Daily Archives: January 13th, 2015

ምርጫ ቦርድ በሶስቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ

nebe

ዛሬ ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድነት፣ በመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ላይ ውሳሳለፉን አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ውሳኔ ብሎ ያስተላለፈው ፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የውስጥ ችግራቸውን መፍታት አልቻሉም በሚል ለዛሬው ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሁለቱ ፓርቲዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈትተው ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ገልጾአል፡፡

ቦርዱ ዛሬ ከሰዓት በሰጠው መግለጫ በአንድነትና መኢአድ ስም የተለያዩ ጉባኤዎች በመደረጋቸው ሁለቱ ፓርቲዎች ጥር 3 ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አለመገኘቱን፣ አንድነት የ2004 ዓ.ም እንዲሁም የመኢአድን የ2001 ዓ.ም ደንብን እንጅ ከዛ በኋላ ያሉትን የፓርቲውን ደንቦች እንደማያውቅ በመግለጽ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ችግራቸውን እንዲፈቱ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡

በሌላ በኩል መድረክ ረግጦ በመውጣት፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድሙ በማድረግ፣ ቦርዱ የማያውቀው ትብብር በመመስረት በሚል በምርጫ ቦርድ ክስ የቀረበበትና ይቅርታ እንደማይጠይቅ በደብዳቤ ለገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውን የማያከብር ከሆነም ቦርዱ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡

የቦርዱ ባለስልጣናት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ህገ ወጥ ትብብር በመመስረት ስትከሱ ሌሎቹን የትብብሩን አባል ፓርቲዎች ለምን አልከሰሳችሁም?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ፓርቲዎቹ 9 መሆናቸውን የሰማሁት አሁን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹እስካሁን ሌሎች ትብብሮችን ምርጫ ቦርድ አያውቃቸውም ብላችሁ ከሳችሁ አታውቁም›› በሚል የ9ኙን ፓርቲዎች ትብብር ህገ ወጥ ነው ካሉ ገዠው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነትን ለምን ህገ ወጥ ነው እንደማይሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎች ሊኖሩት ይቻላል፡፡ እንደ ገዥ ፓርቲ ከአጋሮች ጋር መስራት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ቦርዱ አይመለከተውም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን እንዲፈቱ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቻለሁ ያለው ምርጫ ቦርድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን ካልፈቱ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔውን አሳውቃለሁ ማለቱን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡ አንድነት እና መኢአድ ምርጫ ቦርድ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አድርጉ ባለው መሰረት ያለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረጉት ጠቅላላ ጉባኤ አንድነት ፓርቲ በድጋሚ አቶ በላይ ፈቃዱን ፕሬዘዳንት አድርጎ ሲመርጥ፤ መኢአድም እንዲሁ በተመሳሳይ ቀን ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገ ሲሆን፤ በዕለቱ ምርጫ ቦርድ በህጉ መሰረት በሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ የጥሪ ደብዳቤ ቢደርሰውም በሁለቱም ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካይ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ዛሬ በፅህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

…….

የአንድነት ፓርቲ ሁለት አባላት ድብደባ ተፈፀመባቸው

ወይንሸት ስለሺ በህክምና ዕርዳታ ላይ

ወይንሸት ስለሺ በህክምና ዕርዳታ ላይ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወይንሸት  ስለሺ እና የፓርቲው አባል መሳይ ትኩ ባልታወቁ ሰዎች መደብደባቸው ተሰማ፡፡  ወጣት መሳይ ትኩ ባለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አንድነት ፓርቲ የጠራውን ጠቅላላ ጉባኤውን አጠናቆ ወደ ቤቱ ሲጓዝ አዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት ፓርቲው አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የነበረችና በፓርቲው ንቁ ተሳትፎ እያደረገች የምትገኘው የሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወይንሸት ስለሺ ጥር 6 ቀን 2007 ኣ.ም. ከረፋዱ 5፡30 ላይ አዲስ አበባ በተለምዶ ነፋስ ስልክ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ባልታወቁ ሁለት ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባት የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡ ወይንሸት ነፍሰጡር መሆኗንና ሆዷ ላይም ከፍተኛ ድብደባ በመፈፀሙ በአሁን ወቅት ራሷን ስታ ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

መሳይ ትኩ

መሳይ ትኩ

ሁለቱም የፓርቲው አባላት በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው በመግለፅ፤ በተለይ ወጣት መሳይ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ አንድነት መጪውን 2007 ኣ.ም. በሚደረገው ምርጫ እንዳይሳተፍ የሚደረገውን ሴራ ቀድሞ በማጋለጡ የተወሰደበት እርምጃ እንደሆነ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡ ወይንሸትም በፓርቲው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አስመራጭ ኮሚቴ ሆና ከማገልገሏ በተጨማሪ በፓርቲው ላይ የሚደረጉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በማውገዝ አስተያየት መሰንዘሯ ለተፈፀመባት ድብደባ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የፓርቲው ልሳን መረጃ አመልክቷል፡፡

%d bloggers like this: