቻ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ለብቻቸው ባለአክሲዮን የሆኑበት ኩባንያ ፈቃድ እንደማይገኝም ተደንግጓል፡፡  ምንም እንኳ እስከዛሬ ተግባራዊ ባይሆንም በ1999 ዓ.ም በወጣው ህግ፣ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ፈቃድ እንደሚሰጥ ተገልፆ የነበረ ሲሆን፤ አሁን በተረቀቀው ህግ ግን የቴሌቪዥን ጣቢያ በግል ማቋቋም እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡

መንግስት የቴሌቪዥን ማሰራጫ ኔትዎርክ እንደሚዘረጋ የሚገልፀው ይሄው አዲስ አዋጅ፤ የግል ኩባንያዎች ከመንግስት ቻናል እየተከራዩ ለመስራት ማመልከትና ፈቃድ መጠየቅ ይችላሉ ይላል፡፡

የግል ኩባንያዎች ለጊዜው የራሳቸው የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም ፈቃድ የሚያገኙበት እድል ሊኖር እንደሚችል አዲሱ ህግ ይጠቁማል፡፡ ወደፊት ግን በግል ባቋቋሙት የማሰራጫ ጣቢያ ሳይሆን ከመንግስት የማሰራጫ ጣቢያ ቻናል እየተከራዩ እንዲሰሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ለዚህም መመሪያ እንደሚዘጋጅ በረቂቁ ህግ ተጠቅሷል፡፡

በረቂቁ ህግ ከተካተቱ 60 አንቀፆች መካከል አብዛኞች በሬዲዮና በቴሌቭዥን ስርጭት ቁጥጥር ላይ ያተኮሩ ሲሆን፤ በኢንተርኔት የሚሰራጩና በድረገፅ የሚቀርቡ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የታቀዱ ሦስት አንቀፆች ተጨምረውበታል፡፡ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የግል ድርጅቶች ስለዲሞክራሲና ስለ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የመዘገብ ግዴታ በህጉ የተጣለባቸው ሲሆን፤ በኢንተርኔትና በድረገፅ የሚሰራጩ መረጃዎች እንዲህ አይነት ግዴታ ባይኖርባቸውም ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ማቅረብና ሌሎች በአንቀፅ 33 የተዘረዘሩ ድርጊቶችን ከፈፀሙ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ረቂቅ ህጉ ይገልፃል፡፡

አመፅና፣ ግጭትና ጦርነት መቀስቀስ፣ እንዲሁም የሰውን ስምና ነፃነትን የሚያጠፋ መረጃ ክልክል መሆኑን የሚዘረዘረው አዲሱ ህግ፤ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ባይብራራም የሃይማኖትን፣ የዘርን፣ የፆታን ክብር መንካት ክልክል ነው ይላል፡፡  በደፈናው ስነምግባርን የሚፃረርና የልጆችን አስተሳሰብ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያዘነብል መገፋፋትም ህገወጥ መሆኑን ይገልፃል፡፡

እንደ ፌስቡክ እና ቲዊተር የመሳሰሉትን ጨምሮ አብዛኞቹ ድረገፆች በውጭ አገር የሚገኙ በመሆናቸው እንዴት ሊቆጣጠራቸው እንዳሰበ ሲጠቁም፣ በፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥና ድረገፁ ከሚገኝበት አገር መንግስት ጋር በመተባበር እርምጃ እንደሚወስድ ህጉ ይገልፃል፡፡
ብዙዎቹ ድረገፆች በሚገኙበት በአሜሪካ “ሃሰት አሰራጨህ ወይም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ትገፋፋለህ” የሚል የአስተሳሰብ ቁጥጥር እንደሌለ ይታወቃል፡፡

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

%d bloggers like this: